ወይዘሮ መአዛ መንክር ክሊኒካል ሳይኮሎጂስት ሲሆኑ በሕፃናት የአእምሮ ህክምና ላይ ይሰራሉ። መፅሃፍም ለአንባቢያን አበረከተዋል። ለዛሬም የአእምሮ ጤና በሚል የፌሰቡክ ገፃቸው ካከፈሉን ላይ ፍቃዳቸውን ጠይቀን በዚህ መልኩ አዘጋጅተነዋል።
ስኬታማ ሴት ልጆችን ለማሳደግ የወላጆች ሚና ምን መሆን አለበት? የሚለውን ከማንሳታችን በፊት ስኬታማ ሴት ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን ጥያቄ መመለስ አለብን። ስኬታማ ሴት በራሷ የምትተማመን፣ ውሳኔዎችን የመወሰን አቅም ያላት፣ ምርጫዋን የምታውቅና የሌሎችን ምርጫ የምታከብር፣ ጊዜዋን በዋዛ ፈዛዛ የማታሳልፍ፣ ችግሮችን ለመፍታት የራሷን አስተዋፆ የምታበረክት፣ ስሜትና ሀሳቧን የምትገልፅ፣ እችላለሁ የሚል አመለካከት ያላት፣ ራሷን እና ሌሎችን የምታከብር፣ ሌሎችን ለመርዳት ዝግጁ የሆነች፣ ችግር ባጋጠማት ጊዜ ከችግሩ ይልቅ መፍትሔው ላይ የምታተኩር፣ ለፈጣሪዋ፣ ለባሏ እና ለቤተሰቧ ታማኝ የሆነች፣ የሴቶች የሆነውን ርህራሄ እና ደግነት ያላት፣ ራስ በመቻል የምታምን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የሌሎችን እርዳታ የምትጠይቅ፣ ህይወትን እና ዙሪያዋን በአግባቡ የምትረዳ እና ሌሌችን ለመምሰል ጊዜ የማታባክን፣ በጥላቻ፣ ክፋት እና ሃሜት የሚወረወርባትን ድንጋይ ለውድቀቷ ምክንያት ሳታደርግ ወደከፍታ ለመውጣት ድልድይ የምታደርግ እና ለልጆቿ መልካም አርአያ የሆነች ናት።
ታዲያ እንዲህ አይነት ሴት ለማፍራት ሴት ልጆችን እንዴት እናሳድግ?
1. በዕለት-ተዕለት እንቅስቃሴዋ እኛ እናውቅልሻለን ብለን ለሷ ከመወሰን ይልቅ ራሷ እንድትወስን እድል እንስጣት
2. በውስጧ ጠቃሚ ነገር እንዳለ ተረድተን እናድምጣት
3. ብዙ የህይወት እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንድትሳተፍ በማድረግ ከሚያጋጥሟት ችግሮች እንድትማር እና ከስኬቷ እችላለሁ የሚል መንፈስ እንዲኖራት እናግዛት
4. ሴት ልጅ ማድረግ የምትችለው እና የማትችለው በማለት አንገድባት
5. ኃላፊነቶችን የመወጣት አቅሟ እንዲዳብር ኃላፊነት እንስጣት
6. ብዙ ለውጬ አለም ሚድያ በተለይ በለጋ እድሜ አናጋልጣት ማለትም ስኬት ውበት እና የአርቲፍሻል ጋጋታ እንደሆነ ለማሳየት ስለሚሞክሩ
7. እንደ ቤተሰብ ያለንን ቤተሰባዊ ባህል እናስተምራት
8. ራሷን እንድትወድ እና እንድትቀበል እንርዳት ማለትም ውብ እና አስፈላጊ እንደሆነች በፍቅር እንግለፅላት
9. ከሌሎች ጋር አናወዳድራት፤ ለሌሎች ቀና አመለካከት እንዲኖራት አርገን እናሳድጋት
10. ያላት ዝንባሌ እንዲያድግ እድል እናመቻችላት
ችግር ሲያጋጥማት ችግሮቿን እንዴት መፍታት እንደምትችል እናሰልጥናት እንጅ ችግር አጋጠመን ማለት ወድቀናል ማለት እንዳልሆነ ይልቁንም የምንማርበት እድል እንደሆነ እንንገራት። ሴት ልጆቻችንን እንውደዳቸው፣ እንንከባከባቸው፣ አስፈላጊውን ስልጠና እና ትምህርት እንስጣቸው ደግሞም በነሱ እንደሰት።
ሴት ልጆችን ከላይ በተጠቀሱት መሰረት ማሳደግ ህብረተሰብን ማነጽ ስለሆነ ወላጆች ልጆችን በማሳደግ ሂደት ሊጠቀሙበት ይገባል እንላለን።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/2013