ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ግንቦት 29 ቀን 2013 ዓ.ም የጣና በለስ ቁጥር አንድ የስኳር ፋብሪካን መርቀው በይፋ ሥራ ባስጀመሩበት ዕለት ባደረጉት ንግግር ውስጥ በርካታ አገራዊ ስኬቶችንና ተግዳሮቶችን መጠቃቀሳቸው ይታወሳል:: በተለይም ዛሬ የተጋረጡብንን ጋሬጣዎች በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ባንዳዎችና ባዕዳን” ያሏቸውና በእኩይ ተግባራት የተጠመዱ ሴረኞች እየፈጸሙት ያሉት አገርን የማቁሰል አደጋዎች ምንኛ የተወሳሰቡና የረቀቁ እንደሆኑ ገለጻው በሚገባ አጉልቶ የማመላከት አቅሙ ከፍ ያለ ነው::
“ባንዳነትና ባዕድነት” የሚሉት ሁለት ቃላት የተሸከሙት መልእክት የተዘወተሩና በአዘቦት ተግባቦታችን የምንገለገልባቸው ዓይነት አገላለጾች አይደሉም :: በዚህ ጸሐፊ እምነት ይህ ምልከታ ዳጎስ ላለ መጽሐፍ ርዕስ ቢሆን ብዙ ሃሳቦች ሊስተናገዱበት እንደሚችሉ መገመት አይከብድም :: ስለዚህም ነው ለዛሬው ጽሑፌ በእጅጉ ተማርኬበት “ነዎር!” በማለት በርዕስነት ለመዋስ የመረጥኩት::
“መጀመሪያ በቃሉ ትርጉም እንስማማ”
ይህንን አባባል አዘውትረው ይጠቀሙበት የነበረው ጥንታዊ የግሪክ ፈላስፎች ስለመሆናቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ደጋግመው ይጠቅሳሉ :: አንድ ቃል በተሸከመው ጽንሰ ሃሳብ ልንግባበት ካልተቻለ ትርፉ ከውጤት አልባ ክርክርነት አይዘልም:: በዚሁ መሠረትም “ባንዳነትና ባዕድነት” የሚባሉት እነዚህ ሁለት ቃላት የተሸከሙትን ጽንሰ ሃሳብ ጥቂት ተንተን በማድረግ ካፍታታን በኋላ ወደ ዋናው የመነሻ ሃሳባችን ፈጥነን እንሻገራለን::
“ባንዳ” የሚለውን ስያሜና ጽንሰ ሃሳብ ቋንቋችን ቤተኛ አድርጎ የተላመደው ከኢጣሊያ ወረራ ማግስት ጀምሮ እንደሆነ ይታመናል :: የኢጣሊያንኛው “bandito” ለቋንቋችን እንዲስማማ ተደርጎ ስራ ላይ የዋለው እንደ ኦርጂናል ትርጉሙ “ሽፍታ፣ ዘራፊ፣ ቀማኛ፣ አመፀኛ፣ ወንበዴ ወዘተ.” የሚሉ ትርጉሞችን ተሸክሞ ብቻ አይደለም ::
“ባንዳ” የሚወክለው በዋነኛነት “ከዳተኛነትን” ነው :: ክህደቱ የሚፈጸመው ደግሞ ከእለት ግጭትና አለመተማመን ጋር በተያያዘ መልኩ ሳይሆን ዓይንን ጨፍኖ፣ ኅሊናን አሳውሮ የራስ አገርን በመካድና የራስን ሕዝብን በማቃለል በሚገለጽ የከፋ ድርጊት ነው :: የባንዳነት ዋነኛ መገለጫው መሠሪነት ነው :: ሆድ አደርነትና ተልከስካሽነት ይበልጥ ይገልጸዋል:: ለጊዜያዊ ጥቅም በማበድና በኃላፊ ጠፊ ጊዜያዊ ክብር ማልሎ ከጠላት ጋር በማበርና በመተባበር “ራስን ማዋረድ” ዋናው መታወቂያ ነው::
