ፑቲን«ምእራባውያን በሩሲያ ንብረት ላይ ለፈጸሙት ስርቆት ይቀጣሉ» ሲሉ ዛቱ

ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን “ምእራባውያን በሩሲያ ንብረት ላይ ለፈጸሙት ዝርፊያ ያለ ቅጣት አይታለፍም” አሉ። የቡድን 7 አባል ሀገራት ሩስያ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ካላት እንዳይንቀሳቀስ ከታገደው ገንዘብ 50 ቢሊዮን ዶላር ለዩክሬን በብድር መልክ እንዲሰጥ መወሰናቸው ይታወቃል።

አባላቱ የሩስያ ማዕከላዊ ባንክ በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ያስቀመጠው 300 ቢሊዮን ዶላር ካስገኘው ወለድ ላይ ነው ገንዘቡ ለኬቭ እንዲሰጣት የወሰኑት። ይህንን ተከትሎም ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን “በምዕራቡ ዓለም የሩስያ ንብረት ላይ የፈጸሙት ስርቆት ከቅጣት አያመልጡም ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን አርብ እለት እንደተናገሩት ምዕራባውያን ሀገራት በውጭ ከታገዱ የሩስያ ንብረቶችን በመጠቀም ለዩክሬን ብድር ለመስጠት ማቀዳቸው ሌብነት ነው ብለዋል። ፑቲን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት፥ ምዕራባውያን ሞስኮን የያዙበት መንገድ የትኛውም ሀገር በምዕራቡ ዓለም ተመሳሳይ የንብረት እገዳ ሰለባ ሊሆን እንደሚችል ያሳያል ብለዋል።

“ምንም ምክንያት ቢደረደርም ስርቆት ስርቆት ነው” ያሉት ፑቲን፤ የስርቆት ወንጀል ደግሞ ያለ ቅጣት አይታለፍም ሲሉም ዛቻ የተቀላቀለበት መልእክት አስተላለፈዋል። አሁን ላይ በተለይም በምእራባውያን ሀገራ ተከማችተው የሚገኙ የሁሉም ሀገራት እና ኩባንዎች እና ገንዘቦች እና ንብረቶች በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ አይደለም ያሉት ፑቲን፤ “የትኛውም ሀገር በአሜሪካና እና በምዕራቡ ዓለም ለመበዝበዝ የተጋለጠ ነው” ብለዋል።

ሩሲያ ጦሯን ወደ ዩክሬን መላኳን ተከትሎ ጦርነት ከተጀመረ 843 ቀናት ያስቆጠረ ሲሆን፤ ይህ ጦርነት በሩሲያ ላይ ከስድስት ሺህ በላይ ማዕቀቦች እንዲጣሉባት አድርጓል።

አሜሪካ እና ምዕራባውያን ሀገራት ከማዕቀቡ ባለፈ የሩሲያ መንግሥት እና ባለሀብቶች ንብረት የሆኑ ሁሉንም ሀብቶች እንዳይንቀሳቀሱ ያገዱ ሲሆን ጦርነቱ መቀጠሉን ተከትሎ ዩክሬንን መልሶ ለመገንባት የሩሲያውያንን ገንዘብ ጥቅም ለማዋል ማቀዳቸው ይታወሳል።

ሩሲያ ከዚ ቀደም በሰጠችው መግለጫ፤ እንዳይ ንቀሳቀሱ እገድ የተላለፈባቸው የሩሲያውያን ሀብትን ለዩክሬን መስጠት የሚያስችል ዓለም አቀፍ ሕግ እንደሌለ መግለጿ ይታወሳል። ድርጊቱ ሌላ ዓለም አቀፍ መዘዝ ያስከትላል ስትል በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል አስታውቃም ነበር።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2016 ዓ.ም

Recommended For You