ከወራት በፊት ለሀገር ዳር ድንበር ዘብ የቆመውን የመከላከያ ሰራዊት ነክቶ አይቀጡ ቅጣት የተቀጣው የህወሓት አሸባሪ ቡድን ዛሬም በመሸገበት ሆኖ እንደለመደው ሀገር ለማፍረስና ህዝብ ለማስጨነቅ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት በመፍጨርጨር ላይ ይገኛል:: ባለቀና በተሟጠጠ ተስፋ ውስጥ ሆኖ የለመደውን ትላንትና ዛሬም ሊደግመው በተመሸገበት የዱር ጫካ ውስጥ ሆኖ ይታትራል:: የሽብር ቡድኑ ከሰሞኑ ባደረገው በቴክኖሎጂ የታገዘ ሚስጢራዊ ስብሰባ በሀገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች ላይ ግጭቶችን በማስነሳት ሞትና የንጹንን እልቂት እንደ ትልቅ አላማ በመጠቀም የግል ጥቅሙን ለማስከበር ጥረት ለማድረግ ማቀዱን የሚጠቁሙ መረጃዎች ይፋ ሆነዋል::
ከወደቀበት ተፍጨርጭሮ ለመነሳት እና በተለያዩ ሀገራት ያሉ ርዝራዥ ተከታዮቹን በማስተባበር ለዳግም ጥፋት እየተሰናዳ እንደሆነ አንዳንድ አመላካች ሁኔታዎች ተገኝተዋል:: ስድስት ቀናትን በፈጀው ሚስጢራዊ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያንና የህዝቦቿን ጥቅምና ሉአላዊነት የሚጋፋ አንድን ወገን ብቻ በሚጠቅም የዳግም ጥፋት ሴራ ላይ ከግብረ አበሮቹ ጋር ተነጋግሯል:: በህዝቦች መካከል የብሄር ግጭቶችን በማስነሳት የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ በመቀልበስ ሀገሪቱን ወደ ለየለት የርስ በርስ ብጥብጥ በማስገባት ሁከት መፍጠር ከተወያዩባቸው ነጥቦች ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው:: ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገራት ጋር በማቃቃር ወደ ጦርነት እንድትገባ ለማድረግ እና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ከሆኑት ግብጽና ሱዳን ጋር በማበር እንደ አይናችን ብሌን የምናየውን የህዳሴ ግድብና ሌሎች መሰረተ ልማቶቻችን ዋስትና እንዳያገኙ በማድረግ ሀገሪቱ የሁከትና ትርምስ ማዕከል እንድትሆን ማቀዱን የሽብር ቡድኑ ካደረገው ሚስጢራዊ ስብሰባ መረጃዎች ተገኝተዋል::
በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ የአሜሪካንንና የሌሎች ሀገራትን ጣልቃ ገብነት በመቀበል እንዲሁም በክልሎች መካከል ጠብን በመፍጠር በዚህ ሁሉ ውስጥ ትግራይን ራስ ገዝ ለማድረግ ሴራ እየሸረቡ እንደሆነም ተደምጧል:: ይሄ ብቻ አይደለም መዲናችን አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎችም አካባቢዎችም የመሬት ጥያቄዎች እንዲነሱ በማድረግ የተንኮል ሴራቸውን ሀ ብለው ጀምረዋል:: ሁላችንም እንደምናስታውሰው ከጥቂት ወራት በፊት ይሄው አሸባሪ ቡድን በማይካድራ በንጹሀን ዜጎች ላይ የወሰደው ዘግናኝ ድርጊት ለብዙዎቻችን የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው:: የቆሰለው ልባችን ሳይድን ራስን ለሌላ ወንጀል ማዘጋጀት ምን ማለት እንደሆነ ህዝብ ፍርድ ሊሰጥበት ይገባል:: በአሸባሪው ህወሓት የደረሱ ጥፋቶችና ዕልቂቶች ትላንትን በመጥፎ ከሚያስታውሱን አዳፋ መልኮቻችን ውስጥ አንዱና ዋነኛው ነው:: ዛሬም ፊታችንን ወደ ምስራቅ አዙረን፣ እጆቻችንን ለስራ፣ አእምሯችችን ለልማት ባዘጋጀንበት ሰዓት ላይ የተለመደ የተንኮል ሴራውን ሊደግም ከሰው በላ አውሬ ወዳጆቹ ጋር ጫካ ሆኖ በመምከር ላይ እንደሆነ ስንሰማ ከመገረም ሌላ ምን እንላለን::
