ከዛሬ 26 አመት በፊት በኢትዮጵያ ሬዲዮ ይተላለፍ የነበረው “ኢትዮጵያን እንቃኛት” ፕሮግራም ከብዙ ሰው ህሊና ውስጥ የሚጠፋ አይደለም።ኢትዮጵያ ለቱሪዝም መዳረሻ ሀገር መሆኗን የሚያስተዋውቅ ተወዳጅ ፕሮግራም እንደነበርም ይታወሳል።ፕሮግራሙን በመቅረጽና ተወዳጅ እንዲሆን በማድረግ ደግሞ ጋዜጠኛ ወንድሙ ከበደ፣ ፀሐይ ተፈረደኝ፣አስፋው ገረመው የማይረሱ ባለሙያዎች ናቸው።
ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ለረጅም አመት በተጓዘው በዚህ ፕሮግራም ላይ የማውንቴንስ ሚዲያ ባለቤት ጋዜጠኛ አስቻለው ደምሴም ለአስር አመት የኢትዮጵያን እንቃኛት ፕሮግራም አዘጋጅ ሆኖ ሰርቷል።ጊዜውን ሲቆጥረው አስር አመት ይሁን እንጂ ያን ያህል መቆየቱን አስቦት እንደማያውቅና የአመት ፈቃድም ሳይወጣ ለተከታታይ አመት በፍላጎት መስራቱን ጋዜጠኛ አስቻለው ይናገራል።
ጋዜጠኛ አስቻለው ወደኋላ መለስ ብሎ ሲያስታውስ ከእርሱ በፊት የነበሩትም ሆኑ እርሱ በሥራው ላይ በቆየባቸው አመታት ፕሮግራሙን ለማዘጋጀት የቱሪስት መዳረሻ ወደሆኑት የተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሲጓዙ የተሟላ መሠረተ ልማት አልነበረም።የመንገዱ ወጣ ገባነትና አስፓልት አለመሆን ለመኪናም እጅግ አስቸጋሪ ነበር።መኪና በማይገባባቸው በእግር ረጅም መንገድ መጓዝ ይጠይቃል።
እርሱ ራስ ዳሽን ተራራ ላይ ለመድረስ በቀን ለአስር ሰአታት ለሶስት ቀናት በእግር የተጓዘበትን ጊዜ አይዘነጋውም።ዛሬ ግን መንገዱም የተመቸ ሆኖ በመኪና የቱሪስት መዳረሻዎች ሥፍራ ድረስ መድረስ ተችሏል።በዚያን ጊዜ የመገናኛ ስልክ አለመኖርም ሌላው ፈተና ሲሆን፤ ወደከተማ መመለስ በማይቻልበት ጊዜ መብራት በሌላቸው የገጠር ከተሞችም ማደር የግድ ይል ነበር።
የተሟላ መፀዳጃና መታጠቢያ ቤት ያላቸው ማደሪያ ቤቶች (አልቤርጎ) ማግኘትም ያጋጥሙ ከነበሩ ተግዳሮቶች መካከል ይጠቀሳል።የጋዜጠኛው የቀን የውሎ አበልም አነስተኛ ነበር።በወቅቱ የነበሩት ጋዜጠኞች ይህን ሁሉ ውጣ ውረድ አልፈው ነበር ኢትዮጵያን ሲያስተዋውቁ የነበረው።ውጣ ውረዱን እንደ አንድ የሥራው አካል አድርጎ ከመውሰድ ባለፈ በቅሬታ የሚያነሳ ጋዜጠኛ እንዳልገጠመውና እርሱም የእነርሱን ፈለግ ተከትሎ በሥራው ላይ መቆየቱን ያስታውሳል።በዚህ አጋጣሚም አድካሚውን ጉዞ ተቋቁማ ጣፋጭ የሆነ ዝግጅት ለአድማጭ ጆሮ ለማድረስ ስትተጋ ለነበረችው የኢትዮጵያን እንቃኛት ፕሮግራም መሥራችና አዘጋጅ ለነበረችው ጋዜጠኛ ፀሐይ ተፈረደኝ አድናቆቱን ገልጾላታል።
አስቸጋሪ በሆነው ጉዞ ውስጥ አልፈው የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ፀጋዎችና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መዳረሻዎች ኢትዮጵያን እንቃኛት በሚለው ፕሮግራም የኢትዮጵያ ሬዲዮ ጋዜጠኞች ሲያስተዋውቁ፣ አንድ የሬዲዮ ጣቢያ በነበረበት የማይረሳ ፕሮግራም ሲተላለፍ፣ዛሬስ ምቹ እና አማራጭ በሆኑ የመገናኛ ዘዴዎች ጋዜጠኛው ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ ምን እየሰራ ነው ለሚለውም ጋዜጠኛ አስቻለው ያለፈውን ከአሁኑ ጋር በንጽጽር ነው ያቀረበው።
