ክፍል 1
አሜሪካ መንግስት አፍሪካን ብሎም ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ብርቱ ትስስር ኖራት የአብሮ መሥራትና ከፍተኛ የመግባባት ሁኔታ ስለሚታይ አሜሪካንን እጅግ ሥጋት ውስጥ አስገብቷታል። ኢትዮጵያ ለወደፊት በዓለም ላይ ታዋቂ ሆና የተፅዕኖ ማሳደር አዝማሚያ ስለአላት አፍሪካ አገራትንና እስያ አገራትን አስተባብራ ትጋፋኛለች ለምዕራብያውያን አትታዘዝም የሚል ስጋት ተደቅኖባታል። ኢትዮጵያ በሁሉ ነገር ከተስተካከለች አትቻልም የሚል የሃሳብ ውጥረት በአሜሪካና ምዕራብውያን ዘንድ ጭንቀትን አሣድሯል።
በሌላም በኩል አሜሪካ በዕርዳታ ስም መሰሎቿ ምዕራባውያን ኢትዮጵያ ውስጥ እንደልብ ገብተው ሁሉን አካባቢ በቁጥጥራቸው ስር ለማድረግ ፍላጉት አሣይታለች አልሆነላትም እንጂ። በዚህም የተነሣ በአሁኑ ጊዜ አሜሪካ ሌሎች መሰል አጋሮቿን አስከትላና አስተባብራ በኢትዮጵያ ላይ በማንኛውም ሁኔታ እስካሁን ያልተለመደና ያልተጠቀመችውን የተንኮል መረብ ሥራዋን ሁሉ ዘርግታ ኢትዮጵያን ወደ ኋላ መጎተትና ማስቀረት ጫና እያደረገችባት ነው። የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ እየፈጠረ ያለው ጫና በመንግሥት ላይ ብቻ ሣይሆን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ መሆኑን ህዝቡ መገንዘብ ይኖርበታል። ለጉዳዩም ትኩረት ሰጥቶ መከላከልና በጽናት አንድ ላይ መቆም አለበት።
ግብፅ የውሀ ዕጥረት ሥጋት ሣይሆን የኢትዮጵያ የለም አፈር መቀነስ እንደአንገበገባት ሁሉ አሜሪካም የሌላ ችግር ሣይሆን ኢትዮጵያ ከቻይናና ሌሎች የእስያ አገራት ጋር የቅርብ ግንኙነት ስለአደረገች የስጋትና ፍርሃት ውጤት ነው ኢትዮጵያን ወጥራ የያዘችው።
አሜሪካ ወያኔን ከሞት ለማስነሣት መስሏት ትጥራለች እንጂ ፣ ወያኔ በቁሙም ሞቷል፤ ሞቶም ቀርቷል አይመለስም። በአሁኑ ጊዜ ተረኛ የዘመነ ጉማጉሞች የሆነ የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ወጥመድ አጥምደው የሚያሴሩት መጥፎ ተንኮል፣ ሠይጣን ያልደረሰበትን ጥልቅ ተንኮል ነው :: ይህም ዕብሪታቸውንና ትዕብታቸውን የሚያሣይ ነው:: ግን በአምላክ የሚፈታና የሚሻር ቢሆንም ለጊዜው ኢትዮጵያ እየተጎዳችበት ነው ያለው። ኢትዮጵያን ምን ሊያደርጓት እንደፈለጉ ለኢትዮጵያውያንም ግልጽ አልሆነም።
በተለይ ኢትዮጵያ የ2020 ዓ.ም የአሜሪካ ምርጫ በትውልደ ኢትዮጵያውያን በጎ ሚና መጫወት አሜሪካንን ከዕብደት አመራር ያዳነ ሆነው ሣሉ ምንም እንኳን የዕብደት አመራሩ የቀጠለ ቢሆንም ለጊዜው አሜሪካንን ያረካ ነበር። አሜሪካ ግን በሰበብ አስባቡ እየተደገፈች ኢትዮጵያን በመቃወም ከብዙ ችግር ላይ ለማድረስ ኢትዮጵያን በመዳፈር ክብር መንሣት ክብር ነክ የሆኑትን አባባል እየሠነዘረች ሉዓላዊነቷን ለመንጠቅ እየጣረች ነው ያለችው::
