ብዙዎች አማርኛ ፊደልን በኮምፒውተር እንዲጻፍ በማድረጋቸው ያውቋ ቸዋል። በየጊዜው እያሻሻሉም የተለዩ የአጻጻፍ ስልቶችን በማቅረብ ይታወቃሉ። ኮምፒዩተር ኦሮምኛና ሌሎች የአገሪቱን ቋንቋዎች አይጽፍም ለሚሉትም በሶፍትዌራቸው ምላሽ ሰጥተዋል። የእርሳቸው ሶፍትዌር ማንም ሳይጀምረው ከሰላሳ ዓመት በፊት የተጀመረ እንደሆነና ሰባት ፓተንቶች ያገኙባቸው መሆኑንም መረጃዎ ቻቸው ያመላክታሉ። በውጭው ዓለምም እንዲሁ በተለያዩ ሥራዎቻቸው ይታወቃሉ። በተለይም በእንስሳት ሕክምና እንግሊዝም ሆነች አሜሪካ ልዩ ክብር ትሰጣቸዋለች። በምርምሩ ዘርፍም ከሁለቱም አገራት የባለቤትነት መብት (ፓተንቶች) እ.ኤ.አ. በ1985 የተሰጣቸው ናቸው። ኢትዮጵያ በይበልጥ የምትገለገልበትን የአማርኛ ቋንቋ መክተቢያ እንኳን ሳይቀር አሜሪካ የባለቤትነት መብታቸውን ሰጥታቸዋለች። ይሁንና መቼም ቢሆን በአገራቸው የመጨከን ፍላጎት የላቸውምና አሁንም ቢሆን የሚሰሯቸውን ምርምሮች «ቅድሚያ ለአገሬ» ይላሉ፤ የሚቀበል ካለ። አገር ወዳድነታቸው እያሮጠ አምጥቷቸው ነው ያገኘናቸው።
እናም አዲስ አበባ ሻላ መናፈሻ ቁጭ ብለን ስለሕይወታቸው ብዙ አወጉን። ተሞክሯቸው ዕድሜ ጠገብነታቸውን ይናገራል። መሥራት ልምዳቸው መሆኑን ደግሞ ከብርታት፣ ቆራጥነትና አቋማቸው መረዳት ይቻላል። ከሚናገሩት ንግግርም ወርቅ የሆነ ሀሳቦች ሲወለዱ አስተውለናል። ለዚህም ነው የዶክተር አበራ ሞላን የህይወት ተሞክሮ እንዲህ ለአንባቢያን ማቅረብ የወደድነው። የሸዋው እንቦሳ እንደ ዛሬው ልጅ የልደት ካርድ ባይኖራቸውም የተወለዱበትን ቀን በትክክል የሚያውቁበትን መንገድ ቤተሰቦቻቸው አስረድተዋቸዋል። ምክን ያቱ ደግሞ ዘመናዊ ትምህርት ቤት መግባታቸው ነው። በዚህም የተወለዱት መጋቢት 24 ቀን 1940 ዓ.ም ነው። የትውልድ ስፍራቸው በወቅቱ አጠራር ሸዋ ጠቅላይ ግዛት፣ መናገሻ አውራጃ፣ በረህ ወረዳ፣ ሰንዳፋ ከተማ፣ ቡልጋ ሰፈር ሲሆን፤ ለቤተሰቦቻቸው ሁለተኛ ልጅ ናቸው። አባታቸው ሞላ ወርቁ የጠቅላይ ግዛቱ አርበኛ ከነበሩት ከራስ አበበ አረጋይ ጋር ጣሊያንን በመመከታቸው ጃንሆይ ሲመለሱ ለእርሳቸውና መሰሎቻቸው ሰፊ ጋሻ መሬት ሰጧቸው። ይህም ቤተሰቡ ሳይቸገር እንዲኖር አገዘው።
እናታቸውም የራሳቸው ርስት ነበራቸው። «ከልጅነት ትዝታዬ በይበልጥ የሚታወሰኝ ለምንም ነገር መሸነፍ አለመውደዴና ሁሉን ነገር ለማወቅ መጣጣሬ ነው። በተለይም አንድን ነገር መረዳት የምፈልገው ጠይቄ ብቻ ሳይሆን ሞክሬም ነው። በዚህም ብዙ ጊዜ ቅጠላ ቅጠሎችን ለምን አገልግሎት መዋል እንዳለባቸው ለመረዳት እስከ መቅመስ ደርሻለሁ» ይላሉ። ብዙ ጊዜ ከብት እንዲጠብቁ ቤተሰቦቻቸው ባይፈቅዱላቸውም የእንስሳት ፍቅር ስላላቸው ከእረኞች ጋር ይውሉ እንደነበርም ያስታውሳሉ። ከዚያ ባሻገር እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ እንጨት ሰብረዋል፣ ውሃም ቀድተዋል። የወዳደቁ ነገሮችን አንስቶ ወደ ነበሩበት መመለስም የልጅነት ልዩ ጥበባቸው እንደነበር የሚያስታውሱት ዶክተር አበራ፤ አንድ ጊዜ የሆነውን እንዲህ ያስታውሱታል። ሳይክል