የዓለም ጤና ድርጅት የአዕምሮ ጤና ማለት ‘’የራስን ማንነት አውቆ ራስን መምራት መቻል፣ ሃላፊነትን ማወቅና መወጣት፣ ምክንያታዊ ካልሆነ ጭንቀት ነጻ የሆነ ህይወት መምራት መቻል እንዲሁም ካለበት ማህበረሰብ ጋር በመግባባት ተግባርን ማከናወንና በማህበረሰቡ ተቀባይነት ያለው የኑሮ ዘይቤን የመከተልን ሁኔታ’’ ያመለክታል ይላል፡፡
በተቃራኒው የአዕምሮ ሕመም ክስተቶች ዙሪያ ሣይንሳዊ የሆነና ተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሠረተ ትምህርት ያልተስፋፋ በመሆኑ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ስለ አዕምሮ ህመም ያለው ግንዛቤ በጣም አነስተኛና በአጉል አስተሳሰቦች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡
የአዕምሮ ህመምን አስመልክተው የተሰነዘሩ አስተያየቶች እንደሚሉት ልክፍት ወይም ቁጣ ሣይሆን ማንኛውም የሰው ልጅ አካል እንደሚታመም ሁሉ አዕምሯችንም ይታመማል፤ በተለያዩ ምክንያቶችም መረበሽ ይደርስበታል፡፡ ስለ አዕምሮ መረበሽ ሦስት ዋና ዋና እውነታዎችም ይጠቀሳሉ፡፡
አንደኛው የአዕምሮ ሕመም የርኩስ መንፈስ ውጤት ሣይሆን እንደ ማንኛውም የሰውነት ሕመም በተወሰነ የክፍሉ አካል (አንጎል) መታመም የተነሳ የሚፈጠር ነው፣ ሌላው ደግሞ አብዛኛው የእርስ በርስ ሠላም ማጣት፣ ካለመከባበር እና ካለመተባበር ጋር ይያያዛል። ሦስተኛው የአዕምሮ ሕመም እንደማንኛውም የአካል ሕመም በአብዛኛው በህክምና ሊድን ይችላል የሚሉት ወ/ሮ መዓዛ መንክር ክሊኒካል ሣይኮሎጂስት እና የ”ሁሉም በአንድ” የህክምና መጽሐፍ ደራሲ ሲሆኑ፤ በአዕምሮ ጤና ጉዳይ ላይ ካካፈሉን ሐሳብ መካከል በጥቂቱ እነሆ ብለናል። መልካም ንባብ።
ከ300 በላይ የአዕምሮ ህመም ዓይነቶች አሉ። የአዕምሮ ህመም በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል። ማለትም በሥነ – ህይወታዊ (Biological ወይም Genetical causes)፣ በሥነ-ልቦናዊ (Psychological causes) ከአስተዳደግ ጋር
ተያያዥ በሆኑ ምክንያቶች ማህበራዊ ችግሮች / Social causes፣ በእለት ተለት በሚገጥሙን ችግሮች – ድህነት፣ ሥራ ማጣት፣ የቅርብ ሰው አለመኖር፣ ብቸኝነት፣ ስደት፣ በሰዎች መገለል እንዲሁም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የአዕምሮ ህመም ሊከሰት ይችላል።
በዛሬው ፅሁፋችን ከግብረ ሥጋ ግንኙነት ጋር ተያያዥ የሆኑ የአዕምሮ ሕመም ዓይነቶችን እናያለን።
ሰዎች በእለት ተለት እንቅስቃሴያችን በሚያጋጥሙን ምክንያቶች ልንናደድ ወይም ልንጨነቅ እንችላለን። ነገር ግን ምንም ምክንያት ሣይኖረን የምንጨነቅ፣ የምንረበሽ እና ከልክ ያለፈ ፍርሃት የሚሰማን ከሆነ፤ ምክንያቱን ያልተረዳነው ጭንቀት እና መረበሽ በሥራችን፣ በትምህርታችን፣ በውጤታማነታችን እና በማህበራዊ ግንኙነታችን ላይ ተፅዕኖ ካመጣ፤ የመረበሽ እና የመጨነቅ ሥሜቱ ለረጅም ጊዜ ከቆየ በዙሪያችን ያሉ የቅርብ ቤተሠቦች፣ ጓደኛ እና ለትዳር አጋር የምናሣየውን አዲስ ሥሜት አይተው “ሁኔታህ/ሽ ጥሩ አይመስልም፤ ምን ሆነሃል/ሻል?” ብለው እስኪጠይቁ የሚያደርስ ሁኔታ ላይ ከደረስን፤ የሚሰማን ጭንቀት ከልክ በላይ ሆኖ እርሱን ለመርሳት የአልኮል መጠጥ እና የእንቅልፍ መድሃኒቶችን መፈለግ ከተጀመረ ከሚሰማዎት ጭንቀት ብዛት “አሁንስ ብሞት ይሻላል” የሚል ሀሳብ ከጀማመርዎት እና ያልተለመደ ሃሳብ ማለትም ሰዎችን መጠራጠር እና ያልተለመዱ ድምፆችን መስማት ከጀመሩ በጊዜ ወደ አዕምሮ ሀኪም ጋር በመሄድ የንግግር ወይም የመድሃኒት ህክምና ማግኘት የግድ መሆኑን ወይዘሮ መአዛ ይናገራሉ።
