ኢትዮ ቴሌኮም ‹‹ቴሌብር ››የተሰኘ ለማህበረሰቡ ምቹ እና ሁሉን አካታች የገንዘብ ማስተላለፊያ እና የመገበያያ ዘዴ የሆነውን የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት (Mobile Money service) አስጀምሯል፡፡ አገልግሎቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፣የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ እንዲሁም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በወዳጅነት አደባባይ ግንቦት 3 ቀን 2013ዓ.ም በይፋ ተጀምሯል፡፡
የሞባይል ገንዘብ አገልግሎቱ በአገሪቱ ያለውን የፋይናንስ አካታችነት ክፍተት በማጥበብ፣ ዜጎች ባሉበት ሆነው ፈጣን እና ቀላል በሆነ ዘዴ እንዲሁም በአነስተኛ የግብይት ወጪ የተሻለ የፋይናንስ አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታን የሚያመቻች ነው፡፡ ኩባንያው የሞባይል ገንዘብ አገልግሎትንና ተያያዥ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ለውድ ደንበኞቹና ለሁሉም ህብረተሰብ ለማቅረብ የፈቃድ ጥያቄውን ካቀረበበት ወቅት ጀምሮ ሰፊ የዝግጅት ስራዎችን አከናውኗል፡፡ በተለይ በኢንዱስትሪው የተመረጠና የተሻለ የሞባይል ገንዘብ ቴክኖሎጂን ስራ ላይ ለማዋል፣ ተገቢ ፖሊሲዎችና አሰራሮችን ለመተግበር፣ ሰፊውን ወኪል ኔትወርክ ለማንቀሳቀስና የቴሌኮም እና የፋይናንስ ኢንዱስትሪዎችን የተሻለ ልምዶችን በመቀመር በቂ ዝግጅት በማድረግ በዋናነት የባንክ አገልግሎት ማግኘት ያልቻሉ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችና በገጠር የሚገኙ ዜጎችን የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ሰፊ ጥረቶችን አድርጓል፡፡
በኢትዮጵያ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውና በኩባንያው የሚሰጠው የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ከተደራሽነቱ ባሻገር ለአጠቃቀም እጅግ ቀላል ነው፡፡ ለማህበረሰቡ ብስራት ሲሆን ለህዝቡን ለማገልገል ካለው ፍላጎት አንፃር ለኩባንያው ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ኩባንያው የቴሌኮም አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ የዘረጋውን መጠነሰፊ መሰረተ ልማት በመጠቀም ለህብረተሰቡ አዎንታዊ ተፅእኖ የሚፈጥር አገልግሎት ማስጀመሩ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት እንዲሁም ለህብረሰቡ የእለት ተእለት ኑሮ መሻሻል ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡
የፋይናንስ አካታችነት (Financial inclusion) ሁሉም የፋይናንስ አገልግሎቶች ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል የኢኮኖሚ ፅንሰ ሀሳብ ሲሆን የሞባይል ገንዘብ አገልግሎትም የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ አይነተኛ መፍትሄ ነው፡፡
ኢትዮ ቴሌኮምም በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 35 በመቶ ብቻ የሆነውን የፋይናንስ አካታችነት ወደ 60 በመቶ ለማሳደግ ግብ አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደንበኞች ከውጭ ሀገር የሚላክላቸውን ገንዘብ ቴሌብርን በመጠቀም በቀላሉና በአነስተኛ የአገልግሎት ክፍያ ለመቀበል የሚያስችላቸውን አገልግሎት ለማስጀመር ከዓለም አቀፍ ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል፡፡