በታሪክ እንደምናውቀው ኢትዮጵያን ነክቶ በሰላም የኖረ የውጪም ሆነ የውስጥ ጠላት የለም:: አብዛኞቹ በለኮሱት እሳት ሲቃጠሉ ያየንበት በርካታ ጊዜአቶች ነበሩ:: ዛሬም የምናየው ተመሳሳይ ነገር ነው:: በኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን ያነሱ ሁሉ ዳግም ላይነሱ የሚደርቁበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ልክ እንደኔ ብዙዎቻችሁ የምታምኑት እውነት ይመስለኛል፤ ደግሞም ነው:: በብርሃናችን ዋዜማ ላይ ከእርምጃችን ሊገታን የመጣን ማንኛውም ምድራዊ ሀይል ለመታገስ አቅሙ የለንም:: ትዕግስቱም ሞራሉም የለንም:: ይህ የሁላችንም የጋራ እውነት እንደሆነ አምናለው:: መንግስት ራሱን በማደስ ለሀገርና በህዝብ ቅድሚያ ሰጥቶ ለጋራ ለውጥ እየተጋ ባለበት በዚህ የመንጋት ዘመን ላይ ወደ ትላንት ሊመልሰን የሚሞክረን ማናቸውንም ነገር የምንታገስበት ሙጣጭ አቅም አይኖረንም::
ሀገራችን ኢትዮጵያ በህወሓት የስልጣን ዘመን በርካታ ግፍና በደሎችን ስታስተናግድ ኖራለች:: የህዝቦች ጥያቄ ሳይመለስ እጅግ ጨቋኝ በሆነ ስርዐት ውስጥ አልፋለች:: ይህ የትላንት ግፍና መከራ በምንም አይነት መልኩ እንዲደገም አንሻም:: ለጋራ ጥቅም በጋራ በመቆም ህወሓትና መሰል የሀገር ጠላት የሆኑ ባንዳዎችን ታግለን የመጨረሻው እስትንፋሳቸው እንዲቋረጥ ማድረግ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ነው:: እኛም ሆነን ሀገራችን ትላንትን ስናስብ የሚቆጨን ብዙ ነገር አለ:: ይሄ ነው የምንለው መልካም ነገር በትላንትናችን ውስጥ አልተጻፈም:: ራሳቸውን እንደ ልክና ፍጹማን በሚያዩ አንባ ገነን ጨቋኞች አሳራችንን ስንበላ ከኖርነው ትላንት ሌላ በመልካም የሚጠራ አንድም የትንሳኤ ቀን አልነበረንም:: በርካታ ግፍና በደሎችን የኢትዮጵያ የትላንትና መልኮች ሆነው ኖረዋል:: የቀደመ ቁስላችን ሳይድን ከሞቱበት አንሰራርተው ሌላ ቁስል ሊጨምሩብን ለሚነሱ ከሀዲያን ምህረት የለንም:: በርሀብና በጦርነት አለም ያውቀናል:: በድህነትና በኋላ ቀርነት ከአለም አንደኛ ነን:: ድርቅና ርሃብ ያልነካን ጊዜ የለም:: ይሄን ሁሉ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆነ መከራችንን ታቅፈን በእውቀታችን ሀገር ለመለወጥ ከመስራት ይልቅ ሀገር ለማውደም የምናደርገው ስውር ትግል ይገርመኛል::አሸባሪው ህወሓት ከእንግዲህ ነፍስ የለውም:: አይደለም ህወሓት ቀርቶ ከእንግዲህ አሜሪካና ሌሎች ሀያላን ሀገራት እንኳን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ሀይልም መብትም የላቸውም:: አሸባሪው ህወሓት መሬት ልሶ የሚነሳ ከሆነም ለውጥና ንጋት የናፈቃቸው እጆች በአንድነት ተያይዘው እንደሚጠብቁት ስነግራችሁ ከልቤ ነው:: ከትላንት እስከዛሬ ስር በሰደደ የእኔነት