እንዲህ እንደዛሬው ስልጣኔ ባልተስፋፋበት የኔ ያንተ የሚባል ክፍፍልና መገፋፋት ባልሰፈነበት፤ በዚያ ዘመን ሕዝብ የራሱን መሪ በራሱ ይሁንታ ሲሾም አልታየም። ባለፉት በርካታ ዓመታት አገር የመምራት ስልጣን መለኮታዊ ስጦታ እንደሆነ ታሳቢ ተደርጎ አልፏል። ሻል አለ ሲባል ወታደራዊ ጡንቻ የነገሰበትና የዜጐች መብት ያልተረጋገጠበት ሥርዓትም በሀገሪቱ ተግባራዊ ሆኖ ዜጎች ተሰቃይተዋል ። በዚህ ወቅት ታድያ ሥልጣንን በጥቂት ግለሰቦች መዳፍ ውስጥ በማኖር አብዛኛው ዜጋ በጭቆና ውስጥ እንዲዳክር ሆኖ መቆየቱ አንዱ የታሪካችን ዳራ ሆኖ እንዲያልፍ የግድ ሆኗል።
ይህ የታሪክ ጠባሳም ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጡ ታጋይ ልጆች መሪነትና የትግል መስዋዕትነት የብሔር ብሔረሰቦችንና ሕዝቦችን እኩልነት፣ የኃይማኖትና የእምነት ነፃነት እንዲሁም የመሰብሰብ፣ የመደራጀትና ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ፣ የመምረጥና የመመረጥ ዴሞክራሲያዊ መብትን ለማረጋገጥ ፈታኝ ትግል ተደርጓል። በትግሉም ደርግን ያህል ፈርጣማ ክንድ ያለው ኃይልን በመደምሰስ በአገሪቱ አንጻራዊ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጦችን ማስመዝገብ ተችሏል።
ይሁንና ወታደራዊ መንግሥትን አስወግዶ ስልጣኑን የተቆጣጠረው የኢህዴግ መንግስት በውስጡ ገና በጥዋቱ የመጣበትን ዓላማ ሳይስትና ሳይሰስት ለሕዝቦች መልካም መልካሙን ያደረጉ የኢህአዴግ አመራሮች መኖራቸውን መግለፅ ከእውነት የራቀ ባይሆንም፤ እየቆየ ሲሄድ መልካም ድርጊት መፈፀሙ ላይ ላዩን ማስመሰል ሆኖ ከጀርባ በርካታ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ጥሰቶችን መፈፀማቸው ብዙዎችን አስከፍቷል። ያም ሆነ ይህ መምሰል መሆን አይደለምና ላለፉት 27 ዓመታት አስተዳድረዋለሁ እመራዋለሁ ባለው ሕዝብ ላይ ሲሰራ የነበረው ሸፍጥ አደናቅፎ ሊጥለው ጊዜው ሆነና ዛሬ ኢህአዴግ ከመንበሩ ተነስቶ ብልፅግና ተተክቷል።
ዛሬ ከመንበሩ ቢነሳም ቅሉ ‹‹ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም›› እንደሚባለው ቡድኑ ከተጠናወተው የስልጣን ጥም አልፈወስ ብሎ ዛሬም ድረስ እየቃተተ ይገኛል። በቆፈረው ጉድጓድ መግባቱ አልበቃ ቢለው፤ ከገባበት ጉድጓድ ከተደበቀበት ጎሬ ውስጥ ሆኖ መሰረታዊ አጀንዳው የሆነውን ሀገርን የማተራመስ ተግባር በየአቅጣጫው እንዲቀጥል ምክንያት ሆኗል። ሕዝቡ ከቀዳዳ ይሻላል
ጨምዳዳ ብሎ የተቀበለው ሥርዓት ታድያ ላይ ላዩን በሚሰራው የልማት ሥራዎች ልማታዊ መንግሥት የሚል ስያሜ ይዞ ነገር ግን ውስጥ ውስጡን ዛሬም ድረስ አልጠፋ ያለውን ረመጥ እሳት አስታቅፎን ለማለፍ ምክንያት ሆኗል።
ዛሬ አገር በጉያዋ የታቀፈችውን ረመጥ እሳት የማጥፋት አልያም የማፋፋም ጥያቄ ደግሞ በዛሬው ትውልድ ጫንቃ ላይ ወድቋል። ዛሬ በሀገሪቷ በሁሉም አቅጣጫ የሚታዩት ችግሮች፣ እዚህም እዚያም የሚሰሙት መደነቃቀፎችና አለመረጋጋቶች መነሻቸው ሥልጣን ለምን አጣለሁ በሚል ትእቢት ምክንያት ቢሆንም ሀገርን በማተራመስ እና ሕዝቦችን በማጋጨት የሚገኝ ስልጣን ትርፍ የሌለው ኪሳራ መሆኑን ይኸው ቡድን ማወቅ ይኖርበታል። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ሥልጣን የሚያዘው ልክ እንዳለፉት 27 ዓመታት ሁሉ ለይስሙላ በሚደረግ የምርጫ ሥርዓት ሳይሆን እውነተኛ በሆነና ዴሞክራሲያዊ መንገድን በመከተል ስለመሆኑ ብዙ እየተባለና ሕዝቡም ተስፋ እያደረገ ይገኛል።
