ዘለግ ያለ ቁመት ለስለስ ያለ አንደበት ያላቸው የሰባ ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ ናቸው። ለአስራ ስድስት ዓመታት ኑሯቸውን በአሜሪካ ካደረጉ በኋላ አሁን ወደ እናት ምድራቸው ተመልሰዋል። አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሀረር፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በደብረ ማርቆስ ከተማ ከተማሩ በኋላ ከባህር ዳር ፖሊቴክኒክ ኢንስቲትዩት በኬሚስትሪ ዲፕሎማ አግኝተዋል፤ በመቀጠል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኬሚስትሪ የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝተው ለዓመታተት በቅጥር ሥራ ላይ ቆይዋል – አቶ ብርሃነ መዋ::
አቶ ብርሃነ፣ የግል ሥራ ፈጣሪ የወቅቱ ኢንተርፕረነርም ናቸው። ፖሊ ኢንዳስትሪያል ኬሚካልስ የሚባለው ድርጅት መስራች ሲሆኑ፣ በጣም ትልቅ ያልሆነ፤ ነገር ግን ለአገራችን የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች መለዋወጫ የሚሆን ግብአት በማቅረብ በሚያደርገው ድጋፍ ላቅ ያለ መስሪያ ቤት ነው::
በማህበራዊ ተሳትፎ ደረጃም የኢትዮጵያ የኬሚስትሪ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት በመሆን ለአራት የተለያዩ ጊዜያት ተመርጠው ሠርተዋል። የኢትዮጵያ የግል ኢንዱስትሪ ማህበር ውስጥ በፀሐፊነትና በዋና ፕሬዚዳንትነት አገልግለዋል። ከዚያ በኋላ በአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በመጀመሪያ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ቀጥሎ በአዲስ አበባና በኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንትነት ከሀገር እስከ ወጡበት ጊዜ ድረስ ሲያገለገሉ ቆይተዋል። ከሀገር ከወጡም በኋላ የቅንጅት ፓርቲን በመቀላቀል በሰሜን አሜሪካ የተቋቋመው የቅንጅት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ሆነው ለዓመታት ሠርተዋል። አቶ ብርሃነ መዋን ለዛሬ የአዲስ ዘመን እንግዳ አድርገናቸዋል፤ መልካም ንባብ ይሁንልዎ።
አዲስ ዘመን፦ አቶ ብርሃነ መዋ ለቃለ ምልልሱ ፍቃደኛ ስለሆኑ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ስም ልባዊ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። እንኳን ወደ እናት ምድርዎ በሰላም መጡ።
አቶ ብርሃነ መዋ፦ እንኳን ደህና ቆያችሁኝ። እኔንም ለቃለ ምልልሱ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን፦ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በየዘመኑ የነበረው ገጽታ ምን ይመስላል?
አቶ ብርሃነ፦ ስለሀገራችን ኢኮኖሚ አጠቃሎ መናገር ይከብዳል። ስለ ኢኮኖሚ ስናወራ ግን ኢኮኖሚው ከሀገራችን ህዝብ ብዛት ጋር ከዓለም አቀፍ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ጋር ይገናኛል። ይህን ካልን ዘንዳ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ጊዜ የህዝቡ ብዛት አነስተኛ ነበር። አብዛኛው ሰው በእርሻ ላይ የተሰማራ ነው። ኢንዱሰትሪ ብዙም የለም፤ የነበረው በጣም ጥቂት ነው። መካናይዝድ እርሻም መጀመሩ ነበር። ከዚያ በኋላ የመጣው ደርግ ደግሞ የኢኮኖሚውን አቅጣጫ በመሰለው መልኩ ሊቀይር ችሏል። ሶሻሊዝምን የተከተለ ሀብት ማፍራት፣ ንብረት ማካበት፣ ሰው ቀጥሮ ማሠራትን እንደ ወንጀል ይመለከት የነበረ ስርዓት ነበር። በጊዜው በሀገሪቱ ኢንዱስትሪ ማቆጥቆጥ አልቻለም።
ግብርናው አካባቢ እንደዚሁ ያለውን የመሬት ስሪት በመቀየር ህዝብን የመሬት ባለቤት ለማድረግ መሬት ላራሹን ተግባራዊ ለማድረግ ደርግ የሄደበት መንገድ ያመጣው ውጤት መሬትን ላራሹ ማድረግ ሳይሆን መሬትን ለመንግሥት አድርጎታል። እንደዛም ሆኖ የባላባቱ ጫና ከገበሬው ላይ እንዲነሳ ሆኗል። በመሬት ባለቤትነት በኩል ያለውን ችግር ግን አልቀረፈውም። ኢንዱስትሪ አላቆጠቆጠም፤ ኢንዱስትሪም ቢኖርም መንግሥት እንዲቆጣጠረው ይፈለግ ነበር፤ ስለዚህ የግል ባለሀብቱ የለበትም ነበር። በደርግ ጊዜ ጥሩ የሚባል ነገር የተፈጠረው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ የመዋሃድ ሁኔታ አይታይም ነበር። የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ከባድ ነበር፤ እቃ ማስገባት አይቻልም፤ እቃ ውጭ ወስዶ መሸጥ አይቻልም፤ ይህ በተለይ እቃማስገባት አለመቻሉ የውጭ ምንዛሪ ጉድለት ሀገር ውስጥ በርካታ ነገሮች መሥራት በመሞከሩ የቴክኖሎጂ እድገት ተከናውኗል።