በቀጣይም ኩባንያው በቴሌብር አገልግሎት የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር ትርጉም ያለው ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ የሞባይል አነስተኛ ብድር፣ የቁጠባ አገልግሎትና ተያያዥ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎትን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን በማሟላት የሚያስጀምር ይሆናል፡፡
አገልግሎቱን ለማህበረሰቡ በማቅረብ ሂደት በርካታ ተቋማት የሚሳተፉ ይሆናል፡፡ በተለይም በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሁሉም የፋይናንስና ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ፣ ዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶ እንዲሁም አገልግሎቱን ለደንበኞቹ ቅርብ ለማድረግ የሚያስችሉ ኩባንያዎች ጋር ልዩ ውል ያላቸው ዋና ወኪሎች እና በእነዚህ ዋና ወኪሎች የተመለመሉ እስካሁን 1600 በላይ ወኪሎች ዋነኛ ተሳታፊ ናቸው፡፡
ቴሌብርን በመጠቀም ገንዘብ ከማስተላለፍ፣ ከመቀበል በተጨማሪ ግብይት ለመፈፀም የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠርም ከተለያዩ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር አብሮ እየሰራ ነው፡፡ ለአብነትም፣ የውሃና ፍሳሽ፣ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ገቢዎች፣ሱፐር ማርኬቶች ፣ ነዳጅ ማደያዎች፣ እርዳታ ድርጅቶች፣ ካፌዎችና ሬስቶራንቶች፣የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የህትመት ሚዲያዎች እና ሌሎችም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ይገኙበታል፡፡
አገልግሎቱ ጤናማ የገንዘብ ፍሰትን ከመፍጠሩም ባሻገር ቁጠባን በማሳደግ፣ድህነትን ለመቀነስ፣ስራ ፈጣሪነትንና ኢንቨስትመነትን ለማበረታታት እንዲሁም ገንዘብ የሚታተምበትን ወጪ በመቀነስና ኢኮኖሚን ለማሳደግ የህዝቡን ሁለንተናዊ እድገት ተጠቃሚነት ያሳድጋል፡፡ በተለይ በኮቪድ 19 ጋር በተገናኘ የገንዘብ ንክኪን ለመቀነስ የቴሌብር አገልግሎቱ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡
አገልግሎቱ ኢትዮ ቴሌኮም ካለው ሰፊ ተደራሽነት አንፃር በተለይ በፋይናንስ አገልግሎት ዘርፉ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ እና ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ የምታደርገውን ሽግግር ለማገዝ ሁነኛ አቅም የሚፈጥር ነው፡፡በተለይም በውጭ አገር ከሚገኙ ተጠቃሚዎች የሚደረገው የገንዘብ ማስተላለፍ አገልግሎት፣ ለኩባንያውም ሆነ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ግኝት የሚኖረው አስተዋጽኦ ትልቅ ይሆናል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በኢትዮጵያ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት በይፋ ማስጀመሩም በርካታ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና ግለሰቦችን አስደስቷል፡፡በአዲስ አበባ በአራዳ ክፍለ ከተማ የምግብ መድሀኒት ቁጥጥር ባለሙያ የሆኑት አቶ አለማየሁ መስፍን በቴሌ ብር አገልግሎት መጀመር ደስተኛ ከሆኑ የኩባንያው ደንበኞች አንዱ ናቸው፡፡
