የፖለቲካ ታሪካችን ያወረሰን “ከእንቆቆ” የከፋና የመረረ “ቅርስ” ነው። “ፖለቲካ” የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ የተረዳነውና እየኖርንበት ያለው አንድም በፍርሃት፣ አንድም በጥርጣሬ፣ አንድም በስቅቅ፣ አንድም ባለመተማመን፣ አንድም በራስ ጥቅም ዕይታ፣ አንድም… አንድም… ብዙ አንዶችን መዘርዘር እንችላለን። “ፖለቲካና ኮሬንቲን በሩቁ” እያልን ስንመስለው የኖርነው ምስል ለላይኛው አገላለጻችን ጥሩ ማሳያ ይሆናል።
በግርድፍ ድንጋጌ የፖለቲካችን አመለካከት አስኳል ተፈልቅቆ ውስጡ ቢፈተሽ ፈጦ የሚያገጠው ግላዊ የሥልጣንና የገዢነት ጥማት ነው። ሽፋንና መጠቅለያው ደግሞ “የሕዝብ ፍቅር” ይሉት ዓይነት መደለያ ነው። አብዛኞቹ ፖለቲከኞቻችን ግን በተቃራኒው ሕዝብን መነጽር በማድረግ ሊያሳዩን የሚሞክሩት “ለሕዝባቸው ያላቸውን የማገልገል ጥማትና ላቅ ያለ ርዕይ ነው።” እርግጥ ነው ለሕዝብ ኖረው ለሕዝብ የሞቱ ጥቂት “ኅሊናና እምነት” አደሮች እዚህም እዚያም ነበሩ፣ አሉ ይኖራሉም። ይህንን የጥቂቶች ቁጥር አግዝፈን በአጠቃላይ መስፈርትነት እንከራከርበት ብንል ግን የጉንጭ አልፋ ሙግት ካልሆነ በስተቀር እጅግም ሊያግባባን አይችልም።
“ሀገራዊ መግባባት” በእሳቤ ደረጃ ብዙውን ጊዜ የሚጠቀሰው ለበለፀጉትና ዲሞክራሲን ቤተኛ ላደረጉ ሀገራት ሳይሆን የድሃና የታዳጊ ሀገራት ራስ ምታት ተደርጎ ነው። በተለይም “የመፈንቅለ መንግሥትን ሙያ” ባህርይው ላደረገው የአፍሪካ አህጉር “ሰለጠንን ባዮቹ” ምዕራባዊያን የሚወተውቱት ጤና ኖሮት የማያውቀው የአፍሪካ መሪዎች ጭንቅላት በብሔራዊ መግባባት “ፓራሴታሞል” እንዲፈወስ ነው። “መፍትሔ ይሁንላችሁ” ብለው መምከር ብቻም ሳይሆን በእርዳታና በብድር ጡንቻቸው እየተመኩ ጭምር በግድ ካልጋትን በማለትም ትንቅንቅ ይገጥማሉ።
አፍሪካዊያን መሪዎች ግን በአንጻሩ “ወተትና አጥሚት” አልጋትም ብሎ ጥርስ አልባ ድዱን ጥርቅም አድርጎ በማጋጠም አሻፈረኝ እንደሚል ሞገደኛ ሕጻን “የሀገራዊ መግባባት መፍትሔን” ወደው ከመዋጥ ይልቅ ጠብመንጃ ወልውለው ቢፋለሙ ይመርጣሉ። ከጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ይልቅም የዱር ሽፍትነትን ያስቀድማሉ። ቢቻላቸውም “ሀገራዊ መግባባት” (National Consensus) የሚለው ሀረግ ከመዛግብተ ቃላቶቻቸው ውስጥ ቢጠፋ ደስታቸው ነው።
