የምርጥ ቡና ቅምሻ ውድድር ወደ ሀገራችን ከመጣ ሁለተኛ ዓመቱን ይዟል። ምንም እንኳን የመጨረሻው አሸናፊ ሰኔ ላይ ቢለይም ውድድሩ ዘንድሮም ለሁለተኛ ጊዜ በሀገራችን ተካሂዷል። መካሄዱ የቡና ዕትብት መገኛ ለሆነችው ኢትዮጵያችን ብዙ በረከቶችን ይዞ መምጣቱን ቀጥሏል። በተለይ ወድቆ ከነበረው የቡና ገበያ ዋጋ አንፃር ይዞት የመጣው የገበያ ልማት ሲሳይን ማስፋት ከፍተኛ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ ይናገራሉ።
አንደኛው ዙር የምርጥ ቡና ቅምሻ ውድድር በፈጠረው ሰፊ ገበያ የኢትዮጵያ ቡና በመጠንም በዋጋ በአስደናቂ ሁኔታ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የሚያስችል ዕድገት እያሳየ መሆኑን በማስረጃ ይጠቅሳሉ። አንደኛው ዙር ውድድር 270 ሺህ ቶን ቡና ወደ ውጭ ተልኮ የተሸጠበትን የደራ ገበያ ፈጥሯል።
በዘንድሮ በጀት ዓመት ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ወደ ውጭ የወጣው ቡና መጠንም እጅግ ከፍተኛ ነው። በእርግጥ ይሄኛው ቡና አምና በተመሳሳይ ከተሸጠው ጋር ሲነፃፀር በ40 ሺህ ቶን ቅናሽ ያሳየበት ሁኔታ ነበር። ይሁንና ይሄ ቡና የተሸጠበት በዋጋ ደረጃ ሲታይ ግን የአንድ ቶን ቡና በ10 እጥፍ ያደገበት ሁኔታ በመኖሩ ከገቢ አንፃር ሽያጩ አሁንም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ የተገኘበት ነው። በመሆኑም የዘንድሮው የባለስልጣኑ አፈፃፀም ከአምናው የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል።
ባለፈው ዓመት አንድ ቶን ቡና በአማካኝ ወደ 3 ሺህ 700 የአሜሪካ ዶላር መሸጡን ዶክተር አዱኛ ይገልፃሉ። በዘንድሮው ዓመት ደግሞ አንድ ቶን ቡና እስከ 3 ሺህ 900 የአሜሪካ ዶላር መሸጡንና ዋጋው ከፍ ማለቱን ነው የሚናገሩት።
‹‹ይሄ ገቢ የተገኘው የምርጥ ቡና ውድድር ቡናችን በጥራት እንዲመረት የራሱን አስተዋፆ በማድረጉ ነው›› ብለዋል ዶክተር አዱኛ፡፡ የተገኘው ገቢ በጥራቱ መሻሻል ማሳየቱን ሲገልፁ እስካለፈው ታህሳስ ወር መጨረሻ ድረስ ባለው ጊዜ የነበረው ነባር ቡና ሙሉ በሙሉ ተሟጦ ወደ ውጭ ገበያ መላኩን አመልክተዋል።
‹‹ከጥር ወር ጀምሮ አዲሱ ቡና ወደ ግብይት የገባበት ሁኔታ ነበር›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ይሄ የቡና ሽያጭ አፈፃፀም ከአምናው ጋር በንፅፅር ሲታይ የተሻለ ሆኖ ተገኝቷል። በ10 ወር ጊዜ ውስጥ 180 ሺህ ቶን ቡና ኤክስፖርት ተደርጎ ከ650 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን በማሳያነት ጠቅሰዋል። በሚያዝያ ወር ብቻ 114 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን አፈፃፀሙ የተሻለ ለመሆኑ በማሳያነትም አቅርበዋል።