…ያኔ ጋዜጠኛው ቱሪዝሙን ሲያስተዋውቅ ቅኝቱ ስለቅርስ፣ ስለባህል፣ ስለተፈጥሮ ሀብቱ ህዝቡ ግንዛቤ ኖሮት እንዲንከባከበውና እንዲጠብቀው እንጂ ቱሪዝም ካለው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ወይንም ፋይዳ ጋር የተያያዘ አልነበረም። ሀብቱ ተሸጦ ገቢ አስገኝቶ ለህዝቡና ለሀገር ጥቅም እንዲውል በማድረጉ ላይ የጎላ ሚና አልነበረም።መንግሥትም ለቱሪዝም እንቅስቃሴው የሰጠው ትኩረት አሁን ባለው ደረጃ የሚገለጽ አልነበረም።
ቱሪዝሙን የማነቃቃቱ እንቅስቃሴ ፍላጎቱና ተነሳሽነቱ ባላቸው የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ነበር የሚሰራው ለማለት ይቻላል።በአሁኑ ጊዜ መንግሥት ለቱሪዝም የሰጠው ትኩረት በዚያን ጊዜ ተፈጥሮ ቢሆን ኖሮ በቱሪዝም መዳረሻዎች የሚኖረው ማህበረሰብ ኑሮው ይቀየር ነበር። እንደዛሬው ቱሪስቱን እየተከተለ ለልመና እጁን የሚዘረጋ አይኖርም ነበር። ወደ መኖሪያነት የተቀየሩና ለከብቶች ግጦሽ እየዋሉ የመጡት ፓርኮችም ይጠበቁ ነበር›› ሲል ጋዜጠኛ አስቻለው በቁጭት ይናገራል።
ጎረቤት ሀገር ኬንያና ግብጽ ባላቸው ጥቂት የቱሪዝም መዳረሻዎቻቸው ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው ለመጠቀም በሚሊየን የሚቆጠሩ ቱሪስቶችን እየሳቡ፣ ኢትዮጵያ ግን የተፈጥሮ ፀጋ፣ ባህል፣ ቅርስና ታሪክ ብዝሃ የቱሪዝም መስህብ እያላት ከዘርፉ እያገኘች ያለው ጥቅም አነስተኛ መሆኑንም አንስቷል።በተለይም ካለፉት ሦስት አመታት ወዲህ በመንግሥት የተሰጠው ትኩረትና በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ የመገናኛ ብዙሃን መስፋፋታቸው ያለፈውን ቁጭት ለማስቀረት የሚችሉ ይሆናሉ ብሎ ያምናል።
በግሉ ላለፉት አስር አመታት በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ ሲሰራ ማህበረሰቡ የተፈጥሮ ሀብትን እንዲንከባከብና እንዲጠብቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን፣ አሁን ደግሞ በግሉ በዘርፉ ላይ ትኩረት ያደረጉ መረጃዎችን በመስጠት ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነ ያስረዳል።ግን ደግሞ ቁጭትን የሚያስቀር የበለጠ ሥራ እንደሚጠበቅበት ይገልጻል።
ጋዜጠኛ አስቻለው እንዳለው እስካሁን ባለው ተሞክሮ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ የባለሀብቱ ድጋፍ አነስተኛ ነው። ጋዜጠኛው ውጤት ለማምጣት በተሻለ እንዲንቀሳቀስ የባለሀብቱ እገዛ ያስፈልጋል።እርሱን ጨምሮ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ የሚሰሩት ጋዜጠኞች በግል ጥረታቸው በመሥራት ላይ ይገኛሉ።በተለይም ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ አጋር ድርጅቶች በግል ለሚንቀሳቀሱ በገንዘብ እንዳይደግፉ (ስፖንሰር) እንዳያደርጉ መታገዱ በዘርፉ ለሚንቀሳቀሱ ባለሙያዎች የበለጠ ጫና ማሳደሩንም አስታውሷል።
