ተቀጣሪዎች የሥነምግባርና የፀረሙስና ሥልጠና እንዲወስዱ የሚያስገድድ ፖሊሲ እየተዘጋጀ ነው

አዲስ አበባ፡- ተቀጣሪዎች የሥነምግባርና የፀረሙስና ሥልጠና እንዲወስዱ የሚያስገድድ ፖሊሲ እየተዘጋጀ መሆኑን ተገለጸ።

ኮሚሽኑ ሥራ የሚቀጠሩና በሥራ ላይ ያሉ ዜጎች የሥነምግባርና ጸረሙስና ሥልጠና እንዲወስዱ የሚያስገድድ ፖሊስ አዘጋጅቶ የግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይት ትናንትና አካሂዷል።

የአዲስ አበባ ሥነምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አሰፋ ቶላ ረቂቅ ፖሊሲውን ባቀረቡበት ወቅት እንደገለፁት፤ ፖሊሲው ተመራቂ ተማሪዎች ሥራ ለመቀጠር የሥነምግባር ሥልጠና በመውሰድ የሠለጠኑበትን ምስክር ወረቀት እንዲኖራቸው የሚያስገድድ ይሆናል።

በሥራ ላይ የሚገኙ ሁሉም ሠራተኞችም የሥነምግባርና ጸረሙስና ሥልጠና ወስደው ለአምስት ዓመት የሚያገለግል የምስክር ወረቅት እንዲወስዱ የሚደረግ መሆኑም በፖሊሲው ተቀምጧል ብለዋል።

የፖሊሲው መተግበር ሥነምግባር ያለው ሠራተኛ ለማፍራትና ሙስናን ቀድሞ ለመከላከል እንደ ቅደመ ሁኔታ የሚታይ ነው ያሉት አቶ አሰፋ፤ የፖሊሲው መተግበር ልጆችን በሥነ ምግባር አንጾ ከማሳደግ አኳያ ኢትዮጵያ ያሏትን በርካታ እሴቶች አስጠብቆ ለማስቀጠል የሚረዳ መሆኑንም አስረድተዋል።

ሙስናን በመከልከል ረገድ ኢትዮጵያ ሕግ አዘጋጅታ እየሠራች ቢሆንም፤ ከተቋማት መቀናጀት አንጻር ክፍተቶች እንደሚስተዋል የጠቆሙት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ከሙስና ጋር ተያይዞ የሚቀርቡ ጥቆማዎችን ተከታትሎ አለመሥራትና፣ ለሙስና ተጋላጭ በሆኑ ተቋማት ላይ ጥልቅ ክትትል ያለማድረግ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

በተጨማሪ ሕጉን የሚያስከብረው ፖሊስ፣ አቃቤ ሕግና ጸረሙስና ኮሚሽንም በኩል ተቀናጀተው በመሥራትና ሕግ በማስከበር እረገድ ክፍተቶች ይስተዋላሉ። የፖሊሲው መጽደቅና መተግበር እነዚህን ተግዳሮቶች ለመሻገር የሚያስችል ይሆናል ብለዋል።

በየካ ክፍለ ከተማ የፍትህ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ገብሬ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ አሁን ላይ የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት ሙስናን ለመከላከል የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚና በፖሊሲው ላይ በግልጽ መቀመጥ አለበት።

ከዚህ ቀደም የጸረሙስና ኮሚሽን ሲመረሰረት ከምርመራ ጀምሮ ጥቆማዎችን ተቀብሎ ሀብት የማስመለስ ሥራ ይሠራ ነበር፤ አሁን ለይ ግን ይህ ተግባር ለተለያዩ ተቋማት ተከፋሎ ተሰጥቷል ሲሉ አንስተዋል።

በፖሊሲው በግልጽ ሙስናን መከላከልና ሀብት የመመዝገቡ ሃላፊነት በኮሚሽኑ እንዲሠራ፤ ምርመራው በፖሊስ እንዲካሄድና ክስ የሚመሰርተው አቃቤ ሕግ እንደሚሆን ተለይቶ ቢቀመጥ ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ያስችላል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

«ፖሊሲው ከመከላከል በተጨማሪ ሀብት ማስመልስም ላይ ትኩረት ቢያደርግ መልካም ነው» ያሉት ደግሞ የሥነ ትምህርት ባለሙያ የሆኑት አቶ መልሰው ጥላሁን ናቸው።

ባለሙያው እንዳብራሩት በርካታ ሀብት ከሀገር ውጭ እየወጣ ይገኛል። ይህንን በመከላከል የሕዝብና የመንግሥት ንብረትን ለመታደግ ዓለም አቀፍ መመሪያዎችን መሠረት ያደረጉ ፖሊሲዎችን በማዘጋጀት ወደ ሥራ መግባት የሚጠበቅ ይሆናል ብለዋል።

ሠራተኞች እንዲወስዱት የሚደረገው የሥነምግባርና የጸረሙስና ሥልጠናም በዘርፉ ውጤታማ ሥራ ለማከናወን ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2016 ዓ.ም

Recommended For You