ማህበረሰቡ ከውጭ የሚገባለት እቃ ባለመኖሩ የቴክኒክና የሳይንስ እውቀትን መጠቀም ጀምሯል። እንዲያውም የኢንዱስትሪና የዩኒቨርሲቲ ግንኙነት እንዲኖር የምርምርና የማበልፀግ ሥራዎች በየቦታው እንዲኖር አድርጓል። እኔም የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ነበርኩ። የኔን የግል ሥራ ስጀመር ምንም ነገር ማስገባት ስለማይቻል ሀገር ውስጥ ካለ ከወደቀ ብረታ ብረት ለብዙ ፋብሪካዎች ችግር የሚፈታ የመለዋወጫ እቃ የሚያመርት ኩባንያ እንዲኖር ሆኗል። የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ፣ የሲሚንቶ ፋብሪካ፣ የቢራ ፋብሪካ፣ የለስላሳ ፋብሪካ እና ሌሎችም የድርጅቶች ደንበኞች ነበሩ:: እነዚህ ድርጅቶች የሚሠሩት 24 ሰዓት ሲሆን፣ ያላቸው መሳሪያ ሲሰበር መለዋወጫ እቃ በተለይም ደግሞ ከሀይድሮሊክ ጋር የተያያዘ ከሆነ ኦሮንግ ያስፈልገዋል:: ያ የጎማ ቀለበት ደግሞ ካልተገኘ ፋብሪካው መቆም አለበት:: አብዛኛው ከውጭ አገር ሲመጣ ግን የአገራችን አንዳንድ ፋብሪካዎች ማሽን መሥራት በማቆማቸው እቃውን ወይም መለዋወጫውን ማግኘት አስቸጋሪ ነው:: ድርጅቱ እውቀቱንና ግብአት በመጠቀም ሪቨርስ እንጂነሪግ (Re-Enginering) አድርገው ያንን እቃ አስመሰለው በመሥራት ፋብሪካዎች እና የመኪና ባለንብረቶች ሥራቸውን እንዲቀጥሉ በማድረግ ፋብሪካውን ከመዘጋት፣ ሠራተኛውን ከሥራ ማጣት፣ ተጠቃሚውን ደግሞ ከአቅርቦት ማነስ በመታደግ ለኢትዮጵያ ህዝብ ኢኮኖሚ የሚያደርጉት አስተዋፅኦ ቀላል አልነበረም::
በወቅቱ ሀገር በቀል የሆኑ ኢንዱስትሪዎች እንዲበዙ ሆኖ ነበር። ሳሙና ፋብሪካዎች፣ የዳቦ መጋገሪያዎች፣ የዘይት መጭመቂያዎች የመሳሰሉት እንዲኖሩ ሆኗል። በአጠቃላይ የኢኮኖሚውን እድገት ስንመለከት በመንግሥት ደረጃ ሙስና ስር የሰደደ አልነበርም። ሀብት በማካበትም ቢሆን የደርግ ባለሥልጣኖች ከሌላው የማህበረሰብ ክፍል የተለየ የጎላ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በራሳቸውም ይሁን በዘመዶቻቸው አልነበረም። ወደ መጨረሻ አካባቢ የደርግ መንግሥት ድብልቅ ኢኮኖሚ የሚል መንግሥት ብቻ ሳይሆን የግል ባለሀብቱም ኢኮኖሚው ውስጥ መካተት እንዲችል መሆኑ አምስት መቶ ሺህ ብር ካፒታል ኢንቨስት ማድረግ እንዲቻል መደረጉ የተለያዩ ሆቴሎች እንዲሁም የተወሰኑ ኢንዱስትሪዎች ብቅ ብቅ እንዲሉ አድርጎ ነበር።
ኢህአዴግ ሲመጣ የመሬት ስርዓትን በሚመለከት ምንም ለውጥ አለመጣም። ይህ ሲባል መሬት በመንግሥት ይዞታ ስር የነበረውን አሻሽሎ በቡድኖች ማለትም በብሄሮች ይዞታ ስር እንዲሆን አድርጎታል። በአጠቃላይ የመሬት ይዞታቸውን ብንመለከት መጀመሪያ ባላባቶች፣ ቀጥሎ መንግሥት ከዚያ ደግሞ ብሄሮች ሆኑ። በእነዚህ ሁሉ መንገድ ሲኬድ ግለሰቡ የለም፤ አይታይም። ይህ ማለት የመሬት ላራሹ ጥያቄ እስከአሁን እንዳልተመለሰ ይታያል። መሬት ደግሞ መሰረታዊ የኢኮኖሚ ጉልበት የሚፈጥር ነገር በመሆኑ በዚያው ልክ ችግሩ ሙሉ ለሙሉ አልተቀረፈም።
ኢህአዴግ ከመጣ በኋላ በደርግ ጊዜ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች፣ የተጠኑ ጥናቶች በእነሱ ላይ ነው እመርታ አድርጎ የተነሳው። በኔ እምነት ኢህአዴግ ሲመጣ ሀገሪቱን በጉልበት ማስተዳደር ከባድ እንደሆነ በመገንዘቡ በኃይል ለመቀጠል እንደማይቻል ሲያውቀው የኢኮኖሚ የበላይነት በፓርቲ ደረጃ ያስፈልጋል ብሎ አመነ፤ ከዚያም አልፎ እነዚህ በብሄር የተዋቀሩ የፓርቲው አካላት ማለትም እነ ህወሓት፣ ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደኢህዴን ኢኮኖሚው ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ኢኮኖሚው በከፍተኛ ደረጃ አቅጣጫውን እንዲቀይር አድርጎታል።
ሌላው ነጋዴ ከእነሱ ጋር መወዳደር እንዲኖርበት ሆነ። ይህ ማለት የፓርቲዎቹ የኢኮኖሚ ተቋማት አስተዳደራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የመረጃ ድጋፍ እንዲኖራቸው ሆነው ጠንካራ የኢኮኖሚ አቅም እንዲኖራቸው ተደርገዋል:: ሌሎቹ ነጋዴዎች ከእነሱ ጋር መወዳደር ተራራ እንደመግፋት ሆኖባቸው ነበር። ከዚያ አልፎ ማንነት ላይ የተመሰረተ የሀብት ማካበት ሂደት ቀጥሏል ማለት ነው። ይህ ሲባል በዝምድና፣ በጓደኝነት ከዚያም አልፎ በራሳቸው በርካታ ፎቆች ከባለስልጣናት ጋር ግንኙነት ያላቸው ናቸው። ተራው ነጋዴ በዚያ መንገድ ሊሄድ ሲፈለግ የሚደግፈው የጡት አባት ያስፈልገዋል። በትክክለኛው አካሄድ ተጠናክረው ሠርተው የወጡ የሉም ማለት አይደለም። ግን የተለያዩ ድጋፎች ላይ የኢኮኖሚው እድገት ፍትሐዊ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል። ብዙዎችም በማንነታቸው ተፅእኖ እየተደረገባቸው ከጫዋታው ውጪ እንዲሆኑ ተደርገዋል። በአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እድገት አለ፤ ግን ፍትሐዊ እድገት አይደለም።
አዲስ ዘመን፦ በተለይ ደግሞ በ 27 ዓመታት የኢህአዴግ አስተዳደር ዘመን ኢኮኖሚው ላይ የነበሩ ተግዳሮቶች እንዴት ይገልጿቸዋል?