ናት ግን ጎማ የላትም። በአካባቢያቸው ሲያሽከረክሩት ስለሚያዩ እንደሚሽከረከርና ጎማ ከተተከለላት ወደነበረው ቦታ እንደምትመለስ ያውቃሉ። በመሆኑም ያችን የተጣለች ሳይክል አንስተው ካብ እየሠሩ በጎማ ልክ ድንጋይ ደርድረው ሚዛናቸውን እየተቆጣጠሩ መለማመድ ጀመሩባት። ይህ ደግሞ ከማንም ሳይማሩ ሳይክል መንዳት እንዲችሉ አደረጋቸው። ሳይክል እያከራዩም ማለማመድና ገንዘብ ማግኘት የጀመሩት ከዚህ በኋላ እንደነበርም ያስረዳሉ።
«የተለያዩ ነገሮችን መሞከሬ ዛሬ ላይ ላለሁበት ደረጃ አብቅቶኛል። ይህንን ባህሪዬን አጎልብቼው ባልቀጥል ኖሮ ተመራማሪና ለቴክኖሎጂ ቅርብ አልሆነም ነበርም» ይላሉ። ከወንድማቸው ጋር በጣም ስለሚመሳሰሉ በልጅነታቸው የተሰጣቸው መለያ ስም «ጢኖ ድንቄ» የሚባል እንደነበርና ድንቄ የሚለው መለያ የተሰጣቸው ደግሞ አክስታቸው በአካባቢው ታዋቂ በመሆናቸው እንደነበርም ይናገራሉ። ዶክተር አበራ በልጅነታቸው ፈጣን፤ አትንኩይ ባይ፣ መመራመርን የሚወዱ ነበሩና በዚህ ባህሪያቸው ቤት ውስጥ በጣም በማስቸገራቸው በአምስት ዓመታቸው ትምህርት ቤት እንዲገቡ እንደተደረጉ አጫውተውናል። ለመማራቸው መሠረቱ በቤት ውስጥ የሚያደርጉት ነገር እንደሆነም ይናገራሉ። የእናትን ሕልም የማሳካት ጉዞ እናትና አባታቸው ያልተማሩ ግን ለልጆቻቸው መማር የሚተጉ ነበሩ። በተለይ እናታቸው ወርቄ ድንገቶ የልጆቻቸው መማር በጣም የሚያሳስባቸውና ምንም እንዳይጎድልባቸው የሚጥሩ እንደነበሩ አይረሳቸውም። ትምህርታቸውን “ሀ” ብለው የጀመሩት ሰንዳፋ በሚገኝው ጅማ ሰንበቴ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ በትምህርታቸው ከአንደኝነት ደረጃቸው ፈቅ ብለው አያውቁም። ይህ ደግሞ መምህሮቻቸው ሳይቀር ለትልቅ ነገር እንዲመኟቸው አድርጓቸዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ስምንተኛ ክፍል ሳሉ ምን እንደተባሉ ሲያወሱም፤ የሁሉንም ተማሪዎች የወደፊት ሕልም ዳይሬክተራቸው ሲነግሯቸው እርሳቸውን ግን ምንም ሳይናገራቸው ያልፋል። ተማሪዎቹ ግን ይህንን አስተውለው «ለምን የእርሱንስ አትነግረውም?» ሲሉ ጠየቁ፤ ዳይሬክተሩም «እርሱ ከሁላችሁም ይለያል። በትምህርቱም በጣም ጎበዝ ነው። ስለዚህ የሚሆነው ዶክተር ነው» ብለው መለሱላቸው። ዶክተር አበራም ይህን ጊዜ ዶክተር ማለት ምን እንደሆነ ፍንጭ አገኙ።
መምህሩ የተመኙላቸውንም ለማሳካት ይጥሩ ጀመር። ከዚህ በተጨማሪም አንድ ቀን የተከሰተው የእንስሳት በሽታ ማለትም ደስታ (ሪንደርፔስት) የሚባለው ወደ መንደራቸው በመግባቱ ብዙዎችን ሲያስለቅስ እናታቸውን ደግሞ በጣም አሳዝኗል። ምክንያቱ ደግሞ ላሟ ታልባ ጥጃዋ እስክትጠባ ድረስ እየጠበቁ በነበረበት ወቅት ከታቢው ሥራውን ጨርሶ ሄዷልና በእንክብካቤ ያደገችውንና እንደልጃቸው የሚወዷት ላም በመሞቷ ነበር። እናት ማድ ቤት ገብተው ከልባቸው አነቡ።ይህንን የተመለከቱት ዶክተር አበራም ለእናታቸው «እኔ ሳድግ ሐኪም እሆንና በሽታውን አጠፋዋለሁ» የሚል የማጽናኛ ቃል ሰጡ፡፡
