አፍሪካውያን አገራት አንድነት ሃይል፣ ህብረትም የድል ምስጢር መሆኑን ባለመረዳታቸው፣ እርስ በእርስ ያላቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር እጅግ ደካማ ሆኖ ዓመታት ተቆጥረዋል:: በጋራ ከመበልፀግ ይልቅ የግል እድገታቸውን መሻታቸውም በተለይ ምጣኔ ሀብታቸው የሚፈለገውን ያህል እንዳይሮጥ ጨምድዶ እንደያዘው ይታመናል::
የአፍሪካን ስንክሳሮች በማጥናት የሚታወቁ የተለያዩ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ምሁራንም፣ በአፍሪካ ምድር አህጉራዊ ቀርቶ ቀጠናዊ ትስስር በቅጡ መጎልበት ባለመቻሉ ከጊዜ ጊዜ ዘርፈ ብዙ ኪሳራዎችን እየደመረ ስለመምጣቱ ይመሰክራሉ::
የአፍሪካን የምጣኔ ሀብት በመተንተን የሚታወቁት ናጂንጋ ሃኪናህ ‹‹ዘ ኤክስችንጅ››ላይ ባሰፈሩት ሰፊ ሀተታ፣ ብዙ መባዘን ሳያስፈልግ የምስራቅ አፍሪካ አገራት የጋራ ንግድ ቢሰናሰል ብቻውን ከሁለት ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚችል አስረድተዋል:: ይሁንና የቀጠናው አገራት ከጋራ ይልቅ በተናጥል ጉዞ እየዳከሩ በተለይ የንግድና የኢንቨስትመንት ትስስራቸው ደካማ በመሆኑ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም መነጠቃቸውን ቀጥለዋል::
አፍሪካውን ከመደጋገፍ ይልቅ መገፋፋት በሚመስል መልኩ በተናጥል ለመጎዛቸው ድክመት ታዲያ በርካታ ምክንያቶች ይዘረዘራሉ:: የፖለቲካ ውሳኔና ፍላጎት ማጣት ብሎም ‹‹ከባልሽ ባሌ ይበልጣል›› ራስ ወዳድ ስግብግብነት ከሁሉ ቀድሞ ይጠቀሳል::
‹‹አህጉሪቱን በኢኮኖሚ ለማስተሳሰር የሚያስችል የመሰረተ ልማት ብሎም የንግድ አጋርነት ስምምነት አለመኖርም አፍሪካውያን እርስ በእርስ ያላቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብር ደካማ አድርጎታል›› የሚሉ ምሁራን ቁጥርም በርካታ ነው::
አፍሪካውያኑ እርስ በእርስ ቢተሳሰሩ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም መፍጠር ቢቻላቸው ከጋራ ይልቅ በተናጥል ጉዞ እየዳከሩ ስለመሆናቸውም በተለያዩ ጥናቶችና መረጃዎች ቁልጭ ብሎ ተቀምጦአል:: መረጃዎች እንደሚያሳዩትም፣ አፍሪካ በዓለም አቀፉ ገበያ ላይ ያላት የተሳትፎ ድርሻ ከሁለት በመቶ አይዘልም:: በእሲያ አህጉር በአገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ 60 በመቶ፣ በአውሮፓውያን መካከል ደግሞ 70 በመቶ ሲመዘን በአህጉራችን አፍሪካ በአገራት መካከል ያለው የንግድ አጋርነት ከ17 በመቶ የሚበልጥ አለመሆኑም ለዚህ በቂ ምስክር ይሆናል::
ይህ ከባድ የግለኝነት አባዜ ታዲያ በፓን አፍሪካኒዝም ጥንስስ አንድ አፍሪካ ትፈጠር ዘንድ ከሚሻውና በተለይ በአጀንዳ 2063 ውጥን ድንበር አልባ አህጉር በመፍጠር ለኢኮኖሚ ትስስር ብዙ ከሚታታረው የአፍሪካ ህብረት እይታ የተሰወረ አይደለም::
እናም ህብረቱ በቀደመው የአፍሪካ ቅኝ ግዛት ዘመን የተቀመጠውን ድንበር በመበጣጠስ የየቅል ጉዞን በማስቀረት በአገራት መካከል ተመጋጋቢ የሆነ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር በሚል የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነትን ይፋ አድርጓል::
