ከሚታደሱ የተፈጥሮ የኃይል ምንጮች መካከል አንዱ የጂኦተርማል ኃይል ነው። ይህ ኃይል ከከርሰ ምድር የሚወጣውን የጭስ ሙቀት ወደጉልበት እንዲቀየር በማድረግ ጥቅም ላይ ይውላል። ከከርሰ ምድር የሚገኘው ይኸው የሙቀት ኃይልም በቀጥታ ጠፈርን ለማሞቅ፣ ለዓሳ እርባታ፣ የግብርና ምርቶችን ለማድረቅ፣ ለመዋኛ ገንዳ፣የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨትና ለመሳሰሉት ጥቅም እንደሚሰጥ ይነገርለታል።
በርካታ ሀገራትም ለዚህ ታዳሽ ኃይል ልዩ ትኩረት በመስጠትና ፊታቸውን በማዞር የኤሌክትሪክ ኃይል እያመነጩበት ይገኛሉ። ይህን በማድረጋቸውም የተፈጥሮ ስነምህዳር ሚዛንን መጠበቅ ችለዋል። ኢትዮጵያም 10 ሺ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ከጂኦተርማ ኢነርጂ የማመንጨት አቅም ቢኖራትም ይህን ኃይል ገና በስፋት ጥቅም ላይ አላዋለችውም።
ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተጀምሮ የቆመው የአሉቶ ላንጋኖ ጂኦተርማል ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በዚህ ዘርፍ ያለውን ኃይል ለመጠቀም በሚደረገው ጥረት ፈር ቀዳጅ ሆኗል። በአሁኑ ጊዜ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ኢተያ ከተማ አቅራቢያ እየተከናወነ ያለው የቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ደግሞ ሥራውን መሬት ላይ አውርዶ በመስራት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በማሳየቱ በቀጣይ በዚህ የኃይል ዘርፍ ሌሎች ፕሮጀክቶችም እንዲከናወኑ በር ከፍቷል።
የቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ምክትል ቴክኒካል ዳይሬክተር አቶ የትምጌታ ፋንቱ እንደሚገልፁት፣ ፕሮጀክቱ እ.ኤ.አ በ2017 የተጀመረ ሲሆን ፕሮጀክቱን ለማስጀመር የመጀመሪያው ስምምነት ከኢትዮጵያ መንግሥትና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ተፈርሟል። ባለፉት ሁለት ዓመታትም የተለያዩ ጥናቶች ሲከናወኑ ከቆዩ በኋላ ጥናቶቹ እንደተጠናቀቁ እ.ኤ.አ በ2019 የተለያዩ ሥራዎች መሰራት ጀምረዋል።
በመጀመሪያ ከኢተያ ከተማ እስከ ፕሮጀክት ቦታው
የሚደርሰውን መንገድ የማሻሻል ሥራ ተሰርቷል። በመቀጠልም የቁፋሮ ቦታዎች ተመቻችተዋል። የሚቆፈረውን አካል በጨረታ በማወዳደርም የኬንያ መንግሥት ከ70 በመቶ በላይ ድርሻ ያለው ኬንጄን የተሰኘ ድርጅት እንዲቆፍር ተመርጧል። ድርጅቱ እ.ኤ.አ በመጋቢት ወር 2020 የመጀመሪያውን ቁፋሮ አካሂዷል።
በፕሮጀክቱ ቦታ ላይ የመንገድ ማስተካከያዎችና የቁፋሮ ሥራዎች እየተሰሩ ከመንግሥት ጋር የመጨረሻ ውል እ.ኤ.አ በመጋቢት ወር 2020 የተፈረመ ሲሆን በመቀጠል አስፈላጊ ሁኔታዎች ተሟልተው የውል ስምምነቱ እ.አ.አ በታህሳስ ወር 2020 መቶ በመቶ እውቅና እንዲያገኝ ተደርጓል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ የመጀመሪያው ጉድጓድ ቁፋሮ በህዳር ወር ተጠናቋል። በአሁኑ ጊዜም ሁለተኛ ጉድጓድ ተቆፍሮ የተጠናቀቀ ሲሆን የሶስተኛ ጉድጓድ ቁፋሮ በቅርቡ ተጀምሯል። የመቆፈሪያ ማሽኑ ወደ ሶስተኛው ጉድጓድ በመሸጋገሩም አስቀድመው በተቆፈሩ ሁለቱ ጉድጓዶች ውስጥ ያለውን የጭስ ጥራት በማየት ጭሱ ምን ያህል ኃይል ማመንጨት እንደሚችል ከሁለት ሳምንት በኋላ ፍተሻ ይደረጋል። የመጀመሪያውን የፕሮጀክት ምእራፍ ለማከናወንም ገና ስምንት ጉድጓዶች ይቆፈራሉ።