አቶ ብርሃነ፦ የኢኮኖሚ ጉዳይ ሲነሳ መሰረታዊ ችግር ተብሎ የሚነሳው የፖሊሲ ችግር ነው። በየጊዜው የሚመጡ መንግሥታት የፖሊሲ ችግር የለም፤ የአፈፃፀም ችግር እንጂ ቢሉም ፖሊሲና ህገ መንግሥቱ መሰረታዊ የሆነ ችግር አለው፤ የኢኮኖሚም ሆነ የፖለቲካ ስርዓቱን ለማስተካከል ወደ ውስጥ ገብቶ ራስን መመርመር ያስፈልጋል። በአብዛኛው የአፈፃፀም ችግር የሚገጥማቸው ህጎቹ በራሳቸው ደካማ ስለሆኑ ነው። ህጎቹ መፈፅም ካልቻሉ መሰረታዊ ችግሮች አላቸው ብሎ መመርመር ያስፈልጋል።
ሌላው ትልቁ መሰረታዊ ችግር ሁሉንም ህዝብ አሳታፊ ያለማደረግ ጉዳይ ነው። ኢኮኖሚውን የሚያሳድገው የህዝብ እንቅስቃሴ ነው። አሁንም የህዝብ ተሳትፎ በወገንተኝነት ላይ የተመሰረተ ነው። በኢትዮጵያዊነት ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ እድገት አይታይም። የኢኮኖሚ መሰረቱ በብሄርተኝነት ላይ ነው። እንደ ሀገር እየተናበብን ማንም ሰው በሀገሩ ውስጥ እንደፈለገ ተንቀሳቅሶ ያልሠራ ከሆነ አሁንም ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ክፍፍል የለም ማለት ነው። አሁን ያለው የኢኮኖሚ እድገት ያለ መሆኑ የሚታይ ነው። እንደ አንድ ተራ ዜጋ የማየው የህዝብ እንቅስቃሴ ከአስራ ስድስት ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ ስመጣ በተለይ በአዲሰ አበባ አካባቢ ያለው እንቅስቃሴ ስለኢኮኖሚው የሚነገረውን ያህል ሳይሆን ከዚህም በላይ አድገት መኖሩን ነው።
መንገድ ላይ ስራመድ በየመንገዱ ዳር በርካታ ሱቆች አሉ፥ የሚሸጠው ከበዛ ደግሞ በዛው ልክ የሚገዛ ሰው አለ ማለት ነው፤ የሚገዛ ካለ ኢኮኖሚው እየተንቀሳቀሰ ነው። አብዛኛው ሰው ንፁህ ልብስ ይለብሳል፤ ሴቶች ፀጉራቸውን ተሠርተው አምሮባቸው ነው የሚታዩት:: ሆቴሎች በተለይም መካከለኛ ደረጃን የሚያስተናገዱት ሙሉ ሆነው ሲያገለግሉ ነው የሚታየው። መንገድ ላይ የሚሄደው ሰው በፍጥነት የሚሄድ ሊሠራና ሊያርፍ የሚሄድ መሆኑን የሚያሳይ ፈጣን እንቅሰቃሴ አለ። ብዙ ሰው ፊት ላይ የጭንቀት ሁኔታዎች አይታዩም:: በዚህ ምልከታ ኢኮኖሚው ደህና የሚባል እንቅስቃሴ ላይ ያለ ይመሰላል።
በአሁን ሰዓት አዲስ አበባ ማዕከላዊነቷ ተበትኗል። የትኛውም አካባቢ የሚኖር ሰው የሚፈለገውን ነገር በሙሉ በሚኖርበት አካባቢ ማግኘት ይችላል፤ ይህ ቀላል ነገር አይደለም። የተገነቡ ቤቶች ብዛት ሲታይ እዚህ ውስጥ የሚገባ ሰው ለመኖሩ ያጠያይቃል፤ ይህን ሁሉ ሰውስ የሚያንቀሳቅስ ትራንስፖርት መኖሩም ሌላ ጭንቀት የሚፈጥር ነው፤ ይህ ሁሉ ግን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አካል በመሆኑ እድገት አለ።
በየቦታው የሚታዩ ፎቆች ዲዛይኖች ሁሉ በጣም የተለዩ ናቸው፤ ከሌሎች ሀገራት የተሻለ በሚባል ደረጃ ነው:: ይህ ሲባል ያደጉ ሀገራት ተመሳሳይ ቤቶች በአንድ ቦታ በመሠራት አሰልቺ የሚሆነበት አጋጣሚ ሲኖር፣ እዚህ ግን ያ የለም። በፊት ከነበረው የቆሻሻ ማኔጂመንት ቢስተካከልም አሁን ህብረተሰቡ ውስጥ የአመለካከት ለውጥ ያስፈልጋል። ይህ ሁሉ ነገር የኢኮኖሚ አድገት መለኪያ ሊሆን ይችላል።
አሁን በሀገራችን እየተመለከትኩት ያለና ቅር የሚለኝ ነገር ግለኝነት በዝቶ መከባበርን አጥፍቷል። ግለኝነት በዝቶ ሙስና መጠየቅ ነውር መሆኑ ቀርቷል። አንድ አገልግሎት ለማገኘት ለግለሰቦች ጥቅም ከመስጠት አንድ ነገር ለማግኘት ተጨማሪ ክፍያ ቢጠየቅ ጥሩ ነበር የሚሆነው፤ ያ ግን አይደለም፤ በር ላይ ካለ ጥበቃ አንስቶ ሁሉ ገንዘብ ፈላጊም ጠያቂም ሆኗል። ይህ ደግሞ ኢንቨስትመንቱ ላይ ተፅእኖ አለው። የኢንቨስትመንት አግባብ ያልሆነ ወጪ የሚጨምረው የማይታዩ ወጪዎች ናቸው፤ የተማሩ የሚባሉ በጣም ትልልቅ ሰዎች ማለት አንድ ጉዳይ ለማስፈፀም በሙስና መሄድ ላይ ይታይል:: በአጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት አለ፤ ፍትሐዊ ነው ወይ ለሚለው ግን እሱ ሌላ ጥያቄ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ ያላት የተፈጥሮ ሀብት ከራሷ አልፎ ለሌሎች አገራት ጭምር የሚተርፍ እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፤ ከዚህ ሀብት መጠቀምና እድገት ማስመዝገብ ያቃተን ለምንድ ነው ?
አቶ ብርሃነ፦ እኔ የሚመስለኝ የፖሊሲው የማስፈፀም አቅም ማጣት ነው። ለምሳሌ በደርግ ጊዜ (የእዝ ኢኮኖሚ) ኮማንድ ኢኮኖሚ ነበር። እድገቱም በዚያው ልክ የቀጨጨ ነበር። ነገር ግን እርሻዎችን ለማቋቋም ሞክረዋል፤ ይህም በመንግሥት ቁጥጥር በመደረጉ ማበረታቻ (ኢንሴንቲቭ) አልነበረውም። በሁሉም መንግሥታት ጊዜ የተለያዩ እቅዶች ይታቀዳሉ፤ ማለትም የህዳሴ ግድብ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ታቅዶ አቶ መለስ ያስጀምሩትና አሁን ለመጨረስ እየተደከመ ያለ ነው። ሁሉም መንግሥታት ሀገሪቱ ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ለመጠቀም ወደ ሥራ ለመተርጎ የሚያስችሉ ጥናቶች ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ ጊዜ የተጀመረ ነው። እነሱን ወደ ተግባር ለመቀየር ግን አቅምና ቁርጠኝነት ይጠይቃል። ለምሳሌ በኢህአዴግ ጊዜ ለም ኢትዮጵያ የተባለ ድርጅት ነበር። ይህ ድርጅት በቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ የሚመራ ነበር። በዚህ ማህበር ውስጥ ሰው ዛፍ መትከልን ባህሉ ለማድረግ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ የነበረ ቢሆንም፤ አልተሳካም ነበር። አሁን በዶክተር አብይ ዘመን አዲስ ተነሳሽነት (ኢንሼቲቭ) ተሰጥቶት በስፋት እየተሠራበት ነው። መነሻው መቼም ሆነ መቼም ለመፈፀም ወደሥራ ለመግባት ቁርጠኝነትን ይጠይቃል።
የተፈጥሮ ሀብት አለን፤ የተፈጥሮ ሀብታችንን እንዴት መጠቀም እንዳለብን እናውቃለን። ነገር ግን ሀብትን ለመጠቀም እንዴት እናድርግ የሚል ጥያቄ ነው የነበረው፣ አሁን ግን የተፈጥሮ ሀብቶችን የመጠቀሙ ሂደት የተሻለ መሆኑ ነው የሚታየው። ኢህአዴግ ግብርና መር ኢኮኖሚ ብሎ የተወሰነ ቢሄድም ብዙም ውጤት አላመጣም። ይህ ለምንድነው ኢኮኖሚ ግብርናን መምራት ስለሚኖርበት ነው። አሁን በግብርና ዙሪያ እየተሠሩ ያሉ በርካታ ሥራዎች አሉ። እስከአሁን በመንግሥት እጅ ነው ያሉት። ህዝቡን፣ ባለሀብቱን እንዲሁም ተጠቃሚውን ማህበርሰብ ያካተተ ቢሆን የተሻለ የሀገር ሀብትን ተጠቅሞ እድገት ማስመዝገብ ይቻላል።
ሌላው ደግሞ የማንነት ጥያቄ ከግለሰብ መብለጡ፤ የግለሰብ መብት አንሶ መታየቱ፤ የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ ላለመጠቀም ምክንያቶች ናቸው። በተለያየ ጊዜ የሚደርሰው ውድመት የዚህ ችግር ውጤት ነወ። ችግሩ ኢኮኖሚ ላይ ጫና ይፈጥራል። ይህ ከምን ተነሳ ቢባል የግለሰብ ጥያቄ ተሸፍኖ የብሄር ጥያቄ በመጉላቱ ነው። ለምሳሌ የአባይ ግድብ ያለበት ሲታይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚኮራበት ሲሆን፣ የብሄር ጥያቄ ሲነሳ ችግር አለ። ያ ቦታ የአምስት ብሄሮች ተብሎ ቦታው በህገመንግሥት ስለተሰጠ የሀገር ነው ለማለት ማነቆ አለ። ኢኮኖሚውንም ሀገሩንም እያመሰ የሚገኘው ይህ የብሄር አመለካከት ነው።
የብሄር ጥያቄ ፍትሐዊ ነው ወይ እስከሚለው ድረስ ችግር የለም። እንዳለመታደል ሆኖ በብሄር ጥያቄ ላይ የእኩልነት ጥያቄ ከመጣ በኋላም የበላይነት ጥያቄ ይከተላል። ይህ ደግሞ የሌላውን መብት ይነካል። አንደኛ በብሄር ምክንያት የስልጣን ኮታ ማግኘት፤ የሀብት ክፍፍሉ ላይ የተሻለ ተጠቃሚ መሆን የመሳሰሉት አሉ። ህዝብ እንደ ህዝብ ሲታይ ግን የብሄር ጥያቄ ትልቁ የኢኮኖሚ መሰናክል ነው።
አዲስ ዘመን፦ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ሃገር በቀል የኢኮኖሚ ስትራቴጂን በመከተል ስኬታማ ለማድረግ እንደሚሠራ ገልጿል፤ ይህ ምን ፋይዳ ይኖረዋል?