ባህር ማዶኞቹ “Beat around the bush” እንደሚሉት ዳር ዳሩን እያንዣበብን ፈራ ተባ በማለት ዞርን እንጂ መነሻ ጉዳያችን እኛንው ራሳችንን አልዋጥ ብሎ ሲያገፋፋንና ሲያቆራቁዘን በኖረው በራሳችን የሀገራዊ መግባባት አጀንዳ ጉዳይ ላይ ጫን ብለን በግልጽነት መወያየቱ ይበጃል ብለን በማሰብ ነበር። ይበጃል ብቻም ሳይሆን ግራ ለተጋባንባቸው ብዙ ሀገራዊ ጥያቄዎቻችንም የእንቆቅልሽ ፍቺ ሊሆን አንደሚችልም ይታመናል። መነሻችንን ከቅርቦቹ ነበር ታሪኮቻችን አድርገን ጥቂት የወፍ በረር ዳሰሳ እናድርግ።
ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመኑ በሚፈቅደው ልክ የ“ሀገራዊ መግባባትን” መፍትሔ በአሜንታ አልቀበል ብለው “ለጥገናዊ ለውጥ” እንኳን አሻፈረኝ በማለታቸው የሰማንያ ዓመት ልደታቸውን ባከበሩ ማግሥት በወታደራዊው ጁንታ ከዙፋናቸው ተፈንግለው ፍጻሜያቸው እንደተበላሽ እናውቃለን። ይህ ክስተት በቀዳሚነት ለደንዳናው የሀገራችን የፖለቲካ ባህርይ በጥሩ አብነት ሊጠቀስ ይችላል።
ንጉሣዊውን ሥርዓት ከዙፋን ላይ አጎሳቁሎ ስልጣን የጨበጠው ወታደራዊ ደርግም ለ“ብሔራዊ መግባባት” ቀልቡን አስገዝቶ ከወደረኞቹ ጋራ ተቀራርቦ ከመሥራት ይልቅ “ሥልጣን ወይም ሞት!” በሚል እብሪት በመታወሩ እንደተመኘውም ፍጻሜው በአጓጉል አወዳደቅ ሊደመደም ግድ ሆኗል። ደርግ ሥልጣን ላይ በቆየባቸው አስራ ሰባት ዓመታት ውስጥ ያጣነውን ሁሉ እንዘርዝር ብንል ብዛቱ ከትውልድ እልቂት እስከ ሀገር ውድቀት ስለሚዘረጋ በእህህታ ማለፉ የተሻለ ይሆናል። ይህ ሁለተኛውና ሳይፈርጥ የወረስነው ሀገራዊ የፖለቲካ “ብጉንጅ” ውርሳችን ነው።
በረቀቀ የሴራ ተንኮልና በሀገሪቱ የከፉ ጠላቶች “አይዟችሁ!” ባይነትና ድጋፍ የደርግን ሥርዓት አስወግዶ በሀገሪቱ የሥልጣን ጫንቃ ላይ እንኮኮ እንዳለ ለ27 ዓመታት ያህል ተንሰራፍቶ የዘለቀው የህወሓት/ኢህአዴግ ሥርዓትም “ሀገራዊ መግባባት ከነማን ጋር? ስለ ምንስ ምክንያት?” እያለ በትዕቢት ሰክሮ እንዳልደነደነ ሁሉ “የግፍ ዋንጫው ሲሞላ” የደረሰበት ደርሶበት እትብቱ በተቀበረበት በረሃ ውስጥ በድኑ ሊያርፍ ግድ መሆኑ የትናንት ትዝታችን ነው። በሦስተኛ እማኝነት የምናስታውሰው ይህ “የሀገራዊ መግባባት” ጥላቻ የመጨረሻውና በፈውስ አልባ ካንሰርነት የምንጠቅሰው አንዱ መራራ “የፖለቲካ ታሪካችን” ነው።
ይህንን ሁሉ የመከራ አሸንክታብ አንገቷ ላይ አንጠልጥላና ከቋጥኝ የከበደ አሳር በአናቷ ላይ ተሸክማ ስትንገዳገድ የኖረችው እናት ዓለም ኢትዮጵያ ጉስቁል መልኳ ምን ይመስል እንደነበር አንዘነጋም። ከምንገምተውና ከምንመኘው በላይ በአንድዬ ጣልቃ ገብነት ግፈኛው ሥርዓት መወገዱን በሽብሸባና በዕልልታ በታጀበ ዝማሬ የተቀበልነውም ስለዚሁ ምክንያት ነበር። እውነትም ከለውጡ ማግሥት ጀምሮ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ጭምር ያለ ማንም ቀስቀሳ በተደረጉ መግባባቶችና ቅርርቦች እጅግ አድናቆት የተትረፈረፈላቸውና ያስጨበጨቡ ተግባሮች መከናወናቸውን አንዘነጋም።