‹‹ኩባንያው የቴሌኮም አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በማፍሰስ የዘረጋው መጠነ ሰፊ መሰረተ ልማት በመጠቀም ወደ ደንበኞች ይበልጥ ቅርብ እየሆነ መጥቷል››የሚሉት አቶ አለማየሁ፣ ቴሌ ብር የተሰኘው አገልግሎትም ለህብረተሰቡ ተጨማሪ እና አዎንታዊ ተፅእኖ የሚፈጥር መሆኑን ገልፀዋል፡፡
‹‹በፋይናንስ አገልግሎት ረገድ የህብረተሰቡን የዕለት ተዕለት ኑሮውን ቀለል ባለ መልኩ እንዲከውን ያደርጋል ›› ያሉት አቶ አለማየሁ፣አገልግሎቱ በተለይም የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ ያልሆኑና በዋናነት በገጠር ላሉ ማህበረሰቦች ትልቅ እፎይታን እንደሚሰጥም ነው ያስገነዘቡት፡፡ ይሁንና ኩባንያው የአገልግሎቱን አጠቃቀም በሚመለከት ለህብረተሰቡ በቂ መረጃ መሰጠት እንዳለበትም አፅንኦት ሳይሰጡ አላለፉም፡፡
ሌላኛው የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኛና የሃምሌ 19/67 ትምህርት ቤት መምህር አቶ ስንታየሁ ግርማም፣ ‹‹ኩባንያው ዜጎች ባሉበት ሆነው ፈጣን እና ቀላል በሆነ ዘዴ እንዲሁም በአነስተኛ የግብይት ወጪ የተሻለ የፋይናንስ አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታን ማመቻቸቱ ከወትሮው በላቀ መልኩ ይበልጥ እንዲደነቅ የሚያደርገው ነው››ብለዋል፡፡
በቴሌ ብር አገልግሎት መጀመር ግለሰቦች ብቻ ሳይሆን ድርጅቶችም ደስተኛ ሆነዋል፡፡ በሀገራችን ከሚታወቁት የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አንዱ የሆነው ራይድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሳምራዊት ፍቅሩ ኢትዮ ቴሌኮም ያስጀመረው የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት በፋይናንስ አገልግሎት ዘርፉ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ ፣ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ የምታደርገው ሽግግር ለማገዝ ሁነኛ አቅም እንደሚፈጥር እና በተለይ ለትራንስፖርት ዘርፉ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ነው ያስረዱት፡፡
‹‹እኛ ከሁሉም በላይ ቴክኖሎጂ ላይ ጥገኛ ነን፣የቴሌ ብር የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት መጀመር ረጅም ጊዜያት ስንጠብቀው የቆየነው፣ በደስታ የምንቀበለው እና ዘርፈ ብዙ ትሩፋት ያለው ነው፣አገልግሎቱ ደንበኞች ካሽ ወይም ቼክ ሳያስፈልጋቸው ስልካቸውን በመጠቀም ብቻ ገንዘብ እንዲልኩ፣ እንዲቀበሉና ግዢ እንዲፈፅሙ በማስቻል ስራን ያቀላጥፋል፣ጥሬ ብር የመያዝ ባህል እንዲቀር እና ወደ ዲጂታል መንገድ ለመጓዝ ጉልህ ሚና ይጫወታል፣ጊዜ እና ገንዘብን ይቆጥባል፣አደጋንም ይከላከላል››ብለዋል፡፡
እንደ ዋና ስራ አስፈፃሚው ገለፃ፣አገልግሎቱ ከባንክ አገልግሎቶች በተለየ መልኩ በሳምንት ሰባት ቀን ለ24 ሰአት የሚሰራ እንደሚሆን በተለይ ራይድን ለመሳሰሉ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ትልቅ ትርጉም ያለው ነው፡፡ አሽከርካሪዎች ከፍተኛ ገንዘብ ይዞ ከመዞር እና በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ለዘረፋ እንዳይጋለጡ ይከላከላል፡፡ የባንክ አገልግሎት በቀላሉ ለማግኘት የሚቸገሩና የአሰራሩ ርዝመት አሰልችቷቸው ከገንዘብ ልውውጡ የሚርቁትን ለመቀላቀል ያግዛል፡፡