አባል አገራቱም እ.ኤ.አ በ2018 በሩዋንዳ ርዕሰ መዲና ኪጋሊ በተደረገ ጉባኤ ላይ ይህን ስምምነት ለመፈፀምና በትግበራው ከሚገኘው ትሩፋት ለመቋደስ ፊርማቸውን አስቀምጠዋል:: ስምምነቱም አገሮች በመካከላቸው የሚኖር ንግድ ላይ ቀረጥ ወይንም ሌሎች ንግድን የሚያደናቅፉ መሰናክሎችን ሳይጥሉ እንዲገበያዩ ማድረግን ታሳቢ ያደረገ ነው::
የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና (AfCFTA) ስምምነትም ከተፈርመ በኋላ በድርድሮች መጓተትና የቅድመ- ስምምነት ሥራዎች እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው ዘር፣ ቀለም፣ ቋንቋ፣ የስልጣን ከፍታ፣ የሀብት ደረጃ፣ አዋቂና ታዋቂ፣ መሪና ተመሪን ሳይለይ በሚቀጥፈው የኮቪድ 19 ቫይረስ ምክንያት ተግባራዊነቱ ዘግይቶ እ.ኤ.አ በጥር 2021 ወደ ሥራ ገብቷል::
በተሳታፊ አገራት ብዛት ሂሳብ ከተሰራም በዓለም ትልቁ የሆነው ነፃ የንግድ ቀጠና 55 አገራትን በማሳተፍ ከአንድ ነጥብ ሦስት ቢሊየን በላይ ዜጎችን ያስተሳስራል:: በኢኮኖሚ ትርፉቱም ሲሰላ ደግሞ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ምጣኔውም 3 ነጥብ 4 ትሪሊየን ዶላር ይገመታል::
ተናጥላዊም ሆነ ቡድናዊ አስተዋፆውም ተዘርዝሮ የማያልቅ ነው:: የምጣኔ ሀብት ምሁራኑ እንደሚያስገነዝቡትም፣ ነፃ የንግድ ቀጠታ በተሳታፊ አገሮች መካከል ተመጋጋቢ የሆነ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር፣ በአህጉሪቱ የኢንዱስትሪ ዕድገት እንዲመጣ፣ የግል ባለሀብቱ ተሳትፎ እንዲያድግ፣ ለሥራ ፈጠራ እና ሚዛናዊ የንግድ ሥርዓትን ለመፍጠር ከፍተኛ ፋይዳ አለው::
ስምምነቱም ከተናጥል ጉዞና እድገት ይልቅ ተያይዞ መበልፀግን በማፋጠን አፍሪካ በዓለም የንግድ ሥርዓት ውስጥ ያላትን ቦታ በማሳደግ ከዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች ጋር በእኩል ደረጃ መወዳደርም ሆነ መደራደር የሚያስችላትን አቅም ያጎለብታል::
ኢንቨስተሮችን ለመሳብም አፍሪካን የኢንቨስተሮች ተመራጭ መዳረሻ ያደርጋታል። ኤክስፖርት አማራጮችን ያሰፋል:: በምዕራባውያን ላይ የተንጠለጠለውን የአገራቱን የወጪ ንግድ ከሥጋት ያወጣዋል:: በዓለም አቀፍ ደረጃ የመወዳደር መንፈስን ያጎለብታል:: ኢንዱስትሪያል ፓርኮች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ በማድረግ የገበያ ዕድሎችን ይፈጥራል::
የንግድ ቀጠናው በተሳታፊ አገሮች መካከል ያለውን ንግድ በ2022 በ50 በመቶ ይጨመረዋል ተብሎ ይጠበቃል:: በቅርቡ ይፋ በሆነው የዓለም ባንክ መረጃ መሰረት፣ ቀጠናዊ ገቢን በ7 በመቶ ወይንም 450 ቢሊየን ዶላር ይጨምራል::