እናትም ያደርገዋል ብለው ስላመኑ ወዲያውኑ እንባቸውን ጠራርገው ወደ ሥራቸው መመለሳቸው አይረሳቸውም። ከዚህ በኋላም የልጅነት ሕልማቸው እናታቸውን ያስለቀሰውን የእንስሳት በሽታ ለማጥፋት ሆነ፡፡ የእንስሳት ህክምናውን በልባቸው ይዘውም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመከታተል ለሸዋ ጠቅላይ ግዛት ተማሪዎች ተብሎ ወደተከፈተው ትምህርት ቤት ለመጓዝ ተሰናዱ። ከዚያም ወደ ደብረብርሃን አቅንተው ኃይለማርያም ማሞ ትምህርት ቤትን ተቀላቀሉ። ቀጠሉናም ልዩ ትኩረታቸውን ሳይንስ ላይ አድርገው አዲስ አበባ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ገቡ። እዚህ ግን ከሳምንት በላይ አልቆዩም። ምክንያቱ ደግሞ የያኔው ደብረዘይት/ ቢሾፍቱ/ ላይ ለእናታቸው ቃል የገቡትን ለመፈጸም የሚያስችላቸው የትምህርት መስክ ማግኘታቸው ነበር። ከጓደኛቸው ተስፋዬ ካሳ (ዶ/ር) ጋር ተማክረው ወደ ደብረዘይት እንስሳት ህክምና ኮሌጅ ሕልማቸውን ለማሳካት አቀኑ።
ዲግሪ መማራቸውን ትተውም በእንስሳት ሕክምና የዲፕሎማ ትምህርት ተማሩ። ዶ/ር ኋይት የተባሉ ዳይሬክተራቸው ተስፋ የሰጧቸው መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር አበራ፤ ጥሩ ውጤት ያላቸው በመሆኑ ለዲግሪ እንዲማሩ የሁለቱ ዓመት የደብረዘይት ቆይታቸው ተፈቅዶላቸው በሌላ የውጭ የትምህርት እድል የሚፈለግባቸውን እንዲያሟሉ አዲስ አበባ በሚገኘው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋከልቲ እንደገና ለሁለት ዓመት ትምህርት እንዲገቡ ሆነ። በአንደኝነት ተመርቀውም ለአንድ ዓመት በሥራ መቆየት ግድ ነበርና ጎጃም ገቡ። ቀጥለውም ለእንስሳት ሕክምና ትምህርት በአሜሪካ መንግሥት የኮሎራዶ ስቴት ዩኒቨርሲቲ አጋዥነት የውጭ የትምህርት እድል አግኝተው ወደ ኬንያ በማምራት የድህረ ምረቃ ትምህታቸውን ተምረዋል።
በኮሎራዶ ስቴት ዩኒቨርሲቲም ለአራት ዓመት ትምህርታቸውን ተከታትለው አጠናቀዋል፡፡ ወደ አገራቸው ተመልሰው ሁለት ዓመት ሠርተዋል። የትምህርት ዕድል ስላገኙ ተመልሰው ወደ አሜሪካ ኮሎራዶ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ለሦስተኛ ዲግሪ ትምህርት አቀኑ። ይህ የሆነው በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1975 ነበር። ትምህርታቸውንም በሦስት ዓመታት አጠናቀዋል። በምርምራቸውም ለአገሪቱ ጠቃሚ ውጤት ስላመጡና በኢትዮጵያም የመንግሥት ለውጥ ስለነበረ አሜሪካ እንዲቆዩ ተገደዱ። በዚያም ወቅት በሕክምናውም ሆነ በኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተለያዩ ምርምሮችን ስለሚያደርጉ ዕውቀታቸውን ከመገንባት አላቆሙም። ድል ያደረገው ሕልም ጎጃም የጠቅላይ ግዛቱ የእንስሳት ሕክምና ክፍል ተጠባባቂ ኃላፊ በመሆን ነበር ሥራቸውን በ19 ዓመታቸው የጀመሩት። በዚህ ጊዜ ከሠሯቸው ሥራዎች የሚያስደስታቸው አንድ ነገር እንደነበር ያስታውሳሉ። ይኸውም በልጅነታቸው እናታቸውን