አቶ ብርሃነ፦ መጀመሪያ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ምንድነው? ሀገር በቀል ሲባል ቃሉ ደስ ይላል፤ ግን መሬት ላይ አገር በቀል ኢኮኖሚ ማለት የሀገር ባለ ሀብትን ማሳደግ ማለት ነው ወይ? ለሀገር ምርት ቅድሚያ መስጠት ማለት ነው ወይ? ከውጭ የሚመጡትን በሀገር በቀል መተካት ማለት ከሆነ ትልቅ ነገር ነው። ሳየው ግን እሱ አይመሰለኝም። ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማለት የውጭ ባለሀብትም ቢሆን ሀገር ውስጥ የሚሠራው ነገር ከሀገር በቀል እንዲታሰብ የሚያደርግ ነው። ሀገር ውስጥ በመሠራቱ አንድ እቃ ከውጭ ከሚመጣው ሌላ ዕቃ የተሻለ ድጋፍ ይደረግለታል ወይ? ጥያቄው ነው። ግን አሁን ከነጭራሹ የዓለም የንግድ ድርጅት ውስጥ ለመግባት ነው ዝግጅት ላይ ያለነው። የዓለም ንግድ ድርጅት ደግሞ ሀገር በቀል ነገርን ለማሳደግ አይፈቀደም። ስለዚህ ነው አሜሪካውያኑም አውሮፓውያኑም የራሳቸውን ፋብሪካዎች የሚደግፉት። ስለዚህ ትርጉሙ ይጠቅማል አይጠቅምም የሚለው ሃሳብ ላይ ለውጥ እንዲኖር ያደርጋል። ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማለት ሀገር ውስጥ የሚመረቱ ዕቃዎች ከውጭ ተወዳዳሪ ለማድረግ ጥሩ ይሆናል።
ሀገር ውስጥ የሚያመረቱ ሰዎች ሊበረታቱ የሚገባ ሲሆን፣ ከውጭ ገበያ ጋር የሚወዳደሩበት አቅም ቢፈጠርላቸው፤ ከውጭ የሚመጣው በተወሰነ ቀረጥ የሚገባ ሲሆን፣ ተወዳዳሪ እንዲሆኑም ሲያመረቱ የሚደረግላቸው መንግሥታዊ ድጋፍ ተጠቅመው እዚህ ምንም ድጋፍ ከሌለው ፋብሪካ ጋር ሲወዳደር የንግድ ሚዛኑን ያልጠበቀ ይሆናል። ሀገር በቀለን ከላይ ባልኩት መልኩ ከተረዳነው ግን ለሀገር ኢኮኖሚ ጠቃሚ ነው።
አዲስ ዘመን፦ በሃገራችን የሰላም መጥፋትና የተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት አለመፈጠሩ በኢኮኖሚው ላይ የሚያሳድርውን አሉታዊ ተጽዕኖ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ብርሃነ፦ ምንም ጥያቄ አያስፈልገውም። ሰላም ከሌለ ኢኮኖሚ የለም። አንድ ችግር ሲፈጠር መንገድ ይዘጋል፤ መንገድ ሲዘጋ ኢኮኖሚው ነው የሚበደለው። ነጋዴው፣ ሻጩ፣ ተቀባዩ፣ ባለ መኪናው ሁሉም በየደረጃዎ ተጎጂ ይሆናሉ። ይህ ከአምራቹ እስከተጠቃሚው ያለውን የገበያ ሰንሰለት ያበላሻል። ሰላም ለኢኮኖሚ ወሳኝ ነው። በተለያዩ ሰላም ማጣቶች ሙሉ ከተማ የወደመበት፤ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች የተቃጠሉበት ጊዜም ነበር። ይህ ሁሉ እያንዳንዱ የኢኮኖሚ መሰረት ላይ ጥላ ጥሎ አልፏል። ይህ ደግሞ የብሄር ፖለቲካ ያመጣው ችግር ነው። ይህ የፖለቲካ ስርዓት ካልጠፋ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ላለመፈጠራቸውና ላለመደገማቸው እርግጠኛ መሆን ይከብዳል።
አዲስ ዘመን፦ እንደ ቻይና፣ ሲንጋፖርና መሰል የኢስያ ሃገራት ለማደግ የፈጀባቸው ጊዜ ከግማሽ ምዕተ ዓመት ያነሰ ነው፤ ከዚህ አንጻር እኛ አሁን ያለው የፖለቲካ ሁኔታ ከተረጋጋ በአጭር ጊዜ ወደ እነዚህ ሃገራት እድገት ለመሄድ ዕድል ይኖራል ብለው ያስባሉ ?
