(ክፍል አንድ)
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዘመኑን የማይዋጅ ከመሆኑ ባሻገር መንታ መንገድ ላይ ተቅበዝባዥ ሆኗል። የ”ልዕለ ኃያሏ”ዲፕሎማሲም ሆነ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የቁልቁለት መንገዱን ከተያያዘውም ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ሆኖታል ። በእኛ የተጀመረ በእኛም የሚቋጭ አይደለም ። ቀራጮች/ሪፐብሊካንስ/ አልያም ዴሞክራቶች መጡ ሔዱ ከተያያዘው የቁልቁለት መንገድ አያስቆሙትም ። ሀገራችን ሰሞነኛውንም ሆነ መጪውን የአሜሪካን ዲፕሎማሲያዊ ፍርደ ገምድልነት ለማረቅና አሰላለፏን ከዚህ አንፃር ለመበየን ወይም ስትራቴጂካዊ እይታን ለመግለጥ የአሜሪካንን የውጭ ግንኙነት የቁልቁለት ጉዞ ከተጀመረበት አንስቶ መመልከት፣ መገምገምና መተንተን ግድ ይላል። በመነሻነት ቢያገለግል በሚል ቅንነት ይህን ስንክሳር በአለፍገደም በተከታታይ ክፍሎች ለመቃኘት እሞክራለሁ። የሳትኩት እውነት ቢኖር ለመታረም ፣ ይቅርታ ለመጠየቅ አላቅማማም።
ቀራጮች ነጩ ቤተ መንግሥት ሲገቡ ፖሊሲው በአዲሱ ወግ አጥባቂነት ፈለግ ይወሰድና ዴሞክራቶች በእግሩ ሲተኩ ደግሞ ቀኝ ኋላ ይዞርና በሊበራል ዓለም አቀፋዊነት ይመለሳል። በትራምፕም ሆነ በባይደን የታዘብነው ይሄን ነው ። የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው እንዲህ ባለ ውልውል ከመመናተሉ ባሻገር የዓለምን ተጨባጭ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ አልያም ፕራግማቲስት አለመሆኑ ተደጋግሞ ይተቻል። እንዲያውም እንደ ማይክል ሒርሽ ያሉ አንዳንድ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ጉምቱዎችና ፀሐፊዎች ያለርህራሄ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከሽፏል እስከማለት ደርሰዋል።
ቀራጮች(ሪፕብሊካን) የነፃ ገብያ አክራሪና የነጭ ወግ አጥባቂዎች ማለትም የኮሌጅና የዩኒቨርሲቲ ደጅ ያረገጡ ነጭ አሜሪካውያንና በተለምዶ አንድ በመቶ የሚባሉ ባለጠጎችን ማህበራዊ መሠረት ታሳቢ ያደረገ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዳናን ይከተላል። የባለጠጋዎችን ግብር ይቀንሳል። እነሱን ታሳቢ ያደረገ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ያደርጋል። ስደተኛን ይጠላል። አያበረታታም። በ”አሜሪካ ትቅደም!” ስም የነጭ ወግ አጥባቂዎችን ሁለንተናዊ ጥቅም ለማስከበር ይተጋል። የገበያ ከለላ ይሰጣል። አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ድጎማ ያደርጋል። ሉላዊነትን እንደ መልካም አጋጣሚ ሳይሆን እንደስጋት ይቆጥራል። የመንግሥታቱን ድርጅት፤ የዓለም ባንክን፤ ዓለም አቀፉን የገንዘብ ተቋም፤ የዓለም የንግድ ድርጅት፤ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳንን/ኔቶ/፤ የአውሮፓ ሕብረትን፤ ወዘተርፈ በጥርጣሬ ይመለከታል። ጎልቶ የማይታየው ይህ የቀራጮች ፖሊሲ እድሜ ለትራምፕ አደባባይ ወጥቶ ተሰጥቷል። ከ2ኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ላለፉት 70ና ከዚያ በላይ ጊዜ በዓለም ላይ ለሰፈነው አንፃራዊ ሰላም በባለውለታነት የሚወደሱትን ኔቶንና የአውሮፓ ሕብረት አናንቋል። ያረጁና የጨረቱ ናቸው ሲል በሸንጎ መሀል አጣጥሏቸዋል። አዋርዷቸዋል። ከፓሪሱ ዓለምአቀፍ የአየር ንብረት እና ከኢራኑ የፀረ ኒውክሌር ስምምነቶች አፈንግጧል ።
ሀገሩ ለዓለም ጤና ድርጅት ታደርገው የነበረውን ድጋፍ አቋርጧል። የእንግሊዝን ከሕብረቱ የመነጠል ውሳኔ ሕዝብ ደግፎ ቆሟል። የአሜሪካንን ዓለምአቀፍ ሚና አቀዛቅዟል። በዚህ የተነሳ የተፈጠረውን ክፍተት በተለይ ቻይና እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅማበታለች። ራሽያም በእንግሊዝ መነጠል፤ በኔቶ መብጠልጠልና በአሜሪካና በአውሮፓ ሕብረት ግንኙነት ንፋስ መግባቱ ጮቤ አስረግጧታል። የልብ ልብ እንዲሰማት አድርጓል።
አሜሪካ ስትለቅ ቻይና እግር በእግር ትተካለች። ከሁሉም በላይ ሽንፈቱ አልቀበልም በማለትና ደጋፊዎቹ እንደ አሜሪካ ዴሞክራሲ ቤተ መቅደስ የሚመለከውን ካፒቶል ሒል በማስወረርና በማስቀመጥ መፈንቅለ መንግሥት የማድረግ ያህል ሙከራ በማድረጉ አሜሪካውያንን ለዘመናት ሲመፃደቁበት የነበረውን ዴሞክራሲ አፈር ድሜ አብልቶታል። ቻይናና ራሽያ ድንቄም ዴሞክራሲ እያሉ እንዲሳለቁ፤ ዴሞክራሲ አይሰራም እንዲሉ አደፋፍሯቸዋል። በአምባገነንነት እንዲመፃደቁና የልብ ልብ እንዲሰማቸው እና አሜሪካውያን እርስበርስ እንዲከፋፈሉ አድርጓል።
የዴሞክራቶች የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ደግሞ በተቃራኒው በሊበራል ዓለምአቀፋዊነት ላይ መልሕቁን የጣለ ነው። ሉላዊነትን፣ ትብብርንና ዴሞክራሲያዊ እሴቶችን ለማስፋት የሚሰራ። ከቀራጮች በተቃራኒው የመንግሥታቱን ድርጅት ጨምሮ ከፍ ብሎ ለተዘረዘሩ ዓለምአቀፍ፣ አህጉራዊና ቀጣናዊ ተቋማትና ስምምነቶች ተገዥ ነው ። ለዚህ ነው 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዴሞክራቱ ጆ ባይደን ወደነጩ ቤተ መንግሥት ከመግባታቸው የትራምፕን የውጭ ጉዳይና የሀገረ ቤት ውሳኔዎች መሻርና መቀልበስ የጀመሩት። የፓርቲው ማህበራዊ መሠረትም በተለምዶ 99 በመቶ የሚባለው በመካከለኛና በታችኛው መደብ የሚገኘው አሜሪካዊ ነው። ከሞላ ጎደል በማህበራዊ ፍትሕና ዴሞክራሲ የሚያምን ሲሆን፤ የዩኒቨርሲቲ ደጅ የረገጡ ነጭ ሴቶች፣ ጥቁሮች፣ እስፓኒኮችና መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሌሎች አሜሪካውያን የፓርቲው ማህበራዊ መሠረቶች ናቸው። ዳሩ ግን በየራሳቸው አዕማድ የቆሙ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዎች የታለመላቸውን ግብ ማሳካት እየተሳናቸው እንደሆነ ሒሽ ይተቻል። እኛም ከቻይናና ራሽያ ጋር የገባችበትን ቅርቃር፤ በቬትናም፣ በኢራን፣ በኢራቅ፣ በአፍጋኒስታን፣ በሶሪያ፣ በሊቢያ፣ በሶማሊያ፣ በየመን፣ በፊሊፒንስ፣ በቬኒዞላ፣ ወዘተረፈ የቀራጮችም ሆነ የዴሞክራቶች የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሲከሽፍ ታዝበናል።