ንግድን በማቀላጠፍ ሸማቾችና አምራቾች ሰፊ ገበያ እንዲያገኙ ያደርጋል:: አምራቾች ምርታቸው በመሸጥ ሂደት የትራንስፖርት ወጪያቸው እንዲቀንሱ ያስችላል:: የትራንስፖርት ወጪ መቀነስ ደግሞ ለጊዜው ትልቅ ትርጉም አለው:: ምክንያቱ ደግሞ የሸቀጡም ዋጋ በዚያው ልክ ስለሚቀንስ ነው:: ነፃ የንግድ ቀጠናው አምራቾች ምርታቸውን በብዛት እንዲሸጠ ተጠቃሚዎች በዝቅተኛ ዋጋ የፈለጉትን እጃቸው፤ በማስገባት የኑሮ ሁኔታቸው እንዲያሻሻሉ ያግዛል::
ከፍተኛ መጠን የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያስችላል:: ብዙዎች ከድህነት እንዲወጡ በማድረግ ግለሰቦች መካከል ያለ የኑሮ ደረጃ አለመመጣጠንን ይቀንሳል:: የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ዋና ጸሐፊ ዋምኬሌ ሜኔ፣ ስምምነቱ የንግድ ስምምነት ብቻ አይደለም:: አፍሪካን ከድህነት የማውጣት ሁነኛ ተስፋችን ነው ይላሉ:: የዓለም ባንክ ሪፖርትም ስምምነቱ እ.ኤ.አ በ2035 በአስከፊ ደህነት የሚኖሩ ከ30 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ከድህነት ለማዋጣት እንደሚያስችል ይመሰክራል::
ከላይ የተጠቀሱ ትሩፋቶችን ዋቢ የሚያደርጉት በአፍሪካ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ማዕከል ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ካሮሊን ካንዲ ሮብ፣ የዓለም ግዙፉ ነፃ ቀጠና አፍሪካን ወደ ከፍታው እንደሚያሸጋግራት ኢኮኖሚዋን እንደሚያፈረጥመው ጥርጥር የላቸውም:: የአፍሪካኖች ህብረት ዓለም የኢኮኖሚ ትብብር ምሳሌ እንደሚሆን ይመሰክራሉ:: ‹‹ስምምነቱ ዕድገትን ለማፋጠን፣ በዓለም አቀፍ መድረክ ተፎካካሪ ለመሆን ኤክስፖርት አማራጮችን ለማስፍት እንዲሁም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ብሎም ለማጎልበት ወሳኝ ነው›› የሚሉት አማካሪዋ፣ የአፍሪካው የውጭ በ560 ቢሊየን ዶላር እንደሚጨምረው፣ በመካከላቸው ያለውን የውጭ ንግድ ምጣኔም 81 በመቶ እንደሚያደርሰው ነው ያስገነዘቡት::
ከትሩፋቶቹ ዝርዝር መረዳት እንደሚቻለውም፣ ስምምነቱ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች በርካታ ዕድሎችን ይዞ የሚመጣ ነው:: በተለይ የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ አገራት የንግድ ትስስር መልክ ይለውጣል:: መረጃዎችና የምጣኔ ሀብት ምሁራን እንደሚያስረዱትም፣ ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ያላት የንግድ ትስስር ዝቅተኛ ነው:: ኢትዮጵያ ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት የምትፈፅመው ኤክስፖርት ከአጠቃላይ ኤክስፖርቱ ከ20 በመቶ አይበልጥም:: ሌሎች የአፍሪካ አገራት የምታስገባቸው ምርቶች መጠን ደግሞ ከ4 በመቶ በላይ አይሻገርም:: የስምምነት ተግባራዊ መሆንም ሰፊ ገበያን በመፍጠር ይህን ምስል ይለውጠዋል ተብሎ ይጠበቃል::
