ኢትዮጵያ ለውሃዋ እና ለም አፈሯ ዋጋ የምትጠይቅበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። የዓባይ ወንዝ ውሃ ከጥንተ ዓለም እስከ አሁን ግብፅንና ሱዳንን ሲመግብ ኖሯል። ወደ ፊትም ዓባይ አገራቱን ተጠቃሚ ማድረጉን ይቀጥላል። መረሳት የሌለበት ግን ዓባይ የኢትዮጵያ አንጡራ ሀብት ነው። ይመሻል፤ ጨለማ ይሆናል። ይነጋል ብርሃን ይሆናል። ይህ የተፈጥሮ ክስተት ነው። በሰው ሰራሽ ክስተት ግን ኢትዮጵያ ዘለዓለም በጨለማ አትኖርም፤ ለእኛ እስካሁን የዓባይ ወንዝ በጨለማ አኑሮናል። ከእንግዲህ ግን ብርሃን ይሆናል።
ዓለም በሣይንስ ሥልጣኔ ቴክኖሎጂን በመጠቀም እጅግ ተራቃና መጥቃ ባለችበት በዚህ 21ኛው ክፍለ ዘመን፤ በተንኮል ይዘት ጉድ የሚያሰኝ ነገር እየተፈጠረ ይገኛል።ግብፅና ሱዳን ለማሞኘት ይጥራሉ፤ ሣይንስ ሀቅ እንደመሆኑ ዴሞክራሲ ደግሞ ዕውነተኛ መብት መሆኑ እርግጥ ቢሆንም፤ በሃቅ ዴሞክራሲን ይዘው የተመሩና የተራመዱ የተባለላቸው የዓለም ኃላፊዎች ግብፅና ሱዳን ለማሞኘት የሚጥሩትን ጥረት አስመልክቶ ለመናገር ያሉት የለም? ይህን እጅግ ግልጽ ሆኖ ያለውን የኢትዮጵያ መብትና ሀብት ጥቁር ዓባይ ወንዝ የማን እንደሆነ ሣይረዱ ቀርቶ ይሆን? ግብፅና ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ጭቅጭቅ ሲያስነሱ ሃይ ከማለት ይልቅ አነጋገራቸውን እና ምልከታቸውን ከሃቅና ከፍትሃዊነት ራቅ ማድረጋቸው ያስተዛዝባል፡፡
በዓለም አንዱ ሌላውን በሃቅ ላይ ተመስርቶ ካልረዳና ካልጠበቀ ነገ የሚፈጥረው ከባድ ይሆናል። ግብፃውያን የዓባይን ውሃ ለዝንተ ዓለም ያለዋጋ ሲጠቀሙበት በመኖራቸው ልምድና ባህል አድርገው የግላቸው እንደሆነ ተቆጥሮ የእነርሱ ብቻ ሆኖ ይቀጥላል ብለው ገምተውታል። በእርግጥ ልምድ ሲቆይ ቋሚ የማይቀየር ይመስላል። ጊዜ ሁኔታውን እንደሚያስተካክለው ዘንግተው ሌላ ቀርቶ ግብፃውያን የዓባይ ወንዝ ውሀ ከኢትዮጵያ ምድር መንጭቶ በኢትዮጵያ መሬት ላይ ፈሶ ረጅም ጉዞ የሚሄድ የኢትዮጵያም ሀብት መሆኑን የተረዱ አይመስሉም። በሥርዓተ ትምህ ርታቸው ውስጥ አስገብተው ለትውልዱ የዓባይ ወንዝ ውሃ የኢትዮጵያ ሀብት መሆኑን ከማሳወቅ ይልቅ፤ ትውልዳቸውን አንሻፈው የሃሰት መረጃ በመስጠት ከኢትዮጵያ የሚነሳው የዓባይ ውሃ የግብፅ ንብረት ነው ብለው ለትውልዳቸው በመንገር ጥፋት አስከትለዋል። ግብፃውያን ዘለዓለም የሚታወኩበትን ችግር የፈጠሩት ራሳቸው ትውልዳቸውን በተንሻፈፈ መንገድ በመቅረፃቸው ነው።