እነዚህ ወቅት ወይም ዘመን የአቅበጠበጣቸው የአሜሪካን አስተዳደር የመጨረሻ ዘመን የመጀመሪያ ረድፍ ላይ ሆነው ጠፊ ስለሆኑ የሚያደርጉት ክፉና ሴራ የተጎነጎነበት ሥራ ሁሉ አይታወቃቸውም። እኛንም አያስደንቅም። በተለይ አሜሪካ ለቀረባትና ለአከበራት አትሆንም። ለደፈራት ለናቃትና ለአዋረዳት በጎ ናት፤ ስለዚህ እኛም መጋፈጥና መጋተር አለብን ወይ ፍንክች ለአሜሪካ ከእንግዲህ ጠንከርና ኮስተር እንጂ መለሳለስ ወግዝ እና ዕርግማን ይሁንብን።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከባድ ፈተና ላይ ብትሆንም፤ ፈተናውን ታልፋለች። ሆኖም ኢትዮጵያ ከእንግዲህ የምእራባውያንን ቡራኬ ወይም ይቅር ይበልንን አትፈልግም::
አሜሪካም ሆነ ሌሎች ደፋር ሃገራት ከደቦ ወረራ፣ እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ ያንሱ ፤ ከዚህ ተንኮላቸውና የፕሮፓጋንዳ ማዕበላቸው መገደብ አለባቸው።እንዲሁም ለራሳቸው ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ኢትዮጵያ አጥብቃ ትመክራቸዋለች፣ ታስጠነቅቃቸዋለችም። የሚከተለውንና የሚመጣውን ጉድ አልተገነዘቡትም ወይም አላወቁትምና!!!
ክፍል 2
በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሰው ልጅ በአዕምሮ በስሎ በሃሳብና በጥበብ በመጠቀበት ጊዜ ፣ ከዚህም በላይ ነኝ የሚትለው አሜሪካ ወደ ታች ወርዳ የመታየት ዓለምን ሣያስገርም አልቀርም። ይህን አሜሪካ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ የሚታደርገው ጫናና ቅጣት አስተዋይ ሁሉ በጥሞና ከተመለከተው ከዛሬ 70 ዓመት በፊት ጃፓን ውስጥ በሆሮሽማና ናጋሳኪ ላይ ከጣለችው የአቶሚክ ቦምብ የማያንስ ድርጊት ነው::
ምክንያቱም ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ጥሩ ዴሞክራሲን በተከተለና ባቀፈ የዕድገት ጉዞ ላይ ባለችበት ወቅት ከአገር አዋኪዎች እና ጨለምተኞች የባሰ አሜሪካ ኢትዮጵያን ጥላሸት ለመቀባት እና በጭለማ ለመጋረድ መሞከሯ ነው:: አሜሪካ ኢትዮጵያን አንገት ለማስደፋት ጥረት ብታደርግም አይሆንላትም የጥናት ታርጌቷን ስታለች። ወጥመዷም ተሰብሯል።