የግፍ ማጎሪያ የነበሩት የወህኒ በሮች ወለል ተደርገው እየተከፈቱ ግፉዓን የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ነፃ ሲወጡ ያስተዋልነው ዓይኖቻችን በደስታ እንባ እየረጠቡና የለውጡን መሪዎች እያመሰገንን ነበር። ቀዳሚው ፖለቲካ እንደ ጠላት ፈርጆ ያሳደዳቸውና ፊት ነስቶ እግር በእግር ይከታተላቸው የነበሩ መደበኛና ኢመደበኛ የማሕበራዊ ሚዲያዎች ሰንሰለቱ ከእጃቸው ላይ ወልቆላቸው ተመልክተን “አዲሱ አስተዳደር ሆይ አበጀህ!” ብለንም አጨብጭበን ነበር።
“የፖለቲከ መጻተኛ ወገኖች” ያለገደብ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ኬላዎች በሙሉ ስለተከፈተላቸውም ሰንደቅ ዓላማቸውን “በድል አድራጊነት ስሜት” እያውለበለቡ ሲገቡ በየአደባባዩ እየተገኘን “የጀግና አቀባበል” አድርገንላቸዋል። በዓመታት መካከል በየሃይማኖቶቹ ውስጥ ከራስና ከሌሎች ጋር የነበረው መሻኮትና “ለፈጣሪ ለራሱ አንኳን አንቆቅልሽ ሳይሆንበት አይቀርም” እያልን “ሰማይን” ያማንበት ሀገራዊ ችግሮቻችን በእርቅና በሕግ በተደገፈ ጥረት “ጠበኞቹ የፈጣሪ አገልጋዮች” እርስ በእርስ ሲተቃቀፉ አስተውለን እንደየእምነታችን ለከበረው ፈጣሪ ዝቅ ብለን ምስጋናና ዱዓ በማቅረብና ለመንግሥትም አድናቆታችንን በመግለጽ “ሃሌ ሉያ!” ብለን መዘመራችንም እውነት ነበር።
ከጎረቤትና ከእህት ሀገር ከኤርትራ ጋር የጠብ እሳት ስንጫጫርባቸው የነበሩት የፍም መቆስቆሻ ገሎች እንክትክት ተደርገው ተሰባብረው መሪዎቹና ሕዝቦቹ በፍቅር ሲተቃቀፉ ተመልክተን በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን ከሕዝቦቹ ዓይኖች ውስጥ የፈሰሰው የደስታ እምባ በኩሬ የሚለካ ሃይቅ ሊፈጥር የሚችል ነበር ብንል “ሥነ ጽሑፋዊ ተጋንኖ” ተደርጎ የሚቆጠር አይሆንም።
“በመደመር እንሻገር፤ ድልድዩን እንገንባ!” የሚለው የለውጡ መሪ ሃሳብ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ተግባራዊ ተደርጎ በርካታ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያውና ልማታዊ ተግባሮች ሲከናወኑ አስተውለንም በመደነቅ እጃችንን አፋችን ላይ ጭነን የለውጡ ብርሃን እንዳይጨልም ፈጣሪን ተማጥነናል። የድህነታችንና የኋላ ቀርነታችን ቡቱቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገፎ እንደሚወድቅም በማመን መንፈሳችን በእጅጉ ተነቃቅቶ ነበር።
