ኢትዮጵያ ውስጥ የሥራን ቀለም ሳያማርጡ፣ ለክብደትና ለቅለቱ ልዩነትን ሳያስቀምጡ ያሰቡትን ሆነው የፈለጉትን ለመኖር፤ ጉልበትና እውቀትን ከውስን የገንዘብ አቅም ጋር አቀናጅተው ራአያችውን ለማሳካት ቀን ከሌሊት ሰርተው፣ የላብና ወዛቸውን ፍሬ የሚያጭዱ በርካታ ጀግኖች አሉ::
እነዚህ ጀግኖች ድንጋይ በጫንቃቸው ተሸክመው፣ ማሽን አገላብጠውና ከብረትና እንጨት ጋር ታግለው፣ ራሳቸውንም ሆነ አገራቸው ለመለወጥ የሚራመዱበት መንገድ በአንፃሩ የተደላደለ እና አልጋ በአልጋ አይደለም:: በተለይ ለውጤታማነት የሚያግዙ ድጋፎች ውስንነት እጅ እንዲሰጡ ያስገድዳቸዋል:: ድጋፎችን ቢያገኙ እንኳን ቀጣይነት የሌላቸው መሆኑ ከራስ አልፈው ለሌሎች የሥራ ዕድልና ሀብት የመፍጠር አቅማቸውን እንዳሳነሰው ከእራሳቸው አንደበት በተለያዩ ጊዜያት ሲነገር ተደምጧል::
ለሥራ ፈጣሪዎቹ ለልፋትና ጥረታቸው እውቅና የሚሰጡ እና ፋይዳቸውን አርቀው የሚያስቡ የተለያዩ አገራት በአንፃሩ ፊት ለፊት የተደቀኑባቸው እንቅፋቶችን ለማስወገድ እና ለማብቃት ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋሉ:: ዕድሎችን ያመቻቻሉ:: በቂ ነው ለማለት ባያስደፍርም በኢትዮጵያም የመስሪያ እና መሸጫ ቦታ አቅርቦት ጀምሮ ለሥራ ፈጣሪዎቹ እድገት ወሳኝ የሆኑ የስልጠና፣ የብድር እና የገንዘብ ድጋፎች ይመቻቻሉ::
ይሁንና በተለይ ቀደም ባሉት ዓመታት የሚሰጡ ድጋፎች በዋነኛነት በመንግሥት ላይ ብቻ የተንጠለጠሉ በመሆናቸው በሂደት ለሥራ ፈጣሪዎቹ ራሳቸውን ችለው በገበያ ተወዳድረው እንዲወጡ አላስቻለም:: በአሁኑ ወቅት በአንፃሩ ከመንግሥት ድጋፍና ክትትል ጥረት ባሻገርም የሦስተኛ ወገን ወይንም ባለድርሻ አካላት የመደገፍ እና የማብቃት አስተዋፅኦ ወደ ተሻለ ደረጃ ተጠግቷል::
በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ ሥራ ፈጣሪዎችን በመደገፍ ሂደት ሥራን ከመፍጠር ባለፈ ዘላቂ እንዲሆን በማስቻል ተግባር በመከወን ላይ ከሚገኙ ማዕከላት መካከል ደግሞ የኢንተርፕርነር ሺፕ ልማት ማዕከል -ኢትዮጵያ አንዱ ነው::
የኢንተርፕርነር ሺፕ ልማት ማዕከል -ኢትዮጵያ ከፊል መንግሥታዊ የሆነ በኢንተርፕርነር ሺፕ ልማት ፕሮግራም መዋቅር ሥራ በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እና በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ስምምነት የተቋቋመ ፕሮጀክት ነው::
ማዕከሉ በየካቲት 2005 ዓ.ም ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ሥራ እና ሀብት ለመፍጠር ተነሳሽነት ላላቸው፣ ሥራ ላይ ላሉ ጥቃቅን አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም ከፍተኛ የማደግ አቅም ላላቸው ድርጅቶች የሥልጠና እና የማማከር አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል::