አቶ ብርሃነ፦ ምንም ጥርጣሬ የለውም። ሀገራችን ትልቅ አቅም ያላት ሀገር ናት። የኢትዮጵያ ህዝብ ለማደግ ምንም ጊዜ አይፈጅበትም። የዘር ፖለቲካ ከመካከሉ ከወጣ በጣም ጠንካራ የሆነ ህዝብ ስላለን የኢኮኖሚ እድገት ይኖራል። ሀገራችን አንደኛ በርካታ የተማሩ ሰዎች አላት፤ ሌላው በቀላሉ መማር የሚችሉ ህዝቦች አሏት:: ሦስተኛ በሃይማኖት ምክንያት የመቻቻል ሁኔታ አላት፤ ስለዚህ በእነዚህ ምክንያት የተቀናጀ ሥራ ቢሠራ ለውጥ ምንም ያህል ጊዜ ሳይጠበቅ በአጭር ዓመት ይመጣል።
እንዳለመታደል ሆኖ መልካም እሴቶቻችን እየተቀየሩ ነው። ሰው ተዘቅዝቆ ሲሰቀል ሰው እንደተመልካች የሚያይበት፤ ሌላ አካባቢ ያሉ ችግሮች እዚህ ያለውን ሰው የማይሰማበት ሆኗል። አሁን ራሱ ትግራይ ውስጥ ትልቅ ችግር አለ። ሌላው ህዝብ ጤናማ አድርጎ ነው የሚያየው። አሁን ብቻ አይደለም፤ በተለያዩ ብሄረሰቦች ላይ ብዙ ነገር ሲሆን ራሱ ላይ እሲኪደርስ ዝም ይላል። አንድ ህዝብ አንድ ሆኖ ካልጮኸ ችግሩ ዞሮ ራሱ ዘንድ ይመጣል። ይህ በፖሊሲም፤ በፖለቲካም፤ በኃይል እርምጃም ሊታይ ይገባል።
በተረፈ ግን በአቅም ደረጃ ሀገሪቱ በጣም በቀላሉ ቶሎ የምታደግበት አቅም አላት። አዲስ አበባ ብቻ እንኳን ባለፉት 20 ዓመታት የታየ እድገት ሃምሳ ሠላሳ ዓመታትን የሚፈጅ ነው። እድገቱ ፍትሐዊ አለመሆኑ እንጂ የተሠሩት ሥራዎች ቀላል አይደሉም።
አዲስ ዘመን፦ እርስዎ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ከንግድ ምክር ቤት ምስረታና እድገት ጋር በተያያዘ በግንባር ቀደምትነት ስምዎ ይነሳል፤ ከምክር ቤቱ አነሳስ ጀምሮ ለምን እና እንዴት ከምክር ቤቱ ወጡ ?
አቶ ብርሃነ፦ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት መጀመሪያ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ጊዜ ሲቋቋም የአዲስ አበባ ነጋዴዎች ማህበር ሆኖ ነበር። አዲስ አበባ አካባቢ ያሉ ነጋዴዎች ናቸው ከመንግሥት መሬት ወስደው ሕንፃ የሠሩት። ከዚያ በኋላ የኢትዮጵያ ነጋዴዎች ማህበር ተቋቋመ። የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በአዲስ አበባ ብዙ ነጋዴዎች ስላሉ ተጠናክረዋል። ሌሎቹ ንግድ ምክር ቤቶች በከተማ ላይ የተመሰረቱ የንግድ እንቅስቃሴውን ተከትለው የፖለቲካ ሳይሆን በኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ተቋቁሞ ይሄዳል።
ከዚያ ደርግ ሊቆጣጠረው ፈለገ። ሊያውም በቦርዱ ውስጥ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ብቻ ከግል ተቋም ሲሆን፣ ሌላው ከመንግሥት ነበር። በዚህም ምን ያህል ደካማ ቻንበር እንደነበረ ያሳያል። ከዚያ በኋላ ኢህአዴግ በሀገሪቱ ሙሉ ቁጥጥር ሲያደርግበት ከመንግሥት ጫና እንዲወጣ ሙከራ ተደርጓል። ይህም ማለት ከመንግሥት የሚመደቡትን የቦርድ አባላት በመተው ነጋዴው የመረጠው መሆንና ነፃ መሆን ጀመረ። ቀጥሎም ኢህአዴግን ይህ አላስደሰተውም። መቆጣጠር ፈለገ፤ ያኔ ግጭት ይፈጠራል። በፊት አንድ ነጋዴ ንግድ ፍቃድ ሊያሳድስ ሲሄድ የቻንበር መከፈሉ ይጠየቅ ነበር:: በዚያም አቅም ነበረው። ያ ሲቀር ግን ገቢ ቀነሰ። ሰው ካልከፈለ አቅም ይዳከማል፤ ያንን ክፍተት ለመሙላት በተደረገው ሥራ አቅም ተጠናከረ። በዚህም አልበቃም፤ ቻንበሩን ለመቆጣጠር አደረጃጀቱንም በመከፋፈል ላይ የተመሰረተ አደራጃጀት እንዲሆን የማድረግ ሥራም እየተሠራ ነበር።
የቻንበሩ እምነት አምራቹም አገልግሎት ሰጪውም ንግድ ሥራ ላይ የተሰማራ በሙሉ ነጋዴ ነው የሚል ነበር። ይህ ማህበር በትናንሽ ክፍሎች እንደየአደረጃጀታቸው የተከፋፈለ ቢሆንም በዚያ ልክ ልዩነት መፈጠሩ ጠንካራ ንግድ ምክር ቤት እንዳይኖረ ያደርገዋል። ይህም የነጋዴውን ፍላጎት የማያስጠብቅ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚና ለንግዱ ማህበረሰብ ቋሚ የማጣት ሁኔታ እንዲፈጠር አደረገ። ሀገር ውስጥ ችግር ሲፈጠረ የመጀመሪያው ተጠቂ ነጋዴ ነው፤ ሱቁ ሲቃጠል፣ ንብረቱ ሲዘረፍ፣ ሲጎዳ የሚጮህለት የለም።
በሌላ በኩል ደግሞ የምግብም የሸቀጥም ዋጋ ሲጨምር የመንግሥት ባለስልጣን ስለንግድም ምንም እውቀት የሌለው ተነስቶ አሻጥረኛ ነጋዴ ነው ያስወደደው ይላል። ይህ ከጥፋተኛ ነጋዴዎች ጋር በስርዓት ተመርተው የሚሠሩትን መጨፍለቅ ይሆናል:: ለዚህ የሚጮህለት የለም። ከዚያ ውስጥ የንግድ ሥራ ዋጋ እንዲጨምር የሚያደርገው የፖሊሲ ጉዳይ ነው። የተበላሸ ፖሊሲ ወጥቶ በተበላሸው ፖሊሲ ምክንያት የሸቀጥ ዋጋ ላይ ጭማሪ እያመጣ ነጋዴ ሲጨምር መጠየቀ የለበትም። የመጀመሪያ ተጠያቂ መሆን የሚገባው ፖሊሲ ነው። ፖሊሲ አፈፃፀምና አተገባበር ነው። ነጋዴዎችም ኃላፊነት መወጣት አለባቸው። ዘይት ሲወድድ ነጋዴውን፤ ሸቀጥም ሲጨምር ነጋዴውን መውቀስ ትክክል አይደለም፤ ስለሆነም ፖሊሲው ይመርመር።
ወደ ጥያቄያችን ስንመለስ እኔ በወቅቱ የፖለቲካ ሰው አልነበርኩም። ግን ኢኮኖሚ ከፖለቲካ ጋር ይገናኛል። የሚወጡ መመሪያዎች ሲታዩ፣ የኢኮኖሚ ጉዳይ ሲነሳ የፖለቲካ ሰው ያስመስላል። በወቅቱ በግለሰብ ደረጃ ተግባብተን እንሠራ ነበር። በወቅቱ ጋዜጣ አሳትም ነበር፤ ጋዜጣው ላይ በወጣው ፅሑፍ የተነሳ ታሰርኩ። ጋዜጣው ላይ ህገ መንግሥቱ የኢህአዴግን የፖለቲካ አካሄድ ለማስፈፀም እንዲመች ተደርጎ የተሠራ ነው የሚል ሃሳብ በማንሳቴ ነበር ለወህኒ የተዳረኩት። ከዚያ በፊትም የሊዝ ጉዳይንም አንስቼ አልወደዱትም ነበርና የተለያዩ ነገሮች ተጠረቃቅመው በመጨረሻ የቫት ታክስ ሲመጣ ነጋዴው ስለአሠራሩ እንዲያውቅ ጊዜ ይሰጠው በሚል ያነሳሁት ሃሳብ ከፖለቲካ ጋር ተያይዞ ታሰርኩ።
ከዚያ ሁኔታዎችን ስመለከታቸው አልተመቹኝም፤ ድጋሚ ታስሬ መቆየት ስላልፈለኩ ሌሎች እንደሚሉት በኬንያ በእግሬ ምናምን ሳይሆን በስነ ስርዓት በአውሮፕላን ነው የወጣሁት። ከሀገር በዚህ መልኩ መውጣቴ ፖለቲካ ውስጥ እንድገባ አደረገኝ። በሰሜን አሜሪካ የተቋቋመው የቅንጅት ፓርቲ ውስጥ ዋና ፀሐፊ ሆኜ ሠራሁ። በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሃምሳ በላይ ክፍል ያለው ቅንጅት የመደገፍ ሥራ ሠርቻለሁ። አባሎች ሲታሰሩ በደንብ መግለጫ በማውጣትና በሌሎች የፓርቲው ሥራዎች ተሳታፊ ሆንኩኝ። ፖለቲከኛ ሳልሆን በመገፋቴ ፖለቲከኛ ልሆን ችያለሁ።
አዲስ ዘመን፦ የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች መሰረታዊ ችግሮች ምንድን ናቸው? መፍትሔያቸው ምንድን ነው ብለው ያምናሉ ?
