ከሰሞኑ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ እያደረገችው ያለው ጫና “እጅሽን ቆርጬ በእኔ እጅ ካላጎርስኩሽ” አይነት ነው:: ኢትዮጵያ በራሷ መጉረስ እየቻለች ስለምን አሜሪካ እኔ ካላጎርስኩሽ መብላት አትችይም ብሎ ለመከልከል መጋጋጥ ምን የሚሉት ሩህሩህነት ነው ?
ከምሁራን ትንታኔ በመነሳት ከዚህ በፊት በጻፍኩት አንድ ጽሑፍ ስለሞኖፖሊ ካፒታሊዝም ወይም ኢምፔሪያሊዝም አምስት መለያ ገፅታዎች እንዳሉት ገልጬ ነበር:: ዛሬ ላይ አሜሪካ ኢትዮጵያን እጅሽን ቆርጬ በእኔ እጅ ጉረሺ፤ ካልሆነ ግን ወደ አፍሽ ምግብ መላክ አትችይም ማለቷ ስለሞኖፖሊ ካፒታሊዝም ወይም ኢምፔሪያሊዝም አምስት መለያ ገፅታዎች ደግሜ ልፅፍ ወደድኩ::
እንደምሁራን ገለጻ፤ ሞኖፖሊ ካፒታሊዝም ወይም ኢምፔሪያሊዝም አምስት መለያ ገፅታዎች አሉት:: የእነዚህም የምርት ካፒታል ክምችት መፍጠር፣ የባንክ እና በኢንዱስትሪ ካፒታል ጥምረት የፋይናንስን ካፒታልን መፍጠር፣ የሞኖፖሊስቶች ማህበር በአለም አቀፍ ደረጃ ማደረጃት ፣ ካፒታልን በማንቀሳቀስ ወደ ውጭ በማውጣት(ኢንቨስትመንትን) መፍጠር እና የርካሽ የሰው ጉልበት ፣ ሰፊ የማይነጥፍ ገበያ እና አጥጋቢ ትርፍ ለማግኘት የሚያስችል ሁኔታ እያንዳንዱ ሞኖፖሊስትና እና ድርጅት የሀገሩን ክልል ወይም ብሄራዊ ድንበር ጥሶ በመውጣት በአለም አቀፍ ሞኖፖሊስቶች ማህበር አማካኝነት አለምን በወታደራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተፅእኖ ስር ማኖር ናቸው::
ሞኖፖሊ ካፒታሊስት ወይም ኢምፔሪያሊስት ከላይ የተጠቀሱትን ፍላጎቶች በአለም ሃገራት ላይ ለመጫን በዋናነት ከሚጠቀሟቸው ዘዴዎች መካከል እርዳታ ፣ ኢንቨስትመንት ፣ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ ወዘተ በሚባሉ ማታለያ ከረሜላዎች ነው::
አሁን ላይ የኢትዮጵያ መንግስት የማታለያ ከረሜላዎችን (እርዳታ እና ብድር) ከሃገራቸው ሉዓላዊነት እንደማይወዳደር አስረግጠው ለአሜሪካ እና ለፍርፋሪ ቃራሚዎቿ በግልጽ አሳይቷ:: የማታለያ ከሬሜላን እየሰጡ ሃገርን እንደፈለጉ ማድረግ በዘመነ ህዋሓት መቅረቱን እንዲሁ መንግስት በደማቁ ጽፎ እና አስምሮ አስረድቷል:: አሜሪካ በዘመነ ህወሓት የለመደችውን ኢትዮጰያውያንን በከረሜላ እየደለሉ ወርቅ መዝረፍ አሁን ላይ እንደማይሞከር እና ይህን ማታለያቸውን ህወሓትን የመሰሉ ድርጅቶችን እየፈለጉ ቢሰጡ እንደሚሻል ጠንካራ አቋማ የያዘው የኢትዮጵያ መንግስት “የአባቱ ልጅ” እንዲሉ ከጥንት ጀምሮ በአባቶቹ ሲያደርጉት የነበረውን የውጭ ወራሪ ሃይል የመመከት እና አሳፍሮ የመመለስ ገድል ዛሬም የተደገመ ይመስለኛል:: የአባቶቹን ገድል የተከተለውን ገዥውን መንግስት የተመለከቱት ነጮች አሁንም ደግመው እነዚህ ኢትዮጵያዊን “ውሾች ናቸው” የሚሉ ይመስለኛል::
ኢትዮጵያውያኖች ውሻ ናቸው ሲሉ ምን ለማለት እንደሆነ አዲስ ባይሆንም ስለጉዳዩ ትንሽ ማለቱ አይከፋም:: ውሻ አብሮ ሲኖር ሊጣላ ፣ ሊናከስ ወይም ሊጋጭ ይችላል:: ነገር ግን የውጭ ጠላት የሆነው ጅብ ወይም ሌላ አደገኛ አውሬ ከሰፈራቸው ቢመጣ ሲጣሉ የነበሩት ሁሉ ውሾች ሰፈራቸውን ከአደገኛ ወራሪ ሃይል ለመከላከል ጸባቸውን እርግፍ አድርገው ትተው በአንድ ላይ ይሰለፋሉ:: የመጣውን ጅብ በመጣበት እግሩ አይቀጡ ቅጣት ቀጥተው ከሰፈራቸው ያባርሩታል::
