አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ሰላም እንዳትሆንና እንዳትለማ የሚደረገውን የውጭ ጫና ወጣቱ አንድ በመሆን መመከት እንደሚገባ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለማውገዝና 2ኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ለመደገፍ የወጡ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች አስታወቁ ፡፡ ‹‹ድምጻችን ለነጻነታችን እና ሉዓላዊነታችን›› በሚል መሪ ቃል የውጭ ጣልቃ ገብነትን ለመቃወም የወጣችው ተማሪ ሕሊና አያሌው እንደገለፀችው፣ በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ግድብ ገንብታ እንዳትለማና ምርጫ አድርጋ እንዳትረጋጋ ለማድረግ በርካታ የውጭና የውስጥ ጫናዎች እየተደረጉ ነው። በተለይ ኃያላን ሀገራት በውስጥ ጉዳያችን በመግባት ለመከፋፈል ብዙ ጥረቶችን እያደረጉ ነው ብላለች፡፡
ኢትዮጵያ ከምን ጊዜውም በላይ ወጣቱ የውስጥ አንድነቱን እንዲያጠናክር፣ እንዲተሳሰብ፣ ለሀገር ሉዓላዊነት መስዋዕትነት እንዲከፍል አጥብቃ ትፈልጋለች ያለችው ተማሪ ሕሊና፣ ሁሉም ወጣት ያለመድከም ተቻችሎ ለአገሩ ዘብ ሊቆምና የአባቶቹን ታሪክ ሊደግም ይገባል ብላለች ።የውጭ ጫናን መመከትና መበልጸግ የሚቻለው ጠንክሮ በመስራት በመሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለሀገራችን ልንቆም እንደሚገባም አሳስባለች፡፡
ሌላኛው ሀሳቡን ያካፈለን ወጣት ኑረላ መሐመድ በበኩሉ ዛሬ የተደረገው ተቃውሞ ኢትዮጵያ ታሪክ መድገም የሚችል ወጣት እንዳላት የታየበት ነው ብሏል ። በተለይ ኃያላን አገራት እንደፈለጉ ጣልቃ ስላላስገባናቸው የህዳሴው ግድብን እንዳንገነባ በርካታ እንቅፋቶችን ሲፈጥሩ ቆይተዋል ያለው ወጣት ኑረላ፤ በተለይ አሜሪካ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በግልጽ ለግብጽ ያደላ ድጋፍ እያደረገች መሆኑን ጠቁሟል ፡፡
“ኢትዮጵያ ሁሌም በጠላት እንደተፈተነች ነው፣ ነገር ግን አንድም ቀን ተሸንፋ አታውቅም” ያለው ወጣት ኑረላ፣ ወጣቱ አንድ ከሆነ አሁን የሚስተዋለው ጫና ቀደም ሲል ከነበሩ ጫናዎች የተለየ አይሆንም፤ በዘይትና በስንዴ ሳንደለል ጠላቶቻችንን ድል በማድረግ አድዋን ለመድገም ዝግጁ ልንሆን ይገባል ሲልም አስተያየቱን አክሏል።
ወጣቱ አድዋን እያሰበ ብቻ እንዳይኖር አድዋን የሚያስደግም አጋጣሚ በመሆኑ ተባብሮ የአገሩን አንድነት ሊያስከብር እንደሚገባ የጠቆመው ወጣት ኑረላ፤ እንዲሁም ልማትን በማፋጠን ኢትዮጵያ ሰላም እንድትሆን ሚናውን መወጣት አለበት ብሏል።ይህ ሳይሆን ቀርቶ ሴረኞች ያሰቡት ከተሳካ ወጣቱ በታሪክ ተወቃሽ እንደሚሆንም አስገንዝቧል፡፡
ወጣት ቅድስት ወልዴ በበኩሏ፣ የአገር መሪዎቻችን የአገራችንን ጥቅም አሳልፈን አንሰጥም በማለታቸው ብቻ አሜሪካ የጣለችውን ማዕቀብ እንደምትቃወም ጠቁማ፤ኢትዮጵያን ከውጭና ከውስጥ ሁነው ሊያፈርሷት ያሰቡ አካላት ብዙ በመሆናቸው ወጣቱ የአባቶቹን ታሪክ የሚያስተውልበትና ቆም ብሎ ከአባቶቹ ጥበብን የሚቀስምበት ጊዜ ነው ብላለች፡፡ ለአገር ሲባል የሚከፈል መስዋዕትነት ሁሉ መከፈል አለበት ያለችው ቅድስት፣ ሀገር ከሌለ ማንም አይኖርም ።ሁሉም ዜጋ የጠላት ሴራን በመረዳት ለአገሩ ሰላም ድርሻውን በማበርከት የህዳሴውን ግድብ በመጨረስ ታሪክ የሚሰራበት ጊዜ ነው ስትልም አስተያየቷን አጠቃላለች፡፡
በአዲስ አበባ የወጣቶችና የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ አብርሃም ታደሰ፣ ይህ ተቃውሞ ወጣቶች አንድነታቸውን ያሳዩበት፣ የውስጥና የውጭ ጠላትን አንገት ያስደፋ ተግባር እንደሆነ ጠቁመው፤ አገራችን በተለያዩ ጊዜያት ከውጭ የሚቃጣባትን ጫና ለመቋቋም ሕይወታቸውን በመስጠት ከትውልድ ወደ ትውልድ እንድትሸጋገር ያደረጉ የአባቶች ታሪክ መደገም እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የውጭ ጣልቃ ገብነትን በመቃወም የአገርን ሉዓላዊነት የማታስደፍሩ የቁርጥ ቀን ልጆች ናችሁ ያሉት ኃላፊው፣ ይህ አንድነት ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል። የሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት የምናደርገው እንዳንለማ፣ እንዳንበለጽግና ሰላም እንዳንሆን የሚፈልጉ አካላት እንደሚያወሩት ሳይሆን ከድህነት ለመውጣት እንጅ ማንንም ለመጉዳት አይደለም። በውስጥ ጉዳያችን ኢትዮጵያውያን እንጅ ማንም ጣልቃ መግባት አይችልም፤ እድሉም አይሰጠውም ሲሉም ተናግረዋል ።
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2013