እኛንም ሆነ ሀገራችንን ሊያፈርሰን ላሰበው ሀሳባችን ቀሳ እንውጣ እያልኩ ነው። ምን አስባ ይሆን ላላችሁኝ መልስ አለኝ ። ቀሳ የሚለውን ቃል ለመበየን ከአማርኛ መዝገበ ቃላት ትርጓሜ ልነሳ። ቀሳ ማለት ከቤት ወደ ዱር ኼደ ፤ በደን ተቀመጠ ፤ተኛ ፤ታመመ ፤ ከቤተሰቡ ተለየ፤ የሚጋባ በሽታ ተስቦ ስለ ያዘው የሚል ነው። ታዲያ እኛስ ይህ እያባላ እያፋጀ ሀገራችንን ሊያፈርስ የተነሳው ሕመም እንዳይተላለፍ ለበሽተኛ የሚሠራ ልዩ ቤት (ጎጆ) አያስፈለገንም ትላላችሁ። ሕመምተኛው ሲድን ቀሳው ይቃጠላል የሚል ሀሳብም የታከለበት የቀሳ ትርጓሜ ከዘረኝነተ ህመማችን ስንድን የትናንት ሀሳባችንን አቃጥለን ውብ ሀገራችንን ወደ ፊት ልናሰቀጥልበት የሚችል የተቀደሰ ሀሳብ እናመጣ ከሆነ እስኪ ቀሳ እንውጣ።
በእማማ ኢትዮዽያ ውስጥ ማንም ብሄርን አላሰብም ቢል እንኳን የተቃኘንበት ቅኝት የተሰራንበት የአስተሳሰብ ስሪት እንድናስብ አሰገድዶናልና ብሄራችንን እያሰብን በውሸቱም በእውነትም ትርክት ውስጥ ጥሩ ጎኑን መመልከት እያስተወ ክፉ ክፉውን የሚያሳየን በሽታ ተጣብቶናልና አዲሱን ትውልድ ይህ ወረርሽኝ እንዳይጋባበት ወገኖቼ ልብ እንድንገዛ ቀሳ እንውጣ።
ሀገራችን ስለ መታመሟ የማይካድ እውነት….አለ። ኧረ እንዲያውም እንደሷም ታማሚ የለ። በጣም ክፉ ህመም የከፋ ገዳይ ወረርሽኝ ጎጆ ቤቷን የሚንድ የሚያፈርስ በሽታ መጥቶባታል። በምድሯ የተስተዋለ አንድነት ቁስል ሆኖባት ፤የልዩነት ደዌ፤ የመከፋፈል፤ የመበታተን፤ የክፋት ፤የተንኮል ህመም ፀንቶባት፣ መንገዱን ለሞት እየጠረገ ሀገርን ሊያፈርስ የመጣ ክፉ ወረርሽኝ እኛ ሀገር ገብቷልና ከበሽታችን እስክናገግም ድረስ ታማሚዎች ቀሳ አንውጣ።
የአንድነት ምሶሶ ከላላ፤ ልዩነት ለምልሞ ትልቅ ዛፍ ሊሆን ከዳዳው፤ ለመራራቅ አርቡ ከሰፋ፤ መናናቅ አቅሙ ጎልብቶ የጤንነት አቅም ከጠፋ ፤ደህና መሆን ግራ ገብቶት ሰው በዘረኝነት ህመም ከከፋ፤ ጤንነት ምንድን ነው? መቼ ነው ደህና መሆናችን ታውቆ የጠራ አስተሳሰብ አካል መሆን ካልቻልን ከዚህ በላይ መታመም ከየት ሊመጣ?