የራይድ ዋና ስራ አስፈፃሚዋ፣ ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቱን ውጤታማ በሆነ መልኩ ለማስቀጠል፣ በቀጣይ መስራት ስለሚኖርበት የቤት ስራ ሲገልፁም፣‹‹ኩባንያው ከሁሉም በላይ መሰረተ ልማት ላይ ይበልጥ መስራት አለበት እንዲሁም የዳታ እና ሌሎች የደህንነት ጉዳዮች ላይ ጠንክሮ መስራት አለበትም››ብለዋል፡፡
ከ32 ሺ በላይ አሽከርካሪዎች፣ በሚሊየን የሚቆጠሩ ደንበኞች ያሉት ራይድ፣ የኢትዮ ቴሌኮምን የቴሌብር አገልግሎት ለማስተዋወቅ ብሎም አገልግሎቱ ስኬታማ በሆነ መልኩ እንዲፈፅም ለማድረግ ብብር ለመስራት ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ ስለመሆኑም ሳያስገነዝቡ አላለፉም፡፡
በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይም የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ፣የቴሌ ብር አገልግሎት በኩባንያው 127 ዓመታት ታሪክ ከቀረቡ አገልግሎቶች ለየት ያለ ስለመሆኑ አስታውቀዋል፡፡‹‹ ቴሌ ብር በዋናነት ለፋይናንስ እና የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽ ያልሆነውን በዋናነት በገጠር ያሉትን ማህበረሰቦች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ እና ምንም ገቢ የሌላቸውን ማህበረሰቦች ታሳቢ በማድረግ በፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽና ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ የተወለደ ነው››ብለዋል፡፡
እንደሚታወቀዉ ፣ በአሁን ወቅት በርካታ የፋይናንስ አገልግሎቶች አሉ፡፡የቴሌ ብር የተሰኘው የሞባይል አገልግሎትስ ለምን አስፈለገ፣በአገሪቱ ኢኮኖሚ እና ማህበረሰብ ላይስ ምን ተፅእኖ ይዞ ይመጣል ተብሎ መጠየቁ አይቀርም፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚም ለዚህ ጥያቄ በቂ መልስ አላቸው፡፡እንደ ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ገለፃ፣ሀገራት ውጤታማ እና ጤናማ የኢኮኖሚ እድገት እንዲኖራቸው በርካታ ማህበረሰብን የሚያካትቱ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ለመስጠት የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናሉ፡፡ማሻሻያዎችን ያደርጋሉ፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ በተለይ በአህጉራችን አፍሪካ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዳልሆነ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በዓለም ላይ ካለው ህዝብ 69 በመቶ የሚሆነው ብቻ የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሆነም የቅርብ ሪፖርቶች ያመላክታሉ፡፡በኢትዮጵያም 35 በመቶ የሆነው ማህበረሰብ ክፍል ብቻ የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ነው፡፡ ይህ እንደመሆኑም ውጤታማ ፣ ጤናማ እና ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ ሀገራት ከወሰኗቸው እና ከተገበሯቸው ማሻሻያዎች አንዱ የቴሌኮም መሰረተ ልማት በመጠቀም የፋይናንስ አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ነው፡፡
ይህም በዋናነት ገንዘብ ለመላክ ፤ ለመቀበል እና የግብይት ስርአትን ለማሳለጥ የሚያስችል በስልካችን ብቻ ተጠቅመን ገንዘብ ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ ለመላክ ወይንም ከውጭ ለመቀበል የሚረዳ በቀላሉም ከርቀት ቦታ ሆኖ ክፍያን ለመፈፀም የሚረዳ ነው፡፡ ይህም ሰፊውን ማህበረሰብ ክፍል በፋይናንስ አገልግሎት ለማድረስ ያስችላል፡፡
