መሰረት ባዩ፣ ጉርድ ሾላ አካባቢ ድንች እየጠበሰች ራሷንና ቤተሰቧን ታስተዳድራለች፡፡ ለድንች መጥበሻነት የምትጠቀመው የዘይት አይነት ከውጪ ተመርተው ከሚመጡት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ አንድ ጊዜ መጥበሻው ላይ ባደረገችው ዘይት ብቻ ቀኑን ሙሉ ዘይቱን ሳትቀይር ድንች ስትጠብስ ትውላለች፡፡
ይህንንም የምታደርገው ዘይት ለመቆጠብ እንጂ ዘይቱ ተደጋግሞ ድንች ሲጠበስብት የሚያስከትለውን የጤና ችግር በመገንዘብ እንዳልሆነ ትናገራለች፡፡ ዘይቱ ሳይቀየር በተደጋጋሚ ድንች ሲጠበስበት በውስጡ የትራንስ ፋቲ አሲድ መጠን ከፍ እንደሚልና በተጠቃሚዎች ላይ የጤና ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችልም እንደማታውቅና እንዲያውም ከአሁን ቀደም ስለ ትራንስ ፋቲ አሲድ ፈፅሞ እንዳልሰማችም ታስረዳለች፡፡፡
ትራንስ ፋቲ አሲድ /trans faty acid/ ፈሳሽ የሆነ የምግብ ዘይት ወይም ቅቤ በከፊል አልያም ሙሉ በሙሉ እንዲረጋ ሲደረግ የሚፈጠር የስብ አይነት ነው፡፡ የዚህ አይነቱ የለውጥ ሂደት በተፈጥሮ በአነስተኛ መጠን የሚገኝ ቢሆንም፤ በፋብሪካ በሚመረትበት ሂደት ግን ፈሳሽ በሆኑ የምግብ ዘይቶች ላይ የሃይድሮጅን ንጥረ ነገር በመጨመር በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የረጉ ዘይቶች ወይም ቅባቶች እንዲሆኑ በማድረግ መጠኑ ከፍ እንዲል ይደረጋል፡፡
በዚህ ሂደት የተዘጋጀ ዘይት ደግሞ ምግቦች ለረጅም ጊዜ ጣዕማቸው ሳይቀየር እንዲቆዩ ያደርጋቸዋል፡፡ እንደቅቤ የጠጠሩና የረጉ የምግብ ዘይቶችን መመገብ ደግሞ የደም መጓጎል በማስከተል ደም ወደ ልብ፣ አንጎልና የተለያዩ የውስጥ የሰውነት ክፍሎች በተፈለገው መጠን እንዳይደርስ ስለሚያደርግ ለድንገተኛ ልብ ህመምና አለፍ ሲልም ለአንጎል ውስጥ ደም መፍሰስ እንደሚያጋልጥ የጤና ባለሞያዎች ይናገራሉ፡፡
የአለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ያወጣቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ በአለም አቀፍ ደረጃ በትራንስ ፋቲ አሲድ ምክንያት በሚከስት ህመም 540 ሺ ሰዎች በየዓመቱ ይሞታሉ፡፡ በልብ ህመም ምክንያት ከሚሞቱ 35 በመቶ ከሚሆኑት ውስጥ ደግም 28 በመቶ የሚሆኑት በትራንስ ፋቲ አሲድ ሳቢያ ለሞት ይዳረጋሉ፡፡
በኢትዮጵያ ትራንስ ፋቲ አሲድ በሰዎች ጤና ላይ እያስከተለ ያለውን ጉዳት በተመለከተ እስካሁን የተሰራ ጥናት ባይኖርም፤ በአሁኑ ወቅት ከሌሎች የልብ ህመም መንስኤዎች ባልተናነሰ በተለይ ለድንገተኛ የልብ ህመም ስጋት እየሆነ እንደመጣ በሌሎች ሀገራት የተሰሩ ጥናቶችን የተመለከቱ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የምግብ ሳይንስና የስርዓተ ምግብ ዳይሬክቶሬት ረዳት ተመራማሪ አቶ ክፍሌ ሃብቴ እንደሚገልፁት፤ ለትራንስ ፋቲ አሲድ በአብዛኛው ተጋላጭ የሆኑ ምግቦች ዘይትን ጨምሮ በፋብሪካ ተቀነባብረው የሚዘጋጁ ናቸው፡፡ በምግብ ቁጥጥር ዙሪያ የሚሳተፉ አካላት በርካታ ቢሆኑም፤ ትራንስ ፋቲ አሲድን በሚመለከት ስታንዳርድ በማውጣት የሚደረገው የቁጥጥር ስራ ግን ገና በጅምር ላይ ያለ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ህብረተሰቡ በትራንስ ፋቲ አሲድ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው፣ ስታንዳርድ እንዲወጣለትና የህግ ማዕቀፍ እንዲኖረው በጤና፣ ልማትና ፀረ ወባ ማህበር አማካኝነት የተጀመረው ተግባር ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