“ለሆድ አደር ባንዳነት” የሚሰጡ በርካታ መገለጫዎች ቢኖሩም አዘውትረው የሚጠቀሱትና በተለዋጭ ዘይቤ ከበለጸጉት መካከል “ከሃዲ፣ የእናት ጡት ነካሽ፣ አጋድሞ አራጅ ወዘተ.” የሚሉትን ጥቂቶች ብቻ ማስታወስ ይቻላል:: እርግጥ ነው የባንዳነት ደረጃው ሊለያይ ይችላል:: አንዳንዱ “መሠሪ ባንዳ” ባህርይው የረቀቀ፣ ተግባሩ የተመሳጠረ ዓይነት ሊሆን ይችላል:: እንዲህ ዓይነቱ ባንዳ በጥርሱ እየሳቀ፣ ብብት ሥር ተወሽቆ፣ ፊት ለፊት እያሸረገደ “አገሩንና ሕዝቡን” እሳቱ በተጋጋመ መሰዊያ ላይ አጋድሞ ለመሰዋት ኅሊናውም ሆነ እምነቱ “ተው ይቅርብህ!” እያሉ እንዳይወቅሱት ሁለቱንም የነፍሱን ጩኸቶች አስቀድሞ የሚገድላቸው ኃላፊ ጠፊ ጥቅም ውስጥ ራሱን ወሽቆ በማድፈጥ ነው:: “አፈ ቅቤ ሆደ ጩቤ” የሚለው ተለምዷዊ ብሂል ይበልጥ ይገልጸዋል::
አንዳንዱ ባንዳ እርምጥምጥና ልክስክስ ይሉት ዓይነት ነው :: የአንድ ስንዝር ጉርሻውን እያላመጠ “ኑ! እንደኔ ለጠላት እንደር፤ ለእቅዱም ተንበርክከን እንስገድ!” እያለ የሚደሰኩረው በግላጭና ፊት ለፊት እያቅራራ ነው :: ይህ ዓይነቱ ባንዳ “ፀሐይን ወቅታዊ ደመና ሲጋርዳት” ቢመለከት እንኳን ዳግም ፈክታ የምታበራ ስለማይመስለው ፀፀት ተሰምቶት በንስሃ አይነጻም :: ከዚህም ከፍ ሲል አገር ክብሯ ቢዋረድ፣ ሕዝብ ከሞገሱ ቢጎድልና ቢጠቃ ደንታ አይሰጠውም:: ሆዱን አምላኩ፣ ክህደቱን ክብሩ አድርጎ ስለሚቆጥር ህልሙና ቅዠቱ “የዕለት እንጀራ መሶቡ” እንዳይጎድል አጥብቆ በመትጋት “መጋደል” ነው::
ሌላው የባንዳነት ዓይነት በየዋህነት አረንቋ ውስጥ ራስን በክህደት ውስጥ መዝፈቅ ነው:: እንዲህ ዓይነቱ ተልመጥማጭ ከሀዲነት ነገሮችን ካለማገናዘብና በነፈሰበት በመንፈስ እምነትን በማጉደል “ጀብድ ይመስል” ለክፉዎች የመገልገያ ቁሳቁስ በመሆን መቅለልና የራስንና የአገርን ክብር በጠላት እግር ሥር አንጥፎ መረማመጃ ማድረግ ነው:: እነዚህን ሁሉ የባንዳነት ዓይነቶች አገራችንን በተለያዩ ዘመናት ባዕዳን ወራሪዎች በተተናኮሏት ወቅቶች ሁሉ ተፈጽመዋል:: በታሪክ ተመዝግበው የተላለፉልን ብዙ አብነቶች ስላሉም ማመሳከሪያው አይቸግረንም::
በአንጻሩ “ባዕድነት” የሥጋ ዝምድና ያለመኖር ብቻም ሳይሆን “ለአገር ክብርና ልማድ አደግሽነት የሌለው፣ እንግዳ፣ መጣተኛ፣ ፈላሲ” እያሉ መዛግብተ ቃላቶቻችን ይዘቱን ይተነትናሉ:: ትርጉሙን ከፍ እናድርግ ከተባለም ባዕድነት የመንፈስ ጽናትንና ክብርን መገፈፍ ነው:: ከደም ቁርኝት የከፋ ባዶነትም ጭምር:: ብሂሎቻችን እንደሚያረጋግጡልን “ባዕድነት ሥር የለውም:: ባዕድና ጨለማ አንድ ነው:: ባዕድ ከሳመው ዘመድ የነከሰው::” እየተባለ የሚመሰለውም ስለዚሁ ነው::