ስሜት ሀገር ሲያወድም ቆይቷል:: ያወደማትንም ሀገር በይቅርታ ተጋግዘን እንድንገነባ ሲጠየቅ አሻፈረኝ ብሎ አፈገፈገ:: ጥንት እንደለመደው በድሀ ልጅ ሞትና በወጣቱ ጉስቁልና በሀይልና በጉልበት ስልጣን ለመያዝ ሲሞክር በተባበሩ ክንዶች አፈር ከድሜ በላ:: ይሄው አሁን ከውድቀቱ በኋላ ሀገራችን የተስፋ ብርሀኗን አየች:: ይሄው ነጋልን..:: በዚህ ብርሃን ውስጥ ሳለን ነው እንግዲህ አሸባሪው ህወሓት ለሌላ ጥፋት እየተዘጋጀ ያለው::
በብዙዎቻችን ልብ ውስጥ እንዳይመለሱ የምንፈልጋቸው በርካታ ትላንትናዎች አሉ:: የሞትንባቸው፣ የተጎሳቆልንባቸው፣ ብዙ ነገር የሆነባቸው አምናዎች በእያንዳንዳችን ትላንትናዊ ገጽ ውስጥ ጥቁር ለብሰው አሉ:: በእያንዳንዳችን ህይወት ውስጥ በህወሓት የተጻፈ ክፉ መልኮች አሉ:: እኚህ ትላንትናዎች፣ እኚህ ወያባ መልኮች፣ እኚህ ክፉ ቀኖቻችን ብሩህ ባልንው ዛሬ ላይ ዳግም እንዳይመጡ ለራሳችንም ሆነ ለሀገራችን ዘብ መሆን ምርጫ የሌለው ጉዳይ ነው:: እንደ ትላንት ያለ የጨለማ ዘመን ዳግም እንዳይመጣ ከእያንዳንዳችን የሚዋጣ የሀሳብ መዋጮ አለ:: ከምንም በላይ የሰላምን ዋጋ የተረዳንበት ጊዜ ላይ ነን:: ከምንም በላይ ሰላም ወጥቶ ሰላም መግባት ያለውን ትርፍ ያወቅንበት ጊዘ ላይ ነን:: ከምንም በላይ ሰውነት ዋጋ እንዳለው የተማርንበት ሰሞን ላይ ነን:: በዚህ የሀሳብ ለውጥ ውስጥ አሻግረን ያየናት አዲስ ኢትዮጵያ አለች:: በዚህ የሀሳብ መታደስ ውስጥ አሻግረን ያየንው ልማትና ብልጽግና አለ:: ይሄ ሁሉ እውነት የሚሆነው በውስጥም በውጪም የተነሱብንን የጋራ ጠላቶቻችንን በጋራ ታግለን መጣል ስንችል ነው:: የታደሰ ማንነታችንን ወደ ትላንት ለመውሰድ የውሸት ትርክት ፈጥረው ሊያባሉን ቀን ከሌት የሚሰሩ የህወሓት ቅጥረኞች አሉ:: ንጋታችንን ሊያጨልሙ የበግ ለምድ ለብሰው በአውቅልሀለው የመጡ..እየመጡም ያሉ በርካታ ጡት ነካሾች አሉ:: የጀመርንው የለውጥ ጉዞ እስከፍጻሜው እንዲጓዝ ሁላችንም ሀላፊነት አለብን:: ብርሀናችን ሩቅ እንዲያበራ ጨለማ ለበስ ከሆነ ከሀዲያን ራሳችንንም ሆነ ሀገራችንን በንቃት መጠበቅ ይኖርብናል::
እኛ እያለን በሚል የከሰረ አመለካከት በጀመርናቸው የስኬት ድሎች አይናቸው ደም የለበሰ ብዙ ጠላቶች ከዚም ከዛም አሉ:: ለውጥ ያመጣ ነጻነትና እኩልነታችንን በማጠልሸት ዳግም ወደ እንጦሮጦስ ከተውን በስቃያችን ሊስቁ ጥርሳቸውን የሚፍቁ እንዳሉም ልብ ልንል ይገባል:: በህዝባችን ተሳትፎ በአጭር ጊዜ ውስጥ ባመጣንው ሀገራዊ ለውጥ ተስፋ ቆርጠው የመጨረሻ እድላቸውን በመጠቀም ሊያውኩን የሚሞክሩ አሉና ልንበረታባቸው ይገባል እላለሁ:: በሁሉም መስክ ከሩጫችን ሊያደናቅፉን ወጥመድ የሚዘረጉብን ከእኛው አብራክ የወጡ ከሀዲያን እንዳሉ በማሰብ በንቃት መቆምን ልምድ ማድረግና ጠላቶቻችንን ማሳፈር መቻል አለብን:: ደግሞም ኢትዮጵያዊነት ማሸነፍ ነው:: ኢትዮጵያዊነት ከጥንት እስከዛሬ በበብዙ መከራ ውስጥ ያለፈ ግን ደግሞ አሸናፊ ማንነት ነው:: ሊቀ ነብያት ሙሴ እስራኤላዊያንን ከግብጽ ባርነት መርቶ ያወጣው በኢትዮጵያዊው ካህን በዮቶር ጥበብ ተመርቶ ነበር:: በተለያየ ጊዜ ሊጥሉን መረብ በዘረጉብን ጠላቶቻችን ላይ ተረማምደን አሸንፈን እናውቃለን:: በተለያየ ጊዜ የኢትዮጵያን ኋላ መቅረት ከሚመኙ ከሀዲያን ጋር ተዋግተን ረትተን እናውቃለን:: በተለያየ ጊዜ ሳንነካቸው ነክተውን ተዋርደው የተመለሱ ብዙዎች ናቸው:: የአሸባሪው ህወሓትም ታሪክ ከዚህ የዘለለ አይደለም::