ያስለቀሰውና ላማቸውን የገደለው በሽታ በጠቅላይ ግዛቱ ተከስቶ ያደረጉት ነገር። ከታቢዎቻቸውን በመያዝ በቀላቸውን ለመወጣት ብዙ ተጉዘዋል። በሽታውን እየቀደሙም 8 መቶ 50 ሺህ ከብቶችን ከደጀን ጀምረው ባሕር ዳር ድረስ ከትበው ታድገዋል። እስካሁንም ያ ሪከርድ እንዳልተሰበረም ይነገራል። የከፋና ኢሉባቦር ጠቅላይ ግዛቶች የእንስሳት ሕክምና ኃላፊ ሆነው ሲሠሩም እንዲሁ በእንስሳት ሕክምናው ከተባበሩት መንግሥታት ዶክተሮች ጋር ታላላቅ ተግባራትን አከናውነዋል። ግን በዚህ ሁኔታ ለአንድ ዓመት ያህል ብቻ ነበር የቆዩት። ያስተማራቸው ዩኒቨርሲቲ ኃላፊነት ስላለባቸው ደብረዘይት እንዲያስተምሩ ተላኩ።
በዚያም ዓመት ከቆዩ በኋላ የውጪ የትምህርት እድል በማግኘታቸው ወደ አሜሪካ ሄዱና በዚያው ቀሩ። ባለታሪኩ፤ እዚያም ቢሆን መሥራት ልምዳቸው ነበርና ኮሎራዶ ዩኒቨርሲቲን በመማር ማስተማሩ ዘርፍ ያግዙ ነበር። «አስተማሪ መሆን እምብዛም አልወድም። እኔ የማውቀውን ሰው ሁሉ ያውቀዋል ብዬ አስባለሁ። ለዚህም ነው ሌሎች አማራጮችን ማየት የጀመርኩት» የሚሉት ዶክተር አበራ፤ በተለያዩ የምርምር ሥራዎች ውስጥ በመሳተፋቸው ውጤታማ ሥራ መሥራት ጀመሩ። በተለይም ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ሲሠሩ ይበልጥ በሥራቸው መታወቅ ጀመሩ። ይህ ደግሞ በምርምራቸው የሰውን ቀልብ ለመሳብ አስቻላቸው።
የመከላከያ ክትባቶች ላይ ሰፊ ሥራዎችን ሠርተዋል። ወደ 14 የሚደርሱ የቫይረስ በሽታዎች መከላከያ የክትባት ዓይነቶችን የማምረትና አዳዲስ የመከላከያ ክትባቶችንም የመሥራት ችሎታ እንዳላቸው ይናገራሉ።ይህ በእንዲህ እንዳለ የዓለም ሕዝብ የደስታ በሽታን እ.ኤ.አ. በ2010 ስላጠፋ የዶክተሩ የልጅነት ሕልም ተሳክቷል። በአሜሪካ መንግሥት የሥጋ ምርመራ ውስጥም ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳላቸው፤ እንስሳትን በምግብነት ስንጠቀም ከእንስሳት ወደ ሰው ሊተላለፉ የሚችሉ በሽታዎችን ለማስወገድ የዶክተሮች ሱፐርቫይዘር በመሆን ለብዙ ዓመታት እንዳገለገሉም አጫውተውናል።
ከዚያ ደግሞ እ.ኤ.አ. 1982 ጀምሮ ከሕክምናው ሥራ ጎን ለጎን ወደ ኮምፒዩተሩ ዘርፍ አቅንተዋል። የአማርኛ ቀለማትን በኮምፒዩተር ዶክተር አበራ ሞላ የተስፋ ገብረሥላሴ የፊደል ሠራዊትን ወደ ኮምፒዩተር ያዘመቱ የፊደል ጀኔራል ናቸው። በዚህ የግዕዝ ፊደል ከተራ ጽሑፍ እስከ ተንቀሳቃሽ ፊደልና ሌሎች እንግዳ ጉዳዮችን ወደ ኮምፒውተር ያለምንም መሸራረፍ እንድናሰፍር አድርገዋል። በብዙ ሀብት የሚገዙትን የኮምፒዩተር የእንግሊዝኛ ፕሮግራሞች የግዕዝ ፊደልም እንዲጠቀምባቸው ያደረጉም ናቸው። አማርኛን ያካተተውን እያንዳንዱን የግዕዝ ቀለም ለመጀመሪያ ጊዜ በኮምፒውተር እንዲጻፍ አሜሪካ ውስጥ የፈጠሩት ዘዴ ኢትዮጵያ እንዲመዘግብ ሲሉም ከ30 ዓመታት በላይ የታገሉ ስለመሆናቸው ይመሰክርላቸዋል። የተመዘገበ የአሜሪካ ኮፒ መብትም አላቸው።