እንደ ረዳት ተመራማሪው ገለፃ፤ አብዛኛዎቹ ደረጃ መዳቢ ተቋማት ትራንስ ፋቲ አሲድ በተቻለ አቅም ከምግቦችና ዘይቶች ውስጥ መቀነስ እንዳለበት አልያም፤ ሙሉ በሙሉ መወገድ እንዳለበት ያስቀምጣሉ፡፡ የአለም ጤና ድርጅትም በቀን ውስጥ መወሰድ ካለበት 2 ሺ ካሎሪ መጠን ውስጥ የትራንስ ፋቲ አሲድ መጠን ከ2 ነጥብ 2 ግራም በታች መሆን እንዳለበት በመመሪያው አስቀምጧል፡፡ መጠኑ ከዚህ በላይ ከፍ የሚል ከሆነ በጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችልም ይጠቁማል፡፡
በቅርቡ በተሰራ የኢትዮጵያ ምግብ ፍጆታ ዳሰሳ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ በቀን ውስጥ 28 ግራም ዘይት በነፍስ ወከፍ ሊበላ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡ ይህም 10 ግራም ትራንስ ፋቲ አሲድ አብሮ ይመገባል ተብሎ እንደሚገመትና ከተፈቀደው የትራንስ ፋቲ አሲድ መጠን አምስት እጥፍ እንደማለት ነው፡፡
ረዳት ተመራማሪው እንደሚሉት፤ ከውጪ ተመርተው ወደሀገር ውስጥ የሚገቡ የተቀነባበሩ ምግቦች የትራንስ ፋቲ አሲድ መጠናቸውን ለማወቅና ጤናማነታቸውን ለመፈተሽ የሚያስችል አቅም መገንባት ያስፈልጋል፡፡ በተለይም ላቦራቶሪዎችን ማደራጀትና ስታንዳርዶችን በማውጣት የቁጥጥር ስራውን ማጠንከር ያስፈልጋል፡፡ በቀጣይም የኢትዮጵያ ህብረተብ ጤና ኢንስቲትዩት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የጋራ ስራዎችን ይሰራል፤ ጥናቶችንም የማያካሂድ ይሆናል፡፡
በጤና ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ኦፊሰር አቶ አፈንዲ ኡስማን እንደሚገልፁት፤ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በፖሊሲ ደረጃ ትኩረት እያገኙ የመጡት ከቅርብ ግዜ ወዲህ ነው፡፡ በነዚህ በሽታዎች ላይ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴም ገና በጅምር ላይ የሚገኝ ነው፡፡
በትራንስ ፋቲ አሲድ ምክንያት የሚከሰተው ድንገተኛ የልብ ህመም ጤናማ የአመጋገብ ስርዓትን ባለመከተል የሚከሰት ነው፡፡ ሆኖም ትራንስ ፋቲ አሲድ በጤና ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ለብቻው ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት አይደለም፡፡
እንደ ኦፊሰሩ ገለፃ፤ በኦክስጅን በበለፀገ ደም የተሞሉና ደምን ከልብ ወደ ልዩ ልዩ የሰውነት ክፍሎች የሚወስዱ አርተሪዎች የውስጠኛው ክፍላቸው በትራንስ ፋቲ አሲድ አማካኝነት በሚፈጠር ኮሌስትሮል ከተሸፈነ፣ ከጠበበ ወይም ከተዘጋ ደም በአግባቡ እንዳይዘዋወር ያደርገዋል፡፡ በዚህ ምከንያት ልብ በቂ የሆነ የደም አቅርቦትና ኦክስጅን ስለማያገኝ ለድንገተኛ የልብ ስራ ማቆምና ለአንጎል ውስጥ ደም መፍሰስ አደጋ ያጋልጣል፡፡ ይህ አይነቱ የልብ ህመም ኮሮናሪ ኸርት ዲዚዝ /coronary heart disease/ በመባል ይታወቃል፡፡ በዚህ በሽታ ዙሪያ በቂ የሆነና የተጠናከረ መረጃ ባይኖርም፤ በአሁኑ ወቅት ለሞት መንስኤ እየሆኑ ከመጡ በሽታዎች ውስጥ አንዱ ሆኗል፡፡
ኦፊሰሩ እንደሚሉት፤ የትራንስ ፋቲ አሲድ ለድንገተኛ ልብ ህመም መከሰት ምክንያት እንደሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ጊዜያት የተሰሩ ጥናቶች ቢያሳዩም፤ በሀገር ደረጃ በቂ ጥናቶች ባለመሰራታቸው ለጉዳዩ በቂ ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ በጤና ሚኒስቴር በኩል እየተደረገ ያለው ጥረትም ገና ነው፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አማካኝነት ከትራንስ ፋቲ አሲድ ጋር በተለይም ከምግብ ዘይቶች ጋር በተገናኘ የተጀመሩ መጠነኛ ስራዎች በቀጣይ በጉዳዩ ዙሪያ ለመስራት እንደመነሻ የሚያገለግሉ ናቸው፡፡