በተለይም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር ዓቢይ አህመድ በተለያዩ መድረኮች ላይ እንደገለጹት፤ ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት እንደመሆኑ 6ኛውን አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ እንዲሁም ታሪካዊ ምርጫ እንዲሆን ማድረግ የእያንዳንዱ ዜጋ ግዴታ መሆኑን አንስተው ሕዝቡ ማንን ለምን እንደሚመርጥ አስቦና ተዘጋጅቶ መጠበቅ አለበት። ከመረጠ በኋላም ድንጋይ የሚወረውር አካል ካለ ሕዝቡ በጋራ መቆም እንዳለበት ተናግረዋል። በመሆኑም ማንም ሰው ሥልጣን መያዝ የሚችለው በምርጫና በምርጫ ብቻ መሆኑን አጽንኦት በሰጡበት ንግግራቸውም ኢትዮጵያ ውስጥ ከምርጫ በስተቀር የሚሸጋገር የሚደራደር መንግስት የማይፈጠር ስለመሆኑ ለምርጫው የሰጡትን ትኩረትና ያላቸውን ጠንካራ አቋም በገቡት ቃል አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያም አሁን ከገባችበት ቀውስና ከተጠናወታት ደዌ መንጻት የምትችለው ከፊት ለፊቷ በሚጠብቃት 6ተኛው አገራዊ ምርጫ እንደሆነ አገሪቷን እያስተዳደራት ያለው መንግሥትን ጨምሮ የብዙዎቻችን ዕምነት ነው። ምክንያቱም አገሪቷ ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ ሥልጣንን በኃይል ለመጫን ምቹ ነው ብለው ያሰቡ አካላት ከውስጥም ከውጭም እየገፏት ይገኛሉ። ይሁንና ሀገሪቷ በአሁን ወቅት እየደረሰባት ያለውን ጫና ተቋቁማ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማከናወን ከቻለች ጥቂት የማይባሉ ችግሮቿን መሻገር ትችላለች። ነገር ግን ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ መከራዋን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ሊያተራምሷትና ሊበታትኗት ለቋመጡና ርካሽ ትርፍ ለናፈቁ ይሁዳዎች አሳልፍን ከሰጠናት የምጥ ጊዜዋን እናራዝመዋለን። ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት እያንዳንዱ ዜጋ ሰላም ያለውን ዋጋ በመረዳት ለሰላም ዘብ በመቆም ሊያጠፏት ከተዘጋጁ ጠላቶቿ እንታደጋት። በተለይም ብዙ ተስፋ የተጣለበትና ታሪካዊ ሆኖ ያልፋል ተብሎ የሚጠበቀውን 6ተኛው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ መጠናቀቅ እንዲችል የበኩላችንን በመወጣት ታሪክ መስራት ይጠበቅብናል።
አሁን ላይ ሀገሪቱ ለገጠማት ችግር ሁነኛ መፍትሔ ማምጣት እንዲቻል ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሂደቱ ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የተከተለ እንዲሆን ማድረግ ከመራጩ ሕዝብ፣ ከመንግሥት እና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚጠበቅ ነው። ሂደቱ በሚፈለገው መንገድ ተጉዞ ውጤት ማስመዝገብ ከተቻለ ያኔ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ይሆናል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆነባት እንቅፋት ሁሉ ይወገዳል። አገሪቷ ለሁሉም ጥያቄዎቿ መልስ ባታገኝም መሰረታዊ ለሆነውና ነባራዊ ሁኔታዋን ተጠቅሞ ሥልጣን ለመያዝ ካልሆነለትም እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እንዲሉ ሊበታትኗት ከከጀሉ ይሁዳዎች ትድናለች።
ሁሉም ነገር ተስተካክሎ አፍራሾቿ ፈርሰው፤ አጥፊዎቿም ጠፍተው ትንሳኤዋን ማብሰር ከተቻለን ደግሞ ቀሪ ጥያቄዎቿን በመመለስ ወደ ቀደመው ገናናነቷ ልናሻግራት እንችላለን። ለዚህ ሁሉ ግን ጥቂት ከሆኑት አጥፊዎቿ መካከል የኢትዮጵያ ወዳጆችና አልሚዎቿ እንደምድር አሸዋ በዝተን በተባበረ ክንድ በአንድነትና በፍቅር በጋራ መቆም ይጠበቅብናል። ለሚያለያዩን ጥቃቅን ስህተቶች ሳንበገር እርስ በእርስ ለሚያስተሳስሩን ለሚያጣምሩንና አንድ ለሚያደርጉን ግዙፍ ጉዳዮቻችን ቅድሚያ እንስጥ።
ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለአንድ አገር የሚኖረው ፋይዳ የጎላ እንደመሆኑ ኢትዮጵያም አሁን ከገባችበት አጣብቂኝ ወጥታ ትንሳኤዋን ማብሰር የምትችለው ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ ስትችል ብቻ ነው። ስለዚህ እያንዳንዳችን ከምርጫው አስቀድሞ፣ በምርጫ ወቅትና ከምርጫ በኋላ በሚኖሩ ሂደቶች ተገቢውን ሁሉ በማድረግ ለኢትዮጵያ ትንሳኤ እንትጋ።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ግንቦት 22 ቀን 2013 ዓ.ም