ልክ የዛሬ ዓመት ነበር፤ በወርሃ የካቲት የግብጽ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ‹‹አስዋን ኢንተርናሽናል የባህል ፌስቲቫል›› በሚባል ዓለም አቀፍ ፌስቲቫል ያዘጋጀው። በዚህ ዝግጅት ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የልዑካን ቡድን ተጉዞ ነበር። የልዑካን ቡድኑ ያቀረበው ዝግጅትና ያሳየው ባህል ቀልብ የሳበ ነበርም። ከተለያዩ የዓለም አገራት የመጡ ታዳሚዎች በኢትዮጵያ ባህል ላይ ቀልባቸው ማረፉን የልዑካን ቡድኑ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተው ይዞ ወጥቶ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ባህልም ሆነ የባህል ሙዚቃ የብዙዎችን ቀልብ የሳበው ከሌሎች የዓለም አገራት ልዩ መልክ ስላለው እንደነበርም ተጓዦቹ ገልጸዋል። አፍሪካ ውስጥ ካሉ አገራት እንኳን ይለያል፡፡ ብዙ አገራት በባህል፣ በሙዚቃ፣ በድምጽ ይመሳሰላሉ፣ የኢትዮጵያ ግን የተለየ ነው፡፡ የድምጽ ቅላጼው፣ አጨፋፈሩ ሁሉ ልዩ ነው፡፡ የተለየ መሆኑ ደግሞ የብዙዎችን ቀልብ እንዲስብ አድርጎታል፡፡ በዚህም ሽልማትም አግኝተው ተመልሰውበታል። ብዙ አገራት በቅኝ የተያዙ ስለነበሩ የውጭው ባህልና ቋንቋ ተፅዕኖ ያለባቸው ናቸው፡፡ በእነዚያ ውስጥ ደግሞ የኢትዮጵያን ሲያዩት አነጋገሩም ሆነ አለባበሱ ሁሉ የተለየ ሆነባቸው፡፡ አሁንም አንድ ተመሳሳይ ነገር ልጨምር፡፡ ይሄኛው ደግሞ በዚሁ ዓመት መስከረም ወር አካባቢ የሆነ ነው፡ ፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ‹‹ባዶ እግር›› የተሰኘውን ቴአትር ለማሳየት ወደ ግሪክ ዋና ከተማ አቴንስ አቅንቶ ነበር፡፡ እዚያም እንዲሁ በኢትዮጵያ ባህል በርካቶች ተደንቀው ነበር፡፡
በብሔራዊ ቴአትር በተዘጋጀ የአቀባበል መድረክ ላይ ከተጓዦች አንዱ የሆኑት አርቲስት ደበበ እሸቱ ‹‹እናንተስ ምን ተምራችሁ መጣችሁ?›› ተብለው የተጠየቁትን ጥያቄ ፈገግ በሚያሰኝ መልስ ነበር የመለሱት፤ ‹‹እኛ ከተማርነው ይልቅ አስተምረን የመጣነው ይበልጣል›› ነበር ያሉት። ሁለቱን አጋጣሚዎች ያለምክንያት አላነሳኋቸውም። የልዑካን ቡድኑ ባህላቸውን በውጭ አገር በማሳየታቸውና አገራቱም አድንቀውላቸውና ወደውላቸው ስለነበር እንዲህ ዓይነት ነገር ምን ያህል አገርን እንደሚያስተዋውቅ ለመጥቀስ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት የአገርን ባህል የማስተዋወቅ ዘዴ በአገራችን ብዙም የተለመደ አይደለም።
በዚህ ነገር በውጭ አገራት ልንቀና ይገባል። እስኪ ልብ ብላችሁ ተመልከቱ! ከውጭ አገራት የሚመጡ ሰዎች ከሚታሸጉ ጣፋጭ ከረሜላ መሰል ነገሮች ጀምሮ የአገራቸውን ምርቶች ያስተዋውቃሉ፡፡ ከውጭ አገር በመምህርነት የሚመጡ ሰዎች ክፍል ውስጥ ሲገቡ መጀመሪያ ስለአገራቸው ነው የሚናገሩት፡፡ የአገራቸውን ቋንቋም ለማስተዋወቅ ይጥራሉ፡፡ ባህላቸውንም በድምቀት ያከብራሉ፤ ለዚህም ነው በመዲናችን አዲስ አበባ እንኳን በርካታ የውጭ አገራት የባህል ማዕከላት የተፈጠሩት። ሰሞኑን የኢራን የባህል አብዮት 40ኛ ዓመቱን እያከበረ ነው፡፡ ይህን 40ኛ ዓመት የኢራን የባህል አብዮት አስመልክቶም የአገራቸውን የባህልና ኪነ ጥበብ ሥራዎች ለማስተዋወቅ መድረክ አዘጋጅተዋል፡፡ ይህን ያደረጉት ከኢትዮጵያውያን የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር በመሆን ነው፡ ፡ የኢራን የስነ ጽሑፍ ሰዎች እነ ባባ ጣሂር እና ዑመር ካያም በዓለም የስነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ስማቸው የሚጠቀስ ነው፡፡ የአገራችን ገጣሚዎች እነ በረከት በላይነህም የነባባ ጣሂርን ግጥሞች ወደ አማርኛ ተርጉመው ለኢትዮጵያ አንባቢ አድርሰዋል፡፡
እነዚህ ሰዎች እንዲህ ገናና የሆኑት ሥራዎቻቸውን በተለያዩ አገራት ስላስተዋወቁ ነው አይደል? በኢትዮጵያ የኢራን ኤምባሲ የባህል አማካሪ የሆኑት ሀሰን ሂደሪ እንደሚሉት፤ እንዲህ ዓይነት መድረክ ማዘጋጀት ያስፈለገው የኢራንን ባህል፣ ስነ ጽሑፍና ሥልጣኔ ለማስተዋወቅ ነው። በኢትዮጵያና በኢራን መካከል በጣም የተቀራረበ የስነ ጽሑፍና የሥልጣኔ ባህል አለ። ይህ ደግሞ የሚያሳየው የእነርሱን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያንም ባህልና ወግ እያወቁ መምጣታቸውን ነው፡፡ አማካሪ ሀሰን፤ በቋንቋው መካከልም መመሳሰል መኖሩን ይገልጻሉ፡፡
እንደ ሙዝ፣ ዝንጅብል፣ አናናስ፣ ክብሪት… ያሉ የጋራ ቃላትን ከመጠቀም አንስቶ ተመሳሳይ የሆነ የቃላት ድምጸት አለን ይላሉ፡፡ ይህን የባህል አብዮት ሲያከብሩ የኢትዮጵያን ባህሎችና የስነ ጽሑፍ ሥራዎችም እየቀረጹ ነው፡፡ ‹‹የቀረጽናቸውን ቪዲዮዎችና ፎቶዎች ኢራን ስንሄድ እናሳያለን›› ብለዋልም የባህል አማካሪው፡፡ እንዲህ ሆኖ ግን ባህሉ በሚገባ አልተዋወቀም፡፡ በዚህም ይህ ባህልን ያለማስተዋወቅ ችግር በአፍሪካ ጎልቶ እንደሚስተዋል መታዘባቸውንም ተናግረዋል፡፡ የባህል አማካው ሪ ሀሰን ሂደሪ እንደሚሉት፤ እንዲህ ዓይነት የባህልና የሥልጣኔ ልውውጦችን ማድረግ ባህልን ማስተዋወቅ ብቻ አይደለም፤ ራሱን የቻለ የሳይንስ ምርምርም ነው፡፡ የራሳቸውን አገር ኢራንን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ። ይህ የባህል አብዮት ከተጀመረበት 1980ዎቹ ጀምሮ በትምህርት፣ በባህልና በሳይንስ ምርምር ከፍተኛ ለውጥ መጥቷል፡፡ የኢራን የሥልጣኔና የስነ ጽሑፍ ሀብቶች በዓለም እንዲተዋወቁ ሆኗል፡፡ አገራቸው በውጭ የባህል ወረራ ሳትወረርየራሷን ትውፊት ጠብቃ እንድትቆይ መሆኗን የሚገልጹት አማካሪ ሀሰን፤ ለዚህም ነው የባህል አብዮታቸውን በተለያዩ አገራት በየዓመቱ የሚከበረው ብለዋል፡፡ ምናልባት የዚህ ዓመቱ 40ኛ ዓመት ስለሆነ ይመስላል ሰፋ ባለ ዝግጅት ማክበር ያሰቡት፡፡
ለዝግጅቱ የኪነ ጥበብ ሰዎች መምረጣቸው ደግሞ ጥሩ ያደርገዋል፡፡ ምክንያቱም የስነ ጽሑፍና የባህል ሥራዎች ብዙ ጊዜ የሚተዋወቁት በስነ ጽሑፍ ሰዎች ነው፡፡ በተለያዩ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና በዩኒቨርሲቲዎች ሰሞኑን ሲያስተዋውቁ ቆይተዋል፡፡ እነዚህ ቦታዎች ላይ የሚገኙት ወጣቶች ስለሆኑ አገራት እንዴት ባህላቸውን እንደሚያስተዋውቁ ትምህርት ይሆናል፡፡ ባህልን ማስተዋወቅ በወጣቶች በኩል ሲሆን ደግሞ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ እነዚህ ዝግጅቶች ሲደረጉ ፊልሞች ይታያሉ፣ ግጥሞች ይነበባሉ፣ የኢራን የባህል ሙዚቃዎች ይቀርባሉ። የሚቀርቡ የኢራን ሥራዎች በአማርኛ ይተረጎማሉ፡፡