በሞባይል በኩል የሚደረግ የፋይናንስ አገልግሎት ከማህበረሰብ ባለፈ አገርን ከከፍተኛ የጥሬ ብር የህትመት ወጪ ለማስቀረት እንደሚጠቅም የሚያስረዱት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ፣ ይህ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ተጨማሪ አቅምን የሚፈጥር እንዲሁ በጥሬ ገንዘብ ዝውውር አማካኝነት የሚፈጠሩ የደህንነት ስጋቶችን ብሎም ደህንነቱን ለማስጠበቅ የሚወጣውን ወጪ ለመቆጠብ እንደሚያስችል ያስገነዝባሉ፡፡
ከሁሉም በላይ በመደበኛ የፋይናንስ አገልግሎት ማለትም ለባንክ ተደራሽ የሆነው የህዝብ ቁጥር በጣም ዝቅተኛ ከመሆኑ ባሻገር በሚሊየን የሚቆጠሩ ህዝቦች፣ ገቢያቸው ዝቅተኛ የሆነ እና ምንም ገቢ የሌላቸው ብሎም በገጠር አካባቢ መኖራቸውን ጤናማ የሆነ የፋይናንስ ፍሰት በአንድ አገር እንዳይኖር እና ዘላቂ እድገት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ተግዳሮት ይሆናል፡፡ይህን የተገነዘቡ ሀገራት ካደረጉት አንዱ የሞባይል ቴክኖሎጂን በመጠቀም በገጠር በከተማ ወጣት አዛውንት ሴት ወንዱን በቀላሉ ተደራሽ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ በመሆኑ፣በፋይናንስ ተደራሽ ያልሆኑ ተደራሽ ለማድረግ ይጠቀሙበታል፡፡
የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት እኤአ በ2001 የተጀመረ ቢሆንም በአህጉራችን በአፍሪካ በተለይ በምስራቅ አፍሪካ በ2007 ከተጀመረ በኋላ፣በሰፊው እያደገ እና አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ የሚገኝ ነው፡፡በአሁን ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በአጠቃላይ 310 የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ሰጪዎች ይገኛሉ፡፡ባሳለፍነው የፈረንጆቹ ዓመት ዲሴምበር ላይ በአንድ ወር ውስጥ ገንዘብ በመቀበል፣ በመላክ እና ከፍያ በመፈፀም 70 ቢሊየን ዶላር ልውውጥ ተካሂዷል፡፡ከዚህ ውስጥም 23 ቢሊየን ዶላር የሚሆነው በዲጂታል ሲስተሙ ላይ የተዘዋወረ ነው፡፡
በአጠቃላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሞባይል የገንዘብ አገልግሎት አማካኝነት በቀን 2 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ልውውጥ ይከናወናል፡፡ አገልግሎቱም ለልውውጡ የሚወጣውን ወጪ እንዲሁም ፈጣን ቀላል እና ምቹ የሆነ የግብይት ስርአትን ለማሳለጥ አይነተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ይህ ቁጥርም በቀጣዩ የፈረንጆች አመት 3 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር እንደሚደርስ ይገመታል፡፡ የኢትዮጵያ መቀላቀልም ይህን ለማሳካት ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል፡፡
‹‹እስካሁን ባለው ሂደት ኢትዮጵያ እዚህ ቁጥር ውስጥ የለችም፡፡ኩባንያውም ልንኖር ይገባል በሚል አገልግሎቱን በይፋ አስጀምሯል››የሚሉት ወይዘሪት ፍሬህይወት፣አገልግሎቱም በፋይናንስ ተደራሽ ያልሆኑትን የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ለማድረግ፣ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲካተቱ ለማድረግ በቀላሉ ኑሮዐቸውን ማሻሻል እንዲችሉ እንዲረዳ ታስቦ የመጣ ስለመሆኑም አፅንኦት ይሰጡታል፡፡