“በጥባጭ ካለ ማን ጥሩ ይጠጣል” እንዲሉ የጠጅ ቤት ቤትኞች፤ የሀገሪቱ የዕድገትና የብስለት ጅማሮ ጤና የነሳቸው የህወሓት፣ የእርሱ ውልድና የጡት ልጆች የሆኑት የጥፋት ኃይሎች ያዳቆነው ሠይጣናዊ ባህርያቸው ወደ ከፋ ቅስና አድርሷቸው የፈጸሟቸውና እየፈጸሟቸው ያሉት የግፍ ድርጊቶች ከ እስከ ተብለው የሚዘረዘሩ አይደሉም። ሀገር እንዲተረማመስ፣ ሰላም እንዲጨነግፍ፣ የደም አበላ ምድሪቱን እንዲያጥለቀልቅ፣ የግለሰቦችና የሀገር ሀብት እንዲወድም ያልፈጸሙት አንዳችም ክፉ ድርጊት አልነበረም። የግፍ ድርጊቶቹ ዓይነት በሰው ፍጡር ሊፈጸሙ ቀርቶ ለሠይጣን ለራሱ እንኳን ፈታኝ ነበር ቢባል ኩሸት አይሆንም። የክፋታቸው ጥግ መገለጫው ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ላይ የፈጸሙት ክህደት ነበር።
በዚህ ክፉ ቡድንና በአምሳሉ በፈጠራቸው ጀሌዎቹ አማካይነት ሲጎነጎንና ሲገመድ የኖረው ይህን መሰሉ ሀገራዊ የጥፋት ሴራ እየዋለ እያደረ ያስከተለው ተያያዥ ቀውስ በሀገር ድንበር ብቻ ተከልሎ ያበቃ ሳይሆን ባህር አቋርጦ፣ ውቂያኖስ ተሻግሮ ጠላቶች እስከማበራከት የደረሰ ውጤት አስከትሏል። በሀገር ውስጥ ብሔር ከብሔር አንዲጋጭ፣ ንፁሐን ዜጎች በብሔራቸው ምክንያት እንዲገደሉ፣ እንዲፈናቀሉና እንዲሰደዱ፣ ፖለቲከኞች ከብጤዎቻቸው ጋር እንዲሻኮቱ፣ ሃይማኖት ከራስና ከሌላው ጋር እንዲፋለም፣ የልማት እንቅስቃሴዎች አደጋ እንዲጋረጥባቸው፣ በዲፕሎማሲው መስክም ዓለማቀፋዊ ተጽእኖ እንዲበረታ ወዘተ. የተሸረበው ሴራ ፍሬ አፍርቶ ሀገሪቱ ለችግር እንድትጋረጥ ምክንያት ሆኗል። በዚህ ጡዘቱ ባየለበት ወቅት ነው የ“ሀገራዊ መግባባት” ወሳኝነት ወለል ብሎ ሊታየን ግድ የሚሆነው።
በመሠረቱ “ሀገራዊ/ብሔራዊ መግባባት” ሲባል የግድ በፖለቲከኞች መካከል የሚደረግ የሥልጣን መቀራመቻ ዘዴ ተደርጎ ብቻ መታሰብ አይገባውም። ሀገራችንን ዛሬ ለገጠማት ዘርፈ ብዙ ችግሮች የዚያንው ያህል መልከ ብዙ መግባባቶች ያስፈልጉናል። የመግባባቶቹ ሂደት እንደምንመኘው በቀላሉና በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎም አይታመንም። ቢሆንም ግን ለጅማሮው “ዛሬ” እንጂ “ነገ” ተብሎ ቀጠሮ የሚያዝለት ጉዳይ ሊሆን አይገባም።