ኢትዮጵያውያን ገጣሚዎች ደግሞ በራሳቸው ቋንቋ ያቀርባሉ ።እንግዲህ እነዚህን እንቅስቃሴዎች ሲያደርጉ መንግስት ተገቢውን ድጋፍ እያደረገላቸው ነው፡፡ አስፈላጊ መሳሪያዎች ይሟሉላቸዋል ማለት ነው፡፡ በኤምባሲው በኩል መንግሥት ተገቢውን ድጋፍ እንዳደረገላቸው ነው አማካሪውም የተናገሩት፡፡ የኢራን የባህል አብዮት የተጀመረው በፈረንጆቹ 1979 ነው፡፡ አጀማመሩም አገራቸውን ከመጤ የባህል ወረራ በመከላከል የራሳቸውን ባህል ማዳበርና ማበልጸግ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ለዚህ ዓላማቸውም መንግስት ተገቢውን ድጋፍ ያደርግላቸዋልና በተለያዩ የዓለም አገራት ባህላቸውን ማስተዋወቅ ችለዋል።
ምን እንማር?
በመግቢያው ላይ የኢትዮጵያ የባህል ልዑካን ቡድን በሄደባቸው አገራት ያገኘውን አድናቆት አይተናል። ያ ማለት የኢትዮጵያ ባህል በብዙ አገራት በተደጋጋሚ ቢተዋወቅ አገሪቱ አኩሪ ባህል እንዳላት ለዓለም ሁሉ ግልጽ ይሆን ነበር። ምክንያቱም በተደጋጋሚ እንደሚባለው ኢትዮጵያ በቅኝ ያልተገዛችና የራሱ ቋንቋና ባህል ያላት አገር ናት፡፡ በዚያው ልክ ባህሉንና ቋንቋውን የማስተዋወቅ ሥራ ተሰርቷል ወይ? ብለን ከጠየቅን አፋችንን ሞልተን የምንመልሰው መልስ አናገኝም፡፡ እውነት በውጭ አገራት ያሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች እንዲህ ያደርጋሉ? ለዚህ ችግር ግን መንግስት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ተጠያቂ ነው፡፡
ከኢራን ተሞክሮ እንዳየነው የመንግሥት ኃይል ብቻ አይደለም፤ ሰዎቹ የማስተዋወቅ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፡፡ እርግጥ ነው መንግሥትም ለአገራችን ባህልና ኪነ ጥበብ የሚያደርገው ድጋፍና ክትትል እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤ ቢሆንም ግን መንግሥትንም ቢሆን የሚያነቃው ፈፃሚው አካል ነው፡፡ እነ ዑመር ካያምና ባባ ጣሂር በስነ ጽሑፉ ዓለም ውስጥ ገናና የሆኑት እንዲህ ስላስተዋወቁላቸው ነው፡፡ የኛዎቹስ የስነ ጽሑፍም ሆነ የሌላው ዘርፍ ሙያተኞች በዓለም ያላቸው ዝና ምን ያህል ይሆን? መልሱን ለአንባቢው ልተወው። የአንዲት ሀገር ምንነት የሚታወቀው በባህሏ ነው፡፡
አገራትን የምንለየው በሚከተሉትና በሚያሳዩት ባህል ስለሆነ፡፡ ለዚህም ነው በፊልሞቻቸው የአገራቸውን መልክዓ ምድር ሳይቀር ይነግራሉ፤ ማንነታቸውንም ያሳዩበታል፡፡ በኢትዮጵያ ይህ እየሆነ ነው ወይ? ብለን ከጠየቅን ‹‹ጽድቁ ቀርቶብሽ በቅጡ በኮነነሽ›› የሚለውን አባባል ያስታውሳል፡፡ ምክንያቱም እንኳን በውጭ አገር ሄዶ ማስተዋወቅ እዚሁ እንኳን አላማረበትም፤ እንዲያውም በውጭ የባህል ወረራ የተበረዘ ነው፡፡ እናም ከእነዚህ አገራት ልምድ በመውሰድ መንፈሳዊ ቅናት ሊያድርብን ይገባል!
አዲስ ዘመን የካቲት 10/2011
ዋለልኝ አየለ