አገራት ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ብልፅግናን ለመቋደስ የአንድነትን ሃይል የህብረትንም የድል ምስጢር ጠንቅቀው በመረዳት በተለይ በንግድና ኢንቨስትመንት እርስ በእርስ መተሳሰርን አማራጭ ማድረግ ከጀመሩ አመታትን አስቆጥረዋል።
ከመገፋፋት ይልቅ መደጋገፍ ወሳኝ መሆኑን በመረዳት ራስ ወዳድ እና ስግብግብነትን በማስወገድ እርስ በእርስ ያላቸውን መስተጋብር ለማጠንከር እንዲሁም በኢኮኖሚ አቅም በእኩል ደረጃ መወዳደርም ሆነ መደራደር የሚያስችላትን አቅም ለማጎልበት የተለያዩ ተግባራት ሲያከናውኑ ቆይተዋል።
በኢኮኖሚ ልእልና ስማቸው አንቱ የሚባልላቸውን ጨምሮ በርካታ አገራት በዚሁ መንፈስ እየተመሩ መጪውን ለማሳመር በሚተጉበት በዚህ ወቅት ታዲያ ድንገተኛው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የአመታት ልፋታቸውን ከንቱ አድርጎታል።
አለማችን ዘር፣ቀለም፣ቋንቋ ፣የስልጣን ከፍታ፣የሀብት ደረጃ፣አዋቂና ታዋቂ፣መሪና ተመሪን ሳይለይ በሚቀፅፈው የኮቪድ 19 ቫይረስ ጭንቅ ውስጥ ትገኛለች። ወረርሽኝ በተመለከተም እያደር አስደንጋጭ፣ አሳዛኝና ተስፋ አስቆራጭ እንጂ ይህ ነው የሚባል በጎ ነገር ሳይሰማ አመት ተቆጥሯል።
አገራትም ድንገት በተከሰተባቸው የኮሮና ቫይረስ የጥፋት ማዕበል እየተናጡ ናቸው። ዜጎችም ከመጣው ጥፋት ለማምለጥ ሲጨነቁ ውለው ማደራቸውን ቀጥለዋል። መላውን የሰው ልጅ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ውስጥ የከተተው ወረርሽኝም በእስካሁን ከሶስት ሚሊየን አምስት መቶ ሺ በላይ ዜጎችን ህይወት ነጥቋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ነፍስ ብቻም አይደለም ኪስም ከመንጠቅ ያስቆመው አልተገኘም። የአለም ኢኮኖሚ ከሁሉ በላይ በህዝብ እንቅስቃሴ ላይ መሰረቱን ያደረገ እንደመሆኑ ወረርሽኙ አለም አቀፉን ኢኮኖሚ ክፉኛ በማቃወስና በማሽመድመድ ሚሊየኖች ስራ አልባ አድርጓል።
ወረርሽኙ የዓለም የንግድ ትስስር በመበጣጠስ ግዙፍ ኩባንያዎችን አንገዳግዷል። መንግስታትን ብርክ አስይዛል። ነዳጅ በነፃ በሚባል መልኩ እንዲሸጥ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአክስዮን ገበያ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ እንዲያሽቆለቁል፣ ግዙፍ አየር መንገዶች በረራ እንዲያቋርጡና አውሮፕላኖቻቸውም ከሰማይ ወደ ምድር እንዲወርዱ ምክንያት ሆናል።
ወረርሽኙ በአለምአቀፍ ደረጃ የሰዎችን ጤና ከማቃወስና ለህልፈት ከመዳረግ ባለፈ የአገራት ኢኮኖሚ እንዲሽመደመድ፣ ደረጃቸው እንዲያሽቆለቁልና እድገታቸው አደጋ ላይ እንዲወድቅ ከማድረጉ ባሻገር የኢንቨስትመንትና የንግድ ትስስራቸውን በጣጥሶታል።
የወረርሽኙ መንሰራፋት ታይቶ በማይታወቅ መጠን በአራቱም አቅጣጫ መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚው ድቀት በመከሰት በርካታ ዘርፎች ላይ ያስከተለው ሁለንተናዊ ጉዳት እንደተጠበቀ ሆኖ በተለይም አለምአቀፉን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት (foreign direct investment / FDI/) ፍሰት ከሚጠበቀው በታች ዝቅ አድርጎታል።
የተባበሩት መንግስታት የንግድና ልማት ጉባኤ (ዩኒታድ) ባሳለፍነው አመት ዓለም አቀፍ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት 42 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን አስታውቋል ። ‹‹አለም አቀፍ አስተዋፆውም እኤአ በ2019 ከነበረበት አንድ ነጥብ አምስት ትሪሊየን ወደ 859 ቢሊየን አዘቅዝቋል››ብሏል። ዝቅታውም 30 በመቶ በላይ ሆኖ ተመዝግባል። ውድቀቱም እኤአ በ2009 ከተከሰተው የፋይናንስ ቀውስ ቀጥሎ ታይቶ የማይታወቅ ነው አስብሎታል። የኢንቨስመንቱ ውድቀቱም በተለይም ባደጉት አገራት ላይ ይበልጥ ታይቷል።
