ከሌሎች ዘርፎች ጋር ሲወዳደር ላለፉት ዓመታት የማዕድን ዘርፉ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ሲያበረክት የነበረው አስተዋፅኦ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ ለሀገራዊ አጠቃላይ ምርት ያለው አበርክቶም ዝቅተኛ እንደነበር በተለያዩ ጊዚያት ከማዕድንና ኢንርጂ ሚንስቴር የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ሀገሪቱ ይበልጥ የምትታወቅበት የወርቅ ማዕድን የወጪ ንግድም እጅግ ደካማ እንደነበር እነዚሁ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ይሁንና ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በተሰሩ የሪፎርም ሥራዎች የማዕድን ዘርፉ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ እያንሰራራ መጥቷል፡፡ በ2013 በጀት ዓመት በአስር ወራቶች ብቻ ከወርቅ ማዕድን የወጪ ንግድ 552 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል፡፡ ኦፓልን ጨምሮ በሌሎች የከበሩ ማዕድናት እየተገኘ ያለው የውጭ ምንዛሬም የሚናቅ አይደለም፡፡
በቅርቡ ደግሞ የማዕድን ዘርፉን ግብይት በማዘመን የሚያስገኘውን የውጪ ምንዛሬ ለማሳደግና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ከፍ ለማዕድረግ የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት በማዕድንና ነዳጅ ሚንስቴርና በኢትዮጵያ ምርት ገበያ መካከል ተፈርሟል፡፡
የማዕድንና ነዳጅ ሚንስቴር የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬህይወት ፍቃዱ እንደሚሉት ዘመናዊ የማዕድን የግብይት ሥርዓት ለማካሄድ በቅርቡ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡ ስምምነቱንም የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ እና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ወንድማገኘሁ ነገራ ሚያዝያ 29 ቀን 2013 ዓ.ም ተፈራርመዋል፡፡
የመግባቢያ ሰነዱ ዋና ዓላማም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በዘመናዊ የምርቶች ግብይት ሥርዓት፣ በግብይት ሰንሰለት ቅንጅት፣ በኤሌክትሮኒክ ግብይት ጥራትና በመጋዘን ኦፐሬሽን ያካበተውን ሰፊ ልምድ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የሀገራችንን የማዕድን ዘርፍ በመምራት ካለው ጥልቅ ተሞክሮ ጋር በማጣመር በኢትዮጵያ ዘመናዊ የማዕድናት ግብይት ማዕከል እና ሥርዓት ለመዘርጋት ነው፡፡ ይህም በማዕድን ዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶችና ኢትዮጵያዊያን አምራቾች ግልፅ የሆነ አሠራርን በመዘርጋት እኩል ተጠቃሚነትን ያሰፍናል፡፡
ሁለቱ ተቋማት በመግባቢያ ሰነዱ መሰረት በጋራ ከሚያከናውኗቸውን ተግባራት ውስጥ ለተለያዩ የኢትዮጵያ ማዕድናት (ለምሳሌ እንደ ኦፓል፣ ኢመራልድ፣ ሳፋየር፣ ታንታለም፣ ሊቲየም፣ ፖታሽ፣ ብረትና ለመሳሰሉት) በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት (ተፈላጊነት) ያለው የምርት ደረጃ ውሎችን ማዘጋጀትና ለብሔራዊ የማዕድን ግብይት የሁለቱንም ተቋማት የሰው ኃይል፣ ላቦራቶሪዎችና ተቋማዊ አቅም በመጠቀም፤ የግብይት አሠራሮችን፣ ሞዴሎችን፣ የሥራ ሂደቶችን፣ ደንብና መመሪያዎችን መቅረፅ ይገኙበታል።
እንደ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሯ ገለፃ ስምምነቱ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የማዕድናት ግብይትን ማካሄድና በአገር አቀፍ ደረጃ የሁሉም የግብይት ተዋንያንን ተሳትፎ የማረጋገጥ፤ በምርት ገበያው የሚከናወኑትን የማዕድን ግብይት በቀላሉ ለመቆጣጠር እንዲቻል የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴርን የቁጥጥር ማዕቀፍ የመከለስ፤ የሚከናወነውን የማዕድን ግብይትም ዲጂታላይዝ የማድረግና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የግብይት መድረክን በመጠቀም የኢትዮጵያ ማዕድናት እንደ ምሥራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ነፃ ገበያ የመሳሰሉ ገበያዎች ላይ በቀላሉ እንዲገቡ እና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላል፡፡
በማዕድን ዘርፍ ውስጥ ያሉ ተጠቃሚዎችን በጥራት ደረጃ አጠባበቅና ስለዓለም አቀፍ ግብይት ደረጃ አቅማቸውን ለመገንባት ስልጠና መስጠትና የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ የማዕድናት ዋጋና ሌሎችንም መረጃዎች መሰብሰብ፣ መተንተንና ለተጠቃሚዎች ማሰራጨት የመሳሰሉት ተግባራትም በስምምነቱ ውስጥ ተካተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜም የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት በተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ መሰረት ሁለቱም የቴክኒክ ኮሚቴ አዋቅረዋል፡፡ በቀጣይ ሥራው በምን መልኩ እንደሚሄድም በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት በኩል ተጨማሪ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡
በዚህ ጊዜ በሁለቱ ተቋማት በኩል የተደረገው ስምምነትም በብዙ መልኩ የሚጨምራቸው በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ በተለይ ማዕድን ተመርቶ በመሀል ተጠቃሚ እየሆነ ያለው ህገወጥ ደላላ በመሆኑ ይህን በማስቀረት የማዕድን ንግዱ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል እንዲሆን በማድረግ አምራቾች ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል፡፡ አምራቹ ይበልጥ ተጠቀሚ በሆነ ቁጥር ደግሞ ሀገሪቷም ከዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን ያስችላታል፡፡ በሌላ በኩል ስምምነቱ ዘርፉን ከግለሰብ ወደ ሀገራዊ ተጠቃሚነት ከፍ ያደርገዋል፡፡ በቀጣይም በሁለቱም ተቋማት በኩል ያሉ የቴክኒክ ኮሚቴዎች በአንድ ላይ ሆነው ስትራቴጂክ ፕላን በማውጣት ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2013