አሜሪካ ከእንግዲህ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ዲፕሎማሲ የእኩልነትና የመግባባት ብቻ ነው። ከተፈለገ የማዘዝና የመታዘዝ ዲፕሎማሲ ተቋርጧል። ሞት ራሱ ይሙት ኢትዮጵያ ግን አትሞትም ፤ አትገልምም። ለክፉዎች ጊዜው መሽቶ እየመጣ መሆኑ እየቀጠለ ነው። የአሜሪካ መሪዎች ፍሬን እንደተበጠሰበት ሲኖ ትራክ መኪና ሆነዋል:: ሁሉም ሀገር ሆነ ማንኛውም ሰው መስሎት እንጂ ክፉዎች እየጠወለጉና እየመከኑ ይሄዳሉ። ኢትዮጵያ ግን አትጠወልግም፤ እየፈካች ወደፊት ትገሰግሳለች፣ ትበለጽጋለችም።
አሜሪካ ዞር ብላ ራሷን ብትመለከት በዚህ ዘመን ራሷ በጨለማ ተከባ እንዳለች ትወቅ፣ የዓለም አሸባሪዎች የተባሉት ሁሉ አሜሪካንን ከበው እያመሷት ነው ያሉት። የራሷ ሲያርባት የሌላውን ታማስላለች ይባላል። በአሸባሪነት የዓለም ንጉሠ ነገሥት የሆነው አልቃይዳና እንደራሴ ዘርፎቹ ታሊቫን፣ አልታድ ፣ ኢዝቦላ፣ አልሸባብ፣ አይ ኤስ ኤስ ፣ ሐማስ ቦኮሀራ እና ሌሎችም አሜሪካንን በኢላማ ውስጥ አስገብተው በክፉ ስጋት ወጥረው እያመሷት ከምድረ ገጽም ለማጥፋት በሚቃጡት ወቅት አሜሪካ ሌሎች ነባር፣ ወዳጆቿን ማጣት የለባትም ነበር። ስለዚህ ኢትዮጵያን ከማስቀየም መቆጠብ የተሻለ ይሆናል። የምስራቅ አፍሪካ ዘብ ጠባቂዋም ስለሆነች። የአሜሪካ ሐጢአትና ፍዳ በምርጫ እኤአ 2020 እና በኮሮና ፍንጩ ተጀመረ እንጂ አልተጋመሰም።
በሌላም በኩል ዓለምን በአሸባሪነት ወጥረው ከያዙት አሸባሪዎች ያልተናነሰ በተፅዕኖና የጉልበተኝነት ሥራ በዓለም ሀገራት ላይ አሁን በኢትዮጵያ ላይ እንደምታደርገው ሁሉ አሜሪካም እያከናወነች ነው ያለችው። አሜሪካ የጉዞ መንገዷን ማስተካከል ይኖርባታል። ጨርሶ ደብዛዋ እንዳይጠፋት።
ኧረ ለመሆኑ አሜሪካ እሷ በምትከተለው ዴሞክራሲ ኢትዮጵያም በተሻለ ሁኔታ ዴሞክራሲን ለመከተል ደህና በምትመራበት ወቅት ለምንድ ነው? ይህን ሁሉ ዓይን ያወጣ ሤራና ጫና ያበዛችው?!! ጉዳዩ ከላይ በክፍል አንድ የተገለጸው ለምን ከቻይና ጋር ተወዳጀች ነው። የሆነ ሆኖ ከምን ምን ይጠበቃል ይባልስ የለም ? አሜሪካንን ታላቅና ገናና ኃያልም ያሰኛት፣ ስልጣኔና የስራ ዕድገቷ ሣይሆን በዓለም ላይ በሚታደርገው ማጭበርበር ክፉ ጫና ሸፍጥ ደባና ተንኮል ስራዋ ነው:: አሜሪካ የትናንት ልጅ ናት፤ 529 ዓመታት ዕድሜ ያላት ፣ ግን በተንኮል ስራዋ መጥቃ ወደፊት ሄዳለች ፤ ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ቅመአያት፤ እንኳን ሣትሆን ዘመን ያስቆጠረ ከ3000 ዘመናት በላይ መሠረት ያላት አገር ናት። ከኋላ የመጣ ዓይን አወጣ ነው ድርጊቱ።
