አዲስ ዘመን ድሮ

በ1962 ዓ.ም የታተሙ ጋዜጦችን ለዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን መርጠናል፡፡ ከ1950ዎቹም የተለያዩ አስደናቂ ዘገባዎችን አካተናል፡፡ በኤሌክትሪክ የሚሽከረከር አውቶሞቢል ተሠራ የሚለው ዜና ብዙዎች የዘመናችን ከስተት አድርገው ቢመለከቱትም ግኝቱ የቆየ ስለመሆኑ ይህ ዘገባ ይነግረናል፡፡ ይህንንና ሌሎች ቆየት ያሉ ዘገባዎችን ለትውስታ ያህል እንመልከት፡፡

በኤሌክትሪክ የሚሽከረከር አውቶሞቢል ተሠራ

የጥንቱ ጥበብ ባቀረበው በቤንዚን ናፍጣና በላምባ ሲሽከረከር በኖረው ፤ በድሮውና በዛሬው ተሽከርካሪ ምትክ የሚያገለግል ፤ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሮጥ ኦቶሞቢል ተሠርቷል፡፡ ኦቶሞቢሉ እገበያ ውስጥ የሚውለውና ለሽያጭ የሚቀርበው ጊዜ የጠተወሰነ ባይሆንም፤ ትክክለኛውን ውጤት ለዓለም ጋዜጦች የሚያቀርበው በ ፲፱፻፷፫ የኢትዮጵያዊ ዓ.ም ማብቂያ ግድም እንደሆነ ታውቋል፡፡

ይህንንም መኪና ሠርቶ ለማውጣት የወሰደው የጥናት ጊዜ ፤ ከ፲ ዓመታት በላይ ፈጅቷል፡፡ መኪናውን በእሳት ኃይል ሊያንቀሳቅስ የሚችለው የባትሪው አሠራር ልዩ ዘዴ ነው፡፡

ምንም እንኳ እስከዛ ድረስ በሌላ ሰው እጅ ባይታይም አንዲት አነስተኛ ካሚዎኔት ተሠርቶ ለሙከራ ያህል በሰዓት ፹ ኪሎ ሜትር እየተሽከረከረ ጥሩ ውጤት አሳይቷል፡፡

የተሞከረበት ጐዳና ርዝመት ፩፻፳ ኪሎ ሜትር እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ሆኖም፤በዚህ በረራ ላይ ባትሪው እያለቀ ጉልበት መቀነስ ስለአለበት በየጐዳናው ላይ ስምንት ጊዜ እየተሞላ የተጓዘ መሆኑን ዮዓሣ በሚል የሚታወቀው የጃፓን የመኪና ፋብሪካ አመለከተ ሲል አንድ የፈረንሳይ ዕለታዊ ጋዜጣ ገለጠ፡፡

(አዲስ ዘመን ጥቅምት 22 ቀን 1962 ዓም)

በየዓመቱ ፩፻፶ ሺህ ቶን ዓሣ በእንዱስትሪ ሊዘጋጅ ነው፡፡

በሦስተኛው የአምስት ዓመት ፕላን ዘመን የዓሣ ሀብት ልማት መሥሪያ ቤት በየዓመቱ ፩፻፵ ሺህ ቶን ዓሣ ለማቅረብ ማቀዱን ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ዓሣ ሀብት ኢኮኖሚ አቋም ተስፋ ያለው ነው፡፡ በዚህ የተነሣ በአንዳንድ ቦታ ካፒታል ያላቸው የውጭ ሀገር ሰዎች የንግድ ቤቶችን አቋቁመው ይገኛሉ፡፡ ከተከፈቱትም የንግድ ቤቶች መካል ራስድኮ የሚባል ኩባንያ በኢትዮጵያና በቡልጋሪያ መንግሥት መካከል በተደረገው ስምምነት መሠረት ተቋቁሞ ዘመናዊ ዓሣ ማጥመጃ መርከቦችን አስመጥቶ ሥራውን ጀምሯል፡፡ ከዚህም ሌላ ሦስት የዓሣ ኢንዱስትሪዎች ተቋቁመው አገልግሎታቸውን በመስጠት ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡

