በህንድ ሁለት ባቡሮች ተጋጭተው የሰዎች ሕይወት አለፈ

በህንድ በደረሰ የባቡር ግጭት አደጋ እስካሁን የ13 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ 30 ሰዎች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተነግሯል።

አደጋው የደረሰው ትናንትና የመንገደኞች እና እቃ ጫኝ ባቡሮች በመጋጨታቸው እንደሆነ የገለጸው የአካባቢው ፖሊስ የአደጋውን መንስኤ እያጣራሁ ነው ብሏል። በምስራቅ ህንድ ዌስት ቤንጋል ክልል የደረሰውን አደጋ ተከትሎ የነፍስ አድን ሠራተኞች በሕይወት የተረፉ ሰዎችን በማፈላለግ ላይ ይገኛሉ።

የአደጋው መንስኤ ምን እንደሆነ ያልገለጸው ፖሊስ በአሁኑ ወቅት ሰዎችን ለማትረፍ ርብርብ በመደረግ ላይ ነው ብሏል። የሀገሪቱ የባቡር ትራንስፖርት ሚኒስትር አሽዋኒ ቫይሽናው የመንገደኞች ባቡሩ በእቃ ጫኝ አውሮፕላን ከኋላው በመገጨቱ አደጋው መድረሱን ገልጸው ዝርዝር ጉዳዮች ከሙሉ ምርመራው በኋላ ይፋ ይደረጋል ነው ያሉት።

በአደጋው እስካሁን የ13 ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን ቁጥሩ ከዚህም ሊጨምር እንደሚችል ቢቢሲ ዘግቧል። የ 1.4 ቢሊዮን ሕዝብ ባለቤት በሆነችው ህንድ በከተማ ውስጥ እና ከከተማ ውጭ ለሚደረግ ጉዞ ባቡር ቀዳሚው የትራንስፖርት አማራጭ ነው።

ባለፉት ዓመታትም በርካታ አሰቃቂ የባቡር አደጋዎች ተከስተው የብዙ ሰዎችን ሕይወት ነጥቀዋል። ለአብነት በባለፈው ዓመት በሀገሪቱ ምስራቅ ክፍል ሶስት ባቡሮች ተጋጭተው 290 ሰዎች ሲሞቱ ከአንድ ሺህ የሚልቁት ደግሞ መጎዳታቸው ይታወሳል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2016 ዓ.ም

Recommended For You