አቶ ብርሃነ፦ ሰፋ ያለ ጥያቄ ነው። መጀመሪያ የአንድ ሀገር ህግና ፖሊሲዎች የንግዱ ሥራ ላይ ቀጥተኛ ተፅእኖ አላቸው። ስለዚህ መሰረታዊ ችግሮች ተብለው በመጀመሪያ ረድፍ የሚቀመጡት የፖሊሲ ችግሮች ናቸው። የፖሊሲ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ ይቀያየራሉ። ሁለተኛው እና ትልቁ ችግር የሚሆነው የአስተዳደራዊ ችግር ሙስና ሲሆን፣ ወገንተኝነትም ሌላው ችግር ነው። ሦስተኛ ችግር የምንለው አቅም ነው። አቅም ማለት የካፒታል እጥረት መኖር በሚሠራው ሥራ ላይ በቂ እውቀት አለመኖርም የንግድ ሥራው መሰረታዊ ችግር ሲሆን፣ ይህን ሁሉ አልፎ የሚመረተው ምርትም የገበያ ችግር ይጋጥመዋል።
በአጠቃላይ ሀገራችን ውስጥ ያለውን ነገር ስንመልከት ብዙዎቹ መፍትሔ ለመስጠት እየተሠራ ይመስለኛል፤ በገንዘብ አቅርቦት ላይ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በከፍተኛ ደረጃ መኖሩ አሳሳቢ ነወ። ለውጭ ምንዛሪ ሲባል ሀገር ውስጥ የሚመረት ምርት ላይ መንግሥት ድጋፍ በማድረግ ወደ ውጭ የሚላክ እቃ ቢበዛ የላኪነት አቅም መጨመር የግድ ነው። በመዲናችን ውስጥ ያለው ከውጭ የሚገባ ዕቃ በብዛትም በጥራትም በርካታ ዕቃዎች ሀገር ውስጥ አሉ፤ በአንፃሩ ግን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ችግር አለ። የውጭ ምንዛሪ ላይ መሠራት የንግዱ እንቅስቃሴ ከአሁን በበለጠ እንዲንቀሳቀስ መሆን ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፦ በሃገራችን የነበሩ መንግሥታት ለንግዱ ዘርፍ የሰጡትን ትኩረት እንዴት ያዩታል ?
አቶ ብርሃነ፦ በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ጊዜ የንግድ ዘርፉ ጥሩ ትኩረት የነበረው ይመስለኛል። ግን በወቅቱ የነበረው የህብረተስብ አደረጃጀት በባላባት በገበሬ በምናምን የተከፋፈለ ስለነበረ ንግዱ በሚፈለገው ርቀት እንዲሄድ አልረዳም። በደርግ ጊዜ ለንግዱ ህብረተሰብ ምንም ጥሩ ነገር አልነበረም፤ ነጋዴ እንደ ሌባ የተቆጠረበት፤ ሀብት ማፈራት ወንጀል የነበረበት ጊዜ ነበር። በወቅቱ ግን ሁሉም እንዳይጠቀም የማድረግ አሠራር እንጂ አንዱን የህብረተሰብ ክፍል ብቻውን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሁኔታ አልነበረም። ሀብት አላቸው የሚባሉትም በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ናቸው።
በኢህአዴግ ጊዜ ለንግዱ ህብረተሰብ እንደ ህብረተሰብ የተደረገ ድጋፍ ሳይሆን እንደንግድ ህብረተስብ ተቆጥሮ ለፓርቲ ድርጅቶች ነው ድጋፍ የተደረገው። እነሱ ከሚገባቸው በላይ አብጠው ነበር። ከዚያ ቀጠሎ ለባለስልጣናት አይን ባወጣ መልኩ ድጋፍ ሲደረግ ነበር። አሁን በመዲናችን የሚታዩ ፎቆች ከሆኑ በባለስልጣናት ስም የሚጠሩ ናቸው። የሠላሳ የአርባ ሚሊዮን ብር ሕንፃ አምስት ሺህ ብር የማይሞላ ደመወዝ ያለው ሰው ሲሠራ ነው የሚታየው። ሌላው ነጋዴ እየተሸማቀቀ የሄደበት ነው። በራሳቸው ጥረት ታግለው የወጡ ስለመኖራቸው የማይካድ ሀቅ ነው። የንግድ ህብረተሰቡ እንደ ህብረተሰብ እንዳያድግ ነበረ የተደረገው። አሁንም የጎላ ልዩነት የለም።
አዲስ ዘመን፦ በአሁኑ ወቅት በሃገሪቱ ያለው የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነት እየጨመረ በመሆኑ ዜጎች ለችግር እንደተዳረጉ በተደጋጋሚ ይገልጻሉ፤ ከዚህ ቀውስ ለመውጣት ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
አቶ ብርሃነ፦ የዋጋ ግሽበት ከፖለቲካ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው። የፖለቲካው መስተካከል ብዙ ነገሮች ያስተካክላል ብዬ አስባለሁ። ፀጥታው ያለበት ሁኔታ የዋጋ ግሽበቱን ያባብሰዋል። ከዚያ ደግሞ የሀገሪቱ ዜጎች በእኩል የማይታዩበት አንዱ ልጅ አንዱ የእንጀራ ልጅ የሚመስልበት ሁኔታ ቀርቶ አንድ ሰው እንደ ግለሰብ መታየት አለበት። ሰው እንደ አማራነቱ ወይም እንደ ትግሬነቱ ወይም እንደ ጉራጌነቱ ሳይሆን እንደ ኢትዮጵያዊነቱ መታየት አለበት። ማንም ዜጋ ሀገር ውስጥ እንደፈለገ ተንቀሳቅሶ መሥራት አለበት፤ በእያንዳንዱ የሀገር ውስጥ ችግሮች ግን መነሻ ፖለቲካና ፖሊሲ ነው። ፖለቲካና ፖሊሲ ከተስተከካለ ሁሉም ለአንድነትና ለእድገት ከሠራ የዋጋ ግሽበትም ሆኑ ሌሎች ችግሮች ይቀረፋሉ። ሌላው የግለሰብ ነፃነት የሚከበርበትና ሰው እኩል እንደሰው ከታየ ብዙ ነገሮች ሊቀረፉ ይችላሉ።
አዲስ ዘመን፦ በአሁኑ ወቅት አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እያደረገች ነው፤ ከጫናም ባለፈ የቪዛ እገዳና የኢኮኖሚ ማዕቀብ ሊጣል ይችላል የሚል ሰጋት አለ፤ ይህ ምን ያህል ፍትሐዊ ነው ፤ የኢኮኖሚ ማዕቀቡ የሚቀጥል ከሆነ በሃገራች ላይ ምን ዓይነት ጉዳት ያስከትላል ? ጉዳቱን ለመቀነስ ምን ማድረግ ያስፈልጋል ?