“ብሔራዊ መግባባት” ለሁሉም ሀገሮችና ሕዝቦች እንዲያገለግል ተደርጎ የሚጋገር የአንድ ምጣድ (One-size-fits-all) ሞዴል አይደለም። ለእኛ የምንመርጠው ሞዴል እኛን መምሰል አለበት። ይሁን እንጂ ብዙ ሀገራት የተጠቀሙበትን የጋራና አማካይ አካሄድ መከተሉም ክፋት አይኖረውም። “ብሔራዊ መግባባት” በብዙኃን የጋራ ስምምነት ላይ መመሥረቱ የመጀመሪያ መሰረት ነው። ነጣይ ሳይሆን አካታች መሆኑም ሁለተኛ ባህርይው ነው። በስውር ሃሳብ አመንጭዎች የሚዘወር ሳይሆን በግልጽነት መከወኑም ሦስተኛው መገለጫው ነው። ለጊዜው ችግር ማስታገሻ እንዲሆን ሳይሆን ዘላቂነት እንዲኖረውም ይጠበቃል። ይሄም አራተኛው መለያው ነው። የመግባቢያው አጀንዳ የተሸፋፈነ ሳይሆን በግልጽ የተለየ መሆኑ በአምስተኛ መስፈርትነት ይጠቀሳል። በማስመሰል ሳይሆን በመሆንና በመሰጠት ሊረጋገጥ እንደሚገባ መረዳቱም የሰባተኛ ባህርይው መታወቂያ ነው። በግብር ይውጣ ሳይሆን በተጠና አካሄድ መተግበሩም ስምንተኛ “የሀገራዊ/ብሔራዊ መግባባት” ውጤታማ ባህርይ ነው። እነዚህን የአካሄድ ስልቶች በመከተልና ገለልተኛ ታዛቢ በመካከል በማቆም የሚተገበር “መግባባት” ውጤቱ አመርቂ፣ ሰንባችነቱም “ዘመን ተሻጋሪ” ሊሆን ይችላል።
ለመሆኑ “ሀገራዊ/ብሔራዊ መግባባት” የሚያስፈልጋቸው የጋራ ጉዳዮቻችን የትኞቹ ናቸው? ዝርዝሮቹን በቁጥር ለመገደብ ቢያዳግትም ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ሊሆኑ ይችላሉ። በፖለቲካ ቡድኖች፣ በሃይማኖት ተቋማት፣ በታሪክ አተረጓጎምና አረዳዳችን፣ በቋንቋ መረጣና አጠቃቀማችን፣ በልማት ዕቅዶቻችንና አተገባበራቸው፣ በፌዴራሊዝምና በሕገ መንግሥት ጉዳዮች፣ በክልልና በብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማዎች አወሳሰን፣ በብሔራዊ መዝሙር ጉዳይ፣ በትምህርት ሥርዓታችንና በኢኮኖሚ አመራራችን ወዘተ. “የሀገራዊ/የብሔራዊ መግባቢያ” አጀንዳዎች እየተቀረጹ ከሥልጣን ዓላሚ ፖለቲከኞች ጋር ብቻም ሳይሆን ሕዝቡ ራሱ በነቂስ እየተሰበሰበ በግልጽነት መነጋገርና መከራከር ቢችል የሀገራዊ ደዌዎቻችን እባጮች በስለው የማይፈርጡበት ምክንያት አይኖርም። እያመረቀዙ ፋታ የነሱን ሕመሞቻችንም ቀስ በቀስ ወደ ፈውስ መቃረባቸው አይቀሬ ይሆናል።
የእርቅ፣ የሰላምና የድንበር ኮሚሽኖች፣ ዴስቲኒ ኢትዮጵያና ሌሎች በርካታ መሰል ሀገራዊና ገለልተኛ የሃሳብ ቋት (Think Tank) ተቋማትና ቡድኖች እንደ መነሻ የአቀራራቢነቱን ሚና ቀድመው ሊጀምሩ ይችላሉ። በሽብርተኝነት የተለዩትና ለሀገር የመከራ ምንጭ የሆኑ ጥቂት ቡድኖች ግን በዚህን መሰሉ ሂደት ውስጥ ተካተው ይሰለፉ ማለት ለጥፋታቸው እውቅና መስጠት ስለሆነ “ውሻን ምን አገባው ከእርሻ” ብሎ በፍትሕ አደባባይ የማቆሙ ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2013