እንደ ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ገለፃም፣በአጠቃላይ ባለፈው አመት 767 ቢሊየን ዶላር በሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ገንዘብ ተላልፏል ግብይት ተፈፅሟል፡፡ 767 ቢሊየን ዶላር ውስጥ 64 በመቶ የሚሆነው በአህጉራችን አፍሪካ የተከናወነ ነው፡፡ ይህ አሃዝ በኢኮኖሚ ብሎም በዜጎች ኑሮ ላይ የሚያመጣው መሻሻል በቀላሉ ሊገመት የሚችል ነው፡፡ ከ767 ቢሊየን ዶላር ልውውጥ ውስጥ 273 ቢሊየን ዶላር ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምስራቅ አፍሪካ የተከወነ ነው፡፡ይህ ማለት 35 በመቶ የሚሆነው በምስራቅ አፍሪካ የተከናወነ ልውውጥ ነው እንደማለት ነው፡፡አገልግሎቱን ተግባራዊ ያደረጉ የአፍሪካ አገራትም የዜጎቻቸውን የፋይናንስ ተደራሽነት ደረጃ በእጅጉ በማሻሻል እስከ 90 በመቶ መሸፈን ችለዋል፡፡
‹‹ከዚህ መልካም አጋጣሚ ግን ኢትዮጵያ ተጠቃሚ አልነበረችም፡፡አገልግሎቱን ተግባራዊ ማድረግ ብትችል ይህን ስኬት ለማስመዝገብ አትቸገርም ››የሚሉት ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ፣ኢትዮ ቴሌኮምም ይህን ስኬት ለማስመዝገብ የቴሌኮም መሰረተ ልማት አሟ ጦ ለመጠቀም እና የሞባይል ቴክኖሎጂ ያመጣቸው መልካም አጋጣሚዎችን በአግባቡ በመጠቀም ሌሎች ሀገራት እንዳደረጉት የማህበረሰቡን ኑሮ ለመቀየር፣ኢኮኖሚውን ለማሳደግ፣የፋይናንስ ፍሰቱንም ጤናማ ለማድረግ ቆርጦ ስለመነሳቱም ነው አፅንኦት የሠጡት፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢትዮ ቴሌኮም በህዝብ ቁጥር ብዛት 95 በመቶ ፣በመልክአ ምድር አቀማመጥ ደግሞ 85 በመቶ ሽፋን አለው፡፡የሞባይል ደንበኞች ቁጥር 53 ሚሊየን ደርሷል፡፡ 25 ሚሊየን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች አሉት፡፡ከእነዚህ ውስጥ 44 በመቶ የሚሆኑት ስማርት ፎን ያላቸው ናቸው፡፡አሃዞችም የሞባይል ገንዘብ አገልግሎትን ተግባራዊ ለማድረግ እና ውጤታማ መደላድሎች ስለመኖራቸው አመላካች ናቸው፡፡
ኩባንያው በቅርቡ ክሬዲት ኤር ታይም ወይንም የዱቤ አየር ሰአት አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ ጀምሯል፡፡ ይህ አገልግሎት የተፈጠረበት ዋነኛ አላማም ደንበኞች አስቸጋሪ በሆነ ሰአት የቴሌኮም አገልግሎት መጠቀም ፈልገው፣ ነገር ግን አየር ሰአት መግዛት ካልቻሉ እንደ አቅማቸው ብድር የሚያገኙበት ነው፡፡ኩባንያው ሲያበድር የቆየው ከ5 ብር እስከ 25 ብር ድረስ ብቻ ነበር፡፡በቅርቡ 50 እና 100 ብር አካቶ ማበደር ጀምሯል፡፡በዚህ አገልግሎትም በቀን 37 ሚሊየን ገንዘብ ወይንም የአየር ሰአት ለደንበኞች እያበደረ ይገኛል፡፡ በወር 15 ሚሊየን ደንበኞች እየተበደሩ ነው፡፡ ይህም አንድ ነጥብ አንድ ቢሊየን ገደማ እያበደረ ይገኛል፡፡
ወይዘሪት ፍሬህይወት‹‹ይህም በገጠር ያሉ እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ወደ መደበኛ የባንክ አገልግሎት ሄደው መበደር የማይችሉትን ተበድረው ኑሮአቸውን እንዲቀይሩ እና ምናልባትም ጠዋት ተበድረው ቀን ነግደው ከሰአት በኋላ መመለስ የሚችሉበትን ስርአት ብንዘረጋላቸው ሰፊውን የማህበረሰብ ክፍል ወደ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴው እናስገባለን ብለን እናምናለን›› ብለዋል፡፡