አቶ ብርሃነ፦ አሜሪካ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ የወሰደችው አቋም ፍትሐዊ ነው ወይ ለሚለው ጥያቄ ፍትሐዊ አይደልም የሚል ምላሽ መስጠት ይቻላል። ምክንያታዊ ነው ወይ ካልን ችግር ብለው ያነሷቸው ነገሮች እውነትም የሀገራችን ችግር ናቸው። አሁን ሀገር ውስጥ የፀጥታ ችግሮች አሉ። ሴቶች ተደፍረዋል፤ ብዙ ችግሮች አሉ፤ እነዚህ የተቀመጡ ችግሮች ደግሞ የትግራይ አካባቢ ችግሮች ብቻ አይደሉም። መላውን የሀገሪቱን አካባቢዎች ያጠቃለሉ ችግሮች ናቸው። እነዚህ ችግሮች መጤ ተብለው የሚታሰቡ ሰዎች ላይ በሙሉ የሚደርስ ችግር ነው። ሙሉ ከተማን እስከማፍረስ የደረሰ ችግር በየቦታው ነበር። ደረጃው ይለያየ እንጂ ችግሮች አሉ።
የእነሱ ስህተት ለችግሩ መፍትሔ ብለው የወሰኑት እርምጃ ትክክል አለመሆኑ ነው። ለችግሩ መፍትሔ ከሉአላዊነት ያለፈ ልክ ያልሆነ ነገር አለ። መደረግ አለባቸው የሚሏቸው ነገሮች በነሱ ተፅእኖ መደረግ ያለባቸው ሳይሆኑ በህዝብ ጥያቄ መደረግ ያለባቸው ናቸው። ህዝብ ጦርነት አይፈልግም፤ በሰሜን እዝ ላይ ዕርምጃ ሲወሰድ ዕርምጃው እስከተወሰደበት ጊዜ ድረስ መንግሥት የወሰዳቸው ዕርምጃዎች ዘገምተኛ ነበሩ። መንግሥት የራሱ ምክንያት ነበረው፤ ቢሆንም እንደ አንድ ተራ ሰው ስመለከተው ግን እንደዛ አክርረው ሰውን ማረድ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ዕርምጃ መወሰድ ነበረበት። ያንን ተግባር ካከናወኑ በኋላ ግን ህዝቡ በአንድ ድምፅ ነው የደገፈው።
የተወሰደው ህግ የማስከበር ዕርምጃ አግባብነት አለው ሲባል መታየት ያለባቸው ነገሮች አሉ። ህወሓት የኢትዮጵያ መንግሥት የትግራይ ህዝብና ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ አለ። ህዝብ እንደ ህዝብ ከታየ መንግሥት የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት ከሌላቸው ከሰላማዊ ዜጎች ጋር የሚያያዙ ችግሮች ካሉ መንግሥት መፍታት አለበት። የህዝቡን ድምፅ ማድመጥ መብት ማስከበር የመንግሥት ሥራ ነው።
በምጣድ ስር የሚሽሎኮለክን አይጥ ለመምታት ተብሎ ምጣድ አይሰበርም መቼም። ህዝብ ውስጥ የተከለለ ወንጀለኛን ለማጥፋትም ህዝብ መጎዳት የለበትም፤ ያንን መንግሥት መቆጣጠር ይኖርበታል። ህወሓት ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ስለሚፈልግ የሚፈጥራቸው ችግሮች አሉ። ያንን መቆጣጠር ያለበት መንግሥት ነው ፤ ግን ህዝብን እየጨፈለቀ አይደለም። ስለዚህ ኃላፊነት አለበት:: መንግሥት እስከሚችለው ድረስ የአሜሪካኖች ጥያቄ ችግር የለበትም። ግን ከዚያ አልፈው ሊወስዱ ያሰቧቸው ዕርምጃዎች አግባብነት የላቸውም።
እንወስዳለን ያሉት ዕርምጃ መጀመሪያውኑ ለኢትዮጵያ አስበው ከሆነ የሚያቋርጡት ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚሰጠውን ዕርዳታ ነው። የኢኮኖሚ ማእቀብ ቢኖር መንግሥት ላይ ምንም ተፅእኖ አይኖረውም። የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ህዝብ ላይ የሚያደርሰው ነገር ምንድን ነው ? የሚለው መጠየቅ ነው ያለበት። በአጠቃላይ ብሄር ተኮር የሆኑ እንቅስቃሴዎች መንግሥት መውሰድ ያለበትን ዕርምጃ አልወሰደም። ይሄ መንግሥት የሚያምነው ነገር ነው። ከእያንዳንዱ ጥፋት ጀርባም የመንግሥት ባለስልጣናት እጅ አለበት የተባለውን መንግሥት አምኗል።
መንግሥት ይሄን ነገር ለመቆጣጠር እንዲችል ለህዝቡ የሚያስቡ ከሆነ ማገዝ ይኖረባቸዋል። ጫና ማሳደር ግን ህዝቡ ላይ ጫና ያበዛል። ማእቀብ መጣሉ ብዙ ችግር የሚኖረው አይመስለኝም። ይህ ማለት አሜሪካኖች ለኢትዮጵያ ምን እያደረጉ ነው የሚለው መጠየቅ አለበት። የሚያደርጉልንን ነገሮች በሀገር ውስጥ መሸፈን ከቻልን ጫናውን መቋቋም እንችላለን። ከዚህ ትምህርት መውሰድ ይኖርብናል:: ይህ ምንድነው በኢኮኖሚ በማንም ላይ ጥገኛ መሆን የለብንም:: ዛሬ ልንራብ እንችላለን፤ ነገር ግን ልጆቻችን ራሳቸውን ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ነፃ መውጣት አለባቸው።
ከእነሱ የሚገኘው ከፍተኛ ዕርዳታ ምግብ ነው። በምግብ ምርት ራስን በመቻል ማለፍ ይቻላል። ሌሎች መሰረታዊ ያልሆኑ ነገሮችም ደግሞ በሀገር ህዝብ ላይ የሚያደርው ጉዳት ካልኖረ ይህ ችግር አይደለም። ትልቁ ጠቃሚ ነገር መንግሥት ችግሮቹ ዘንድ መጥቶ መፍታት ሲጀምር እነሱ ከለከሉም ፈቀዱም ህዝብ በሚያምነው ደረጃ መንግሥት ሰላም ከፈጠረ የዜጎችን ደህንነት ካረጋገጠ መንግሥትና ህዝብ ከተናበበ የሌሎቹ ጫና አያሰጋንም።
