በኢትዮጵያ ታሪክ በተለያዩ ጊዜያት እያበቡ የመጡ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን በማስተናገድ በኩል የትምህርት ተቋማትን ያህል የላቀ ሚና የተጫወተ የለም ቢባል አልተጋነነም። ስለ ዓለም የፖለቲካ ሁኔታና በአገሪቱ ስለሚኖረው አንደምታ እንዲሁም ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታን ለመቀየርና ለውጥ ለማምጣት ከሌሎች የአገሪቱ ዜጎች በተለየ ሁኔታ ዘመናዊ ትምህርትን ለመቋደስ የበቁት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከፍተኛ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በማድረግ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ታሪክ ይመሰክራል። በተለይም በ1960ዎቹ በተካሄዱት አጠቃላይ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ተቋማቱ ዋነኛ ተሳታፊ ነበሩ።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተራማጅ ተማሪዎች በወቅቱ የነበረውን የዘውዳዊ አገዛዝ በግልጽና በጽኑ በመቃወም በአገሪቱ አብዮት እንዲነሳና በመላ አገሪቱ እንዲቀጣጠል ያበረከቱት አስተዋጽኦ ምን ያህል እንደነበር ጸሓፍት በከተቡት ብዕራቸው ይገልጹታል። ይህም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት መነሻ ለምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር፤ ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ የአገልግሎት ፓኬጅም ሆነ ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች በዘመናዊ አኳኋን እንዲመነደጉ ከማድረግ በተጨማሪ ተቋማቱ የአንድን ሀገር ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በማዘመን ጥያቄዎችን ወደ ለውጥ በማንደርደር ረገድ ያላቸውን ሚና ያመላክታል። በተቋማቱ እነዚህንና መሰል ውጤቶችን ማየት የሚቻለው ተቋማቱ በአግባቡ ከመደራጀት፣ ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ መቋቋም እንዲሁም የትምህርት ጥራትን ዐቢይ ትኩረት ማድረግ ከመቻል እንደመነጩ ይታመናል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶቻችን ጉዞ የትናንት መልኩ ከዚህ ፍጹም የተለየ ሆኗል። በመንግስትም ሆነ በግሉ ዘርፍ የተመሠረቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በቁጥር አድገው በጥራት ወርደው ዛሬ ላይ ቆመዋል።
በሀገራችን ባለፉት 20 ዓመታት መንግሥት የትምህርት ተደራሽነቱ ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ መጓዙን የትምህርት ባለሙያዎች እንደ ስህተት ያነሱታል። ጥራትን መሠረት አድርገው የሚጓዙ ተቋማት እንዳይፈጠሩም ማድረጉን ይገልጻሉ። በአብዛኛዎቹ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የሚታየው እንዝህላልነት እየጨመረ በመሄዱ ለተማሪ እውቀትን ለመሸጥ መቋቋማቸውን እስከመዘንጋት አድርሷቸዋል ይላሉ። ስለዚህ በጥራት የማይደራደሩ፣ በትምህርት ጥራታቸው ሊመሠገኑ የሚገባቸው ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለመፍጠር ከታሰበ ራሱን የቻለ ገለልተኛ ተቋም መመሥረት ያስፈልጋል። በተገቢው መንገድ የሚጓዙትን አንጽሮ፣ የሚያወጣ በትምህርት ጥራታቸው ለውጥ ያላመጡትን ተከታትሎ ርምጃ መውሰድ የሚያስችል ማዕቀፍ መዘርጋት ያስችላል። በመንግሥትም በሀገሪቱ በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት መጓደል እንቅልፍ የነሳው ችግር መሆኑን በማመን ለመፍትሄው እንደሚሰራ በተደጋጋሚ ሲናገር ይሰማል። በተለይ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ የተለያዩ ማሻሻያዎች የተደረጉ ሲሆን፤ ከሰሞኑ ደግሞ የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ምክር ቤትን እንዲመሠረት መደረጉ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ እንደሚሆን ታምኗል።