በንግድ ሚኒስቴር የንግድ ግንኙነትና ድርድር ዳይሬክተር አቶ ሙሴ ምንዳዬ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ‹‹የአፍሪካ ነፃ ገበያ ስምምነቱ ለኢንዱስትሪ ፓርኮች አስተማማኝና ሰፊ የገበያ ዕድል ይፈጥርላቸዋል:: በዋናነት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ጥሬ ዕቃን ከአፍሪካ አገራት በማስገባት በሙሉ አቅማቸው አምርተው በስፋት ወደ ገበያ እንዲገቡ ያስችላቸዋል ››ነው ያሉት::
ይሁንና የአህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠናው ብዞ እድሎችን እንደሚፈጥር ሁሉ የራሱ ተግዳሮቶች ብሎም በጥንቃቄ መታየት ያለባቸው አደጋዎችም አሉት:: በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የተለያየ ትንታኔዎች የሚሰጡ የምጣኔ ሀብት ምሁራን፣ በአገራት መካከል ያለው የኢኮኖሚ አቅም ጉራማይሌ መሆን ትግበራውን ፍትሃዊ አያደርገውም በሚል የሚነሰቱ ቅሬታዎች ለስምምነቱ ዋነኛ ተግዳሮት መሆኑን በቀዳሚነት ያቀርባሉ::
ሌላው የነፃ ገበያው ዋና ተግዳሮት የቀረጥ ስምምነት መሆኑንም ይጠቁማሉ:: የቀረጥ ስምምነት ተስማሚ አገሮች በመካከላቸው የሚኖርን ቀረጥ ከማስወገድ በተጨማሪ አባላት አገሮች ከስምምነቱ ውጭ ከሆኑ አገሮች ጋር በሚኖራቸው ንግድ ላይ የሚጥሉትን ቀረጥ ማቀናጀት ከባድ ራስ ምታት እንደሚሆንም አጽዕኖት ይሰጡታል::
እንደ ባለሙያዎቹ ገለፃም፣ የንግድ ቀጠናው ተሳታፊ አገሮች ከአፍሪካ ውጭ የሚመጡ ቁሶች ላይ ተመሳሳይ ቀረጥ እንዲጥሉ አለማድረጉ አስቸጋሪ ተግዳሮት አለው። በታክስ ልዩነት ምክንያት በተለይም ከቀጠናው ውጭ የተመረቱ ሸቀጦች በአንድ አገር በኩል ገብተው ሌሎች የቀጠናው ተሳታፊ አገሮች ውስጥ መሸጥ መቻል በተሳታፊ አገሮች መካከል ፍጥጫ ሊፈጥር ይችላል።
መንግሥታት ወደ አገር እንዲገቡ የማይፈልጋቸውና አገር ውስጥ እንዲመረቱ የሚፈልጋቸው ሸቀጦች ላይ ከባድ ቀረጥ በመጣል እንዳይገቡ መከላከል አለመቻላቸውም ሌላው ከባድ ፈተና ነው:: ለዚህ ደግሞ ተጨማሪ ስምምነቶች መተግበር የግድ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። በእርግጥ ሁሉንም ቀረጦች በፍጥነት ማንሳት በስምምነቱ አልተካተተም:: ይሁንና ነገ ከነገ ወዲያ የሚመጣውን ታሳቢ ማድረግ የግድ ይላል::
ፖለቲካ ስክነትም ሌላው የተስማሚ አገራቱ ፈተና ነው:: አንዱ አገር የውስጥ የቤት ሥራውን በአግባቡ መከወን ካልቻለ ተመሳሳይ ምህዳር እስኪደረስ ኢንቨስተሮች የቀጠናው አባላት ወደሆኑ ሌሎች አገራት ሊላመዱ ይችላሉ:: በዚህም ምክንያት የውጭ ምንዛሬ እና የሥራ እድሎችን ጨምሮ ከኢንቨስትመንት ጋር የሚያያዙ ሌሎች ጥቅሞችን ሊያጡ ግድ ይላቸዋል:: አሁን ላይ በአፍሪካ ደረጃ ያለው የመሰረተ ልማት ሁኔታ ነፃ የንግድ ቀጠናው ፈተና እንደሚሆን ተገምቶአል:: የብቁ ነጋዴዎች፣ የጥሬ እቃ አቅርቦት፣ ቴክኖሎጂ ክፍተት እና ጥራት ያለው ምርት ያለመኖር ችግር ለሚንፀባረቅባቸው ኢትዮጵያ የመሳሰሉ አገራት ደግሞ ተወዳዳሪ የመሆን አቅምን ያሳጣል::
የተለያዩ ምሁራን ለነፃ ንግድ ስምምነቱ ውጤታማ ትግበራ በተለይ ቅድሚያ መፍትሄ ሊሠጣቸው የሚገቡ አብይት ተግባራት እንዳሉ ያስገነዝባሉ:: በቀላል ባይሆንም በተለይም በአሁን ወቅት በሥራ ላይ የሚገኙ ታሪፎችን እና ሌሎች የንግድ እንቅፋቶችን ማስወገድ ቀዳሚ አድርገውታል:: አገራቱ ከምዕራባውያን በተለይ ከቻይና፣ አሜሪካ እና አውሮፓ ጋር በተናጠል የተፈራረሟቸው የንግድ ስምምነቶች እና ወደፊት የሚያበጇቸው ተመሳሳይ ግንኙነቶች ምን መልክ እንደሚኖራቸው መፍትሔ ማበጀት ይጠበቅባቸዋል።