አሜሪካ ቀውስና አዙሪት ተጸናውቷታል፤ ገና ክፉ የራስ ምታትም ይጠብቃታል። አልታወቀንም እንጂ አሜሪካ በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ በኢትዮጵያ ላይ ጦር ሰብቃለች ግን እሷ በሚዳሰስ መሣሪያ ብትወጋንም እኛ በማይዳሰስ ጦር እንመልሳታለን። ምስጢሩም በተግባር የጦርነት ጊዜ ይገለጣል። በድብቅ የቆየው የአሜሪካ ምኞት ኢትዮጵያ የአሜሪካ ጥገኛ ሆኖ ዘለዓለም እንድትኖር ፍላጎቷን ማሣየቷም አሁን ተገለጠ። በማንኛውም አቅጣጫ ኢትዮጵያ ራሷን ችላ እንዳትኖር የማገድ ያህልም ነው እያሣየች ያለችው::
የዓለም ባንክ ወይም አሜሪካ ሣትሆን ተፈጥሮ የቸራት፤ አንጡራ ሐብቷ በሆነው በዓባይ ውሀ እንዳትጠቀም በገርሻ ድርሻ እንጂ ንብረቱ ላልሆነ ቀጥታ ለማይመለከተው ሀገር መወገኗ የዓለም አሣፋሪ ድርጊት መሆኑን ምነው በተረዳች። ለአሜሪካ ዕውነትና ታሪክ ወደፊት ይገልጽላታል። አሜሪካ ስለ ዓባይ ታሪክስ ምን ታውቃለች?! ዓባይ መፍሰስ ሲጀምር አሜሪካ ምድሯ አልተገኘም ፤ አልታሰበምም።
አሜሪካ ባትረዳትም ድጋፍ ፈላጊዋ ሀገር ራሷ ሁሌ መሰላል ላይ ወጥታ ለዓለም ከመለፈፍ አልተቆጠበችም፣ አልሆነላትም እንጂ ፣ ጊዜ ተገለባባጭ ወይም ተለዋዋጭ ነው:: በሁሉ የምትኩራራውን አሜሪካ ኢትዮጵያ ዳብራ አሜሪካንን በሐብት ምጣኔና በሁሉም ታስተዳድራት ይሆናል፤ ይህን ፈጣሪ አምላክ ብቻ ያውቀዋል። ለሰው ግን ተረት ይመስላል።
አሜሪካ አልገባትም ወይም አልመሰላትም እንጂ ኢትዮጵያን ያለአግባብ የነካት ሁሉ ምን እንደደረሰባቸው ከታሪክና ካለፉት ሁኔታዎች ማወቅ ነበራባት። ሀገራትን ስም መጥራት አስፈላጊ ባይሆንም ፈራርሰው መንግሥት አልባ የሆኑት ሀገራት ሁሉ ኢትዮጵያን የተተናኮሏት ናቸው።
አሜሪካም ኢትዮጵያን መነካካት ከጀመረች ወዲህ በእሷም የደረሰውን እስቲ ታጢነው የዴሞክራሲ አካሄድና አመራር በ2020 የተበላሸባት መሆኑ፤ በማንኛውም ያልበለፀጉ ትናንሽ የዓለም ሀገራት የተከላከሉትን ያህል እንኳን የዘመኑን ወረርሽኝ በሽታ ያልተከላከለች አቅመቢስ ሀገር ሆና የመታየቷና ብዙ ህዝቦቿን የማስጨረሷ ፤ በጦር ኃይልም አሜሪካንን ማንኛውም ደካማ ወይም ዝቅተኛ የተባለ አገር ብትገጥማት አሜሪካንን ድል እንደሚያደርጓት ምልክቶች ሁሉ የመታየቱ::
አሁንም ትንቢት ነው፡- አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ በምታውጠነጥነው ሤራ ዘመናትና ዓመታትን ሣያስቆጥር በአጭር ጊዜ ውስጥ ምን እንደሚደርስባት ተመራማሪዎች እና አዋቂዎች ከአሁኑ ይረዱ፤ በሀገሯ ላይ እስካሁን ያልታየ ብልሹ ሁኔታዎች እንደሚጐበኛት፤ አሜሪካ በሥልጣኔና በሐብት ምጣኔ የዓለም ቁንጮ ነኝ ብትልም በአንዳንድ ብልሹ መሪዎቿ ተዋርዳ የዓለም ዝቃጭ ላይ መሆኗን ትረዳ፤ አሜሪካ ካሁን በኋላ ከኃያልነቷ ተነስታ ጡረታ መውጣት ይኖርባታል። ማንኛውም ሰውም ሆነ መገልገያ መሣሪያ የመጨረሻ ጊዜው ላይ ሲደርስ መገለያው ለዕቃ ጋርቬጅ ውስጥ ማስገባት ለሰው ዕረፍት ወይም ጡረታ ነው።