የኢንተርፕርነር ሺፕ ልማት ላይ ምርጥ ተሞክሮዎችን በማውጣት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ታታሪና ስኬታማ ኢትዮጵያውያንን የሥራ እና ሀብት ፈጣሪዎችን መፍጠርና ማበልፀግን እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን እድገት ለማጎልበት አልሞ ይሰራል:: በዋነኝነት የኢንተርፕርነርሺፕ ሥልጠናዎችን፣ የተቋም አቅም ግንባታዎች፣ የንግድ ማጎልበቻዎችን የቢዝነስ የገበያ ትስስሮችና የፋይናንስ አቅርቦቶችን የማመቻቸት ሥራዎችን ያከናውናል::
ማዕከሉ ከሚያከናውናቸው ሥራዎች አንዱም የፋይናንስ አቅርቦትን ማመቻቸትና ማጠናከርን ታሳቢ ያደረግ ውድድር ማዘጋጀት ነው:: ለመጀመሪያ ጊዜም ከካሊፎርኒያ እና ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ‹‹ኢትዩ ስፐር የቢዝነስ እድገት እቅድ ውድድር›› በሚል መሪ ቃል ውድድር አዘጋጅታል::
ነባር የንግድ ሥራዎችን ለማሳደግ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ሥራ ፈጣሪዎች መሸለም እና መደገፍ አላማው ያደረገው የ2012/13 ዓ.ም ውድድር አሸናፊዎችም ባሳለፍነው ማክሰኞ ተለይተዋል:: በውድድር ላይ ከተሳተፉት ተወዳዳሪዎች መካከል የመጨረሻ አምስት አሸናፊዎች ተለይተዋል::፡
በሂልተን ሆቴል በተካሄደው የሽልማት መርሃ ግብር ላይም የውድድር አሸናፊዎቹ በአጠቃላይ 840 ሺ ብር ሽልማት ተካፋይ ሆነዋል:: የመጀመሪያው አሸናፊ 300 ሺ፣ ሁለተኛው 220 ሺ፣ ሦስተኛው ደግሞ 140 ሺ ብር አሸንፈዋል:: አራተኛ 100 ሺ ብር እንዲሁም አምስተኛው ደግሞ የ80 ሺ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል::
አምስቱ ኢንተርፕርነሮች ሥራ ፈጣሪዎች በውድድሩ ላይ ከአዲስ አበባ እና ከክልሎች ከተሳተፉ ከ900 በላይ አመልካቾች ውስጥ የተመረጡ ናቸው:: የውድድሩ የማመልከቻ ጊዜ ለሦስት ወራት የቆየ ሲሆን ከአጠቃላይ ተወዳዳሪዎች ውስጥ 44 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው::
ውድድሩ አሸናፊ የሆኑትን ተወዳዳሪዎችን የማሳወቁ ሂደት በውድድሩ ተሳታፊዎች ቁጥር መበራከት፣ በኮቪድ ወረርሽኝ ስጋት፣ በተደጋጋሚ በተደረጉ የምዘናዎች ክንውንና ምርጥ 20 አሸናፊዎችን መረጃ በትክክለኛነት የማረጋገጥ ሥራዎች ምክንያት ረዘም ያለ ጊዜ ወስዷል::
የውድድሩ ምዘና ሂደት ከተለያዩ ባንኮች ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የተውጣጡ ከ100 በላይ የሚሆኑ ዳኞች ተካተዋል:: የአንድ ቢዝነስ እድገት እቅድ ከ6 ዳኞች የመመዘን ዕድል እንዲኖረው ተደርጓል:: ከዚህ ባሻገር ምዘናዊ የአመልካቾችን ማንነትና የንግድ ድርጅቶቻቸውን ስም ሳይጠቀም ቀድሞ በተቀመጠው ግልፅ የምዘና መስፈርቶች ብቻ የተከናወነ ነው:: ‹‹ይህም ውድድሩ ሙሉ በሙሉ ተአማኒ እንዲሆን አድርጎታል›› ነው የተባለው::