ዶክተር አበራ በሕክምናው ዓለም ፈውስ ሲሰጡ፤ በፊደል የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂያቸው ደግሞ ለቃላት እውቅና ከመስጠታቸው ጋር ተያይዞ «የግዕዝ አባት» የሚል የቅጽል ስም ተሰጥቷቸዋል። ዶክተሩ ኮምፒውተርና ፊደላቱን ለማዋሃድ ብዙ ለፍተዋል። ብዙ ገንዘብ፣ ጊዜና ጉልበትም አፍሰዋል። ኢትዮጵያ የፓተንት ሕግ የላትም ቢባሉም አላማቸውን ሳይለቁ ከልጃቸው ጋር የመጀመሪያውን የግዕዝ የእስክሪንና የማተሚያ ቀለሞች ሠርተው ለተጠቃሚ አቅርበዋል። ከዓመት በኋላ ደግሞ የፊደሉን ችሎታ በማሳደግ መጀመሪያ ፖስት እስክሪፕት ከዚያም በ1981 ዓ.ም. ትሩታይፕ በኋላም ተንቀሳቃሽ እያሉ ዛሬ ላይ አድርሰውታል። አማርኛን ወደ ኮምፒውተር ሲያስገቡ ለመጀመሪያ ጊዜ የስምንት እንግሊዝኛ ሥፍራዎችን አስለቀቁ። ቦታ በየተራ በማጋራትም ይጠቀሙ ነበር። ከዚያ በዩኒኮድ (Unicode) መፈጠር የተነሳ እያንዳንዱ የግዕዝ (Ethiopic) ቀለም የእራሱን ስፍራ እንዲያገኝ አስቻሉት።
የግዕዝ ቀለሞችም የዓለም ፊደላት በዩኒኮድ መደብ ዕውቅና ከአገኙበት ከ1989 ዓ.ም. በኋላም ሠርተው ጨምረዋቸዋል። ትክክለኛዎቹና ሁሉም የግዕዝ ቀለሞች የዩኒኮድ መደብ ውስጥ እንዲገቡም አስችለዋል። የዶክተር አበራ የሁለተኛው ፊደላቸው መነሻ ተወዳጁና ለረዥም ዘመናት ጥቅም ላይ የዋለው የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት አንደኛው የሞኖታይፕ የፊደል መልቀሚያ መኪና ነው። ሌላው ደግሞ የተስፋ ገብረሥላሴ ማተሚያ ቤት 1917 ዓ.ም. ቁምፊ (Typeface) ነው። የቀለማቱም መልኮች ከዩኒኮዱ ጋር አንድ ዓይነትና መደበኛ የኢትዮጵያ ፊደላትን ያካተተ ሲሆን፤ ቁምፊያቸው ግዕዝ ኤዲት ዩኒኮድ (Geez edit Unicode) በመባል ይታወቃል። ውብ ቀለሞቻችንን በወጉና በማዕረጉ መጠቀም የተቻለውም በእዚህ የተነሳ እንደሆነ የሚገልጹት ዶክተር አበራ፤ የዕውቀት ክምችት እንዲስፋፋ በሶፍትዌር እንዲጠቀሙ ያስተማሩም ናቸው። በታይፕራይተር እየጻፉ ሰዓታትን የሚፈጁ፣ በሰልፍ የሚጨናነቁና መጽሐፍ ለመጻፍና ለማጻፍ ብዙ ወጪ የሚያወጡትንም ያሳረፉት ለመሆናቸው ምስክር አያሻቸውም። ዶክተሩ የአማርኛን ፊደላትን ከሌሎች የዓለም ፊደላት እኩል እንዲራመዱ አድርገዋል።
ለምሳሌ ያህል እነ “ሀ”፣ “ሐ”፣ “ኀ”፣“አ”፣ እና “ዐ”አይነት ቀለሞች ምን ይሠራሉ፤ አንዱ በቂ ነው ተብሎ በምሁራኑ ዘንድ ክርክር ተፈጥሮ ነበር። ለእንግዳችን ግን ፊደላት ከዚህ ይልቃሉ። ድምጾቻቸው፣ ስሞቻቸውና ጥቅሞቻቸው ይለያያሉ ብለውም ያምናሉ። ይህ ደግሞ ትግርኛ፣ አማርኛ፣ ቤንች፣ ጉሙዝ፣ ጉራጌ፣ ምኢን፣ ጋሙ ጎፋ፣ ዳውሮ፣ ባስኬቶና እንዲሁም የኦሮምኛ ቋንቋዎችንም ይመለከታል። ሁሉም ቋንቋዎች የእራሳቸው ትልቅ ፋይዳ አላቸው ብለው ስለሚያምኑ ሁሉም በኮምፒውተር እንዲከተቡና ዩኒኮድ ውስጥ እንዲገቡ ከሚመለከታቸው ጋር ተባብረው ሠርተዋል። የግዕዝ ምልክቶችን በተመለከተም መብት፣ ንግድ፣ ብር፣ ሣንቲም፣ ማጥበቂያ፣ ማላያና አልቦ አኃዝ ፈጥረው በፓተንታቸው ውስጥ ታትመው አገልግሎት እንዲሰጡ አስችለዋል። አልቦ ዜሮን መፍጠራቸው ለምን አስፈለገ ለሚሉም ከአልቦና ከዜሮ በታች በአሉ (ኔጋቲቭ) ቁጥሮች እንድንጠቀምባቸው የዜሮ አኃዝ ቀለም መፍጠራቸው አስፈላጊ ነው ይላሉ። ሞዴት (ModEth) በመባል የታወቀውን የቃላት ማተሚያ የማይክሮሶፍትን ዶስ በመጠቀም እ.