ምርጫ ደርሶም አይደል? ታዲያ እርሱን ተንተርሶ ህዝቡን ማእከል ስላደረጉ ነገሮች ብዙ ብዙ ይባላል። እኔን ከመረጥከኝ “ይህንና ያንን አደርግልሃለሁ” ወተት በቧንቧ አይነት የማይመስሉ የተለጠጡ ቃል መግባቶች ይጎርፋሉ። በዓለም ላይ ያሉ ፖለቲከኞች አንድ የሚያመሳስላቸው ነገር እንዳለ ይነገራል። እርሱም ምንም ሳይሸማቀቁና “ነገ ምን እሆናለሁ” ሳይሉ ለጆሮ የሚከብዱ ቃሎችን መግባታቸው ነው። ምክንያቱም ጭንቅ ነዋ። በካርዱ ሊቀጣቸው የተዘጋጀ ህዝብ በምን ቀልቡን ያሸፍቱታል። ቃል በመግባት ነዋ! ታዲያ ይህንን መላ ያለምንም ማቅማማት ይፈጽሙታል።
ከላይ ያነሳሁትን ጉዳይ ለመንደርደሪያነት ተጠቀምኩት እንጂ በዋነኝነት ላነሳውና ላሰምርበት የምፈልገው ጉዳይ ወዲህ ነው። እርሱም ለብዙ ጊዜያት ስማረርበት የቆየሁት የኢትዮ ቴሌኮም የኔትወርክ መጨናነቅ፣ አለመኖርና ሌሎች የአገልግሎት ችግሮችን ይመለከታል። ድርጅቱ የኔትወርክ ችግርን የሚፈቱ ስራዎች ሰራሁ ብሎ ብዙም ሳይቆይ የኔትወርክ ችግር ውስጥ ሲገኝ ሳስተውል ኖሪያለሁ።አሁንም ማስፋፋያዎች አርጌያለሁ እያለ ነው፤ ማስፋፊያው ዘላቂ መፍትሄ መሆኑን እጠራጠራለሁ፤ ያለፈው ተሞክሮዬ ይህን እንዳደርግ ነው የሚያስገድደኝ።
“ታዲያ ይሄ ከምርጫ ጊዜ ቃል መግባት ጋር ምን ያገናኘዋል?” ካላችሁኝ መልሴ “በቀጥታ ይገናኛል” የሚል ይሆናል። ምክንያቱ ደግሞ እጅግ በጣም ቀላል ነው “ የቴሌኮሚኒኬሽን ዘርፍ አሰራር ማዘመንና የአገልግሎት ግድፈት ማረም ላይ በተጨባጭ እሰራለሁ” በሚል ቃል የሚገባ የፖለቲካ ፓርቲ ካገኘሁ በቀጥታ ድምጼን ለእርሱ እሰጣለሁ። ታዲያ “ቃል ገብቶ ባይተገብረውስ” ካላችሁኝ ምላሼ የምእራባውያኑ አባባል ይሆናል “ወንዙ ጋር ስንደርስ እንሻገረዋለን”! የሚል።
ለመሆኑ ምን ያህል ብማረር ነው፤ ድምጼን አንድ ተቋምን ለሚያሻሽልልኝ የፖለቲካ ፓርቲ እስከመስጠት ያደረሰኝ? ነገሩ ቀላል ነው። እድሜዬ ለአቅመ ስልክ መጠቀም ከደረሰና ቤተሰቤ የስልክ ቀፎና ሲም ገዝቶ ከሰጠኝ እለት አንስቶ በኔትወርክ መቆራረጥና ጭርሱኑ ያለመኖር ለዓመታት ጨጓራዬ ሲላጥ ቆይቷል። በየጊዜው እንደ ኤሊ እያዘመነ ከሚያመጣቸው አገልግሎቶች “የስልክ ኢንተርኔት፣ ካርድ መግዛት፣ መበደር፣ ክፍያዎችን መፈጸም” የመሳሰሉት ጉዳዮች ሲጨመሩ ደግሞ የስኳር፣ የጨጓራና ሌሎች መሰል በሽታዎች መምጣት መንስኤ የሆነ የተንቀራፈፈ አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቶቹ የምሬቴ መነሻዎች ናቸው።