በኢትዮጵያ የባህል፣ ቱሪዝምና የመገናኛ ብዙሃን ታሪክ በተለያየ መንገድ ሀገርንና ባህልን የማስተዋወቅ ሥራ ተሰርቷል።ነገር ግን ቱሪዝም አንድ የልማት ዘርፍና ለዜጎች እንዲሁም ለሀገር ጠቃሚ እንደሆነ የሚያስተዋውቅ ቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ መገናኛ ብዙሃን አልነበረም።ለረጅም አመት ሲሰራ የቆየውም በመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን ብቻ ነበር።ከጥቂት አመታት ወዲህ ግን የመገናኛ ብዙሃን ዘርፉ እየሰፋና ከዚያም አልፎ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ ብቻ የሚሰሩ ጋዜጠኞችንና የመገናኛ ብዙሃን መፍጠር ተችሏል።
እንደሀገርም ግልጽ የሆነ አሰራር አልነበረም። ቱሪዝም ወይንስ ልማት ይቀድማል የሚሉ እሳቤዎች ነበሩ።በአሁኑ ጊዜ ግን ኢንዱስትሪው እንደ አንድ ትልቅ የልማት ዘርፍ ተደርጎ ትኩረት ተሰጥቶታል።መገናኛ ብዙሃንን እንደ አንድ ትልቅ መሳሪያ በመጠቀም ዘርፉን ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገር ይቻላል በማለት ሀሳቡን ያካፈለን የኢትዮ ቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ፕሮግራም አዘጋጅ፣ የባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኛ ዘሪሁን ግርማ ነው።
በአሁኑ ወቅት በዘርፉ የሚንቀሳቀሱ ጋዜጠኛች እየተፈጠሩ ቢሆኑም የቀደመው አሻራ አሁን ለተጀመረው እንቅስቃሴ መሠረት መሆኑ መዘንጋት እንደሌለበት አስታውሷል።ቱባ የሆነውን ባህልና የተፈጥሮ ፀጋ ለማስተዋወቅ ለብዙ ቀናት በመጓዝ ዘልቆ ገጠር ውስጥ መግባት፣ የማህበረሰቡን ኑሮ በመጋራት፣ ወደ ፓርኮች በሚኬድበት ወቅት የሚተናኮሉ የዱር እንስሳት ሊያጋጥሙ ይችላሉ።ይኼን ሁሉ በመቋቋም በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ ታልፎ ነው የማስተዋወቁ ሥራ የሚሰራው።የቱሪዝም ጋዜጠኛ ለመሆን ፍላጎት፣ ክህሎትና የገንዘብ አቅም ይጠይቃል።በመሆኑም ወጪን ሸፍኖ ብዙ ለመንቀሳቀስ አቅም ስለማይኖር የመንግሥትና የሌሎች አጋር ድርጅቶች ትብብርና ድጋፍ ይጠይቃል።
ኢትዮጵያ ያላትን የቱሪዝም ዕምቅ ሀብት መጠቀም ያልቻለችው መገናኛ ብዙሃን በደንብ ባለመሥራታቸው ነው በሚል ለቀረበለት ጥያቄ ጋዜጠኛ ዘሪሁን ሲመልስ፣ ‹‹በግሌ ለገበያ የሚቀርበው የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ሰፊ ነገር ይዞ ነገር ግን በድፍረት የሚሻለውን ለይቶ ተጠቃሚ መሆን ላይ ክፍተት ያለ ይመስለኛል።ብዙ ሀብት ሲኖር ለመምረጥም ሳያስቸግር አይቀርም።ክፍተቱን ለይቶ የማስተዋወቁን ድርሻ መወጣት ከመገናኛ ብዙሃን ይጠበቃል›› ብሏል።
ጋዜጠኛ ዘሪሁን በሥራ ቆይታው ያጋጠመውንም እንዲህ አካፍሎናል።በነጭ ሣር ብሄራዊ ፓርክ ውስጥ ሥራውን ጨርሶ ሲወጣ ከባድ ዝናብ ያጋጥመዋል። ባለበት ለማደር በአጋጣሚ ድንኳን አልያዘም።ከካምፑም ርቋል። በእግርም፣ በመኪናም ከጭቃው ውስጥ ለመውጣት አስቸጋሪ ሆነ።ስልክ ደውሎ ድረሱልኝ ለማለትም የመገናኛ አገልግሎት የለም። ዝናቡና ምሽቱ ሁኔታውን እጅግ አስፈሪ አደረገው። ሆኖም ግን በመከራ ከፓርኩ ውስጥ ለመውጣት ችሏል።ከማይረሱ የሥራ አጋጣሚዎቹ መካከል እንዲህ ያጫወተኝ ጋዜጠኛ ዘሪሁን፣ በባህል ዙሪያም ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ሲያሳልፍ ዘና ያለባቸው አጋጣሚዎችንም አይዘነጋቸውም።
‹‹ቱሪዝምን ከመገናኛ ብዙሃን ጋር የሚያቆራኘው ከሌሎች ዘርፎች ለየት ይላል።ምን አይነት ልማት ብናካሂድና ምን ብንሰራ ነው ቱሪዝሙ የሚያድገው ለሚለው የመገናኛ ብዙሃን የቅድመ ልማት መሳሪያ ነው። የባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኛው ብርቅዬ ዱር እንስሳቶቻችንን ጎብኙ ብቻ ሳይሆን አይገደሉ ብሎም የሚጮህ ነው። ቱሪዝም ማለት ጥቅሙ ሰፊ ነው። የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ላይ ሲሸጥ የማን ሀገር ነው የሚባለው። እንዲህ ያለውን ነገር መፍጠር የሚቻለው ቀድሞ ሀገሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ፀጋ ማስተዋወቅ ሲቻል ነው።አንዱ የሌላውን የቱሪዝም ሀብት ማወቅ የሚቻለው እንደሀገርም እርስ በርስ መተዋወቅ ሲቻል ነው።
በአጭሩ ቱሪዝም ሀገር ይሰራል።ቅድመ ልማቱን ካሳካን በኋላ ደግሞ የድህረ ልማቱ ውጤት ጎብኝዎች በብዛት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ማድረግ ነው።የዘርፉ ልማትና ጥበቃ ሥራ ገና ባልተጠናቀቀበት፣ በዘርፉ በቂ የተማረ የሰው ኃይል ያላመረትንበት፣ ስለቱሪዝም ያለው ግንዛቤም ገና ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ብዙ ሥራ ይጠበቃል።የብዙ ባለሙያዎች ርብርብም ይጠይቃል።›› ያለን ደግሞ የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ጋዜጠኛ ሄኖክ ሥዩም ነው። ማህበሩ በጥቂት የሙያው ባለቤቶች ተነሳሽነት ለምሥረታ እንደበቃና ወደፊት ዕቅዱ ሠፊ እንደሆነ ተናግሯል።
በመላ ሀገሪቱ ወኪሎች እንዲኖሩትና የቱሪዝም ኢንዱስትሪውም በመላ ሀገሪቱ ሽፋን አግኝቶ እንደሀገር ከዘርፉ የሚፈለገውን ገቢ ለማግኘትና ለማሳደግ ይሰራል። ቱሪዝምን የሚዘግብ ጋዜጠኛ ለመፍጠርም ጭምር ነው ጥረቱ።
የቱሪዝም ጋዜጠኝነት ሱስ ነው የሚለው ጋዜጠኛ ሄኖክ እርሱን ጨምሮ በተመሳሳይ ሙያ ላይ የሚገኙት ሌላ የሥራ ዘርፍ አስበው አያውቁም።ከዱር እንስሳት ጋር መጋፈጥ፣ የውሃ ሙላትን ተሻግሮ ለማለፍ መቸገር፣ የመኪና አደጋ፣ ከቤተሰብ ርቆ መቆየት ሌሎችም የሚያጋጥሙና ፈተና የበዛበት፣ በገንዘብም ይህ ነው የሚባል ጥቅም የማያስገኝ በተለይ በግል የአየር ሰአት ገዝተው ለሚንቀሳቀሱ ባለሙያዎች ተስፋ የሚያስቆርጥ መሆኑን በሥራ አጋጣሚው ካያቸው መካከል ይጠቀሳል።