ሰው መሆን ውሉ ግራ የገባው፤ ሰብአዊነት ትርጉሙ ላንቺ የጠፋ? ወገን አንደ ቅጠል እየረገፈ ሀዘኔታን ከውስጣችን አሟጦ የአንዱ ሞት ላይ ዳንኪራ የሚያስረግጠን በሽታ ተጠናውቶናል። ሀቁ ይነገር ፤ማበሉ ካልተቀየረ መድሃኒት ህልም ነውና እኔ እናገራለሁ፣ በሽታውን የደበቀ መድሃኒት አይገኝለትም አይደል ከነተረቱ፤ ስሙኝ እናገራለሁ ፤ሀገሬ ታማለች! ህመሟ ፀንቷል የወለደቻቸው አቅላቸውን መሰብሰብ ተስኗቸው በመፍረሷ ጫፍ ላይ ሆነው፤ ከመውደቋ ገደል አፋፍ ላይ ተቀምጠው ምንም ቅር የማይሰኙ ልጆችን አፍርታለች። ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን ፤ከመተባበር ይልቅ መገፋፋትን፤ከመመሰጋገን ይልቅ መወቃቀስን ልማዳቸው ያደረጉ በየጎጣቸው የሚያስቡ ልጆችን ወልዳለች።
አያት ቅድመ አያቶቻችን በነፃነት ያቆዩልን ሀገር ጠልተን የሰው ናፋቂ ሆነናል። የሰው እያስናፈቀ ከራስ የሚያጣላ፣ ለሌላ የሚያሰግድ ስር የሰደደ የጭንቅላት እጢ ከአዕምሯችን ገብቶ ያባክነን ይዟል፤ ጎጠኝነት መላ አካላታችንን አደንዝዞ እግር ከወርች አስሮናል። ሃገሬ ኢትዮዽያ ታማለች! ከህመሟ ፈውስ ትፈልጋለች፤ ሊገድላት ሊሰብራት፤ ሊከፋፍላት የተነሳው ህመም አዳኝ በልጆቿ አእምሮ ሞልቶ ፈውስ ሳያሳጣት በፊት ሁሉም ራሱ ጊዜ ይስጥ አአምሮውን ፈትሾ ከህመሙ ድኖ በጤና ተመልሶ የሀገር ልጅ እናቱን ይመልከታት። ከበሽታዋ ሳትፈወስ፤ ሳትታከም ከሀኪም ሳትደርስ፤ በሽታው እንዳያጠፋት፤ ለመዳን አንድ ለመሆን ወገን በአንድ ልብ፤ በአንድ አካል ኑ ቀሳ እንወጣ።
ይበቃል፤ ብልጥ ከሰው ሞኝ ከራሱ ነውና፤ ሞኝነታችን በዝቶ በራሳችን እስኪበቃን ከስቃይና ከመከራ ተምረናል፤ ስቃይ በዝቶ ልቦናችንን ሲያደድረው ሀዘን በሀዘን ላይ ተደምሮ ውሉ ሲጠፋብን የተፅናናን የዳን መስሎን ከሆን ገና ነን፤ ገና ነው የሀገሬ ህመም፤ ገና ናት አልተሻላትም፤ መታመሟን ያዩ ልጆቿ እየሸሽዋት፣ ህመሟ እየፀና፣ ጉልበት እየከዳት፣ ጤና ነኝ ለማለት ብትፈልግም አስተውሎ ላያት ስቃይዋ ፊቷ ላይ ይነበባል። ጨለምለም ያለ ፈገግታ ከጥርሷ አካባቢ ብልጭ ቢልም ስቃይና መከራ ምን ያህል ልቧን እንዳቆሰለው ከፊቷ ላይ ይነበባል ፤አይሸሸግም።