ተሸላሚዎቹ በዶሮ እርባታ፣ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በቆዳ ውጤቶች፣ በእንጨትና በብረታ ብረት ማማረቻ እንዲሁም በዳቦ ማምረት የንግድ ሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ሲሆኑ አራቱ ከአዲስ አበባ ቀሪው ከኦሮሚያ ሆለታ ነው:: በፆታ ረገድ አንድ ሴት ኢንተርፕርነር በውድድሩ ላይ የሦስተኝነት ደረጃን በማግኘት ተሸላሚ ሆናለች::
ውድድሩን በቀዳሚነት ማጠናቀቅ የቻለው የሃዊ ጉዲና አክሲዮን ማህበር ባለቤት አቶ አንዱአለም ያዴሳ ነው:: ከዩኒቨርሲቲ እንደተመረቀ መንግሥት ሥራ እስኪሰጠው እጁን አጣጥፎ ከመጠበቅ ይልቅ የግል ጥረቱን መጠቀም ምርጫው በማድረግ ከብዙ ጥረት በኋላ የድርጅት ባለቤት ለመሆን መብቃቱን የሚገልፀው አንዱአለም፣ ድርጅቱም ከራሱ ተርፎ ለሌሎች ስምንት ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል::
‹‹ድርጅቱን ለማጎልበት እና ውጤታማ ለማድረግ ዘወትር አማራጮችን መቃኘት ደከመኝ አልልም›› የሚለው አንዱአለም፣ የኢንተርፕርነር ሺፕ ልማት ማዕከል ኢትዮጵያ የሚሰጠውን ሥልጠና መውሰዱም የንግድ ሥራዎቹን ለማሳደግ እንዳስቻለው ይጠቁማሉ::
መሰል ውድድሮች ሥራ ከመፍጠር ባለፈ ዘላቂ እንዲሆን የማድረግ አቅምን እንደሚፈጥሩ የሚያስገነዝበው አንዱአለም፣ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ሳይሳኩ የቀሩ ግቦችን እውን ከማድረግ ባለፈ የተወዳዳሪነት አቅምን ለማጎልበት ከፍተኛ አቅም የሚፈጥሩ ስለመሆናቸውም ነው አፅእኖት የሰጠው::
ከውድድሩ ያገኘውን ገንዘብ ጨምሮ በቀጣይ ራእዩን እውን ለማድረግ እንደሚተጋ የሚገልፀው አንዱአለም፣ ከመንግሥት ባገኘው 5 ሺ ካሬ ሜትር መሬት ላይ የዱቄት ፋብሪካ ሆለታ ላይ ለመገንባት 150 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አቅድ አለው:: ይህ ውጥኑ እንደሚሳካም ጥርጥር የለውም::
ውድድሩን በሁለተኝነት ያጠናቀቀው ደግሞ የኤቴኤ ሆቴል እና ቱሪዝም ተቋም መስራችና ሥራ አስኪያጅ የሆነው አቶ አብዱልፈታህ ተማም ነው:: ድርጅቱ በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን ማፍራት አላማው ያደረገ መሆኑን የሚጠቁመው አቶ አብዱልፈታ፣ በውድድሩ ያገኘው ውጤት ለተሻለ ሥራ እና መነቃቃትን እንደሚፈጥርበትም ነው ያስታወቀው:: ቀጣይም የራሱን ኮሌጅ ለመገንባት በየዓመቱ የሚቀበላቸውን ተማሪዎች ቁጥር የማሳደግ አቅድ አለው::
በውድድሩ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ 140 ሺብር ተሸላሚ የሆነችው ደግሞ የሽርሽር ኢትዮጵያ የቆዳ ውጤቶች አምራች ድርጅት መስራች እና ባለቤት ሂሩት ዘለቀ ናት:: ከ40 በላይ ሠራተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረው ድርጅቷ የእጅ እና የኪስ ቦርሳዎችን ፣ ጫማዎችን፣ ጃኬቶችና ቀሚሶችን በማምረት ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ያቀርባል::
