አሸባሪው ህወሓት ባለብዙ ማንነት ነው። እንደ ሁኔታው የሚቀያየር እስስት። መርህ የሚባል ነገር ያልፈጠረበት ነውረኛ። ፈሪኣ እግዚአብሔር የሌለው ጉግማንጉግ። ጓዶቹን ገሎ ሀዘን የሚቀመጥ። ሀውልት የሚያቆም፣ ክፍለ ጦር፣ ማሰልጠኛ የሚሰይም አይነ ደረቅ። የንጹሐንን ደም ምሱ ያደረገ ጣኦት። እንደ ዘንዶ እርስ በርሱ የሚዋዋጥ አረመኔ። ለፓለቲካዊ ጥቅም ሲል ሀገሩንና እናቱን ከመሸጥና ከመግደል የማይመለስ። አይደለም በቁሙ ላለ ሰው ለሬሳ እንኳ ክብር የሌለው አረመኔ። ሰላማዊ ዜጎችን የሚያስጨፈጭፍና የሚጨፈጭፍ አውሬ። የሀውዜን፣ የበደኖን፣ የአርባጉጉን፣ የማይካድራን፣ ወዘተረፈ ጭፍጨፋ ልብ ይሏል። ሬሳ እንዳይለይ አንገት የሚቆርጥ አሪዎስ ነው። አዲስ አበባ ላይ ፈንጂ አፈንድቶ ንጹሐንን ገሎና አቁስሎ በተቀናቃኞቹ አላኮ የሚያስር፣ የሚያሰቃይና የሚገድል አሸባሪ ነው።
ወደ ወንበዴነት ከተቀየረ በኋላ ደግሞ ሲገድል ግዳይ የሚጥል ጀግና፤ ሲሞት ንጹሕና ሰላማዊ ሰው የሚሆን እንደ ሮማውያኑ ጣኦት ቬኑስ/Janus/ባለ ሁለት ተቃራኒ ፊት ጭራቅ ወይም ዙምቢ ነው። ሲቭል ለብሶና በሰላማዊ ሰዎች መሀከል ሆኖ ጥቃት ይከፍትና ገድሎ ሲፈረጥጥ ጀግና፤ ሲገደል ግን ሰላማዊ ሰው የሚሆን የምድር ጉድ ነው። በቀድሞው የአክሱም ከንቲባ አይዟችሁ ባይነት የለብለብ ስልጣን የወሰዱ ወጣቶች በመከላከያ ሰራዊት ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከፍተው በውጊያ ሲገደሉ ንጹሀንና ሰላማዊ ሰዎች ተገደሉ ብሎ ሀገር ይያዝልኝ የሚል ማፈሪያ። እንደ አፄ ልብነ ድንግል “ ጦር አውርድ “ እያለ መሬትን 40 እየገረፈና በዕብሪት ባመጣው ጦርነት በጀግናው የመከላከያ ሰራዊት አይቀጡ ቅጣት ሲቀጣ ደግሞ የድረሱልኝ ጩኸቱን ከሀሰተኛና የተዛባ መረጃ ጋር አዛንቆ ያቀልጠዋል። ይህ ማለት ግን በጦርነት ሒደት የንጹሐን ሞት፣ ቁስለትና መፈናቀል/collateral damage/የለም እያልሁ አይደለም። ይህ እንዳይሆን ነበር ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ እናቶች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች መቐሌ ድረስ እየተመላለሱ እግር ላይ ወድቀው እርቅን የለመኑት።