ለዘርፉ አለማደግ ከሚቀርበው ወቀሳ አንዱ ዘርፉ በአግባቡ አልተመራም የሚል ነው።በሚመራው አካል እንቅስቃሴው ደካማ ሆኖ ከተገኘ የዘርፉ ጋዜጠኛ ክፍተቱን በማሳየትና መፍትሄውንም ጭምር በማመላከት መሥራት ይኖርበታል።መንግሥት ፖሊሲ፣ ህግና መመሪያ ያወጣል።ነገር ግን የወጣው ህግ ውስኑነት ሊኖረው ይችላል።ቱሪዝሙን የተረዳና የተገነዘበ እንዲሁም ቱሪዝሙን አለማለሁ ብሎ የተቋቋመ ጠንካራ የቱሪዝም የሚዲያ ማህበረሰብ የህጉን ውስኑነትና ወደፊት በዘርፉ ሊደረስበት በታሰበው ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ከሆነ አቅጣጫና መሥመር በማሳየት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።መገናኛ ብዙኃኑና ጋዜጠኛው ቀድሞ መገኘት አለበት።
የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበር ለምሥረታ የበቃው ባለሙያዎቹ በብዙ ሥራና ውጣ ውረድ ውስጥ አልፈው እንደሆነ ካነጋገርኳቸው ባለሙያዎች ለመረዳት ችያለሁ።ምሥረታው በቅርቡ ይፋ ይሁን እንጂ ማህበሩ ከተመሠረተ ቆይቷል የሚለው የማህበሩ ፕሬዚዳንት ጋዜጠኛ ሄኖክ ‹‹ህጋዊ ሆነን ለመንቀሳቀስ ጊዜ ከመውሰዱ በስተቀር ጀማሪ ማህበር ልንባል አንችልም።ከአስር አመት በላይ አብረን የተጓዝን የሙያ አጋሮች አብረን ተጉዘን ማህበር ለመመሥረት የበቃነው›› ይላል።ማህበሩ የራሱን የመገናኛ ብዙሃን አቋቁሞ ስለኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ሀብት ተቆርቋሪ የሆነ ማህበረሰብ ለመፍጠርና እንደሀገርም ተጠቃሚ ለመሆን እንደሚሰራ ተናግሯል።
በባህልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይ ብቻ የሚሰሩ ጋዜጠኞች መፈጠራቸው አንድ በጎ ጅምር ነው።ህብረት ሲፈጥሩ ደግሞ አቅማቸው ይጎለብታል።ጠንካራ የሆነ ሥራም በመስራት የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ያስችላቸዋል።በቱሪዝም ላይ የሚሰራ ጋዜጠኛ መብዛት አለበት፣ ድጋፍም ያስፈልገዋል ብለው የቀድሞ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ታደለች ዳለቾ አሁን የተሰባሰቡት የዘርፉ ባለሙያዎች የሚዲያ ፎረም እንዲያቋቁሙ በማድረግ ጭምር በማበረታታት እዚህ ስላደረሷቸው የማህበሩ መሥራቾች ውለታቸውን አስታውሰው በምሥረታ ዕለት ጋብዘው አመስግነዋቸዋል።ማህበሩም ከዚህ በኋላ የማህበሩን አባላት መብት በማስጠብቅ፣ አቅም በማጎልበት ከመንግሥትና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ችግሮችን የመፍታት ሥራ ለመሥራትም ተዘጋጅቷል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2013