ሥራዋን ይበልጥ ለማስፋፋት ብዙ ብትወጥንም የገንዘብ እጥረት ሃሳቧን እንዳታሳካ ማነቆ ሆኖባት መቆየቱን የምታስታውሰው ሂሩት፣ በውድድሩ አሸናፊ በመሆኗም የችግር ታሪኳን የመለወጥ አቅም እንዳለው ጥርጥር የላትም::
‹‹በመሰል የውድድሮች አሸናፊ መሆን ከገንዘብ ባለፈ ለሥራ ፈጣሪዎች ከፍተኛ የሥነልቦና ልእልናን የሚላብስና የበለጠ ለመስራት የሚያነሳሳ ነው›› የምትለው ሂሩት፣ በቀጣይም ከመንግሥት ባገኘችው ሼድ አዳዲስ ማሽኖችንና ተጨማሪ ሠራተኞችን በማዕከል የንግድ ሥራዋን ብሎም የገበያ ተደራሽነትን ለማስፋት አቅዳለች::
መሰል ውድድሮች መስራት እየቻሉ አቅም ያጠራቸውን በመደገፍ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑም ሊበረታታና ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚገባ አፅእኖት የምትሰጠው ሂሩት፣ ሥራ ፈጠራ ከባድ እና ሁሉን ነገር አልጋ በአልጋ ባይሆንም ጠንክሮ መታገል እና መሰል የውድድር አጋጣሚዎች አነፍንፎ የመጠቀም ልምድን ማዳበር እንደሚያስፈልግም ሳታስገነዝብ አላለፈችም::
የአንተርፕርነር ሺፕ ልማት ማእከል -ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሃሰን ሁሴንም ኢትዮጵያ ውስጥ ቢዝነስን እንዴት መመስረት እና ማስቀጠል ይቻላል የሚለው እውቀት አለ ከማለት ይልቅ የለም ለማለት የቀረበ መሆኑን ይስማሙበታል:: በርካቶች ቢዝነስ ከጀመሩ በኋላ የአስተዳደር ችግር፣ የገንዘብ አያያዝ እና አጠቃቀም ክፍተት፣ እድገትን በአግባቡ የማስቀጠል እንዲሁም የንግድ ተደራሽነት ውስንነትን ጨምሮ የተለያዩ ፈተናዎች እንደሚጋፈጡም ይጠቁማሉ::
መሰል የውጤታማነት ተግዳሮች እስካልተፈቱም እንደ ግለሰብም ሆነ እንደአገር ስኬታማ መሆን እንደማይቻል አፅእኖት የሚሰጡት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ እርሳቸው የሚመሩት ማእከልም በቢዝነስ አካባቢው ላይ የተጋረዱ የአመለካከትም ሆነ እውቀት ክፍተቶችን ለመሙላት እንዲሁም የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ያስረዳሉ::
እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ፣ ማእከሉ የመንግሥት እና የግል ተቋማትን የሥራ መፍጠር ችሎታ ለማጎልበት የአቅም ግንባታ ሥራ ይሰራል:: ሥራ ለሌላቸው እና ያላቸውም ውጤታማ ለመሆን ለተቸገሩ እንዲሁም አዲስ ሥራ ለመስራት እቅድ ለሚያስቡ አመለካከትን የሚቀይሩና ክህሎት ተኮር የሆኑ ስልጠናዎችን ይሰጣል:: የዩኒቨርሲቲ መምህራን የቴክኒክና ሙያ አሰልጣኖች ሥራ ፈጠራን የሚያበረታታ አቅጣጫን እንዲከተሉ እንዲያበረታቱ የሚያግዙ የስልጠና ድጋፎችን ይሠጣል::