ግብፅ ሁሌ ቆጥ ላይ ወጥታ ለዓለም ድንቅ የውሸት ብሶቷን ከመግለጽ የተቆጠበችበት ጊዜ የለም።በአሁኑ ወቅት ሱዳንም በዓባይ ወንዝ ውሀ የተቀጣጠለው እሣት ሣይጠፋ በድንበር መድፈር ሌላ እሳት ጭራ ለማንደድ በመሞከሯ ለኢትዮጵያ ዝንተ ዓለም የማይረሣ መጥፎ ትዝታ ጥላ አልፋለች። ባለሀብቷ ወይም ባለቤቷ ኢትዮጵያ በተሻለ ሁኔታ ተደራጅታ ‹‹የዓባይን ውሀ ለጋራ እንጠቀም›› ስትል ግብፅ ወይ ፍንክች ብላ ጊዜው የማይቀበለውን ባዶ አባባልና ምዕራፍ የሌለው ሃሳብና ምኞት እያነበነበች ነው። ወቅታዊ እብደት ይሏቸዋል ይህ ነው።
ግብፃውያን እዚህ ውስጥ የገቡት የኢትዮጵያ ዓባይ ውሀ በምዕራባውያን በውርስ እንደተረጋገጠላቸው አድርገው በማሰባቸው ነው። ኢትዮጵያ ለወደፊት በልማዳዊ ወይም በቅኝ ገዢዎች ተረት ሣይሆን፤ ሣይንሳዊና ህጋዊ በሆነ ማረጋገጫ መታየት ስትጀምር ወደ ግብፅ ፈሶ ህይወትና ልማት ለሚሰጠው ለም አፈርና ውሀ ዋጋ የምትጠይቅበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም።
ኢትዮጵያውያን በከተሞች ውሃ እየገዛን ነው።እንኳን ህይወት የሚሰጠው ውሃ ያለ ዋጋ ሊሰጥ ቀርቶ፤ ሽታ ያለው ቆሻሻው ነዳጅ በዓለም ላይ በውድ ዋጋ እየተቸረቸረ ባለበት በዚህ ጊዜ ውሃን የሚያህል ህይወት ገዢ መተኪያና አማራጭ የሌለው ሃብት ኢትዮጵያውያን እየገዙ፤ በተቃራኒው ለውጪ ዘራፊ አሳልፎ መስጠት አያሻም። ውሀ ባይኖር ህይወት ከሰው እስከ ዕጽዋት በምድር ላይ አይኖሩም። ነዳጅ ባይኖር አማራጭ መገልገያ ሰጪ ይፈለስፋል፤ አሁንም ወደ ፊትም በዓለም እንደታቀደው የነዳጅ ተተኪ ኤሌክትሪከ ለማመንጨት የሚስችሉት ውሃና የፀሃይ ብርሃን እንዲሁም ንፋስ ናቸው። ስለዚሀ ከነዳጅ ይልቅ ለውሀ ዋጋ መስጠት ያሻል። እናም ዋጋ ሊጠየቅበት ይገባል፡፡
ግብጽና ሱዳን ተረፈ ውሀ እንጂ ዋናው ፍሳሽ የነሱ እንዳልሆነም ሊያውቁ ይገባል።ድርሻም ብሎ አባባል የለም። ኢትዮጵያ ባለድርሻም ሣትሆን ባለቤት ናት።ድርሻ ወይም ክፍፍል ሊባል የሚቻለው በግብጽና ሱዳን መካከል በሚደረገው የውሀ አጠቃቀም ነወ። በተፈጥሮ መናጋት፣ በወረርሽኝ በሽታ መጠቃት፣ በውስጥ የፖለቲካ ሹክቻቸውን ለማርገብ የቅኝ ገዢዎችን የተበተነና ያልተ ቋጨ ቀልድ ይዘው መዝረክረክና ማወናበድን ትተው ወደ ራሳቸው ውሳኔ ቢመለሱ ይሻላቸዋል። ግብፅና ሱዳን፣ ለአፍሪካ የውስጥ ጉዳይ በአሁኑ ጊዜ የቀድሞው የቅኝ ገዥዎችን ድንጋጌ ወይ ውሳኔ ማንሳት አፍሪካ አሁንም በቀጥታ በቅኝ ገዥዎች ትተዳደራለች ወይም ትመራለች እንደማለት ሊያስቆጥራቸው ያስፈልጋል።