እማማ ታማለች…. መድሀኒቶቿ እኛው ነን፤ የኛን ቁስል ቁጥቋጤ የምናውቅ፤ ሌሎችማ መታመሟን ያዩ፤ እንኳን ሊያስታምሙን ትሞታለች ብለው ጉድጓድ እየቆፈሩላት ነው፤ የመቀበሪያ ሳጥን ለማቅረብ ይሽቀዳደማሉ። እኛ “ሞኞቹ” ግን መድሃኒቱ በእጃችን በእርጋታችን ውስጥ ፈልገን ማግኘት አቅቶን እናት ሀገራችን ክንዳችን ላይ ታማ በአምሮት ያያታል ሞት። የእናትም የልጆቿም ፈውስ ለማግኘት ማገገሚያ ያሰፈልገናልና እንደ ሀገር አንድ ሆነን መቀጠል ካለብን ከየወስጥ ጩኸታችን ወጥተን አንድ የሚያደርገንን ሀሳብ ለማግኘት መጀመረያ በሽታው ይልቀቀን ኑ ቀሳ እንውጣ።
ሀገር በአጉል ዘመን ታማ፤ ልጆቿ መድሃኒት አግኝተው፣ ማዳን ከማይችሉበት ሰአት ላይ የደረሱ ሲመሰላቸው ጥለዋት የሸሹበት ጊዜ ላይ ደርሰናል። ከመከራዋ ጋር መከራ ላለመቁጠር ቢሸሹም በተቀመጡበት ዝም ብለው እንዳይኖሩ እነሱ የተደላደሉ ሲመስላቸው ቁስላችንን እየነካኩ እንዳንድን አድርገውናል። መዳናችን ደሰ የማይላቸው እናት ምድራቸውን ጥለው የኮበለሉ ቢሆንም የዘረኝነት ህመም ከማናለብኝነት ጋር ተደምሮባቸው እሳቱ ላይ ቤንዚል እያርከፈከፉ አላስቀምጥ ከላሉንም መፍትሄው የኛ በአንድነት መፈወስ ነውና የሀገር መዳን ያማራችሁ ወገኖቼ ትንሽ ጎጆ እንቀልስ፤ እዛው ተኝተን እግር ከወርች ካሰረን በሽታ እንፈወስ።
ሀገሬ የራሷ ህመም ሳያንሳት የሌሎቹ በትር እየጎሻሸማት የፈረንጅ በሽታ የነጭ ትልቅ ህመም በቀኑ እየደቆሳት ነው። ለሀገርኛው ህመም ሀገር በቀል መድሀኒት ነውና ፈውሱ የራስን የመጣል መፍትሄ ከሌላ መጠበቅ ቀርቶ ወደ ሌላ መዝመም፤ ተከፋፍሎ ማሰብ፣ ተነጣጥሎ መፍትሄ መሻት የትም አያደርስምና ድብልቅልቅ ቁርጥማት፣ የታሪክ ወለምታ የታሪክ ስብራት……እየቀሳሰፈ፣ እየቆላለፈ ጤናችን ተናጋ፣ ወጌሻውም ባለመድሃኒቱም ከቤታችን ነውና የቤት ቁስል ቤቱ ይታከም፤ ስብራቱም በሀገር ወጌሻ ታሽቶ ይጠገን።
ኢትዮዽያ የሚለው ስም ወደፊት ይቀጥል ዘንድ ህመማችን መካከላችን የገባው ክፉ ወረርሽኝ ወደ መቃብር ሳያወርደን በፊት የጥሞና ጊዜ ያስፈልገናል፤ ማገገሚያው ቤት እንግባ ፤የተጣባንን በሽታ ማሻሪያ መድሃኒት ይፈለግ፤ ስር ይማስ፤ ቅጠል ይበጠስ፤ ከቀስታው ከእርጋታው መካከል አንድ የሚያረግ ወደፊት የሚያስኬደንን ልዩ ሀሳብ በጥሞና እንመልከትና መፍትሄ እናምጣ።ወገኔ ለአንድነታችን ስንል ከሚከፋፍለን ሀገር ከሚያፈርስ ክፉ በሽታችን ለመፈወስ ነገ ዛሬ ሳንል ቀሳ እንውጣ።
ብስለት
አዲስ ዘመን ግንቦት 29 ቀን 2013 ዓ.ም