ልቡ የማይገኘውና ሸረኛው ህወሓት ግን ለጦርነትና ለሌላ ዙር ክህደት እየተዘጋጀ ስለነበር ሽምግልናን መግፋት መረጠ። ደባው ሲከሽፍ ደግሞ የምዕራባውያን፣ የአለማቀፍ ድርጅቶችንና ሚዲያዎችን ስሜት ኮርኳሪ የሆኑ ሀሰተኛና የተጋነኑ የሰላማዊ ሰዎች ሞትን፣ አስገድዶ መደፈርንና እርሀብን በመለፈፍ ዳግም ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ጎን ቆመ። ይህ ጊዜያዊ የዲፕሎማሲ ድሉ ግን እውነቱ እያደረ ሲገለጥ መሟሸሹ ባይቀርም በሀገራችን ገጽታ ላይ ያደረሰው ጉዳት ግን የሚታበል አይደለም። ይሄ ክህደቱና ውሸቱ ግን ትላንት የተፈጠረ ሳይሆን አብሮት ያደገ ባህሪው ነው።
ማሕበረ ገሰገስቲ ብሔረ ትግራይ/ማገብት/፣ ተጋድሎ ሓርነት ሕዝቢ ትግራይ/ተሓህት/ ፣ ማርክሲስት ሌኒኒስት ሊግ ትግራይ/ ማሌሊት/እና ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ/ ህወሓት/፤ እነዚህ በሙሉ የትግራይ ሕዝብ ነጻነት ግንባር/ትህነግ/ በተለምዶ የወያኔ እስስታዊ ባህሪና ማንነት መጠሪያ ስሞች ናቸው። በእነዚህ ሁሉ ምዕራፎች ራሱን የቻለ አስመሳይነትና ነጭ ውሸት አለ። ነጻነትን ሳያውቁ ነጻ አውጭነት፤ የላብ አደር መደብ በሌለበት ሌኒኒስትና ማርክሲስትነት፤ አብዮትም ዴሞክራሲ በሌለበት አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊነት፤ ሀቀኛ ፌደራላዊ ስርዓት በሌለበትና የወያኔ ጉጅሌ የበላይነትና የሞግዚት አስተዳደር በሰፈነበት የፌደራል ስርዓት፤ ሪፐብሊክም ዴሞክራሲም በሌለበት ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ፤ ሕገ መንግስታዊነት ባልዋለበት ሕገ መንግስት፤ ወዘተረፈ ከወያኔ አስመሳይነት፣ ውሸታምነትና መልቲነት መገለጫዎች ጥቂቶቹ ናቸው። የማይታረቅ ግጭት ላይ የርዕዮተ አለም፣ የታሪክ፣ የጥሬ መረጃ ውሸት። የማርክስ፣ የኤንግልስ፣ የሌኒን፣ የስታሊን፣ የማኦ፣ የፊደል፣ የቼጎቬራ፣ የሆቺሜኒ፣ የገሰሰ አየለ/ስሁል/፣ የአረጋዊ በርሔ (ዶ/ር)፣ የአብርሃም ያየህ፣ የገብረ መድህን አርአያ፣ ወዘተረፈ እውነቶች ለጉጅሌ/ለቡድናዊ ጥቅምና ፍላጎት ሲባል ተበርዘዋል። ተከልሰዋል። ሰሞኑን ለንባብ ከበቃው የጋዜጠኛ አርዓያ ተስፋማሪያም “ከህወሓት ጓዳ” ወደ ኋላ 30 አመታት ሄደን የእነ አብርሃም ያየህንና ገብረመድን አርዓያ፣ “የወያኔው ታላቁ ሴራ” ፣ ወዲህ የአረጋዊ በርሔን(ዶ/ር)፣ “A Political History of Tigray People’s Libration Front” ወይም የገብሩ አስራትን፣”ሉዓላዊነትና ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ”ን ብታገላብጥ፤ በአናቱ የተስፋዬ ገብረዓብን፣ “የጋዜጠኛው ማስታወሻ”ን ፣”የደራሲው ማስታወሻን” ወይም የኤርሚያስ ለገሰን፣ “የመለስ ትሩፋቶች”ን እና “የመለስ ልቃቂት”ን፤ ሰሞነኛ ካሰኘህ “የኢህአዴግ የቁልቁለት ጉዞ(2005_2010)” የብርሀነ ፅጋብን ወግ ብትሰልቅ፤ የጌታቸው ሽፈራውን” የሰቆቃ ድምጾች” በነካ እጅህ የአንዷለም አራጌንና የሀብታሙ አያሌውን ተከታታይ መጽሐፍት ብታነብ ወይም ስለ ህወሓት የተጻፈ ስንክሳር በድረ ገጽ ብትጎለጉል ውሸት፣ ሴራ፣ ጭካኔ፣ ማጭበርበር፣ አሪዎስነትና ዘረፋ የጋራ አካፋዩ ሆነው ታገኛቸዋለህ ። ከማገብት እስከ ዛሬው የአሻባሪው ህወሀት ተክለ ሰዕብናን ብታስስ ተነቅሷቸው ታገኛለህ ። የዛሬው መሰናዘሪያ የህወሓት ውሸትና ማጭበርበር ነውና እሱ ላይ የእጅ ፍሬን ልያዝ።
አሸባሪ ህወሓት የዛኔው ፋኖ ሲሰማራ ማለትም፤ ወደ “ትግል” ሜዳ ለመውጣት ሲወስንም ሆነ እንደወጣ ታሪክን፣ እውነትን፣ ሰንደቃላማን፣ አብሮነትን፣ ሰብዓዊነትን፣ ኢትዮጵያዊ ማንነትን፣ ፍቅርን፣ ሰውነትን፣ ፈጣሪን፣ ወዘተረፈ ሽምጥጥ አርጎ ክዶ የራሱን የፈጠራ ትርክት ነው የነበረው። የሀገሪቱን ታሪክ ወደ 100 አመታት አራክሶ፤ እውነትን ኅልቁ መሳፍርት በሌለው ውሸት ተክቶ፤ ሰንደቃላማን ጨርቅና የአንድ ሃይማኖት አርማ ነው ብሎ፤ አብሮነትን በመለያየት ቀይሮ፤ ሰብዓዊነትን በአረመኔነት ለውጦ፤ ኢትዮጵያዊ ማንነትን በጎሳ ለንጥቆ፤ የትግራይ ሕዝብ ጠላት የአማራው ገዥ መደብና ኦርቶዶክስ ነው፤ ፈጣሪን ክዶ ራሱን ወደጣኦትነት ቀይሮ እስከማምለክ የደረሰ ወዘተረፈ የራሱን ተረክና እውነት በይኖ በራሱ አለም ሲዳክር የኖረ ባተሌ ጉጅሌ/ስብስብ ነው። የእውነትን፣ ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታን፣ የዜጋውን የልቦና ውቅርና የታሪክን ፈለግ ተከትሎ ርዕዮት አለም መንደፍ የማታገያ ስልት መትለም ሲገባው፤ በተቃራኒው እውነትን፣ ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታን፣ የዜጋውን የሞራል ልዕልና፣ የልቦና ውቅርና ታሪክ በድቡሽት ላይ ለተቀለሰ ማንፌስቶው እንዲመጥኑ እጃቸውን ጠምዝዞና አጣሞ እንደገና መበየኑ እና ካፈርሁ አይመልሰኝ በሚል በስሁት መንገዱ ልምምዱን መቀጠሉ ጎልማሳው ከሀዲና መልቲ አድርጎታል ። ከጥፋቱና ከዕድሜው የማይማር ልበ ቢስ። ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉት ያለፈውን ታሪክን የመርሳት አባዜ ስላለብን ዋና ዋና ክህደቶቹን ብቻ እናስታውስ።