ይሁንና በአሁን ወቅት ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ወደ ትግበራ እንዳይገባ የአሰራር ማነቆዎች ብቻ ሳይሆን ሌሎችም መሰናክሎች ተደቅነውበታል:: በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የበርካታ አገራት እርምጃ እንዲያዘግም ማድረጉ በተለይም ግለኝነትን አንግሶ ቅድሚያ መቀመጫዬን ማስባሉ የስምምነቱን ፈጣን ትግባራ አጠራጣሪ አድርጎታል::
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ዋና ጸሐፊ ዋምኬሌ ሜኔ ምንም እንኳን ስምምነቱ በይፋ ወደ ትግበራ ምዕራፍ ቢገባም፣ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ የማድረግ ሥራ ግን ረጅም ርቀት ከፊቱ ይጠብቀዋል፣ ረጅም ጊዜም ይወስድብናል›› ሲሉ አረጋግጠዋል:: ዋና ጸሐፊው፣ ከፋይናንሺያል ታይምስ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የመሰረተ ልማት ተደራሽነት እንዲሁም ገቢዎች እንዲሁም ድንበር አካባቢ የሚከናወኑ ሥራዎች ቀልጣፋ ብሎም ውጤታማ ማድረግ ካልተቻለ ስምምነቱን እርባና ቢስ እንደሚያደርገው አፅዕኖት በመስጠት መሰል ችግሮችን መፍትሄ ማስቀመጥ የግድ ስለመሆኑ አስምረውበታል::
ይህን ለዓመታት የዘለቀ ስንክሳር ለመሻገርና በጋራ ለመበልፀግ ቀጠናዊው አጋርነት መቀላጠፍ ግድ ስለ መሆኑ አፅዕኖት የሚሰጡ የምጣኔ ሀብት ምሁራን፣ አገራትም በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው ይህ ታሳቢ ያደረገ ተግባራትን መከወን፣ ከሁሉም በላይ ነፃ ገበያው መመስረት ከድህረ ኮቪድ በኋላ ለሚኖረው ኢኮኖሚ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም መረዳት እንዳለባቸው አስምረውበታል::
እንደ ባለሙያዎቹ ገለፃም፣ የስምምነቱ ትግበራ ሙሉ በሙሉ እውን እስኪሆን እጅን አጣጥፎ መቀመጥን ምርጫ ማድረግ አዋጭ አይደለም:: ቀኑ ሲደርስ ‹‹ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ›› እንዳይሆን ከወዲሁ የቤት ሥራዎችን ማጠናቀቅ የግድ ይላል:: ከሁሉ በላይ የሚፈለገው ይሆን ዘንድ የአፍሪካ ህብረትም ሆነ በአባል አገራት በመካከላቸው የእርስ በእርስ ትስስር እንዳይሳለጥ የሚያስሩ ሸምቀቆዎች እንዲበጣጠሱና የተደቀኑ ስጋቶችም እንዲቃለሉ ይበልጡን መድከም ግድ ይላቸዋል::
በኢትዮጵያም ጥቅም ባገናዘበ መልኩ ተፎካካሪ ሊያደርጉ የሚችሉ ለብልጽግናዋ መሰረት የሆኑ ዘርፎችን አማራጮችን በጥናት ለይቶ ኮሪደሩን መቀላቀል ኢንቨስትመንቱ ከወዲሁ ተወዳዳሪና ተፎካካሪ መሆን የሚያስችለውን አቅም ማጎልበት አቅጣጫዎችን ማመላከት ሊታሰብብት ይገባል:: የንግድ ማህረቡን ማንቃት፣ አምራች ድርጅቶችን ብቁና ተወዳዳሪ ማድረግ የግድ ይላል::
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2013