ኤ.አ. በ1987 አሜሪካ ውስጥ ለገበያ ያቀረቡት ዶክተር አበራ፤ ጊዜው ኮምፒውተሮችና ማተሚያዎች በቂ ኃይል ግኘት የጀመሩበት በመሆኑ በብዙ ጥረትና ወጪ ተግባራዊ እንዲሆን አስችለዋል። ኢትዮጵያ የፓተንት ሕግ ስላልነበራት የኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ሕጉ ሲወጣ ጉዳዩ ይታያል በማለት መጋቢት ፲፪ ቀን ፲፱፻፹፪ ዓ.ም. ቢወስንም ከሚፈለገው በላይ ጊዜ በመውሰዱ ፈጠራዎቻቸውን በአሜሪካ ፓተንቶች ያስጠበቁት ባለታሪኩ፤ ይህ የሆነው የዓለም ኮምፒውተሮች ፊደላችንን እንዲያውቁ ለማስቻል፤ ማንኛውም ሰው አከታተቡን አሻሽሎ ፓተንት ሊያወጣ ስለሚችል ኢትዮጵያ እንዳትጎዳና መብቷን እንዲጠበቅ እንደሆነ ይናገራሉ።
ዶክተር አበራ ሞላ በግዕዝ ፊደላት የተለያዩ ቋንቋዎችን በኮምፒዩተርና ተንቅሳቃሽ ስልኮች እንድንከትብ የፈጠሩ ሊቅ ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያ በፊደልዋ የመጠቀም መብትዋ እንዳይቀማባት ፓተንቶች በማውጣት ዜግነታዊ ግዴታቸውን የተወጡ ታላቅ ባለውለታ ናቸው። ብዙ ሰዎች ይኸን ረዥምና እልህ አስጨራሽ ሥራቸውን ሳይረዱ የግዕዝ ፊደል ያልሆነውን የአማርኛ ታይፕራይተር አማርኛ ነው በሚሉ ጭምር ተወናብደዋል። የአማርኛ ታይፕራይተር ፊደል የአማርኛ ፊደልን የማይጽፍ ከመቶ ያነሱ ቁርጥራጭ የፈጠራ ነገሮችን የሚቀጣጥል ጊዜው ያለፈበት መሣሪያና አጠቃቀም እንደሆነ የሚገልጹት ዶክተሩ፤ ፊደል ሳይከትቡ ከተብን በሚሉና አንዱን ፊደል በሦስትና አራት መርገጫዎች የሚጽፉ የግዕዝን ፊደል በማዳከም ትልቅ ችግር ፈጥረዋል፤ እየፈጠሩም ነው ይላሉ።
ሥራቸውን እንደጀመሩ የቢለን፣ ጉራጌ እና ሳሆ ምሁራን የቋንቋ ፊደሎቻቸውን እንዲጨምሩላቸው ናሙና ጽሑፎችን የላኩ ሲሆን፤ ከእዚሁ ጋር በማያያዝ እያንዳንዱ ቀለም በሁለት መርገጫዎች እንዲከተብ አዲስ የአከታተብ ዘዴ ፈጥረው አዳዲስ የፊደል ገበታዎች አቅርበዋል። አበርክቶ ለአገር ወደ ኢትዮጵያ የመጡበት ምስጢር «ሕዝቡ እየተግባባ መሆኑ አበረታቶኝና ኢትዮጵያም ፓተንቶቼን( የፈጠራ ዕውቅና) ስለሰጠችኝ ነው። ያስተማረኝን ሕዝብ ውለታውን በትንሹም ቢሆን እንድመልስ ለብዙ ዓመታት በኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ሳቀርብ የነበረውን ስጦታዬንም በሥራ ላይ ለማዋል ነው። ለኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶችና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተለያዩ ሶፍትዌር ፕሮግራሞቼን በነፃ በመስጠት አገሬን የምትጠቅምበትን ለማዘጋጀትም ነው» ይላሉ። ዶክተሩ ሕዝቡ የሚያውቃቸውና የማያውቃ ቸው ስጦታዎችን ይዘው መጥተዋል። በዋጋ ግምቱም በዶላር በሚሊዮኖች ይቆጠራል ይላሉ። ኮምፒውተራይዝ ያደረጉት የግዕዝ ፊደል ለብዙ ሺህ ዓመታት ኢትዮጵያውያን በእጃቸው ሲጽፉ የነበረበትን ሁኔታ ያሻሻለ እንደሆነ ሁሉ በተለያየ መንገድ ብዙዎችን ለመጥቀምም ነው ወደ አገራቸው የመጡት። ውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያውያንም በነፃ የሰጡትን ድረገጽ (http://freetyping.geezedit.com/) በመጠቀም በአማርኛ እንዲከትቡ ለብዙ ዓመታት አድርገዋል። ዶክተር አበራ ኮምፒውተር ለአማርኛ ጽሑፍ እንዲጠቅም ያሰቡት እ.ኤ.አ. በ1982 ሲሆን፤ ጊዜው ብዙ ሰዎች ኮምፒውተርን መንካት የሚፈሩበት ነበር።
ይሁንና እርሳቸው «የተለያዩ ኮምፒውተሮችንና ፕሮግራሞችን እየሞከሩ ሁለተኛ ሥራ አደረጉት። ከአምስት ዓመት በኋላ ለአይቢኤም ፒ.ሲ. (IBM PC) ለሕዝብ ሽያጭ አቅርበው አማርኛን በኮምፒውተር ለመጻፍ አስችለዋል። ዛሬ በተለያዩ የውጭ አገር ዩኒቨርሲቲዎች ጭምር በግዕዝና አማርኛ ቋንቋዎች ማስተማር የመጀመሩም መንስኤ እርሳቸው እንደሆኑም ይነገራል። አምስት መቶ የሚጠጉትን የግዕዝ ፊደሎቻ ችን ለሰማንያ ቋንቋዎቻችን ለመጥቀም ተዘጋጅተው ሳለ በሚገባ ስላልተጠቀምንባቸው ይህ ትውልድ ሊያስብበት ይገባል ብለዋልም። ለስኬታቸው መንስኤ የሆኑት ቤተሰቦቻቸው፣ ወንድሞቻቸውና ሶፍትዌሩን የገዙት ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፤ ሄልወት ፓካርድ በየጊዜው በአዋሷችው ማተሚያዎች በመጠቀ ምም ነበር። ፊደሉን እየከፈሉ ማሠራት ስለከበደ ዲጂፎንት የሚባል ኩባንያ ራሳቸው እንዲቀርጹና እንዲሠሯቸው ፈቅዶላቸዋል።
ሽልማት የግዕዝ ፈጠራ ግኝቶቻቸውን ለዩናይትድ ስቴትስ በማቅረብ እስካሁን አራት የፈጠራ ባለቤትነት መብት አግኝተዋል። ኢትዮጵያም ሶስት የግዕዝ ፓተንቶችን በ2011ዓ.ም. ሰጥታ ቸዋለች። እነዚህም ግዕዝን በአንድና ሁለት መርገጫዎች በኮምፒዩተሮች፣ በስልኮችና በመሳሰሉት መጠቀም ያስቻሉ ዘዴዎች ናቸው። ኮምፒውተሩ ግዕዝ ፊደላትን እንዲከትብና እንዲመዘግብ ሲያደርጉ ግኝቶቹ በፕሮግራሚንግ ብቻ ሳይሆኑ ለእንግሊዝኛ ፊደላት የተሠራውን ቴክኖሎጂ ለ37 የግዕዝ ቤት ቀለሞችና እንዚራኖቹ ጥቅም መሥራታቸውም ነበር የባለቤትነት መብት እንዲያገኙ ያደረጋቸው። ኑሮ በአሜሪካ አርባ አራት ዓመታትን አሳልፈውበታል። በዚህ ቦታ እውቅናና ሙያ ካለ መኖር እንደሚቻልም አይተውበታል። ችግሬ የነበረው ዘመድ አዝማድ በአካባቢዬ አለመኖሩ ነበር ይላሉ። አንዳንዶች አሜሪካ ሲኬድ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ የሚሆን ይመስላቸዋል።
ይሁንና ማንኛውም ሰው ወደ አሜሪካ ሲመጣ ዝቅ ብሎ መጀመር እንዳለበት ማሰብ ይኖርበታል። ይህ አስተሳሰብ ብዙዎችን መጸዳጃ ቤት ከማጽዳት አውጥቶ ትልቅ ደረጃ ያደረሰ እንደሆነም ያስረዳሉ። አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን በዓላማ ላይ የተመረኮዘ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ በመሆናቸው ስኬታማ ናቸው። ተስፋ መቁረጥም አይታይባቸውም ። በዚህም የትም