አገልግሎቱ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጁን ዳግም አሻሽሎ እንዲያቀርብ ቋሚ ኮሚቴው አሳሰበ

አዲስ አበባ፡- የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ያዘጋጀውን የማሻሻያና እንደገና የማቋቋሚያ አዋጁን ዳግም አሻሽሎ እንዲያቀርብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ::

ምክር ቤቱ ባዘጋጀው የሕዝብ አስተያየት መስጫ መድረክ ለይ የተገኙ የሕግ ባለሙያዎች አገልግሎቱ ያዘጋጀው የማሻሻያ እንደገና የማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻያ አንዲደረግበት ጠይቋል:: ተሳታፊዎች በተለይም እገዳንና ተጠርጣሪን ማቆየትን በተመለከተ የተቀመጡት አንቀጾች መሻሻል የሚገባቸው መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል::

የአገልግሎቱ የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እንደገና ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ በክፍል ስድስት የአገልግሎቱን ሥልጣንና ተግባር በተመለከተ ባስቀመጠው አንቀጽ ከኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ጋር በተያያዘ በወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች የሚቆዩበትን ጊዜያዊ ቦታ ያዘጋጃል፤ ያስተዳድራል፤ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ለፍትህ ሚኒስቴርና ለሚመለከተው አካልም ያሳውቃል ይላል።

በተጨማሪ በኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 354/95 ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ አንቀጽ ሰባት ከዚህ በፊት ማንኛውም ሰው ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ ሊታገድ የሚችለው በሕግ መሠረት በፍርድ ቤት ሲታዘዝ ነው። ነገር ግን በማሻሻያው የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ከሚመለከታቸው የደህንነት አገልግሎትና ሕግ አስከባሪ አካላት ከሚያገኘው መረጃ፤ ወይንም አገልግሎቱ በራሱ ከሚያገኘው መረጃ በመነሳት ብሄራዊ ጥቅምና ደህንነት ለይ ሊቀለበስ የማይችል ግልጽና ፈጣን የሆነ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል ሁኔታ መኖሩን ሲያምን ማንኛውንም ሰው ከሀገር እንዳይወጣ ለማገድ የሚያስችለውን ሥልጣን አስቀምጧል።

የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ፉአድ ኪያር ከላይ በተቀመጡት ሁለት አንቀጾች ላይ ባቀረቡት አስተያየት አዋጆቹ መሻሻል ቢኖርባቸውም የተካተቱት አንቀጾች ግን ክፍተት አለባቸው። ከዚህም ውስጥ እንደገና በማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጁ የአገልግሎት ሥልጣንና ተግባርን በተመለከተ በተቀመጠው አንቀጽ ስድስት የተቀመጠው የማቆያ ቦታን የተመለከተው መፈተሽ ያለበት ነው። ምክንያቱም በወንጀል ሕጉ የሰዎችን ማሰሪያ ቦታ የማዘጋጀት ሥልጣን የተሰጠው አካል ፖሊስ ብቻ በመሆኑ ከህጉ ጋር የተጣረሰ ሊሆን ይችላል። ከተያዙ በኋላም እነዚህ ሰዎች መቅረብ ያለባቸው ለፖሊስ ሲሆን በ48 ሰአት ውስጥ ለፍርድ ቤት መቅረብ ይኖርባቸዋል። በመሆኑም ይሄ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ እንዳይጣስ ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል።

በተመሳሰይ ከሀገር ለመውጣት እገዳን በተመለከተ ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 32 የመዘዋወር መብትን አስቀምጧል። በዚህም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንዲሁም በሕጋዊ መንገድ በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመንቀሳቀስ የመኖሪያ ቤት የመመሥረት እንዲሁም በፈለገ ጊዜ ከሀገር መውጣት እንደሚችል ያስቀምጣል። ይህም ሆኖ በተለያዩ ጉዳዮች ከሀገር እንዳይወጡ የሚደረጉ ዜጎች ውሳኔ ሊሰጥባቸው የሚገባው በፍርድ ቤት ነው። በመሆኑም የተቀመጠው አንቀጽ ይህንን የሚጣረስ እንዳይሆን ሊፈተሽ ይገባል። ማገዱ አስፈላጊ ቢሆን እንኳን ለምን ያህል ጊዜ ሊሆን እንደሚገባ ሊቀመጥ ይገባል ብለዋል።

የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት ለተነሱት ጥያቄዎች በሱጡት ምላሽ የአዋጁ ዓላማ የሀገርን ደህንነትና ብሄራዊ ጥቅም መሠረት ያደረገ ነው። በአንዳንድ ጉዳዮች እርምጃው ካልተወሰደ ሀገርን ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍሉ የሚችሉ ሊሆኑ ይላሉ። በመሆኑም ሊታይ የሚገባው የሰዎችን የመንቀሳቀስ መብትና የሀገርን ደህንነት እኩል ለመጠበቅ ከግምት በማስገባት ይሆናል ብለዋል።

ከሀገር እንዳይወጡ እገዳ የሚጣለውም በብሄራዊ ጥቅምና ደህንነት ላይ ሊቀለበስ የማይችል ግልጽና ድርስ ከፍተኛ አደጋ ሊያስከትል የሚችል ሁኔታ ሲኖር ብቻ ነው። እርምጃው የሚወሰደውም ሁሉም ሰው ላይ ሳይሆን ሀሰተኛ ዶክመንት ይዘው የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው የተረጋገጠባቸው ላይ ይሆናል። ይህ አሠራር የተለያዩ ሀገራት እየተጠቀሙበት ያለና ውጤት ያስመዘገበ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ራስወርቅ ሙሉጌታ

አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2016 ዓ.ም

Recommended For You