በተለይ የየካቲት፣ መጋቢትና ሚያዝያ ወራቶች አፈፃፀም ከ100 ፐርሰንት በላይ በመሆኑ እጅግ ከፍተኛ ውጤት መመዝገብ ችሏል። ይሄውም መጋቢት ላይ 27 ሺህ ቶን ቡና ተልኮ 107 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የተገኘበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ሚያዝያ ወር ላይም 28 ሺህ ቶን ቡና ተልኮ 114 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በመገኘቱ ገቢው ከፍ ማለት ችሏል።
እንደ ዶክተር አዱኛ በቀጣይ ሁለት ወራቶች ገቢውን ከዚህ በበለጠ ከፍ ለማድረግ እየተሠራ ይገኛል። የዘንድሮው ሁለተኛው ዙር የቡና ቅምሻ ውድድር በመጪው ሰኔ 30 በቀጥታ ግብይት ይካሄዳል። በዚህ ኦን ላይን ቀጥታ ግብይት አሸናፊ የሆነው ኩባንያ በውጭ ገበያ ቡናውን እንዲወስድ ይደረጋል። ይሄ ይዞት የሚመጣው የውጭ ምንዛሪ እጅግ ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም የካፕ ኦፍ ኤክሰለንሲ ግብይት ላይ አምራቾችና ላኪዎች ቡናቸውን የሚሸጡበት መድረክ ግንቦት 23 ጀምሮ መካሄዱ ሌላው ነው። ይሄ የግብይት መድረክ ዓለም አቀፉ ገበያ ወደ ሀገር ውስጥ የመጣበትና በየወሩ ለየት ያለ ጠዓም ያላቸው ቡናዎችን በጨረታ የሚቀርቡበት ነው።
ይሄን የገበያ ልማት በማስፋት ለውጭ ምንዛሪ ገቢ መገኘት መሰረት የሚጥል አወቃቀር ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮና ከምርት ገበያ ጋር አንድ ላይ በመሆን ባለስልጣኑ ማዘጋጀቱንም ዶክተር አዱኛ ገልፀዋል። እንደ ዋና ዳይሬክተሩ በዚህ መድረክ አርሶ አደሮች ምርቶቻቸውን በቀጥታ ሀገር ውስጥ መሸጥ እንዲችሉ ዕድል ይሰጣል። ሁለተኛም ጥራትን ያበረታታል። ሦስተኛም ለጥራት የተሻለ ዋጋ እንዲከፈል ያስችላል።
አሁን ላይ 52 ቡናቸው ከፍ ያለ የጥራት ደረጃ ያላቸው ቡና አምራች አርሶ አደሮች ቡናቸውን ዛሬ በሚከፈተው ገበያ ለመሸጥ ፍላጎት ያሳዩበትና የተመዘገቡበት ሁኔታ አለ። ከዚህ ባሻገርም ቡናውን መግዛት የሚፈልጉ አርሶ አደሮች እንዲመዘገቡ በመገናኛ በዙሃን ማስታወቂያ ወጥቶ ምዝገባ እየተካሄደ ይገኛል።
ይሄ ሁሉ ጥረት ተደማምሮ በቀሪዎቹ ቀጣይ ሁለት ወራቶች ገቢው 800 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይገባል ተብሎ ይጠበቃል። በነዚህ ወራት ለማግኘት የታቀደው ደግሞ በቀሪው ሁለት ወራት ከ65 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለመላክ ነው። ከዚህም 300 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ይገኛል ተብሎ ይታሰባል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ በውድድሩ ቀጥታ ቡና ላይ የሚሳተፉ ከተለያዩ አገራት የተውጣጡ እንደ መሆናቸው የገበያ ልማቱ ይሰፋል። በተጨማሪም ከዚህ በፊት ያልተገኙ ለየት ያለ ጠዓም ያላቸው ቡና ዝርያዎች እንዲገኙ ያስችላል። በውድድሩ ከዚህ ውጭ ያልታወቁና ገበያ ላይ ያልነበሩ ተለይተው እንዲወጡ ተደርጓል። የባለ ልዩ ጣዓም ቡናዎች በከፍተኛ ዋጋ ስለሚሸጥ በቀጥታ አርሶ አደሩን ተደራሽ ያደርጋል። በቀጥታ ወደ ውጭ እንዲልኩ በማድረግ የተሻለ ዋጋ እንዲያገኙና የአገራቸውን ኢኮኖሚ እንዲያሳድጉ ያደርጋል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2013