አሸባሪው ህወሓት የማይወዳትን ሀገር ከመምራቱም ባለፈ ታሪካዊ ስህተት ፈጽሞ ነው ከስልጣን የተባረረው:: እኔ ሳውቅ እንኳን አደገኛ የሚባሉ ውሸቶችን ካለፈው ገዢ መንግስት ነበር የተማርኩት:: እስካሁን ድረስ ብዙ ውሸቶችን ሰምቻለው:: ፈጽሞ ውሸት የሆኑ በእውኑ አለም ስለመኖራቸው የሚያጠራጥሩ በርካታ ማጨበርበሮችን በፊልምም አይቻለው:: በታሪክም ሰምቻለው ህወሓት እንደሚፈጥራቸው ያሉ ውሸቶችን ግን በየትም አልሰማሁም:: በነገራችን ላይ በህወሓት የስልጣን ዘመን ላይ ያለው የዘጠናዎቹና የሰማኒያዎቹ ትውልዶች የህወሓት ዱላ ያረፈባቸው ናቸው:: ይሄ ትውልድ በትክክል እንዲያስብና ተምሮና ሰልጥኖ ሀገርና ህዝቡን እንዲያገለግል የስነ ልቦና ግንባታ ያስፈልገዋል ባይ ነኝ:: ያለፉት የኢህአዲግ የስልጣን ዘመናት ለትውልዱ የፈየደለት አንዳች ነገር የለም:: ወጣቱ ውስጡ በተዘራ የጥላቻ ዘር ዛሬ ላይ እንደ እናትና አባቱ ማሰብም ሆነ መኖር አቅቶታል:: ያለፉት ሀያ ሰባት አመታት ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው እጅጉን የበዛ የጨለማ ዘመናት ነበሩ እላለው:: ያለፈው ጊዜ ሀገርንም ትውልድንም እንዳፈረሰ ነው የማምነው:: የታመመ ትውልድ፣ ሊፈርስ ያለ ሀገር ትቶልን ነው ያለፈው:: የዛሬ አዳፋ መልኮቻችን በትላንት ቀለም የተሳሉ የአዳፋ እጆች ውጤት ነው:: ትላንታችን ምን ያክል አዳፋ እንደነበረ ዛሬአችንን ማየቱ በቂ ነው:: በክፋት እጆች ተወላግደንና ተጨማደን ተስለናል.. ዛሬ ላይ ብሩካን እጆች ያስፈልጉናል:: ከትላንት እስከዛሬ ኢትዮጵያዊያን በጠላቶቻችን ፊት ሀቅን ይዘው ነው የምንከራከረው:: ጀግንነታችን እንዳለ ሆኖ የማንወድቀው በዚህ ሀቅ ውስጥ ስለቆምን ነው እላለው:: ሊጥሉን ተንኮል በሚሸርቡብን ከሀዲያን ፊት እንደ አንበሳ በክብር ቆመን እናውቃለን:: አሁንም ቢሆን መንገድ እየዘጉብን ከጉዟችን ሊያዘገዩን በሚፈልጉ የኢትዮጵያ ጠላቶች ፊት በክብር መቆማችን ይቀጥላል::
በዚህ ሁሉ የጠላት ሴራ ውስጥ በርትተን በመራመድ ጀግንነታችንን እስከመጨረሻው ማሳየት ይኖርብናል ብዬ አምናለው:: አንድነታችን ከዛሬ አልፎ ነገም የሚዘልቀው እንደ ህወሓት ያሉ አሸባሪ ቡድኖችን ታግለን ስንጥል ብቻ ነው:: በማይወዱት ሀገርና ህዝብ መካከል ተፈጥረው ሀገር ለማውደም ከሚሰሩ ከነሱ ታሪካችሁን ስትጠብቁ፣ ሀገርና ህዝባችሁን ስትታደጉ ያኔ የእውነት ጀግና ትባላላችሁ:: የነአብዲሳ አጋና የነበላይ ዘለቀ ጀግንነት ከትውልድ ትውልድ የሚዘከረው እኮ በሀገራቸውና በርስታቸው ከመጣው የጠላት ሀይል ጋር በመታገላቸው ነው:: እነዘርዐ ደረስ፣ እነባልቻ አባ ነፍሶ ዛሬም ድረስ የሚታወሱት እኮ ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ክበር በመቆማቸው ነው:: ከኢትዮጵያ ጠላቶች ከማናቸውም ጋር ለመጋፈጥ ራሳችሁን ለትግል አዘጋጁ እያልኩ ላብቃ:: ቸር ሰንብቱ::
ዘለዓለም የሳጥን ወርቅ (የእፀ ሳቤቅ አባት)
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2013