አሜሪካም በማንኛውም ዕድገት የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሻለሁ ብላ የተኩራራች ሀገር ስለሆነች ዕውቀት ዝቶባት ወፈፌ ሆናለች። ከዚህ በኋላ በመጃጀት በዓለም ላይ ጥፋትን ከመሥራት በስተቀር በጎ ነገር ስለማታበረክት ገለል ማለቷ ይበጃታል። ቢሆን! ኖሮማ አሜሪካ በነገርና ደባ ሥራ ባትሣከር በዕድሜዋ ትንሽ ለጋ ሀገር ናት መሬቷም የተገኘው ከ1492 ዓ.ም ወዲህ ነው። ከቅኝ ተገዥነቷም በነፃነት የኖረችው ለ241 ዘመናት ያህል ነው። ስለዚህ የመልካም ሥራ ዘመኗ ገና አላለቀባትም ነበር።
ዳሩ ከዓለም ሀገራት ሁሉ አንቀዠቀዣት፣ አወራጫት፣ የምትሠራው ተንኮልና ነገር መብላት አስረጃት። አዋቂዎች በጥናት እንደሚሉት ከሆነ በሰው ልጅም ዘንድ የተንኮል ሥራ የሚያበዛ ሁሉ በጭንቀት ስለሚጠመዱ ደማቸው ተመጦ ለእርጅናና ለጉዳት ቶሎ ይዳረጋሉ። (ብዙ የማሰላሰልና የመቀባዠር) ሥራ ስለሚያበዙ። እስቲ በተጨባጭ ማስረጃ እናስተውል ፣ ፖለቲከኞች የሆነ ሁሉ ደመ ቁጡና ችኩል ከመሆናቸውም ፣ሽፍጥ ያበዛሉ ፣ ነገርን ማወላከፍ ይወዳሉ፣ እርስ በርስ ንትርክን ያበዛሉ። በዚህ ምክንያት አዕምሮአቸው በጭንቀት ስለማያርፍ የሰውነት ጉዳት የአእምሮ መሳት ድረስ ከመድረሳቸውም ቶሎ ይገጅፋሉ ያረጃሉም። ጥቂቶቹ ደግሞ ደባ እና የውሸት ሥራ ስለሚከተሉና ነገር ማውጠንጠን ስለሚያበዙ ፈጥነው ይወድቃሉ። አሜሪካንም ወደፊት የሚጠብቃት ይሄው ነው።
አሜሪካ ኢትዮጵያን ከማወክ ፈቀቀ ትበል፤ ውርደት ሳይደርስባት ቶሎ ራሷን በራሷ መክራ ትመለስ። ያለበለዚያም ወዳጅ ሀገራ ሰሜን ኮሪያ መክራት ወደ በጎ ትመልሣት፣ ህግ ያልገዛውን ነፃነት ኃይል ይገዘዋልና!
በሌላም በኩል ሽብር ነዥ እና የመርዝ መዓት የሚረጩ የዓለም ሟርተኛ ጋዜጠኞችም ከጦር ኃይል መሣሪያ ድብደባ የበለጠ በውሸት ወሬ ዓለምን እያደሙ ስለሆነ አደብ ብትገዙ ይሻላል። በተለይ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ላይ አተኩረውና አልመው የውሸት ወሬና አደጋ እያዘነቡ ይገኛሉ። ባካችሁን ዕውነትን አክብሩ ። ምንም ይሁን ምን ሰማይም ተዳሰሰ ምድርም ተበረበረ፤ ኢትዮጵያ በሀቅ፣ በፅኑ ዕምነት እና በመልካም አመራር የሠራባት ሴራ ይከሽፋል። ኢትዮጵያ ታብባለች።
ከመኮንን አበበ ተሰማ
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2013