“ታዲያ ምን አለፋህ ግማሽ የሚደርሰውን አገልግሎቱን እኮ በዓለም ላይ ለሚገኙ ታዋቂ ካምፓኒዎች ሸጧል” ትሉኝ ይሆናል፤ ነገሩ ግን ወዲህ ነው “ነገ አይንህ ይበራል ሲባል የዛሬን እንዴት አድሬ” እንዳለው ማየት የተሳነው።እኔም የዛሬ ሁለት ዓመት የኔትወርክ ዝርጋታና የአሰራር ስርአት ገንብተው አገልግሎት እንሰጣለን ያሉ ካምፓኒዎች ስራ እስኪጀምሩ አልታገስም ይሆናል መልሴ።
ከሰሞኑ አንድ የገረመኝ ነገር አለ። ኢቲዮ ቴሌኮም ያደረጋቸውን የተለያዩ ማስፋፊያዎችን ተከትሎ ምረቃዎችን በመላ ኢትዮጵያ የተለያዩ አቅጣጫዎች ሲያካሂድ ተመልክተናል። የኢንተርኔት መገበያያ መተግበሪያ “አፕሊኬሽኖችን” ጭምር በማስተዋወቅ አዳዲስ ማሻሸያዎቹን እያደረገ መሆኑን ሲገልጽም ሰንብቷል። በእርግጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተለያዩ ማሻሻያዎችና ለውጦች መደረጋቸውን መካድ ባይቻልም ገበያውና ማህበረሰቡ ከሚፈልገው ጥራት፣ ፍጥነት እንዲሁም ተደራሽነት አንፃር ሩቡን እንኳን ስራ ተሰርቷል የሚል እምነት የለኝም።
ድርጅቱ ዛሬ 3ጂና 4ጂ ትውልድ የኔትወርክ ፍጥነትና ዝርጋታዎችን አቀላጥፌ እየሰራሁ ነው ቢለንም ሶስትና አራት ደቂቃ በጥራት ማውራት፣ መረጃዎችን በኢንተርኔት መላክ፣ የክፍያ ሥርዓቶችን መፈጸም አዳጋች መሆኑን ለመግለጽ የተግባር ምስክር ነኝ። “ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነኑኝ” እንደሚባለው እኛም የአራትና አምስት ትውልድ የኢንተርኔት ኔትወርክ አገልግሎት እያሉ ከሚያቁለጨልጩን አንደኛቸውን የቀድሞውን ሥርዓት በቅጡ ቢያቀርቡልን የሚል እምነት አለኝ።
ለዚህም ነው በቀጣዩ ሳምንት በሚደረገው ምርጫ ላይ ለቴሌኮም ዘርፉ ልዩ ትኩረት የሚሰጥ የፖለቲካ ፓርቲ እመርጣለሁ ብዬ በድፍረት የምናገረው። ምክንያቴ ደግሞ ግልጽ ነው ፤ አሁን ላይ ሁሉም አገልግሎቶች የሚፈጸሙት በኔትወርክና ኔትወርክ፣ በስልክና በስልክ ብቻ ሆኗል። ከዚህ ቀደም መብራት በየጣቢያው ተሰልፈን ነበር የምንከፍለው። አሁን በስልክ ሆኗል። ታዲያ ዘንድሮም ለኔትወርክ ሰልፍ ይዘን ስልካችን ላይ አፍጥጠን መሆን የለበትም። በዚህ ምክንያት ድምጼን የምሰጠው ቴሌኮምን ለሚያዘምንልኝ ኑሮዬን ለሚያቀልልኝ ፓርቲ ይሆናል።
ይሄ ብቻ አይደለም። በእጅ ስልኬ ላይ ያለ ፍላጎቴና ምርጫዬ የሚመጡ መልእክቶችን የሚያስቀርልኝ አሰራር ሥርዓት የሚዘረጋ መንግስት እንደሚያስፈልገኝ ከወሰንኩ ቆይቻለሁ። እጅግ አሰልቺና ለምንም ነገር ጠቀሜታ የሌላቸው ተራ መልእክቶችን በእጅ ስልኬ ላይ ያለፍቃዴና ፍላጎቴ በመላክ ገንዘቤን የሚበዘብዙ “የአጭር የጽሁፍ መልእክቶችን” የሚያስቀርልኝ የፖለቲካ ፓርቲ ያስፈልገኛል። ለዚህም በ994 ስደውልና ቅሬታዬን ሳቀርብ “እህ” ብሎ በጥሞና የሚያደምጥና ለዛም ፈጣን የተጠያቂነት ምላሽ የሚሰጠኝን መንግስት የሚመሰርት ፓርቲ የኔን ካርድና የድምጽ ይሁንታ ያገኛል።
አሁን ላይ ግን እጅግ ብዙ የአጭር የጽሁፍ መልእክቶች የኢትዮ ቴሌኮም ይሁንታን አግኝተው ያለአግባብ ገንዘቤን እየበዘበዙኝ ይገኛሉ። እነሱ ወደ ስልኬ በገቡ ቁጥር ባትሬዬም ያልቃል እኮ።መንግስትም ከእኔ መሰሉ ምስኪን ያለአግባብ በካርድ መልክ በርካታ ቢሊዮን ገንዘቦችን ቢሰበስብም በምከፍለው የአገልግሎት ገንዘብ ልክ የኔትወርክ ፍጥነት እንዲሁም መሰል ግልጋሎቶችን ሊሰጠኝ አልቻለም።
አሁን አዳዲስ ካምፓኒዎችን ወደ አገር ውስጥ አስገብቶ ቀልጣፋ ግልጋሎት ለመስጠት ሙከራ ቢያደርግም፣ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው የቀድሞው ተግባር አሁንም በኢትዮ ቴሌኮም እጅ ስለሚገኝ ይህን ተቋም ማሻሻል እንደሚኖርበት አምናለሁ። ስለዚህ የምርጫ ካርዴን ይህን ፍላጎቴን ለሚያሟላልኝና የተሻለ የተቋም ግንባታ ለማድረግ መንግስት መሆን ለሚፈልግ ፓርቲ ለመስጠት ተዘጋጅቻለሁ።
በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተደራሽነት አስፈላጊ ነው። ፍላጎትን ለማርካት የግዴታ ሰፊ ተደራሽነትን መዘርጋት ሊኖር እንደሚገባ ይሰማኛል። ይሁን እንጂ ተደራሽነትን ለማስፋት ሲባል የጥራትን ጉዳይ ለነገ ማሳደር አይገባም እላለሁ። ለዚህም ነው ከሰሞኑ ኢትዮ ቴሌኮም በተለያዩ አካባቢዎች አስፋፍቼያቸዋለሁ የሚላቸውን ፈጣን የኔትወርክ ዝርጋታዎች በጥንቃቄ ሁሌም እንዲፈትሻቸው የምፈልገው። ምክንያቱም ድሮም ኔትወርክ ያስቸግራል አሁንም እንደዚያው ነው።
ታዲያ ችግሩ ምን ላይ ነው? መቼም “ከጆሯችሁ ነው” እንደማልባል ተስፋ አደርጋለሁ። በተለይ ደግሞ አዳዲስ የምታስተዋውቋቸውን እንደ “ቴሌ ብር” ያሉ ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓቶችን ቀልጣፋነት በአግባቡ መፈተሽ ያስፈልጋል እላለሁ። “አለበዚያ የተሻለ አማራጭ ወደሚያቀርብልን እና መንግስት ለመሆን የሚሰራ የፖለቲካ ፓርቲ ፊታችንን እናዞራለን” በሚል ማስፈራሪያ የዛሬውን እሮሮ ለመዝጋት እገደዳለሁ። አሁን አማራጭ አለኛ! ሰላም!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2013