ቢያንስ ወደ ስምንት ሺህ አመት የሚጠጋ ቀደምት ሀገረ መንግስትና ታሪክ ያላትን ጥንታዊት ሀገር በልኩ ካሰፋው የታሪክና የርዕዮት አለም ቁምጣ ጋር ለማስኬድ ሲል እንደ ኮለምበስ ወይም ቫስኮ ደጋማ በአሳሽ የተገኘች ሀገር ይመስል ታሪኳን የ100 አመት ነው ሲል በአደባባይ የካደ የነውረኞች ስብስብ ነው። የዛሬዋ ኢትዮጵያ ቅርጽ ስሪት በአጼ ምኒልክ የተፈጠረ ነው ሲል ሀፍረት አልፈጠረበትም። በጎሳ ላይ የተመሰረተው አስመሳይ ፌደራሊዝም የተዋቀረው በዚህ ክህደት ላይ። የአንድ ሀገር ጥንታዊነት ተካደ ማለት የቁጥር ጉዳይ ብቻ አይደለም። የዜጎችን አብሮነት፣ የሀገሪቱን የሀገረ መንግስት ልምምድና አጠቃላይ ማንነቷን የሚያኮሰምን ክህደት ነው። ዜጋው በሀገሩና በታሪኩ ያለውን እምነት ለመሸርሸርና አንድ አርገው አጋምደው ያቆዩትን ወረቶች ለማስጣል የተከናወነ መሰሪ ክህደት ነው። ይህ ብቻ አይደለም ለሀገሪቱ ያለው ጥላቻ ግዘፍ ነስቶ የተገለጠበት ደባ ጭምር ነው። በአለማችን ላይ የሀገሩን ታሪክ አሳንሶ ሽንጡን ይዞ የተከራከረ እና አምርሮ የሚጠላትን ሀገር በአፈሙዝ የገዛ እንደ ከሀዲው ትህነግ ያለ ቡድን የለም። ይህን ጥላቻውን አገዛዝ ላይ እያለ በሚያራምዳቸው ስሁት ፓለቲካዊ አቋሙና አይን ያወጣ ዘረፋው አረጋግጧል። ከገዢነቱ በሕዝባዊ ማዕበልና በለውጥ ኃይሉ ከተሽቀነጠረ በኋላ እኔ ረግጬ የማልገዛትና የማልዘርፋት ሀገር ትውደም በሚል የሔደበትን እርቀት ታሪክም ትውልድም በቁዘማ ሲያስታውሰው ይኖራል።
አፌን ሞልቼ ከሀዲውና እፉኝቱ ትህነግ የጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሰሜን ዕዝ ጥቃት እና የጥቅምት 30ን የማይካድራን ትውልድና ታሪክ ይቅር የማይለውን የክፍለ ዘመኑን ታላቅ ክህደትና ጭፍጨፋ ለመፈጸም ዝግጅቱንና ልምምዱን የጀመረው ከደደቢት ውልደቱ ከየካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም አንስቶ ነው የምለው ለዚህ ነው። ለግማሽ ክፍለ ዘመን በዝግ የተዶለተበት የክህደት ደባ። የጭካኔ ልምምድና ዝግጅት ውጤት። የመከላከያ ሰራዊት ትጥቅ፣ ስንቅና ከባድ መሳሪያ በትግራይ ክልል እንዲደራጅና እንዲከማች የተደረገው የጥቅምት 24ቱን ክህደት ታሳቢ በማድረግ ነው። “ …በነገራችን ላይ የመከላከያ ትጥቁም ስንቁም ለአመታት እዚያ ብቻ እንዲከማችበት የተደረገበት ምክንያት አሁን የመጣው ለውጥ ቢመጣም ባይመጣም፤ የሀገሪቱ የመከላከያ እዚያ ብቻ እንዲሆን ታስቦ ነው። ምንም ጥርጣሬ ሚስጥርም የለውም። …” ይህ የክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ ትንተና ከፍ ብሎ ክህደቱ ቀድሞ የታሰበበትና የተመከረበት ስለመሆኑ ያነሳሁትን ሙግት ያጠናክርልኛል። የክህደት ልምምዱ አሀዱ ብሎ ከጀመረበት እስከ ፍጻሜው የሚመዘዙ ቅጥልጥል ክህደቶችን እንዳሉ ልብ ይሏል።