ከሁሉ በላይ ደግሞ ትራንስ ፋቲ አሲድን በሚመለከት ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ልክ እንደሌሎቹ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መንስኤ ሁሉ ትራንስ ፋቲ አሲድም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ የጤና ሚኒስቴርም በዚሁ አግባብ ስራዎችን በማቀድና በማደራጀት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለመሄድ በመንደርደር ላይ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ ምን ያህሉ የህብረተሰብ ክፍል የትኞቹን የዘይት አይነቶች እንደሚጠቀምና ምን ያህል የዘይት ተጠቃሚዎች ከልብና ከልብ ጋር በተያያዘ እንደሚሞቱ የሚያሳይ ጥናት አለመሰራቱን የሚጠቅሱት ኦፊሰሩ፤ በቀጣይ በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናቶችን ማካሄድና መረጃዎችን መሰብሰብ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆን ይኖርበታል፡፡
ትራንስ ፋቲ አሲድን ለማስወገድ በአለም አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የተደረጉ ስትራቴጂዎችን ተሞክሮ በማየት በሀገር ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግም ከወዲሁ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ የተሳካላቸው ሀገራትን ተሞክሮ በመውሰድ ቀምሮ ተግባራዊ ማድረግም ይጠበቃል፡፡
በኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የምግብ ምዝገባ ዳይሬክተር አቶ ሃይለሚካኤል ካሳዬ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ የኢትዮጵያ ስታንዳንርድ ኤጀንሲ ዘይትን ጨምሮ በእያንዳንዱ በፋብሪካ የተቀነባበሩ የቅባት ምግቦች ላይ ደረጃዎችን ያወጣል፡፡ በፋብሪካ ተቀነባብረው የሚመረቱ ቅባትነት ያላቸው ምግቦችና ዘይቶች ከትራንስ ፋቲ አሲድ ነፃ መሆን እንዳለባቸውም ስታንዳርዱ ያስቀምጣል፡፡ ስታንዳርዱ ባስቀመጠው ቅድመ ሁኔታ መሰረት በእያንዳንዱ ምርት ላይ ትንተና በማውጣት ለገበያ እንዲቀርብ ይደረጋል፡፡
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፤ የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት በስታንዳርዱ መሰረት ምርቱ ማለፉንና መውደቁን ያረጋግጣል፡፡ የላቦራቶሪ ውጤትን መነሻ በማድረግ ደግሞ በኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ትራንስ ፋቲ አሲድ ከተቀመጠው ስታንዳርድ በላይ ከሆነ ምርቱ ለገበያ እንዳይቀርብ ያደርጋል፡፡
ከፓልም ኦይል ውጪ የትራንስ ፋቲ አሲድ ይዘት ያለባቸው የዘይት ምርቶች ይኖራሉ ተብሎ ባይገመትም፤ የትራንስ ፋቲ አሲድ መጠናቸው ከፍ ባሉ በፋብሪካ ተቀነባብረው የሚዘጋጁ የቅባትና የዘይት ምርቶች ላይ እስካሁን የተወሰዱ እርምጃዎች ብዙም የሉም፡፡ ሆኖም ምርቶቹ ከተገኙ ለህብረተሰቡ እንዳይቀርቡ ይደረጋል፡፡ የአመራረት ሂደቱንም በማየት አምራቾች ማሰተካከያዎችን እንዲያደርጉ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲወሰድም ይደረጋል፡፡
የአለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ በ2017 ባወጣው መረጃ መሰረት በአለም አቀፍ ደረጃ 17 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በድንገተኛ የልብ ህመም እና በአንጎል ውስጥ ደም መፍሰስ አደጋ እንደሚሞቱ ያመላከተ ሲሆን፣ ለዚህም የትራንስ ፋቲ አሲድ ይዘት ያላቸው ምግቦች የራሳቸውን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ ጠቁሟል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2011
አስናቀ ፀጋዬ