የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኙ በአጠቃላይ ከ300 በላይ የሚሆኑ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚያስተምሩ ከ20 ሺህ በላይ መምህራንን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ የተደራጀ የሙያ ማህበር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከአጠቃላይ ትምህርት ባሻገር በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኙ ኮሌጆች የሚያስተምሩ መምህራን የተለያዩ የመብትና የጥቅማ ጥቅም ጉዳዮችን እንዲሁም የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ እረገድ መሠራት ያለባቸውን ተግባራት በመወከል በየኮሌጆቹ የተቋቋሙ የመምህራን ማህበራት የሚገኙ ሲሆን፣ በተጠናከረና በተደራጀ መንገድ ሥራቸውን እንዳያከናውኑ የአደረጃጀትና የፋይናንስ አቅም ተግዳሮት ሆኖባቸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በዋነኛነት የከተማ ነዋሪ በትምህርት ሥራ ላይ በባለቤትነት በማሳተፍ ለትምህርት መዋቅሩ አካላትና በትምህርት መስክ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ሙያዊና ቴክኒካዊ ድጋፍ በመስጠት፣ አጋር ድርጅቶችን በማስተባበር የትምህርት ተቋማትን በፍትሐዊነት በማስፋፋት የከተማዋን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘበ ዓለም አቀፋዊ ደረጃውን የጠበቀና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ትምህርት በተስማሚ ፕሮግራሞች ለህብረተሰቡ ለማድረስ የተቋቋመ ነው፡፡ በተጨማሪም የትምህርት ጥራት እንዲመጣ ለማስቻል አስፈላጊ የሚባሉ ግብዓቶችን ያሟላል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮና መምህራን ማህበር በጋራ የመምህራንን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ሥራዎችን አከናውነዋል፡፡ ነገር ግን ማህበሩ መምህራንን ለመደገፍ እየተደረገ ያለው ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ መምህራኑ ለትምህርት ጥራት አተኩረው እንዳይሰሩ አድርጓል ሲል ይገልፃል፡፡
በትምህርት ቢሮ አካባቢ የሚሠሩ ሥራዎች መምህራኑን ያማከሉ ባለመሆናቸው ውጤት አለመምጣቱንም ይናገራል፡፡ ያም ሆኖ ግን ማህበሩ ከአባላቱ ከሚሰበስበው ገቢ ሆስፒታልና ሁለገብ ማዕከል ለመገንባት እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፣ ለዚህም ከተማ አስተዳደሩ ከሊዝ ነፃ የሆነ መሬት ሰጥቶታል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ በአንደኛም ይሁን በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲሰጥ በዕቅድ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ከዚህም ውስጥ የመምህራንን ብቃት ለማሳደግ የተሠሩ ሥራዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ነገር ግን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ መምህራን የቤትና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች ባለመሟላታቸው የትምህርት አሰጣጡ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩ ይስተዋላል፡፡ በሌላም በኩል የመምህራን ደመወዝ አነስተኛ በመሆኑ ብቃት ያላቸው መምህራን ወደ ሌሎች ዘርፎች እንዲሸሹ በማድረግ የመምህራን እጥረት በትምህርት ቤቶች አካባቢ እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኙ መምህራን ከጊዜው የኑሮ ሁኔታ ጋር የሚመጣጠን የደመወዝ ጭማሪና ቤት እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበዋል ።
መንግሥትም ጥያቄውን ተቀብሎ የቤት እና የደመወዝ ጭማሪ ቢያደርግም ችግሩን ያቃለለ አለመሆኑን ይናገራል፡፡ ሰሞኑንም የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮና የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር በመተባበር ባዘጋጁት መድረክ መምህሩ ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት ችግር አለበት፣ በተማሪዎቻችን ወላጆች ቤት ተከራይተው እንደሚኖሩ፣ ከዚህ በፊት ለመምህሩ ተብሎ የወጣው የቤት እጣ መምህሩን ለመከፋፈልና ለመግዛት እንጂ ፍትሀዊ በሆነ መንገድ በየደረጃው መምህሩን ለመጥቀም አለመሆኑን እንዲሁም በቂ የሆነ የደመወዝ ጭማሪ አለመደረጉን ተናግረዋል።