ይህ እፉኝት ጉጅሌ በሀገርና በሰሜን ዕዝ በፈጸመው ክህደትና ጭፍጨፋው መንግስት ተገዶ ወደ የህልውናና የሕግ የበላይነትን የማስከበር ዘመቻ ገብቶ ድባቅ ሲመታ ወዲያው የሀገርንና የመንግስት ስም በሀሰተኛና በተዛባ መረጃ ለማጠልሸት የተቀናጀና የተናበበ ዘመቻ ሲከፍት ጊዜ አልወሰደበትም ። የሀገሪቱን ሚዲያ ሲያዘምርና ሲያስጨበጭብ ኖሮ የራሱን መደበኛና ማህበራዊ ሚዲያ ግን በአራት ትላልቅ ዘርፎች አደራጅቷል። እርሱም፦ 1ኛ. መደበኛ ሚዲያ 2ኛ. ማህበራዊ ሚዲያ 3ኛ. አለማቀፍ ሚዲያና ተቋማት 4ኛ. ስፒን ዶክተርስና ሎቢስትስ ናቸው። የመጀመሪያው ማለትም እነ ትግራይ ቴሌቪዥንን፣ ድምጺ ወያኔን፣ ወይንን፣ ትግራይ ሚዲያ ሀውስን (TMH )፣ ትግራይ ፈርስትን፣ አይጋ ፎረምን፣ ትግራይ ፕሬስን፣ ቮይስ ኦፍ ትግራይ፣ ትግራይ ኦን ላይንና አውራምባ ታይምስ የሚያካትት ሲሆን ሁለተኛው ዲጂታል ወያኔ አካልና ምን አልባት በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የዲጂታል ጭፍራ ያለው ሲሆን በአንድ ለአምስትና በአንድ ለሃያ ተደራጅቶ በማህበራዊ ሚዲያ በተለይ በፌስ ቡክ፣ በቲዊተር፣ በዩቲውብ፣ በቴሌግራም፣ ወዘተረፈ የተዛባ መረጃን፣ ውሸትን፣ ጥላቻን፣ ልዩነትን፣ መጠራጠርን፣ ሴራን፣ ወዘተረፈ የሚነዛ ተከፋይና ምንደኛ ስብስብ ሲሆን፤ ሶስተኛው አለማቀፍ ሚዲያውን የተዛባ መረጃ የሚመግብ ምድብተኛ ነው። አራተኛውና ሶስተኛው ምድብተኛ ተመጋጋቢ ናቸው። በዚህ ምድብ ነጮች ስፒን ዶክተርስና ሎቢስትስ ( spin doctors & lobbyist ) የሚሏቸው ሲሆን አላማቸው እንደቅደም ተከተላቸው አንድን ርዕሰ ጉዳይ እነሱ ከሚፈልጉት አቅጣጫ አንጻር እንዲተረጎምና እንዲበየን ጥረት ማድረግ ሲሆን ሎቢስቶች ደግሞ ከፍተኛ ገንዘብ እየተከፈላቸው የመንግስት ባለስልጣናትን፣ የምክር ቤትና የሴኔት አባላትን በማግባባትና በማባበል ከቀጠራቸው ወይም ከከፈላቸው መንግስት ወይም ቡድን ጎን ለማሰለፍ ግፊት የሚያደርጉና የሚያግባቡ ናቸው ። እነዚህ አካላት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ አለማቀፍ ሚዲያውንና እንደ መንግስታቱ ድርጅት ያሉ አለማቀፍ ተቋማትን የሚመግቡና ተጽዕኖ የሚፈጥሩ ናቸው።
ሀገራችን ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ፈጣሪ አብዝቶ ይጠብቅ !
አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2013