አዲስ ዘመን፦ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለሀገራዊ እድገትና ለኢኮኖሚያዊ ሽግግር የሚኖረውን ሚና እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ብርሃነ፦ ይህ ግድብ የዚህ ትውልድ ህልም አይደለም። ይህ ግድብ ያባቶቻችን ህልም ነው የነበረው። ይህ ትውልድ ዕድለኛ ሆኖ ለመገንባት አቅምና ድጋፍ አግኝቷል፤ አጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ መሰረታዊ የሆነ በስነልቦናም ይሁን በቁሳዊ ሁኔታ እጅግ በጣም ሀገሪቱን ከፍ የሚያደርግ ነው። ይሄ ግድብ አሁን መጠናቀቁ ብቻ አይደለም ግድቡ በዘላቂነት ለሀገር ኢኮኖሚ ዘላቂ መሆኑና የግድቡ አካባቢ ዘላቂ መሆን አለበት። ለቀጣይ ትውልድ የሚተላለፍ ችግር እንዳይኖር ከአሁኑ ፖለቲካዊ መፍትሔ ያስፈልገዋል።
ሁሉም ሊቀበለው የሚችል ማለትም ሀረር አካባቢ ያለ አደሬ፣ ኦጋዴን አካባቢ ያለ ሶማሌ፣ ባሌ አካባቢ ያለ ኦሮሞ፣ ደቡብ አካባቢ ያለ ሀዲያ፣ ጎንደር ያለ አማራ ሁሉም የሀገሪቱ ህዝብ ይህ ግድብ የኔ ነው የሚል ሰሜት ውስጣቸው መስረፅ አለበት። እነዚህ ሁሉ ግድቡ አካባቢ ሰፍረው መብታቸው ተጠብቆ ለመኖር የሚችሉበት ዓይነት ህገ መንግሥት ሊኖረን ይገባል። ያ ለግድቡ የኢትዮጵያውያን መሆኑ ለዚህ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለልጆች የሚተርፍ የሚሆን ዘረኝነት ሲጠፋ እና ኢትዮጵያዊነት ከፍ ሲል ነው።
አዲስ ዘመን፦ ለውጡን ተከትሎ የተጀማመሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ እያየን ነውና እነዚህ ጅምሮች ወደ ስኬት እንዲወስዱን በቀጣይ ምን መሠራት አለበት ይላሉ?
አቶ ብርሃነ፦ በእኔ እምነት ሀገሪቱ ውስጥ ሊሠራ ያልታሰበ ሥራ፤ ያልተጠና ፕሮጀከት የለም፤ ወደኋላ ቢታይ በየሚኒስቴሩ ጥናቶች ቢታዩ አሁን አዲስ ተብለው የሚጀመሩት የድሮ ጥናቶች ናቸው። መሰረታዊው ነገር ማቀዱ ሳይሆን ፕሮጀክቱን ተግባራዊ አድርጎ ፍፃሜ ላይ ማድረሱ ነው። አሁን እንደሚታየው ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ብዙ ፕሮጀክቶች የማጠናቀቅ አዝማሚያ ይታይባቸዋል። ይህ ደግሞ እንደስኬት መወሰድ አለበት። አሁን ያለው ከእቅድ ባለፈ ወደ ተግባር እየተገለጠ ቢሆንም በእኔ አምነት ለእያንዳንዱ ሥራ ማነቆ የሆነው የዘረኝነት ማነቆ መቀረፍ አለበት። ይህ ችግር ከተቀረፈ ሀገር ወደ ከፍታ የማትወጣበት ምክንያት አይኖርም።
አዲስ ዘመን፦ በውጭ ቆይታዎ ካገኙት ልምድ በመነሳት ሀገርዎን ለማገልገል ያቀዱት ነገር ካለ ቢገልጹልኝ?
አቶ ብርሃነ መዋ፦ ውጭ መኖር እውቀት አይደለም። ውጭ የኖረ ሰው ሁሉ ሀብትና እውቀት ይዞ ይመጣል ማለት አይደለም። ብዙ እውቀትና ችሎታም ሀገር ውስጥ አልጠፋም። ሌላው ሰው ከሀገሩ ሲወጣ የሄደበት ዓላማ ይዞት ለሚመጣው መንገድ ይለያል። ለኢኮኖሚ ጥቅም ከተወጣ ገንዘብ ይገኛል፤ ለትምህርትም ከተወጣ እውቀት ይገኛል፤ በፖለቲካ ምክንያት ከሆነም እዚያ ሆኖ መታገል ወይም በቃኝ ተብሎ ይተዋል። እኔ ግን መውጣት ፈልጌ አልወጣሁም፤ የግድ መውጣት ስላለብኝ ነው የወጣሁት፤ አሜሪካ ውስጥ በህይወት ኖሬያለሁ፤ ህይወትን ግን አልኖርኩም። ህይወት ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነበር። በተረፈ ግን ያሰብኳቸው ነገሮች ማለትም ከመሄዴ በፊት ያሰብኳቸውን እነሱን ማስቀጠል ዋና እቅዴ ነው። ሌላው ደግሞ እዚያ ካሉ ሰዎች ጋር የመድሃኒት ፋብሪካ ለማቋቋም እየሞከርን ነው ያለነው። እሱም በሥራ ሂደት ውስጥ ነው ያለው።
አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ አንዴ በሶሻሊዝም፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ነፃ ገበያ በሚል የተዘበራረቀ የፖለቲካ አካሄድ መጓዟ በኢኮኖሚው እድገት ላይ ምን አሉታዊ ተጽዕኖ አስከተለ ብለው ያሰባሉ ?
አቶ ብርሃነ፦ ሁሉም የፖለቲካ ስርዓቶች የራሳቸው የኢኮኖሚ አጀንዳ አላቸው። ኢኮኖሚውን በሚፈልጉት መልኩ ነው የመሩት። በአንፃራዊነት በቀደማዊ አጼ ኃይለስላሴ ጊዜ የባላባቱን ስርዓት በማሳደግ ወደ ካፒታሊዝም የማሳደግ ሃሳብ ነበራቸው። ደርግ ከመጣ በኋላ መንግሥት የሚቆጣጠረው ኢኮኖሚ ሆነ። ኢህአዴግ ከመጣ በኋላ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚቆጣጠራቸው ሆኑ። በኢኮኖሚው ላይ አንድ ዓይነት ፖሊስ ስላልነበራቸው እንደየ ፖሊሲያቸው ወጣ ገባ እድገት ነው የነበራቸው።
በሀገሪቱ ውስጥ ሀገራዊ መግባባት ከተፈጠረ ፖለቲካው ኢኮኖሚውን እንዲከተል የሚገደድበት ደረጃ ላይ ይደርሳል። ጤናማ የሚሆነው ኢኮኖሚው ፖለቲካውን ነው የሚመራው። እዚያ ለመድረስ ግን እርስ በእርስ መናበብ፣ መከባበርና ዋስትና ሊኖረን ይገባል፤ ያኔ ጤናማ ኢኮኖሚ ይኖረናል ማለት ነው።
አዲስ ዘመን፦ ውድ ጊዜዎትን ሰውተው ሃሳብዎን በዚህ መልኩ ስላካፈሉን እናመሰግናለን።
አቶ ብርሃነ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2013