ባለፉት የልማት ዘመን በዓሣ ሀብት ልማት በኩል ለማከናወን ከታሰበው ግብ ባይደረስም፤ ከሞላ ጐደል መፈጸሙ አልቀረም፡፡ በጣም ተስማሚ በሆኑ ቦታዎች ላይ የተሻሉትን ልዩ ልዩ ዓይነት ዓሣዎች የሚያደርቅና በቆርቆሮ የሚያሽግ ፤ ምርጥ ያልሆኑትንም ዓሣዎች ወደ ከብት ምግብነትና ዘይት የሚለውጥ ኢንዱስትሪ ተቋቁሟል፡፡ ለዚህም ኢንዱስትሪ የሚያገለግሉ ዓሣዎች ዓይነትና ብዛት እንደዚሁም ወደፊት በብዛት ለማርባት የሚቻልበትን በአዋሳና በላንጋኖ ሐይቆች ውስጥ ሰፊ ጥናት ለማድረግ ታስቧል፡፡ የዚህ ፕላን ከግቡ እስኪደርስ ድረስ የዓሣ ሀብት የሚሰበስብ ስድስት ሺህ ሠራተኞችና ከ፷ በላይ አነስተኛና ከፍተኛ ዓሣ አጥማጅ ጀልባዎች የሚገኙበት ኢንዱስትሪ ይገኛሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ፤በአሁኑ ጊዜ የሚገኙት ኢንዱስትሪዎች ከሚሠሩት ከዓሣ ሀብት ውጤት ውስጥ አብዛኛው ሰርዲንና ከሊል እናት ዓሣ ነባሪ ተብሎ ከሚሠራው አዝራር ቁልፍ ነው፡፡ እንደዚሁም ልዩ ልዩ ጌጣ ጌጦች ይሠራሉ፡፡ ከዓሣም ጥፍር ለሽቶ መቀመሚያ የሚያገለግል ያወጣሉ፡፡

( አዲስ ዘመን ኅዳር 20 ቀን 1962 ዓም)

ሁለት ራስና ሁለት አፍ ያላት ኤሊ ተገኘች

በሎሣአንጀለስ ከተማ ክልል ውስጥ ባለው የአራዊት ማርቢያ ውስጥ ሁለት አፎች ያሏት ኤሊ በጥንቃቄ በመጠበቅ ላይ መሆኗ ተነገረ፡፡

ኤሊዋ በሁለቱም አፎችዋ በአንድ ጊዜ የምትመገብ ናት፤ ለዘወትር ምግቧ የሚቀርብላት ሠላጣና ሌላ ቅጠላ ቅጠል ነው፡፡

የሎሣአንጀለስ አራዊት ሰብሳቢ ጠበብት ሲናገሩ፤ ኤሊዋ በመብል በኩል ብርቱ ናት፡፡ በልታ በቶሎ አትጠግብም ፤ አንድ ጊዜ መብላት ከጀመረችም ደግሞ የቀረበላትን በሙሉ ልታግበሰብስ የምትችል ናት ብለዋል። ከዚህም በቀር ባለሁለት አፍ ኤሊ በሌላው ክፍል የሌለ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ኤሊዋ አሁንም በሙሉ ጤንነት እዚያው ሎስ አንጀለስ ትገኛለች ሲል የአዲስ ስዋር አራዊት ማርቢያ ዜና አቅራቢ አመለከተ።

(አዲስ ዘመን ጥቅምት 15 ቀን 1962 ዓም )

238 ሰዎች በሦስት ወር ማንበብና መጻፍ ቻሉ

በአድአ ወረዳ ዕድገት ሚኒስቴር አማካይነት ለ3ወር የማንበብና የመጻፍ ችሎታ የሚያስገኝ ትምህርት ሲከታተሉ የቆዩ 238 ጎልማሶች ሚያዚያ 18 ቀን ባለፈው እሑድ ከሕዝባዊ ዕድገት ሚኒስቴር ከክቡር አቶ ጌታሁን ተሰማ እጅ የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል።

(አዲስ ዘመን ሚያዝያ 4 ቀን 1951ዓ.ም)

የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ነርስ

ነርስነት ለምልክት፣ ለደመወዝና ለሌላ ነገር የተሰጠ ስያሜ አይደለም። ሰው ሳያማርጡ በሽተኞችን በቅን መንፈስ ማገልገልና ታዛዥ መሆን ግን የነርስ ተቀዳሚ ሥራ ነው” አሉ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ነርስ ሲስተር ምሕረት ጳውሎስ።

(አዲስ ዘመን የካቲት 26 1956ዓ.ም)

የአምቦ ውሃ ውጭ አገር ሊላክ ነው

በቀን 116ሺህ ውሃ እያዘጋጀ የሚያቀርብ በአምቦ(ሀረር ሕይወት) እንዲቋቋም ስለታዘዘ በኢትዮጵያ ቴክኒክ ድርጅትና በኢጣሊያን ስታይም ኩባንያ ጋር የካቲት 27 ቀን ፩፱፻፶፯ዓ.ም አንድነት ተፈርሟል።

ስምምነቱን የፈረሙት በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የመንግሥት ንብረት ስም አቶ ሀብተ አብ ባይሩ በረዳት ሚኒስትርነት ማዕረግ የቴክኒክ ድርጅት ጽሕፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ሲሆኑ፣ በኢጣሊያ አጥኝነት ሥራ አስፈጻሚ ኩባንያ በኩል ወኪሉ ሚስተር ማንካ ናቸው።

(አዲስ ዘመን የካቲት 28 ቀን 1957ዓ.ም)

አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2016 ዓ.ም

Recommended For You