• አገራችን የጤፍ ባለቤትነት መብት ክርክርን አሸነፈች የሚለው ዜናም የተሳሳተ መሆኑ ታውቋል
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ጊዜያዊ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ብሩክ ወርቅነህ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ከአስርት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ ‘ሄልዝ ኤንድ ፐርፎርማንስ ፉድ ኢንተርናሽናል’ ከተባለ የሆላንድ ድርጅት ጋር በአውሮፓ ላይ የጤፍ ምርትን ለማሳደግና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከግምት ውስጥ በማስገባት የተፈራረመችውን ስምምነት ተከትሎ የባለቤትነት ውዝግብ መፈጠሩን ገልፀዋል፡፡
በመሆኑም የአገራችንን የጤፍ ምርት የባለቤትነት መብት ለማስጠበቅ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት፣ ከሳይንስና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከጠቅላይ አቃቤ ህግ የተውጣጣ አምስት አባላት ያሉት ሀገራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱንና በአሁኑ ወቅትም ኮሚቴው ለክርክሩ የሚያስፈልጉ ሁሉንም መረጃዎች አሰባስቦ ለጠቅላይ አቃቤ ህግ መላኩን ገልጸዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ከሰሞኑ የጤፍ ባለቤትነት መብትን አስመልክቶ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ተከራክራ አሸነፈች በሚል በማህበራዊ ሚዲያዎችና በአንዳንድ መገናኛ ብዙኃን አማካኝነት የተሰራጨው ዜና የተሳሳተ መሆኑን አቶ ብሩክ ተናግረዋል፡፡
እንደኃላፊው ገለፃ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የጤፍ ውጤቶች ባለቤትነት መብትን ይዞ የቆየው ኤንሺየንት ግሬይንስ የተባለ የሆላንዱ ድርጅት በባለቤትነት መብቱ ላይ ቤክልስ በተባለ የሀገሩ ድርጅት በተነሳበት ጥያቄ ሲከራከር ቢቆይም ፍርድ ቤቱ ግን የባለቤትነት መብት አይገባውም ሲል ውሳኔ ማሳለፉን ገልፀዋል፡፡
ኢንሺየንት ግሬይንስ የጤፍ ውጤቶች በጁስ መልክና በተለያዩ መንገዶች አምርቶ በመሸጥ እያከናወነ ባለው ሥራ የባለቤትነት መብት አለኝ በሚል የፈጠራ መብት ጥያቄ ቢያቀርብም ይህ ሥራ አዲስ ፈጠራ ሳይሆን የቆየና በሌሎችም ጤፍን በሚጠቀሙ አገራትና ድርጅቶች የተለመደ በመሆኑ «ባለቤትነቱ አይገባውም» በሚል ክስ ካቀረበው የሀገሩ ድርጅት መሸነፉን ተናግረዋል፡፡
በዚህ መልኩ በራሱ አገር ድርጅት ተከስሶ የባለቤትነት መብቱን መነጠቁ ኢትዮጵያ ለጀመረችው የይገባኛል ክስ አወንታዊ አስተዋፅኦ እንደሚኖረውም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በተለይ በድርጅቱ የተነሳ ኢትዮጵያ ምርቶቿን እንዳትልክ ተከልክላ በቆየችባቸው ከአምስት በላይ የአውሮፓና የአሜሪካ አገራት እንደገና ምርቶቿን ለመላክ ያስችላታል ያሉት ኃላፊው ሁለተኛ ለጀመረችው የባለቤትነት መብት የማስመለስ ጥያቄም ድርጅቱ ባለቤትነቱን መነጠቁ ለዓለም ህዝብ የሚያስተላልፈው መልዕክት ትልቅ ነው ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2011
ይበል ካሳ