የትምህርት ጥራት ችግርን ለመፍታት የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ምክር ቤት ማቋቋም አስገዳጅ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። ምክር ቤቱ በሀገሪቱ የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራትን ቀጣይነት ባለው መልኩ እንዲያረጋግጡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ምሩቃንን ለማፍራት ፋይዳ የሚኖረው ገለልተኛ ምክር ቤት መሆኑ ተነግሯል። በሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ በአዲስ አበባ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ በተዘጋጀው የከፍተኛ ትምህርት ጥራት ምክር ቤት ምሥረታ ላይ የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሣሙኤል ኡርቃቶ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ይህንኑ አረጋግጠዋል።
ዶክተር ሣሙኤል እንደተናገሩት በእውቀትና በክሂሎት የዳበሩ ተማሪዎችና ተፈላጊነት ያላቸው ባለሙያዎችን ማፍራት ይጠበቅብናል። የትምህርት ጥራት ችግሮችን ለመፍታት የሙያ ማህበራትን ያሣተፈ የትምህርት ጥራት ምክር ቤት ተቋቁሟል። በምክር ቤቱም የሙያ ማህበራት የትምህርት ጥራትን በየጊዜው እንዲፈትሹ፣ ጥናት እንዲያካሄዱና ስታንዳርድ እንዲያወጡ የሚያደርግ ይሆናል። የትምህርትና ሥልጠና ፕሮግራሞች የሀገሪቱን ፍላጎትና ገበያ ማዕከል ያደረጉ እንዲሆኑ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርትና ሥልጠና ጥራትና አግባብነትን ለማስጠበቅ እንዲቻል የሚኖረው ሚና ወሣኝ ነው። ከዚህ ባሻገር የሀገሪቱ የትምህርትና ሥልጠና ፕሮግራሞች በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲመዘኑ እና ተቀባይነት እንዲኖራቸው የሚያግዝ ይሆናል።
የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሩቃን በአገር ውስጥና በውጭ ተፈላጊነታቸው እንዲጨምር የትምህርት ጥራት ችግርን ለመፍታት እየተሰራ ስለመሆኑ ዶክተር ሣሙኤል ገልፀዋል። የተቋቋመው ምክር ቤት የትምህርት ጥራት ችግርን በመፍታት ከተቋማቱ የሚመረቁ ተማሪዎች በአገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊነታቸው እንዲጨምር በማድረግና ሌሎች ትላልቅ ሥራዎች ይሰራል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ የሙያ ማህበራት የትምህርት ጥራት ምክር ቤት ማቋቋማቸውን ያመላከቱት ደግሞ የኢትዮጵያ የሙያ ማህበራት ፕሬዚዳንት ዶክተር ቢቂላ ወርቅነህ ናቸው። በዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ራሳቸውን እንዲገመግሙ፣ ፕሮግራሞቻቸውን እንዲቃኙና ችግሮች እንዲፈቱ የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል። ምክር ቤቱ ጥራቱን የጠበቀ ቀጣይነት ያለው የጥራት ባህል እንዲፈጠር ማድረግ የሚያስችል ገለልተኛ መሆኑን ያስታወቁት ፕሬዚዳንቱ “የሰለጠነ የሠው ሀይል፣ ለምርምር ብቁ የሆኑ ተመራማሪዎችን ማፍራት፣ በብቃትና በጥራት የሚመሩ አመራሮችና የሁሉንም ማህበረሰብ ህይወት መለወጥ የሚችሉ ተደራሽና ፍትሃዊ የሆነ የትምህርት ጥራትን የሚያስጠብቅ ምክር ቤት ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል። በ2030 በአፍሪካ የታወቀ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ምክር ቤት ለመሆን ይሰራል” ሲሉ ነው አብራርተዋል።
በአጠቃላይ የምክር ቤቱ በይፋ መመሥረት ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ አጠቃላይ የትምህርት ጥራት ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ተነግሯል። ኢትዮጵያን የሚመስል የትምህርት ሥርዓት ለመገንባት እየተሰራ ያለውን ሥራም በከፍተኛ ደረጃ እንደሚደግፈው ይታመናል። በመሆኑም ምክር ቤቱ የሁሉም የሙያ መስኮች ማህበራት ውክልና ያለውና የኢንዱስትሪ ማህበራትንና ተቀራራቢ ሲቪክ ማህበራትን አካቶ የተደራጀ ነው። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተቋማዊ ነፃነት ሲያገኙ፤ ተጠያቂነታቸው ለጥራት መለኪያ እንዲሆን ነፃና ገለልተኛ አካል ሆነው በትምህርት አግባብነት ማረጋገጥ ሥራ ሂደት ሙያ ነክ ተግባራትን በማገዝ በንቃት እንደሚሣተፉም ይጠበቃል። የሣይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከምክር ቤቱ ጋር በጋራ በመሆን በሚያደደርገው ጥናት መሠረት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ላይ ከምደባ ወደ ቅበላ የሚሸጋገሩበትን ሂደት የሚጀምሩ መሆኑ ተነግሯል።
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2013