ለወደፊት በሁሉም የጋራ ተጠቃሚ አገሮች ዘንድ የሚሆን መልካሙ ሁሉ መሆን አለበት።የግብፅ መንግሥት ትልቁ ስጋት የውሀ ዕጥረት ወይም ዕጦት አይመስለኝም፤ አይደለምም።በአሁኑ ጊዜ በግብርናው ዘርፍ አፈር እንዳይሸረሸር ዕርከን ስራ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ እጅግ በላቀ ሁኔታ እየተሠራ በመሆኑ በወኪሎቻቸው መረጃ ስለሚደርሳት፤ ግብፅ የኢትዮጵያ ለም አፈር ስለቀረባት አቅበጥብጧት በአባይ ውሀ አሳበበች እንጂ የውሀ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡
ግብፅ የህዳሴ ግድቡን ለሃሳብ ልውውጥና ድርድር ማቅረብም የለባትም ነበር።ኢትዮጵያ ግን የራሷ ሀብት በሆነው የዓባይ ወንዝ ውሀ ሳትመጻደቅና መብቴ ነው ብላ ለራሷ ብቻ ልጠቀም ሳትል ከሌሎች ሀገራት ጋር ለጋራ ልማት እንጠቀም ማለቷ የምትደነቅበት ሊሆን ሲገባ፤ የውሀ ማግኘት ሰፊ አማራጭ መንገድ ያሏት ግብፅ ፤ እውነትና ሃቅ ላይ ተመስርታ ብትጠቀም ይበጃታል።
ግብፅ አብዛኛውን ጊዜ የማወናበጃ መሠረቷ ወይም አባባሏ ውል የሚል የራሷ የሆነ ኃይለ ቃል ትጠቀማለች። ውል በህግ ይፈርሣል። ውል በህግ ይጸናል እንጂ ማንም ተነስቶ ውል ነው ብሎ ሊያነብ ወይም ሊያነበንብ አይችልም።ውል የሚፈርሰው በህግ ቅብ ያልተያዘ ወይም በህግ ያልተቀረፀ እንደ 1902 ዓ.ም 1929 ዓ.ም እና 1959 ዓ.ም ባለቤት አልባ እማኝ እና ሰሚ የለሽ የቢሮ ሣይሆን የጓሮ ፊርማ ዓይነት ነው። ውል የሚፀናው ሰው ሰውን ማወቅ ከጀመረ ማለትም ማህበረሰብ ተመስርቶ ሸንጐ ወይም ፓርላማ በጉዳዩ ሀሳብ ሰንዝሮበት ውል አስፈጻሚና ፈጻሚ ተገኝተው ወይም የሀገር ተወካዮች በጋራ ተወያይተውበት የሚደረግ አፈጻጸም ነው። በሀገር ጉዳይ ሲሆን፤ ግብፅ ግን የቅኝ ገዢዋ ጌታ ፊት ቆማ በሰሀራ ምድረ በዳ አእምሮ የሚያዛባ ሐሩር ላይ ሆኖ በደረቀ ቀለም፣ የሌላው የእኔ ነው ብላ የፈረመችውን ውል ይጽናልኝ ብላ አራዳነቷን በማሣየት ማንገራገሯ አያዋጣትም።
ግብፅ ዓለም ከተፈጠረ እስካሁን የሞኝነት ጊዜ በሰጣት ዕድል በኢትዮጵያ ውሃ ህይወቷን ስታኖር ቆይታለች፤ አሁንም ኢትዮጵያ ግብፅንም ሆነ ሌላውን ውሀ አሳጥታ ህይወትን አትነፍግም።ኢትዮጵያ የምትለው ሥርዓት፣ ህግና፣ ዕውነት፣ ይኑሩ ነው። በጋራም ውሀውን እንጠቀም ከማለት አልቦዘነችም።ከዚህ ውጪ ዓሣ ከውሀ ውስጥ ከወጣ ዕድሜው አንድ መቶ ሃያ ስከንድ ነው።የግብፃውያን ዕድሜ ግን የዓባይ ውሃን መጠቀም ከጀመሩ እስካሁን ድረስ ቆይተዋል።ካሁን በኋላ ለዓባይ ውሀ ዋጋ ካልተከፈለ በህይወት ለመኖር ወይም እንደ ዓሣው ለመሆን ምርጫው የእነሱ ነው፡፡
ከመኮንን አበበ ተሰማ
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2013