‹‹በአሁን ሰአት ግን ከብሄራዊ ባንክ የተፈቀደልን እና የተሰጠን ፈቃድ በዋናነት ገንዘብ ማስተላለፍ እና በግብይት ስርአት የሚያገለግል ሲሆን በቀጣይም እንዲህ አይነት ቴክኖሎጂን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ኢኮኖሚያችንን ልናሳድግ እና ዜጎችም ከዚህ ተጠቃሚእንዲሆኑ አስፈላጊው የፖሊሲ ማሻሻያ እንዲደረግበት ተስፋ እናደርጋለን››ብለዋል፡፡
‹‹ቴሌ ብር በኢኮኖሚው ላይ ምን አይነት አበርክቶ ይሰጣል››የሚለው መልስ ሊሰጠው የሚገባ ወሳኝ ጥያቄ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡እንደ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ማብራሪያም፣በተሰሩ እቅዶች መሰረትም በመጀመሪያው አመት 21 ሚሊየን ደንበኞች ቴሌ ብር ይመዘገባሉ፡፡ከዚህ ውስጥም 12 ነጥብ 7 ሚሊየን የሚሆኑት አክቲቭ ደንበኞች ይሆናሉ ተብሎ ታስቧል፡፡ በመጀመሪያው አመት በሀገር አቀፍ ደረጃ 710 ሚሊየን ልውውጥ በቴሌ ብር ይንቀሳቀሳል ተብሎ ታስቧል፡፡ይህም በብር 69 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የሚያወጣ ልውውጥ እንደማለት ነው፡፡
ከአምስት አመታት በኋላ 33 ሚሊየን ደንበኞች ይኖሩናል፡፡በአጠቃላይ 3 ነጥብ 5 ትሪሊየን ብር በቴሌ ብር እንደሚንቀሳቀስ ተገምቷል፡፡ ይህን ያህል ገንዘብ በዲጂታል በማንቀሳቀስ፣ለማተም የሚያስፈልገንን ወጪ ቀንሰን ወይንም ቆጥበን በቀጥታ ኢኮኖሚው ላይ እንዲካተት ማድረግ እንደሚቻል ታሳቢ በማድረግ ከወዲሁ እየተሰራ ይገኛል፡፡በአጠቃላይ በመጀመሪያው አመት 15 ሺ የሚሆኑ ኤጀንቶች ይኖራሉ፡፡እነዚህ ኤጀንቶችና የኢትዮ ቴሌኮም ወኪሎች ገንዘብ ለማስገባት እና ለማስወጣት በመላ አገሪቱ የተሰማሩ ይሆናሉ፡፡ ይህን በማድረግ የፋይናንስ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ታስቧል፡፡
‹‹በአጠቃላይ በአምስት አመት ይህን ለውጥ ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ ከ40 እስከ 50 በመቶ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በቴሌብር ይንቀሳቀሳል ብለን ስትራቴጂ ሰርተናል››ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ፣ተሞክሮ የተወሰደውም ከጎረቤት ሀገሮች ከሌሎችም የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ተግባራዊ ካደረጉ ሀገሮች ልምድ በመቅሰም ብሎም በመቀመር መሆኑን አስረድተዋል፡፡አሁን ካለው በተጨማሪ የፋይናንስ አካታችነትን ከ25 እስከ 30 በመቶ ለማሳደግ እንደታሰበም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡፡
እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ገለፃም፣በአጠቃላይ የአፈፃፀም ሂደት ቴክኖሎጂ ብቻ በቂ አይሆንም፡፡ የባለድርሻ አካላት፣ በቴሌ ብር አማካኝነት ክፍያን መፈፀም፣የመንግስት ብሎም የንግድ ተቋማት ከቴሌ ብር ጋር አሰራራቸውን በማገናኘት ብሎም በመጠቀም ተጠቃሚ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡የፋይናንስ ተቋ ማት የመንግስት አገልግሎት ሰጪዎች ብሎም ተቆጣጣሪ ተቋማት በቴሌ ብር አገልግሎት የታለመለትን እቅድና ግብ እንዲያሳካ በጋራ መስራት አለባቸው፡፡
የሞባይል ገንዘብ ቴክኖሎጂን ተግባራዊ ያላደረጉ (ስሊፒንግ ጃይንት) የሚል ቅፅል የወጣላቸው ሶስት የአፍሪካ ሀገራት አሉ፡፡አንደኛዋ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ‹ስሊፒንግ ጃይንት) ስያሜን ያገኙትም የሞባይል ቴክኖሎጂ አቅም እና ኢኮኖሚ ላይ ሊፈጥር የሚችለውን ፋይዳ ተግባራዊ ያላደረጉ በመሆናቸው ነው፡፡
