
ገላን:- በአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባውና በ23 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ሜልባ ማተሚያ ቤት ለአፍሪካ የህትመት ቴክኖሎጂ ፈር ቀዳጅ ይሆናል ሲሉ የሜልባ ፕሪንቲንግ፣ ፐብሊሺንግ እና ፓኬጂንግ አክሲዮን ማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዳባ ደበሌ ገለጹ፡፡
የቦርድ ሰብሳቢው አቶ ዳባ ትናንት በምረቃው ሥነሥርዓት ላይ እንደተናገሩት፤ በገላን ከተማ የተገነባው የመጀመሪያው ዘመናዊ ዲጂታል የህትመት ቴክኖሎጂ ሲሆን፤ ለአፍሪካ ፈር ቀዳጅ ለምስራቅ አፍሪካም ብቸኛው ተቋም ነው ብለዋል፡፡
ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ እውን የሆነው የህትመት ተቋሙ በመደበኛ የህትመት ስራው መፃህፍት፣ መፅሄቶች፣ ጋዜጦችና ሌሎችም የህትመት ውጤቶችን በፍጥነት እንደሚያትም ገልጸዋል፡፡ በቀን 138 ሺህ በሰአት ደግሞ 65 ሺህ ወረቀቶችን ማተም የሚችል አቅም እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በመንግስትና በባለሀብቶች እንዲሁም በባለድርሻዎች ሽርክና በአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ወጪ መገንባቱን ገልጸዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው፤ ኩባንያው መቋቋሙ በትምህርት ዘርፉ ለህትመት የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪና እንግልት የሚያስቀር በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከሚወጣው ወጪ በተጨማሪ ለህትመት ጨረታ ከሰባት እስከ ስምንት ወራት ስለሚወስድ ስራዎች እየተጓተቱ እንደነበር አስታውሰው፤ ሜልባ ፕሪንቲንግና ፐብሊሺንግ እና ፓኬጂንግ ስራ መጀመሩ ከምንም በላይ የትምህርት ዘርፉን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል፡፡
የኩባንያው ስራ መጀመር በወሳኝ ጊዜ መሆኑን በመጠቆም፤ በተለይም በ2014 ዓ.ም ለሚጀመረው አዲስ ሥርዓተ ትምህርት የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ በዓመት ከ40 እስከ 50 ሚሊዮን መፅሀፍትን ማተም የሚችለው ኩባንያ የዘርፉን ችግር ከመፍታት አንፃር ያለው አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም ብለዋል፡፡
የግብዓት ችግር እንዳያጋጥም እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በቅርቡም በምእራብ ኦሮሚያ ትልቅ የወረቀት ፋብሪካ ስለሚመረቅ ያለውን ችግር በማቅለል ረገድ ተስፋ እንዳለ ገልጸዋል፡፡
ኩባንያው ለ900 ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ፈጥሯል፡፡ ሜልባ ማለት ከአምስቱ የገዳ አባላት አንዱ ሲሆን፤ አሁን ያለው የገዳ አባልም የሜልባ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለትምህርት መጽሀፍት ብቻ በዓመት እስከ ሁለት ቢልዮን ብር ወጪ እንደምታደርግ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ሳምራዊት ግርማ
አዲስ ዘመን ግንቦት 24 ቀን 2013 ዓ.ም