ኢትዮጵያ በተለያዩ ጉዳዮች የዓለም ሀገራትን ቀልብ ስባለች። ብዙዎች ዓይናቸውን በጣሉባትና መነጋገሪያ አጀንዳቸው ባደረጓት ወቅት ላይ ትገኛለች። በተለይ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የዓለም ሀገራትን ቀልብ ከሳቡት ጉዳዮች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው።
በሀገራችን ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ልዩ ትኩረት የተሰጠው፣ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንደ ምሳሌ ተጠቃሽ ሊሆን የሚችል ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት የተደረገበት ስለሆነ ነው። ለዚህም መንግሥት ቆራጥነቱን አሳይቷል። ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ ተቋቁሟል። ነጻ የዴሞክራሲ ተቋማትና የፍትህ አካላት ተደራጅቷል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም ዴሞክራሲያዊ ፣ ነፃ እና በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው ምርጫ ለማካሄድ ጥረቶች ተደርገዋል ። ከዚህ ጎን ለጎን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በሀገራችን እንዳይካሄድ የሚፈልጉ ኃይሎች ከውስጥም ከውጭም ሂደቱን ጥላሸት ለመቀባት ብሎም ለማደናቀፍ ጥረት ሲያደርጉ ከርመዋል፤ አሁንም ቀጥለዋል።
ምርጫ ለሀገራችን ሰላምና ደህንነት ወሳኝ ጉዳይ ነው። ዴሞክራሲን የምንለማመድበት፣ በመረጥነው ፓርቲና መንግሥት የምንተዳደርበት፣ አሁን ከሚታዩና ከሚሰሙ አስከፊ ችግሮች ሁሉ የምንሸጋገርበት ዋነኛው መንገድም ነው። ስለዚህ ለምርጫው ስኬታማነት ሁላችንም ልንረባረብና የግዴታ ውዴታ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል።
በሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረጊያው አንዱ መንገድ መራጩ ህዝብ በምርጫ ቦርድ በተቀመጠለት የመራጮች ምዝገባ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ምዝገባውን ማካሄድ ነው። ይህ በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል። ተፎካካሪ ፓርቲዎችም የሀገሪቱን ህግ ተከትለውና የምርጫ ቦርድ የተወዳዳሪ ፓርቲዎችም መመሪያና ደንብ ጠብቀው በመስፈርቱ መሰረት ምዝገባ አካሂደዋል። በዚህም ምን ያህል የክልልና የእንደራሴ ምክር ቤት ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉና እነማን ለምርጫ እንደቀረቡ ህዝቡ በይፋ አውቋል ።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ከህዝባቸው ጋር የሚገናኙበት ፕሮግራምና ዓላማቸውን ለመራጩ ህዝብ የሚያስተዋውቁበት የመገናኛ ብዙሀን የአየር ሰዓት እና የዓምድ ድልድል አድርገው ከመጋቢት 30 እስከ ዛሬው ዕለት ድረስ የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን ሲያካሂዱ ቆይተዋል። በተለያዩ መድረኮችና አደባባዮች ጭምር በነጻነት ደጋፊዎቻቸውን ሲያገኙና ሲቀሰቅሱ ራሳቸውን ሲያስተዋውቁ ቆይተዋል። ይሄ በሰላማዊ መንገድ የተካሄደ ጥሩና ስኬታማ ጊዜ ነበር።
የፊታችን ሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ምርጫ የሚካሄድበትና መራጩ ድምጽ የሚሰጥበት ጊዜ ነው። ይሄን ለሁሉም አጓጊና የዓለምን ትኩረት ያገኘ ምርጫ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ማድረግ ከሁሉ ኢትዮጵያውያን ይጠበቃል።
ነገር ግን ኢትዮጵያ ጠንካራ ሀገር እንዳትሆን ጠንካራ መንግሥት እንዳይመሰረት በተለያየ አቅጣጫ ምርጫውን ለማደናቀፍ ጥረት የሚያደርጉ ኃይሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገመታል። ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ግን ኢትዮጵያ ምርጫውን ታሸንፍ ብሎ መስራት ከሁሉ ዜጋ የሚጠበቅ አገራዊ ግዴታ መሆን አለበት።
በምርጫ ሂደት ወሳኝ ሚና ቢኖረውም የመንግሥት ጥረት ብቻውን ውጤት አያመጣም። ስለዚህ ምርጫው ሰላማዊ ፣ዴሞክራሲያዊና በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ሁሉም የራሱን ጥረት ማድረግና ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። ለዚህም ህዝቡ፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና መንግሥት ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።
ህዝቡ የሀገር ሰላም ከምንም በላይ መሆኑን በመረዳትም ህጋዊ መንገዶችን ተከትሎ የምርጫ ድምጽ ለመስጠትና ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ በነቂስ ወጥቶ መምረጥ ይጠበቅበታል። የሰለጠኑና ዴሞክራሲያዊ የሆኑ ሀገሮች ብሎ የሌላውን ሀገር ከማንቆለጳጰስ የምንሻው ምርጫ በሀገራችን እንዲለመድና የምንመኘው ዴሞክራሲ ስርዓት እንዲሰፍን መስራት ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ከመራጩ ህዝብ የሚጠበቀው አንደኛ ካርዱን ሳያበክን በነቂስ ወጥቶ ድምጽ መስጠት ነው። ከዚሁ ጎን ለጎን ሀገር ሰላም እንዲሆን የራስን አካባቢ ነቅቶ መጠበቅ፣ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር መተባበርና አብሮ መስራት ነው።
ተወዳዳሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችም በሀገራችን የተጀመረው ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። ምርጫውም ሆነ ሂደቱ ምንም ይሁን ምን መራጩን ህዝብ ለጸብ ከሚገፋፉ ንግግሮች መታቀብ፣ ከምርጫው በኋላም ውጤቱን በጸጋ መቀበል ያስፈልጋል። ለዚህም ዝግጁ መሆን ይገባል።
ሌላው ትልቁ ሀገራዊ ኃላፊነት የወደቀው በመንግሥት ላይ ነው ። መንግሥት የሀገርን ሉአላዊነት ማስከበር፣ የሀገር ሰላም እና የህዝቡን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታ አለበት። ይሄንን ግዴታውን ለመወጣት ጠንክሮ መስራትና በየአቅጣጫው የንስር ዓይን መሆን መቻል ይጠበቅበታል።
ውጤቱ ምንም ይሁን ምን፤ ማንም ያሸንፍ ማን፤ መታሰብና መቅደም ያለበት ሀገርና ህዝብ ነው። መምራትም መመራትም የሚኖረው ሀገር ሲኖር በሀገር ላይ ሰላም ሲሰፍን ብቻ ነው። የምንመኘውን ዴሞክራሲ ማስፈን የምንችለው በቅድሚያ ሀገር ስትኖር ነው። ስለዚህ አሁን በምርጫው ቀዳሚ ዓላማችን መሆን ያለበት ኢትዮጵያን አንድታሸንፍ መስራት ነው። ምርጫውን በድል ስናጠናቅቅ የምታሸንፈው ኢትዮጵያ ናት። የውስጡም የውጪውም ጠላት የሚያፍረው ኢትዮጵያ ስታሸንፍ ነው። ስለሆነም ምርጫው የሀገራችን ማሸነፊያ መሳሪያ መሆኑን በመገንዘብ ኢትዮጵያ እንድታሸንፍ ሁላችንም የራሳችንን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት አለብን።
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2013