ለውጭ የቀጥታ ኢንቨስትመንት መውደቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ ያሳደረው ተፅዕኖ ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል ተብሏል።የእንቅስቃሴዎች መገደብ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን እድገት አዝጋሚ እንዳደረውም ተመላክታል። ቀውሱም በመላ አለም በርካታ ኢንቨስተሮችና ኩባንያዎች የኢንቨስትመንት እቅዳቸውን ለመተግበር እንዲያመነቱ አሊያም ለሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፉ አስገድዷቸዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እንደየዘርፉ የሚለያይና ሁሉም ኢንዱስትሪዎች የቀውሱ ሰለባ መሆናቸው እርግጥ ቢሆንም ከሁሉ በላይ ግን የአቭየሽን፣ የሆስፒታሊቲ ቱሪዝም፣ የመዝናኛው ኢንዱስትሪዎች ላይ ይበልጥ ጡንቻውን አሳርፏል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ያደጉት አገራት ላይ ቢበረታም አፍሪካንም አልማራትም ። በተለይ በአንዳንድ አገራት ከፍተኛ ሆኖ ተስተውላል። ለአብነትም የግብፅ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስመንትም እአአ በ2019 ከነበረው የ8 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በ 2020 ወደ 5 ነጥብ 5 በመቶ አሽቆልቁሏል። ይሕ 39 በመቶ ቅናሽም በታሪክ ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግባል። ይሑንና አገሪቱ አፍሪካ ምድር ከፍተኛ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ቀዳሚ እንጂ ተከታይ እንድትሆን የማድረግ አቅም አልነበረውም።
የምስራቅ አፍሪካዊታ አገር ኬንያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ባለ ሁለት አሃዝ ውድቀት አጋጥሟታል። የአገሪቱ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ በኮሮና ቫይረስ ጦስ እእአ በ2019 ከነበረው ጋር ሲነፃፀር በ2020 የ18 በመቶ ቅናሽ አሳይቷልም ብሏል።
በኮቪድ-19 ምክንያት የተስተጓጎለውን የዓለም አቀፍ ንግድና ዓለም ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት ላይ ተፅእኖ ማሳደሩ አልቀረም። ተፅእኖው ግን ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ግንባር ቀደም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መዳረሻ እንዳትሆን የማድረግ አቅም አልነበረውም።
ወረርሽኝ ተፅእኖ እንዳለ ቢሆንም ከሌሎች አገራት ጋር ሲነፃፀር ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ ውጤታማ ሆኖ ታይታለች። በአመቱም ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊየን ዶላር ገቢን አግኝታለች። መረጃዎች በዘንድሮው አመትም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቱ ፍሰት በመልካም ቁመና ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።፡
የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፣ በ2013 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከሁለት ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን አሳውቀዋል። ኮሚሽኑ ከሌሎች የመንግስት ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን የንግድ ከባቢን በማሻሻል ረገድ ባለፉት ሁለት ዓመታት በትኩረት ሲሰራበት መቆየቱን አስታውሰዋል።ለአብነትም የአንድ ማዕከል አገልግሎት በኦንላይ እንዲሆን መደረጉን ነው ያብራሩት።