ታዲያ ይህ ህመም በህይወታችን ተፅዕኖ ማሳደሩ ሣይታለም የተፈታ ነው። በተለይም የግብረ ሥጋ ግንኙነት የማድረግ ችግርና የአዕምሮ ህመም በሚል ሀሳብ ላይ ትኩረት አድርገን እንነጋገር የሚሉት ወይዘሮ መአዛ የግብረ ሥጋ ግንኙነት የማድረግ ችግርና የአዕምሮ ህመም ማለት በሁለት ጥንዶች ወይም ባለትዳሮች መካከል በግንኙነት ወቅት የሚያገኙትን እርካታ የሚያዛባ ህመም ነው። ይህ ችግር በሴቶች ላይ በልጦ ይተያል። ይህም ሲባል 43 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ሲያጋጥማቸው በወንዶች ላይ ደግሞ ሦስት በመቶ ያህሉ ይህ ችግር ሊኖርባቸው የሚችል መሆኑን ይናገራሉ።
በጥንዶች ወይም በባለትዳሮች መካከል ወሲብ ለማድረግ መፈለግ እና ለወሲብ መነሳሳት ጤነኛነት ነው። ከታች የተገለፁት ችግሮች ካሉ ግን የሥነ-አዕምሮ ህክምና ማድረግ የሚያስፈልግ መሆኑን ያስረዳሉ።
1. የግብረ ሥጋ ግንኙነት ለማድረግ ምንም ፍላጎት ከሌለ (Desire disorders)
2. የግብረ ሥጋ ግንኙነት ለማድረግ አካላዊ መነሳሳት ከሌለና በግንኙነት ወቅት ደስታ የማይሰማዎት ከሆነ (Arousal disorders)
3. የግብረ ሥጋ ግንኙነት በሚያደርጉበት ወቅት የእርካታ ጫፍ ላይ የማይደርሱ ወይም የሚዘገዩ ከሆነ (Orgasm disorders)
4. በግብረ ሥጋ ግንኙነት ወቅት ሕመም የሚሰማዎት ከሆነ (Pain disorders) ችግሩ አለብዎት ማለት ነው። ይህ ችግር በማንኛውም እድሜ ላይ ሊከሰት የሚችል ሲሆን፤ በተለይም በ40ዎቹ እድሜ ክልል ላይ ሊጎላ ይችላል።
በወንዶች ላይ የሚታየው ምልክት የብልት አለመቆም (erectile dysfunction)፣ የእርካታ መዘግየት (retarded ejaculation)፣ ቀድሞ የመጨረስ ችግር (early or premature ejaculation)፣ ሲሆን፤ በሴቶች ላይ የሚታየው ምልክት የእርካታ ጥግ ላይ አለመድረስ (Inability to achieve orgasm)፣ በግንኙነት ወቅት በቂ ፈሣሽ አለመኖር (Inadequate vaginal lubrication) እና የዝግጁነት ችግር (Inability to relax the vaginal muscles) ናቸው።
የችግሩ መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉት ነገሮች አካላዊ ምክንያት የተለያዩ አካላዊ ሕመሞች ሲኖሩ፤ ለተለያዩ ህመሞች ታስበው የሚወሰዱ መድሀኒቶች የሚፈጥሩት የጎንዮሽ ጉዳት ያመጣው ተፅዕኖ፤ የተለያዩ አልኮል መጠጦች መውሰድና የእፆች ተጠቃሚነት፤ ሥነ አዕምሯዊ ምክንያት፤ ከሕይወት ወይም ከሥራ ጋር ተያያዥ የሆኑ ጭንቀቶችና ጫና ሲኖር፤ ወሲብ የማድረግ ችግር አለብኝ ብሎ ማሰብ፤ በጋብቻ ውስጥ ችግሮች ካሉ ጥሩ ያልሆነ የወሲብ ታሪክ ካለ የደባቴ (depression) ሕመም ካለ ለችግሩ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
ለዚህ ችግር መፍትሄው ወደ ሥነ አዕምሮ ሐኪምና የሥነ አዕምሮ ባለሙያ ጋር በመሄድ ማማከርና ህክምና ማግኘት ነው። በተለይ Cognitive Behavior Therapy በጣም የሚያግዝ ሕክምና ነው።
የአዕምሮ ሕመም ዓይነቱ ብዙ ነው። ሕክምናውም እንደዚያው ብዙ አማራጭ ያለው መሆኑን ነው ወይዘሮ መአዛ የሚያስረዱት። ስለሆነም አዕምሯችን እንደ ማንኛውም የአካል ክፍላችን ሊታመም የሚችል መሆኑን ተረድተን በጊዜ መፍትሄ መፈለግ የግድ የሚል ተግባራችን ሊሆን እንደሚገባ ይናገራሉ። በጤና ያሠንብተን።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2013