መምህራኑ በውይይቱ ትኩረት ከሰጡባቸው ጥያቄዎች መካል ሌላው የመምህራን አሰለጣጠን ላይ ያሉ ክፍቶች ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር የሚመለከታቸው አካላት መለየት መቻል እንዳለባቸው በመጥቀስ፤ በተለይ ከአስርኛ ክፍል የመሰናዶ ውጤት ያልመጣላቸው ተማሪዎች መግባታቸው የጥራት ችግር እንዲመጣ በማድረጉ የሚስተካከልበት መንገድ እንዲፈጠር ጠይቀዋል፡ ፡ ለመምህራን ደመወዝ በሚጨመርበት ሁኔታ ላይ ትኩረት አለመሰጠቱንና ለሌሎቹ ዘርፎች ሲጨመር የዋጋ ንረት ታይቶ ሲሆን ለመምህራን ደመወዝ ግን የዋጋ ጭማሪን ታሳቢ ያደረገ አይደለም፡፡ ከርዕሳነ መምህራን አመዳደብ ጋር ተያይዞም ቀደም ሲል የነበሩ አሰራሮች እንደሚፈተሹ ጠቁመዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ለተወሰኑ መምህራን ቤት የተሰጠ ቢሆንም የአሰጣጥ ሁኔታው መታረም እንዳለበት በመጥቀስ፤ በቤት አሰጣጡ የተቀመጡ መስፈርቶች በድጋሚ መታየት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ሌላው መምህራኑ ያነሱት ወቅቱን ያልጠበቁ ዝውውሮች መብዛት የመምህራን እጥረት እንዲፈጠር ማድረጉን፣ ጥፋት ያጠፉ መምህራን ከመቅጣት ይልቅ ሌሎች ክፍለ ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤት ውስጥ መመደባቸው አግባብ አለመሆኑን፣ ለአካል ጉዳተኛ መምህራን የሚሰጠው ትኩረት አናሳ ከመሆኑ ባሻገር ይቀጠርላቸው የነበረው ረዳት ይቅር መባሉ ጎድቷቸዋል፣ ለአካል ጉዳተኛ መምህራን ቅድሚያ ቤት ሊሰጣቸው ሲገባ ተከልክለዋል፤ እንዲሁም ከክፍለ አገር ለሚመጡ መምህራን የስራ ልምድ አለመያዙ እድገት ለማግኘት መቸገራቸውን ጠቁመዋል፡፡ የአንጋፋና ጠንከራ መምህራን ሽልማት መቆሙ ተነሳሽነት መቀነሱን የጠቆሙት መምህራኑ፤ የሽልማት አሰጣጡ ፍትሀዊ በሆነ መንገድ የሚካሄድበት መንገድ መዘርጋት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በታሪክ መፅሀፍት ላይ ያሉ መዛባቶችን ለማስቀረት መምህራን በመጽሀፍ ዝግጅት ላይ መሳተፍ እንዳለባቸው አንስተዋል ።
በየትምህርት ቤቶቹ ያሉትን ብልሹ አሰራሮች የሚስተካከሉበትን መንገድ ትምህርት ቢሮ መፈለግ እንዳለበት ጠይቀዋል፡፡ በቅርብ ዓመታት ከህዝብ ወደ መንግሥት የተዘዋወሩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚሰሩ መምህራን ጥቅማ ጥቅም እንዲከበር መምህራኑ ጠይቀዋል፡፡ ከክፍለ አገር መጥተው ከአስር ዓመት በላይ ያገለገሉ መምህራን የነዋሪነት መታወቂያ እንዲሰጣቸው፣ በትምህርት ቤቶች አካባቢ ያሉ ሺሻ ቤቶችና ጫት ቤቶች፣ ጭፈራ ቤቶችና የአምልኮ ስፍራዎች ትኩረት እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡ ፡ የከተማ አስተዳሩ የጀመረው ለመምህራን የትራንስፖርት አገልግሎት ጥሩ ቢሆንም ውስጡ መፈተሸ እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ታቦር ገብረመድህን በበኩላቸው፤ በውይይቱ ወቅት የተነሱት ጥያቄዎች አግባብነት እንዳላቸው ተናግረዋል። የርዕሳነ መምህራን ምደባ በተመለከተ፣ ለአካል ጉዳተኞች ረዳት መቅጠር እንዲሁም ከክልል መጥተው ሲቀጠሩ በዜሮ ልምድ የሚሆነው አሰራር ጥናት ተደርጎበት በቅርቡ ይፈታል ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ከክልል መጥተው አዲስ አበባ ሲቀጠሩ ልምዳቸውን ደብቀው መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ታቦር፤ ከክልል አስተማሪዎች ሲመጡ የአስተማሪ እጥረት እንዳይኖር ለማስቻልና አዲስ አበባ ያሉትን አዳዲስ አስተማሪዎችን ለማበረታታት መሆኑን ተናግረዋል’ በቀጣይ ግን መምህራኑ ከክልል ሲመጡ የትምህርት ደረጃቸው ላይ ያለውን ዓመት እንደሚታይ አመልክተዋል።
ለመምህራን ቤት ለመስጠት የተጀመሩት ስራዎች እንደሚቀጥሉና በቀጣይ አስተዳደሩ ሲወስን ቤቶች እንደሚሰጡ ጠቅሰዋል፡፡ ቤት ኖሯቸው ቤት የወሰዱ አስተማሪዎች ካሉ ጥቆማ በመስጠት የማጣራት ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል። በተጨማሪም በትምህርት ቤቶች ውስጥ ፖለቲካ መልክ ያላቸው ስብሰባዎች መከልከሉንም ተናግረዋል። ነገር ግን በትምህርት አሰጣጡ ዙሪያ በየትምህርት ክፍሉ ይደረግ የነበረው ውይይት እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ እየተሰራ የሚገኘው የትምህርት ፍኖተ ካርታ የትምህርት ጥራቱ ላይ የሚነሱ ችግሮች መፍትሄ እንደሚሰጥ በመጥቀስ፤ ለመምህራን የሚሰጠው ተከታታይ ስልጠናም ያለበትን ክፍተት ተለይቶ ማስተካከያ ይደረግበታል ሲሉም አብራርተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ፤ ከመኖርያ ቤትና ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ በመምህራን ላይ እየተፈጠረ ያለውን ጫና መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚፈታ ተናግረዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የመምህራንን ችግር ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ጠንክሮ እንደሚሰራ የጠቀሱት ምክትል ከንቲባው ለዚህም አዲስ የተዋቀረው የተቋማት አደረጃጀት እስከ ትምህርት ቤት የመዘርጋት ስራ እንደሚከናወን ገልፀዋል፡፡ አስተማሪነት በተማሪ ህይወት ላይ የማይተካ ተፅዕኖ ያሳርፋል ያሉት ኢንጅነር ታከለ ኡማ፤ በስነ- ምግባር የታነፀ ዜጋን ለማፍራት የከተማ አስተዳደሩ ከመምህራን ጋር ለመስራት ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የተሳተፉት መምህራን ትውልድን ለተሻለ አላማ ለማብቃት ከምንጊዜውም በላይ ለትምህርት ጥራት ቅድሚያ ሰጥተው እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2011
መርድ ክፍሉ