አገር ሄደው ስኬታቸውን ያሳያሉ ይላሉ። የኢትዮጵያውያን የመሥራት አቅማቸው ትልቅ እንደሆነም ይናገራሉ። «ትልቅ ነን እያልን መጓዛችን ለልቦናችን ጠቅሞናል። ይህ ችሎታችንንና ጥንካሬያችንን እንድናሳይም እድል ሰጥቶናል። ስለዚህም በቅኝ ግዛት አለመገዛታችንና በአቅማችን መሥራትን የለ መድን መሆኑ በአሜሪካ ችግር እንዳይገጥመን አድርጓል» ይላሉ። የእኔ ደስተኛ ሕይወት መምራት መሰረቱ ያለመገዛት ወኔ፤ በራስ መተ ማመን፣ ጥንካሬን የማሳየት ልምድነው ይላሉ። በጓደኛ የተገኘው ትዳር ከፋ ጠቅላይ ግዛት በሚሰሩበት ጊዜ ነበር በጓደኛቸው ፍቅረኛ አማካኝነት ዓይንና ልባቸውን ያሸነፈችውን ሠናይት ከተማን ያገኟት። ከ45 ዓመት ጋብቻ በኋላ ዛሬ የሦስት ልጆች አባትና የአምስት የልጅ ልጆችን አይተዋል። ይህ በፍቅር የበሰለ መስተጋብራቸው ደግሞ በሥራ መተጋገዛቸውንም አጠንክሮታል። ባለቤታቸው በሶሻል ወርክ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለመጨረሻ ግዜ ከአፄ ኃይለሥላሴ እጅ ዲግሪ የተቀበሉና በመስኩም ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኮሎራዶ ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው በመሆናቸው በሚያስፈልገው ሁሉ ያግዟቸዋል።
ልጆቻቸውም በምህንድስና፣ በሕግና በኢኮኖሚክስ የተመረቁ በመሆናቸው ሁሉም በየዘርፉ ይደግፏቸዋል። መልዕክተ ዶክተር አበራ «ቴክኖሎጂን ተጠቅመን ለማደግ ከተባበርን ብዙ ጊዜ አይፈጅብንም። ለዚህም ነው ሌሎች አገራት የእኛ የሆነውን ቶሎ ተቀብለው ወደ ሥራ የሚያስገቡት። አገር የሚለውጥ ነገር ላይ ሁላችንም መሥራት አለብን። ይህ መሆን ያለበት ግን በመሰራረቅ ሳይሆን በመተጋገዝ ነው።በትክክል አገራችንን ሊያሳድግ የሚችል ተግባር ላይ መሰማራት አለብን» ይላሉ። በተለያዩ ጊዜያት ብዙ ሰዎች «በኮምፒዩተር አማርኛ ማጻፍ የጀመርነው እኛ ነን» እያሉ ብቅ ብለዋል። ከ30 ዓመት በፊት ይህንን ተግባራዊ ያደረገ የለም፤ የፓተንት መብት የትኛው ሰው የለም። «ግኝቶቼን መነፈግ የለብኝም። እኔ ባልኖርና መብታችንን ባላስጠብቅ ኖሮ በፊደላችንና በቋንቋችን ለዘለቄታው መጠቀ ማችን አጠራጣሪ ሊሆን ይችል ነበር። ስለዚህ ሕዝቡ እንዲያውቅ የምፈልገው ለአገሬ እድገት ምን ያህል እንደደክምኩና አሁንም ማድረግ ያለብኝን ሁሉ እንደማግዝ ነው» ብለዋል። በእያንዳንዱ ሥራችን ላይ የማስተማሩ ተግባር ከምሁራን ይጀምራል የሚሉት ዶ/ር አበራ ሞላ በአሁኑ ጊዜ የአማርኛውን ፊደላት መልኮች በትክክል የማናውቅና አንድ የአማርኛ ዓረፍተ ነገር እንግሊዝኛ ሳንቀላቅል የማናወራ ዜጎች የመፈጠሩ መንስኤ ተገቢውን ሥራ ባለመሰራቱ ነውና ልብ ያለው ልብ ይበል መልዕክታቸው ነው። ሰላም!
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው
機票 價格比較了一下發現HOPEGOO很便宜,這網站也很方便容易用,有中英文介面。之後會推薦我的朋友來這邊訂!
假期带小孩岀行,要提前的行程和車票都儘量安排好,發現这里订票很方便,服務也不錯。HOPEGOO這個訂票的系統很贊!期待下次。