እንደ እርሳቸው ገለፃም፣ ከአሰራር ማሻሻያዎች ጋር በተያያዘም የኢንቨስትመንት አዋጅን መሰረት አድርጎ ደንብ ወጥቷል። ደንቡን መነሻ በማድረግ ባለሃብቶች የሚያቀርቧቸውን አቤቱታዎች ምላሽ የሚሰጥ ጉባኤ ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል።
የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ ዓለም በኮቪድ 19 እየተናወጠች በምትገኝበት በዚህ ወቅት በተለያዩ አገሮች በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንጽላ ጽህፈት ቤቶች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት አቅም የማስተዋወቅ ስራ ተሰርቷል። ይህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ እድል ፈጥራል።
ወደ ኢትዮጵያ መሳብ የተቻለው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መካከል 58 በመቶ የሚሆነው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ፣ አምስት በመቶ በግብርና እንዲሁም 37 በመቶ ደግሞ በአገልግሎት ዘርፍ መሆኑ ተመላክቷል። በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት በዘጠኙ ወራት 70 በመቶ ክንውን ማድረስ ተችሏል። ፍላጎት አሳይተው ከተመለመሉ የውጭ ባለሀብቶች ውስጥ ለ132 ባለሃብቶች አዲስ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል።
የተለያዩ የምጣኔ ሃብት ምሁራንም አለምአቀፉን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት (foreign direct investment /FDI/) ፍሰት ከሚጠበቀው በታች ዝቅ እያለ በቀጠለበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ይሕን ያህል መጠን ማሳካት መቻሏን አድንቀዋል።
ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት፣ አንድን አገር ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ተፈላጊና ሳቢ የሚያደርጋት የዘረጋችው አገራዊ ምቹ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ነው። ሆኖም ግን ምቹ የህግ እና የፖሊሲ ማዕቀፍ መኖሩ ብቻ ፍሰቱን እንዲጨምር ላያደርግ ይችላል። ለምን ቢባል በተግባር የወጡት ፖሊሲዎች እና ህጎች በአስፈጻሚው አካል ዘንድ የመተግበራቸው ሁኔታ ስለሚያጠያይቅ ጭምር ነው።
እነዚህ አስተዳደራዊ ስነስርዓቶች ነጻ የኢንቨስትመንት ፈቃድ በሰጡ አገራት ጭምር ከፍተኛ ስጋት ያጭራሉ። በብዙ ሃገራትም በርካታ ኢንቨስተሮች የሚያቀርቡት ስሞታ እና እሮሮ በተለይም አሰልቺ ከሆኑ አሰራሮች መኖር ጋር ይያያዛል።
ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ጥሩ የህዝብ ግንኙነት ወይም የገበያ ጥናት ባለሙያዎች መኖራቸው መልካም ተግባር ነው። በተለይም ቢዝነስ ተኮር የህዝብ ዲፕሎማሲ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ተግባር ነው። ታዲያ በዚህ የማስተዋዋቅ ተግባር የተመሰጡ የውጭ ኢንቨስተሮች የተባለችውን አገር በመሄድ ሁኔታውን ለመመልከት ከመቼው ጊዜ ልባቸው ይነሳል።