ይሁን እንጂ ከባዕዳን ጋር መወዳጀትና መቀራረብ አብሮ መሥራትም አይቻልም ማለት አይደለም:: አይቻልም ብንልም ከእውነት ጋር ተላትመን መሸነፋችን አይቀርም :: ከባዕዳን ጋር የሩቅ ተመልካች በመሆን ተካባብሮና ተደጋግፎ መኖርም ይቻላል:: ይህም እውነት ነው:: እርስ በእርስ እየተጠራጠሩ በባዕድነት ስሜት “አትድረስብኝ እኔም አልደርስብህም እየተባለ ሩቅ ለሩቅ ቆሞ መተያየትም ይቻላል:: ከሁሉም የከፋው ባዕድነት ግን በጠላትነት ስሜት “ሌላውን አጥፍቶ ራስን ለማዋረድ” የሚሴረው ሴራ ነው:: ይህ ዓይነቱ ጭካኔ የተሞላበት የባዕድነት መሰሪ ድርጊት ዛሬ በብዙ መልኩ እየተገለጠ እንዳለ በነጋ በጠባ የምናስተውለው እውነታ ነው::
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የወቅቱን ሀገራዊ ፈተና ሲገልጹ እነዚህን ሁለት ቃላት የተጠቀሙት በላላው የመዛግብተ ቃላት ድንጋጌ ይዘታቸው ሳይሆን በመጨረሻውና በከፋው ገላጭ ብያኔያቸው ነው:: በተለይም ተባብረው፣ ተናበው፣ ተሻርከውና ግንባር ፈጥረው ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ለመዋጥና ለማስዋጥ ሌት ተቀን የሚያደቡትን ጠላቶቻችንን ምን ያህል እንደተደራጁብን ለማሳየት ጭምር:: እርግጥ ነው የዛሬው የሀገራችን ወቅት ወለድ ፈተናዎች በታሪክ ከምናስታውሳቸው መሰል ተግዳሮቶች መካከል ምናልባትም በብዙ መልካቸው የሚለዩና “እስከ ዛሬ ድረስ እንዲህ ዓይነት ሀገራዊ ዘርፈ ብዙ የጠላቶች ሰልፍ ገጥሞን ያውቅ ኖሯልን?” ብለን ለመጠየቅ የምንገደደውም በዚሁ ምክንያት ነው::
በዚህ ጸሐፊ እምነት የዛሬዎቹ የጥፋት ባንዳዎች የዘመቱብን በብብታችን ውስጥ ተወሽቀው፣ በባዕዳን ሀገር ተጠልለው፣ በሩቅና በቅርብ ተመሳስለውና በክህደት ታውረው እየተደነባበሩ እንደሆነ ለመረዳት አይከብድም:: ባንዳዎቹ የጨካኝ ተኩላነት ባህርይ የተላበሱ ስለሆነ “ቆሌያቸው የሚደሰተው” የወገንን ደምን ሲያፈሱ፣ የሀገር ንብረትን ሲያወድሙ፣ የአመጽ ስልቶችን ቀይሰው የአገርና የሕዝብ ክብር የተዋረደና የቀለለ መስሎ ሲታያቸው ነው:: ከጠላት ጋር ተሰልፎ በፊት አውራሪነት አመጽ የማስተባበርና የማስፈጸም ተልእኳቸውን የሚወጡትም “ክብራቸው ነውራቸው፤ ሆዳቸው አምላካቸው” እንደሆነ ስለሚያምኑ ነው::
ለከበቡን ታሪካዊ ባዕዳን ጠላቶች ፈረስ ሆነው እንዲጋልቡባቸው ጀርባቸውን የሚሰጡት በዕለት ጥቅም ተደልለው፣ የኅሊናንና የዜግነትን ክብር አራክሰው ራሳቸውን ካሳመኑ በኋላ ነው:: “ባንዳነት” ለአገር ይሉት ክብር፣ ለሕዝብ ይሉት አክብሮት የለውም:: ለባንዳ ሆዱ አገሩ፣ ክብሩ ውርደቱ ስለሆነ ሰብዕናው የተቃወሰ ብቻም ሳይሆን በቁም ሞቶ የከረፋ ጭምር ነው::
ባዕዳኑ ግብጽና ሱዳን ፊታውራሪ አድርገው ያሰለፏቸው የእኛዎቹን የባንዳዎች ጥርቅም መጥቀሱ ብቻ ለምሳሌነት በቂ ይሆናል:: እንደምን “የእትብት መቀበሪያ አፈርን፣ የበድን ማረፊያ ዘላለማዊ ቤትን፣ ጀግኖች በደማቸው ማህተም፣ በአጥንታቸው ማገርነት ገንብተው ያስረከቡንን አገር” እንደ ቀላል ቁስ ለድርድር ለማቅረብ እንደምን የሞራል ብርታት ሊገኝ ቻለ? ባንዳነት ማለት ይህ ነው:: ባንዳነት በባዕዳን እግር ሥር ወድቆ ጭነት ለመሸከም ራስን “ጌኛ” ማድረግም ነው::
አሜሪካ ሉዓላዊ ክብራችንን ተዳፍራ ካላዘዝኳችሁ በማለት “ዱታ” ነኝ እያለች የምትፎክረውም የእኛዎቹ ዘመንኛ ባንዳዎች በሚቀልቧት የሀሰትና የፈጠራ መረጃዎች ቅንብር ማስረጃነት ነው:: እንዲያማ ባይሆን ከራሷ ከአሜሪካ መፈጠር ሺህ ዘመናት አስቀድሞ የተፈጠረች፣ የዘፍጥረት ታሪኳ የሚያስደንቅና የሚያኮራን ኢትዮጵያን ያህል ሀገር ለድርድር ማቅረብ እንደምን ተቻላቸው? ልምሻ በያዘው ቡጢያቸውስ ሊመቷት እንደምን ወኔ አገኙ? ወኔም ሞራልም የሚባል ነገር እንዳልፈጠረባቸው ድርጊታቸው ጥሩ ማሳያ ነው ::
ባዕዳኑና ባንዳዎቹ ዛሬ ተበረታተው ኃይላቸውን በማስተባበር ሊፈነጩ የተነቃቁት የውስጣችን ችግር መረማመጃ ስለሆናቸው፣ የልዩነታችን ስፋት ወለል ብሎ የሚያሾልካቸው ስለመሰላቸው ይመስላል:: አያውቁትም እንዳንል የታሪካችን ምስክር በሼልፋቸው ላይ ተደርድሯል :: አያውቁንም እንዳንልም የኢትዮጵያዊነት ክብራችንና ዝናችን ተደጋግሞ ሲዘመርለትና ሲቀነቀን መስማታቸው አልቀረም:: ይሁን እንጂ አገራዊ ችግሮቻችን የገዘፉ ቢመስልም እንኳን ከእርምጃችን ፊት ተገሽረው የተስፋ መዳረሻችን ግን በፍጹም ሊገቱ አይችሉም::
የትኛው ድምጻዊ ነበር “አያውቁንም እኛን አያውቁንም” እያለ ያዜመው? እውነት ነው አላወቁንም:: ቢያውቁንም ግድ የለም:: ለጊዜያዊ ችግራችን መርዳታቸውንና ማበደራቸውን ብናከብርላቸውም በሉዓላዊነታችን ላይ እንዲደራደሩ ግን ልንፈቅድላቸው አይገባም:: የባንዳዎች ፍጻሜ በጉም ይመሰላል:: አለን ሲሉ ተዋርደው ሊሟሽሹ እንደሚችሉ የተረዱት አይመስልም:: ይብላኝ ለባንዳዎችና ለባዕዳኑ ወደረኞቻችን እንጂ ኢትዮጵያ ነበረች፣ አለች ወደፊትም በክብር ከፍ ብላ እንደምትኖር ለማረጋገጥ መሐላ አያስፈልግም::
ባንዶች ሲርመጠመጡ የጀግኖች ጥንካሬ ይበረታል:: ባዕዳን ሲያሴሩ በደም የተሳሰሩ ቤተሰቦች ወኔያቸው ከፍ ብሎ ሴራቸው ሳይተገበር ይሽመደመዳሉ :: ይህ እውነት ነው:: በታሪክ ፊትም ተፈትኖ የተረጋገጠ ነው:: ዋናው ጉዳይ የባንዶችንና የባዕዳንን የልቅሶ ቀረርቶ ለማድመጥ ጆሮን መክፈት ሳይሆን የጓዳችንን ቆሻሻ አጽድቶ መንጻት ነው :: ሰላማችን ብርድ እንዳይገባው በኅብረ-ሸማ ሸፍነን መንከባከብም ግድ ነው:: በጥቃቅን ጉዳዮች ከመሻኮት ይልቅ በትልልቅ አገራዊ ጉዳዮቻችን ላይ አትኩሮ መረባረብ ተመራጩ ስልት ነው:: ያኔ ባንዳ ኮስምኖ ይሟሟል፤ ባዕዳን ጠላቶችም ሟሸው ሀፍረት ይከናነባሉ:: ይሄው ነው:: ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2013