ኢትዮጰያውያንም በተመሳሳይ ምንም እንኳን በውስጣቸው ጉዳይ የቱንም ያህል ባይስማሙ የውጭ ጠላት ሲመጣ ግን የውስጡን ግጭታቸውን እርግፍ አድርገው በመተው ከመንግስታቸው ጋር አብረው ይቆማሉ:: ይህ አንዴ ብቻ ሆነ አይደለም:: በስንት አጋጣሚዎች የተፈተነ ሃቅ ነው:: ነጮች ኢትዮጵያን ለመውረር በተደጋጋሚ የውስጥ ስምምነት ወይም ግጭት የሚኖርበትን ጊዜ ጠብቀው ኢትዮጵያን ለማጥቃት ይሞክራሉ:: ነገር ግን አንድም ጊዜ ኢትዮጵያኖች ጠላት ሲመጣ ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ሃገራቸውን አሳልፈው የሰጡበት ጊዜ የለም:: ይህን ስል የባንዳነት ታሪክ በኢትዮጵያ የለም ለማለት አይደለም:: ነገር ግን ባንዳ ለመሆን የሞከሩት እና ሃገርን ከጠላት ጋር በማበር የወጉ የሉም ማለቴ አይደለም:: ሆኖም ግን እነዚህ አካላት በህዝብ ላይ ወይም በሃገር ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሚባሉ ሰዎች አይደሉም::
አሁንም ሞኖፖሊ ካፒታሊዝም ወይም ኢምፔሪያሊዝም ቁንጮ የሆነችው ሀገረ አሜሪካ ከላይ የተጠቀሱትን የካፒታሊስቶች ፍላጎት በሉአላዊ ሃገራችን ለመጫን የምታደረገው ሙከራ ተቀባይነት እንደሌለው ኢትዮጵያኖች የፖለቲካ ፣ የጎሳ ልዩነት ሳያሳዩ ከዳር ዳር በአንድነት ቆመው ሲሞግቱና ለመመከትም ዝግጁ መሆናቸውን አሳይተዋል:: ይህን የአየችው አሜሪካ ኢትዮጵያ የቱንም ያህል ድሃ ብትሆንም ሉአላዊነቷን ግን አሳልፋ እንደማትሰጥ መገንዘቧ አይቀሬ ነው::
በዘመነ ደርግ የሶማሌው አምባገነን መሪ ኢትዮጵያን በወረረበት ዘመን ኢትዮጵያ ለጦር መሳሪያ መግዣ በሚል ከአሜሪካ ጋር ስምምነት አድርጋ ገንዘብ ለአሜሪካ መንግስት ከከፈለች በኋላ አሜሪካ የጦር መሳሪያውን ብቻ ሳይሆን ለመሳሪያ መግዣ የተሰጣትን ገንዘብ ጭምር አላየሁም በማለት ለጠላት አብራለች:: ይህ ብቻ አይደለም ከጦርነቱ መጠናቀቅ በኋላ ኢትዮጵያን ለማሽመድመድ ህወሓትን የመሰሉ በብሄር የተደራጁ ሃገር አፍራሽ የፖለቲካ ድርጅቶችን እንደ አሜባ ዘር በፍጥነት በማባዛት ኢትዮጵያን ማመሰቃቀሏ ይታወቃል::
በአለም ፖለቲካ ቋሚ የሚባል ወዳጅ እና ጠላት የለም በሚለው የመንግስታት አካሄድ በወቅቱ ወርራን የነበረችውን ጎረቤት ሶማሊያን ለማዳን የጸጥታ ሃይላችንን አሰማርተናል:: በሌላ በኩል ደግሞ ከአሜሪካም ጋር ዘርፈ ብዙ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ጥሩ የሚባል ግንኙነት ፈጥረን ነበር:: ነገር ግን ከህዳሴው ግድብ መገንባት ጋር ተያይዞ አሜሪካ የጡት ልጇን ግብጽ ለማስደሰት በሚል ኢትዮጵያን እንደ ውጋት አላስተነፍስ ብላ ወጥራ ይዛታለች:: ይህ ግብጽን ለማስደሰት የሚደረግ የአሜሪካ ጥረት በአሜሪካ እና ኢትዮጵያ መካከል የነበረውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት ከማጠልሸት ባለፈም የሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የተረጋጋ እንዳይሆን ያደርጋል:: በመሆኑም አሜሪካ እና መስል ካፒታሊስቶች የቀጣናው አለማረጋጋት እነሱንም ስለሚጎዳ ቀም ብለው ሊያስቡበት ግድ ነው::
በመጨረሻም ውድ ኢትዮጵያውያን በሀገርህ የመጣውን ለመመከት አብረህ ስትቆም እንዴት እንደሚያምርብህ በቅርቡ በተመለከትነው አገር አፍራሽ የሆነውን ጁንታ አስራ አምስት ቀን ባልሞላ እንደ ገለባ መበተንህ ይታወቃል:: የኢትዮጵያ ህዝብ አሁንም አንድነትህን ጠብቀህ አገርህን የማሻገር ኃላፊነትህን ተወጣ:: መልዕክቴ ነው::
አሸብር ኃይሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 2 ቀን 2013 ዓ.ም