በጠንካራ ፉክክር የተጠናቀቀው የክለቦች የፈረስ ስፖርት ቻምፒዮና

የኢትዮጵያ ፈረስ ስፖርት አሶሴሽን በየዓመቱ የሚያዘጋጀው የክለቦች ቻምፒዮና የማጠቃለያ ውድድር በፉክክሮች ታጅቦ ፍጻሜውን አግኝቷል። ስምንት ክለቦች በተሳተፉበት በዚህ ቻምፒዮና በስድስት የውድድር ዓይነቶች ፉክክሮች ተደርገዋል፡፡

ዓመታዊው የፈረስ ስፖርት ክለቦች የማጠቃለያ ውድድር ሰኔ 8/2016 ዓም በአዲስ አበባ ጃንሜዳ የተካሄደ ሲሆን ስምንት ክለቦች ጠንካራ ፉክክር አድርገውበታል፡፡ ክለቦቻቸውን የወከሉ የፈረስ ስፖርት ተወዳዳሪዎች በተሰጠው ሰዓትና የመሰናክል ከፍታ ዝላይ አስደናቂ ትርኢቶችን ማስመልክት ችለዋል፡፡በርካታ ዙሮችን ባፋለመው የፈረስ መሰናክል ዝላይ ውድድር የታየው ፈታኝና እልህ አስጨራሽ ፉክክርም የተመልካቹን ቀልብ የሳበ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ፈረስ ስፖርት አሶሴሽን ለአራተኛ ጊዜ ባዘጋጀው ዓመታዊ የማጠቃለያ ውድድር ላይ ድንቅ ፈረሶችን እና ስፖርተኞችን አቅማቸውን በማሳየት ውድድሩን በፉክክር የታጀበ አድርገውታል፡፡ ይህም በደማቅ የተመልካች ድጋፍ እንዲታጀብ ያደረገ ሲሆን፣ የቤተ መንግስት አስተዳደር፣ አዲስ አበባ ፖሊስ፣ አዲስ አበባ ሶሳይቲ፣ ዲኤች ገዳ፣ ቤካ ፈርዳ፣ ፍሬተስ፣ ካቫሊኖ እና ወታደራዊ አካዳሚ በውድድሩ የተሳተፉ ክለቦች ናቸው፡፡

በአዋቂዎች እና በህጻናት ምድብ 89 ስፖርተኞች በስድስት የውድድር ዓይነት ተፋልመዋል፡፡ በህጻናት (በኤክስ ክላስ፣ ዋይ ክላስ)፣ ዜድ ክላስ (እድሜያቸው አነስተኛ ሆኖ በችሎታ ላቅ ያሉ ስፖርተኞች) እና የአዋቂዎች (ኖቪስ) ወይም ከዚህ በፊት በውድድር ተሳትፎ የማያውቁ ፈረሶችና ስፖርተኞች ተሳትፈዋል። የአዋቂዎችና ከፍተኛ ልምድና ብቃት ያላቸው ስፖርተኞች በሶስት (የሲ ክላስ፣ ቢ ክላስ እና ኤ ክላስ) ምድቦች በጠንካራ ውድድር አድርገዋል፡፡

በዚህም መሰረት በየምድቡ ውድድራቸውን በማድረግ ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቁ ስፖርተኞች የሜዳሊያና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ በየምድቡ ድንቅ ፉክክር በማስመልከት አሸናፊ ለሆኑ ስፖርተኞች እንዲሁ የዋንጫ ሽልማት ሊበረከትላቸው ችሏል፡፡

በኤክስ (ህጻናት ክላስ) ብርቄ ንጉሱ ከቤካ ፈርዳ ፈረስ ስፖርት ክለብ አንደኛና የዋንጫ ተሸላሚ መሆን የቻለች ሲሆን፣ በዋይ ክላስ ፈጠነ ንጉሱ በተመሳሳይ ከቤካ ፈርዳ፣ በዜድ ክላስ ናትናኤል ሙሉጌታም እንዲሁ ከቤካ ፈርዳ፣ በኖቪስ (አዋቂዎች) ዳንኤል በላይ ከአዲስ አበባ ፖሊስ፣ በሲ ክላስ ትንሹ ተወዳዳሪ ፈጠነ ንጉሱ ዳግም ከቤካ ፈርዳ አሸናፊና ዋንጫ ተሸላሚ መሆን ችለዋል፡፡ በአዋቂዎች (የኤ ክላስ) መሃመድ ሳሚ ከካቫሊኖ ፈረስ ስፖርት ክለብ የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊና የዋንጫ ተሸላሚ ሆኖ ውድድሩን አጠናቋል፡፡

ውድድሩ ዓመታዊ የክለቦች የማጠቃለያ እና ክለቦች በዓመቱ ሶስት ውድድሮች ያሳዩት አቋምን የሚለኩበት እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡ በዓመቱ በጃን ሜዳ፣ ጣሊያን ኤምባሲ እና ፈረንሳይ ኤምባሲ ሶስት ውድድሮች የሚካሄዱ ሲሆን ይህም የማጠቃለያ ውድድር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፈረስ ስፖርት አሶሴሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘሪሁን ቢያድግልኝ፣ ውድድሩ በዝግጅትና በፉክክር ከምንጊዜውም የተሻለ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በፈረስ ስፖርት ተወዳድረው የማያውቁ አዳዲስ፣ ህጻናትና አዋቂ ስፖርተኞች በመሳተፋቸው ተተኪዎችን ለማፍራት ያግዛልም ብለዋል፡፡ በህጻናት (ኤክስ ደረጃ) ከዚህ በፊት በውድድር ተካፍለው የማያውቁ ስምንት የሚደርሱ አዳዲስ ስፖርተኞችም መሳተፍ ችለዋል፡፡

የማጠቃለያ ውድድር እንደመሆኑ ስፖርተኞች በዓመቱ ውድድሮች አቋማቸውን የሚገመግሙበት እና በቀጣይ ለሚደረጉ ውድድሮች የሚዘጋጁበት ነው። ውድድሩ ስኬታማ በሆነ መልኩ መካሄዱን የገለጹት ኃላፊው፤ በርካታ ተቋማትና የመገናኛ ብዙኃን ድጋፍቸውን እንዳሳዩም ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም የስፖርት ቤተሰቡ ለፈረስ ስፖርት ያለውን ፍቅር ማሳየቱ ለየት ያለ ውድድር እንዳደረገው ጠቅሰዋል፡፡

የፉክክሩን ደረጃ ከፍ የማድረጉ እና የክለቦችን ቁጥር የመጨመሩ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው ፣ የፈረንሳይ ኤምባሲ ዘጠናኛ የአሶሴሽኑ አባል ሆኖ መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡ የጀርመንና የእንግሊዝ ኤምባሲዎችም እንዲሁ የአሶሴሽኑ አባል ለመሆን በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ በመሆኑም በ2017 ዓም የአሶሴሽኑ አስረኛና አስራ አንደኛ አባል ሆኖ እንደሚቀጥሉ እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዓመቱ ውድድሮች ላይ የተስተዋሉ ችግሮችና ጠንካራ ጎኖች የተለዩ ሲሆን እነዚህን በመገመገም ለሚቀጥለው የውድድር ዓመት አሻሽሎ ለመቅረብ ይሰራልም ተብሏል፡፡

አለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2016 ዓ.ም

Recommended For You