በአሁን ወቅት ግን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚሰሩ ስራዎች በሙሉ መልካቸውን ቀይረዋል። በጉዳይ ላይ ሰፊ ትንታኔ በመስራትን አስተያየቶችን በማሰጠት ላይ የሚገኙ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንና ምሁራንም፣ አገራት የኢንቨስትመን ፍሰቱን ለማጎልበት የሚያደርጉት ድጋፍ የሚበረታታና ይበልጥ ሊጠናከር የሚገባው መሆኑን ከማስገንዘብ ባሻገር የወረርሽኙን ሁለንተናዊ ተፅእኖ ለመቋቋም በቀጣይ ሊራመዱበት የሚገባው መንገድ ጠቁመዋል።
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አገራት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የሚያደርጉትን ፉክክሩ ይበልጥ እያጦዘው በመምጣቱ የተቀናጀ ጠንካራ ስራ መስራትና ተወዳዳሪነትን ማጠናከር ግድ እንደሚል፣ ኢንቨስትመንት በመሳብ ረገድ አሰራሮች በቀደመው መልኩ ይቀጥላሉ ብሎ መገመት ትልቅ ስህተት ስለመሆኑም አፅእኖት ሰጥተውታል።
‹‹አዳዲስ የፕሮሞሽን ሁኔታዎች እንደሚፈጠሩ ተግባራቸውም በቴክኖሎጂ የተደገፉ መሆኑንና በርካታ አገራትም ይሕን አቅጣጫ ወደ መጠቀም ፊታቸው በማዞር የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ መጠመዳቸው መረዳት ይገባል›› ተብላል።
ኢትዮጵያም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት በማሳደግ እና ብዘሀነት በማስፋት ላይ ትኩረት ሰጥታለች። የኢንቨስትመንት ኮሚሽንም በተለይ የኢንቨስትመንት አቅምና አማራጮቻቸውን በዌብ ሳይቶች ላይ በተሻለ ሁኔታ የማሳየት፣ ወደ ኢንቨስትመንቱ የሚመጡ ተዋናዮችም ከምዝገባ ጀምሮ የኢንቨስትመንት ፈቃድ እስከመስጠት ድረስ በቀጥታ የመረጃ መረብ የኦን ላይን ግልጋሎቶችን የማቅረብ ተግባራትን በትኩረት መከወን ላይ ይገኛል።
የተለያዩ የምጣኔ ሃብት ምሁራንም፣ አገራት የወረርሽኙን ስርጭት ለመከላከል ብሎም ቫይረሱን ሁለንተናዊ ጉዳት ለመቀነስ የወሰናቸው የክልከላ እርምጃዎች ቀስ በቀስ እያኑሱ በሚጓዙበት ወቅት ለውጦች መታየት እንደሚጀምሩና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እኤአ ከ2022 ማግስት ቀስ በቀስ እያንሰራሩ፣ ኩባንያዎችም ወደ መልካም ተክለ ቁመና እንደሚመለሱ ተማምነዋል።
አንዳንዶቹ በአንፃሩ የወረርሽኙን ስርጭት እንዴት በማያዳግም መልኩ መግታት ይቻላል የሚለው እስካልታወቀና የዚህ ፈተና መልስ የሚርቅ ከሆነም ፍሰቱን ለማጎልበት አስቸጋሪ መሆኑንና አስተዋፆውም ዳግም ወደ ቀደመ ተክለ ቁመናው ለመመለስም ምናልባት አመታት ሳያስፈልጉት እንደማይቀር ገምተዋል።
በድንገተኛው ወረርሽኝ ምክንያትም አለም አቀፉ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለቀጣዮቹ ሁለት አመታት ሸክሙ እንደማይቀልለት የሚስማሙበት የተባበሩት መንግስታት የንግድና ልማት ጉባኤ የኢንቨስትመንትና የኢንተርፕራይዝ ዳይሬክተር ጀምስ ሃን፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቱ እጣ ፈንታ የሚወሰነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የእድሜ ቆይታ እንዲሁም መንግስታት በሚወስዱት ውጤታማ ስትራቴጂዎች የፖሊሲ ትግበራዎች ላይ መሆኑን ታሳቢ ማድረግ እንዳትዘነጉ›› ብለዋል።
ጉዳዩን በተለይ መነፅር የሚመለከቱትን የተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃኑና የምጣኔ ሃብት ምሁራኑ በአንፃሩ፣ አፍሪካውያን ኢንቨስትመንትን ለማጎልበት እርስ በእርስ በንግድና ኢንቨስትመንት መተሳሰር ቢችሉ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም መፍጠር እንደሚችሉ ሳይጠቁሙ አላለፉም።
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አገራት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያደርጉትን ፉክክሩ አጡዞታል፤
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2013