በዚህም በርካቶች ቢዝነሳቸውን በችሎታና በእውቀት እንዲመሩ በማድረግ ውጤታማ አድርጎናል የሚሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፣ በተለይም መንግሥት ሥራን መጠበቅ ዋነኛ ህልም መሆን እንደሌለበት የተለያዩ ሃሳቦችን በማውጠንጠን ሌሎች አማራጮችን መቃኘት ብሎም የግል ሥራን በመፍጠር ሀብት መፍጠር እንደሚቻል በማስገንዘብ ረገድ ተጨባጭ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት መቻሉን ነው ያስረዱት:: ከሥራ ዕድል ፈጠራ ባሻገርም በኢኮኖሚ ረገድም ሚሊዮኖችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ነው›› ያሉት::
‹‹ማእከሉ ከተቋቋመ ሰባት ዓመት ቢሆነውም አደረጃጀቱ ችግር አለበት፣ ከሁሉ በላይ የራሱን ሀብት እንዲያመጣ ፈቃድ የሚሰጥ አይደለም›› ያሉት ዶክተር ሀሰን፣ ከሥራ ፈጠራ እና ከቢዝነስ እውቀት ጋር የተገናኙ ሥራዎችን የሚሰሩ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር የሚሰሩ ሥራዎች ቢኖሩም የሚገኘው ገንዘብ ውስን በመሆኑ ማእከሉ እንደፈለገ እንዳይራመድ ሥራዎቹን ይበልጥ እንዳያሰፋና በርካቶችን ተደራሽ እንዳያደርግ ዋነኛ ማነቆ እንደሆነበትም ሳያስገነዝቡ አላለፉም::
የፌዴራል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ገብረመስቀል ጫላ፣ ማእከሉ የተመሰረተው በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሥራ ባህል ለማስተካከልና ዜጎች ሥራ ጠባቂ ሳይሆኑ ፈጣሪ እንዲሆኑ፣ እንዳያማርጡ ከጀመሩ በኋላም እንዲያስፋፉና ዘላቂ እንዲያደርጉ ለማስቻል መሆኑን ያረጋግጣሉ::
በማእከሉ የሚሰጠውን ስልጠና ለየት የሚያደርገው ዜጎች የሥራ ፈጠራ ባህሪያትን ጠንቅቀው በመረዳት ገንዘብ ባይኖራቸውም ወደ ሥራ መግባት፣ ሥራ መፍጠርና ትርፋማ መሆን የሚያስችል በመሆኑ ነው የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከየትኛውም ተቋማት የተሻለ የንግድ ምክር አገልግሎት እንደሚሰጥና ለዚህም ብቃት ያላቸውም ባለሙያዎችን ማካተቱን ነው ያስገነዘቡት::
ማእከሉ ባለፉት ዓመታት ተግባራቱ በርካቶች ተጠቃሚ ማድረጉንና በቀጣይም ይህን እንደሚያስቀጥል አጽእኖት የሰጡት አቶ ገብረመስቀል፣ ዜጎች የማእከሉን አገልግሎቶች በመጠቀም የውጤታማነት መንገድ መራመድ እንደሚችሉ በመገንዘብ ዕድሎችን መጠቀም እንዳለባቸው ሳያስገነዝቡ አላለፉም::
የአንተርፕርነር ሺፕ ልማት ማእከል-ኢትዮጵያ ከዚህ ውድድር የተገኙ ስኬቶችና ልምዶችን በመጠቀም ሁለተኛውን የኢትዮ ስፐር የቢዝነስ እድገት እቅድ ውድድር በብሔራዊ ደረጃ ለማካሄድ ከካሊፎርኒያ እና ከዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ለማዘጋጀት ከስምምነት ላይ ተደርሷል::
የውድድሩ አሸናፊዎች ከሶስት መቶ ሺህ እስከ 80 ሺህ ብር እንደየደረጃቸው ተሸላሚ ሆነዋል፤
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2013