‹‹እኛ ከዚህ በኋላ ስሊፒንግ ጃይንት አይደለንም፣ኢትዮጵያ ይህን ታሪክ አድርጋለች››ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ፣ ኩባንያው አሁንም ሆነ በቀጣይ ቴክኖሎጂ የፈጠራቸውን መልካም አጋጣሚዎች በአግባቡ በመጠቀም ሰፊውን የማህበረሰብ ክፍል በፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽና ተጠቃሚ ለማድረግ መቁረጡን እና ሌሎችም አብረውት እንደሚሰሩ ባለሙሉ ተስፋ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ኩባንያው በዚህ አጋጣሚም የቴሌ ብር አገልግሎት የበለጠ ፍሬ እንዲያፈራና የሀገሪቱ የዲጂታል ፋይናንስ ፍላጎት ለማሟላት እና ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚደረገው ሀገራዊ ጥረት ከግብ ለማድረስ በኢኮሲስተም ሚና ያላቸው ባለድርሻ አካላት በተለይም የፋይናንስ ተቋማት፣ የንግድ ድርጅቶችና አገልግሎት ሰጪ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት አብራችሁን እንድትሰሩ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዋና ስራ አስፈፃሚዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ኩባንያው በ2011 ዓ.ም ይህ ን አገልግሎት ለመስጠት አስቦ ያዘጋጀውን ስትራቴጂ ተመልክተው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመምከር ለህዝቡ በሚጠቅም መልኩ ተግባራዊ እንዲደረግ በማድረግ ለሰጡት አቅጣጫም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም የቦርድ አባላት በተለይ አምባሳደር ግርማ ብሩ እንዲሁም የብሄራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ ኩባንያው ህልሙን እውን እንዲያደርግ እና አገልግሎቱን ተግባራዊ እንዲያደርግ አስፈላጊውን የህግ ማዕቀፍ እና ፈቃድ በመስጠት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና ሳያቀርቡም አላለፉም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎቱን በይፋ ሲያስጀምሩ፣ኢትዮጵያ በሞባይል ገንዘብ የማዘዋወር አገልግሎትን ከአመታት በፊት መጀመር ሲገባት ባለመጀመሯ እና በመዘግየቷ ምክንያት ከፍተኛ ኪሳራን ለመቀበል መገደዷን አስታውሰዋል፡፡‹‹አሁን ግን መጀመሩ የግድ ስለሆነ እንዲጀመር ተወስኗል ››ብለዋል፡፡
በሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ካለው ኢኮኖሚያዊ ትሩፉት አንፃር እንዲጀመር ከ10 ዓመት በፊት ለመንግስት ቀርቦ የነበረ ቢሆንም መንግስት እንዲጀመር ፍላጎት አለማሳየቱን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ይሁንና የቴሌኮም ሴክተር ለሌሎች በዚህ ስራ ውስጥ ለተሰማሩ ኩባንያዎች ክፍት ይሁን በሚል ከሁለት አመት በፊት ሲወሰን ፣ አንዱ እና ከፍተኛ አከራካሪው ጉዳይ፣ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር ነበርም››ብለዋል፡፡
ቴሌብር የሞባይል ገንዘብ የአገልግሎት ፈቃድ ለኢትዮ ቴሌኮም ሲሰጥ ድርጅቱ አቅም አጎልብቶ ከውጭ ተቋማት ጋር የመወዳደር አቅሙን እንዲያጎለብት እንዲሁም ተወዳዳሪነቱን እንዲያጠነክር መሆኑንም ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መሰል ውሳኔዎች ዘላቂ አለመሆናቸውንና ከአንድ አመት በኋላ ለሌሎችም ክፍት ሊደረጉ የሚችሉ በመሆናቸው ኢትዮ ቴሌኮም በጥብቅ ዲሲፕሊን ሥራውን በውጤታማነት መፈጸም እና አቅሙን ማጎልበት እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2013