በመጀመሪያ የፕሮጀክቱ ምእራፍ 50 ሜጋ ዋት ኃይል የሚመነጭ ሲሆን እ.ኤ.አ በ2023 መጨረሻ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። በሁለተኛው የፕሮጀክቱ ምእራፍ ደግሞ 100 ሜጋ ዋት በላዩ ላይ በመጨመርና 150 ሜጋ ዋት በማድረስ በ2025 መጨረሻ ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ ይገመታል።
ለመጀመሪያው ምእራፍ 270 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የተመደበ ሲሆን የሁለተኛው ምእራፍ ፕሮጀክት ተጨምሮበት አጠቃላይ ፕሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ እስከ 800 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ይፈጃል ተብሎ ይጠበቃል። አጠቃላይ ወጪውም የፕሮጀክቱ ስፖንሰር በሆኑት ሜሪዲየምና ሬጄቪክ ጂኦተርማል በተሰኙ የፈረንሳይና አይስላንድ ኩባንያዎች ይሸፈናል።
በቀጣይ የተለያዩ የውጭ ሀገር የብድር ተቋማት ለፕሮጀክቱ ብድር የሚያቀርቡ ሲሆን በመንግሥት በኩል ግን ምንም የሚወጣ ወጪ አይኖርም። ኩባንያዎቹ ሙሉ ወጪውን ችለው ኃይሉን ካመነጩ በኋላ ግን ለመንግሥት ያቀርባሉ፤ መንግሥትም ኃይሉን ይገዛል ተብሎ ይጠበቃል። ዋናው ሥራም ኃይሉን ለመሸጥ የሚደረገው ድርድር ነው።
ከሃያ አምስት ዓመት በኋላም ኩባንያዎቹ የኃይል ማመንጫውን ሙሉ በሙሉ ለመንግሥት አስረክበው እንደሚወጡ የሚጠበቅ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የኃይል ማመንጫውን የሚገነባ ድርጅት ለማግኘት የጨረታ ሂደት ተጠናቋል። ኃይል የማመንጫ ግንባታውም በቀጣዩ ዓመት ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት የኮቪድ ወረርሽኝ መከሰትና ፕሮጀክቱ አዲስ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ በቁፋሮ ሂደት የመለዋወጫ እቃዎች በሀገር ውስጥ ስለማይገኙ ከውጭ ሀገር እቃዎቹን ለማስገባት ረጅም ጊዜ የመፍጀት ችግሮች ነበሩ። ይሁንና በተቻለ መጠን ችግሮቹን በማቃለል ከስር ከስር ሥራዎችን ለማከናወን ተችሏል።
ከሁሉ በላይ ደግሞ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ተችሏል። አርባ የሚሆኑ የአካባቢው ወጣቶችን በኤሌክትሪክሲቲና ሜካኒካል ሙያ በማሰልጠንም እዛው የሥራ እድል እንዲፈጠርላቸው ተደርጓል። ኃይል ሲመነጭ ለአካባቢው ማህበረሰብ እንዲደርስ በራስ ወጪ ከአሁኑ ሥራዎች እየተሰሩም ይገኛሉ። ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለመጀመር የሚያስችሉ የቴክኖሎጂ ሽግግሮችም ተደርገዋል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2013