አንዳንድ ጉምቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሊቃውንት ቢቸግራቸው የ98 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ወደ ሆነው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ደራሲ እስከ መባል ወደ ሚሞካሸው ሄነሪ ኪሲንጀር ዘመን ተጨባጭ ሁኔታ ላይ የታነፀ ዲፕሎማሲ ማማተር ጀምረዋል። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከመሠረቱ ተናግቷል በማለት ማሳያዎቻቸውን ያነሳሳሉ። በቀዝቃዛው ጦርነት ርዕዮት ዓለምን ተከትሎ ያራምደው የነበረው የእመቃ ዲፕሎማሲ በዊልሰናዊያን የተስፋፊነት የተሳሳተ አባዜ ከቬትናም ጋር የተካሄደው ጦርነት የ50 ሺህ አሜሪካዊ ወታደሮች ያስገደለ፤ ከ70 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ አክስሯል። ከሁሉም በላይ የሽንፈት ከል አከናንቦታል። የአሜሪካን ገጽታ ክፉኛ ጎድቶታል።
እንዲሁም በድህረ ቀዝቃዛው ጦርነት በአዲሱ የሬጋን “ሰይጣን”አገዛዞችን በኃይል የማስወገድ እርምጃ ከፍ ብሎ እንደተመለከተው ተሞክሮ ከሽፏል። 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ደግሞ የ1950ዎቹንና 60ዎቹን “አሜሪካ ትቅደም!” ፖሊሲ አቧራውን አራግፎ ወደፊት ቢያመጣውም አሜሪካን ነጥሎ ብቻዋን በማስቀረት ከስሯል። ባሪ ጌዌን”The Inevitability of Tragedy” በተሰኘው የሄነሪ ኪሲንጀርና የዛን ዘመን የዲፕሎማሲ አካሄድ በሰነደበትና በተነተነበት ማለፊያ መጽሐፉ”በእርግጥ ሔነሪ ኪሲንጀርን ልትጠላውና ከይሲ ነው ብለህ ልታስብ ትችላለህ። ልትረሳው አልያም ልትተው ግን አትችልም። ለዛውም በዚህ ጊዜ። እውነት ለመናገር የኪሲንጀር እሳቤም ሆነ ተፈጥሮው ወይም ደመነፍሱ ክፉኛ ያስፈልገናል።” በማለት የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚታደገው ኪሲንጀርና መንፈሱ ብቻ እንደሆነ ይነግረናል። ቀራጮች የሚከተሉትም አዲሱ ወግ አጥባቂነት Neoconservative አልያም ዴሞክራቶች የሚያራምዱት ሊበራል ዓለምአቀፋዊነት Liberal internationalism የአሜሪካን ዲፕሎማሲ ከገባበት ቅርቃር አያወጣውም። ለዚህ ነው ጌዌን በተጨባጭ ሁኔታ ላይ ወደተቀረፀው የሔነሪ ኪሲንጀር የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንመለስ ሲል የሚወተውተው ።
ማይክል ሒርሽ”WELCOME To Kissinger’s World” በሚል ርዕስ በፎሪን ፖሊሲ መጽሔት ባለፈው ዓመት ባስነበበን ወግ፤ የኮሮና ወረርሽኝ የትራምፕን”አሜሪካ ትቅደም!”የሚለውን የተነጣይነት አጀንዳ ለማጉላት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። የንግድ ወኪሉ ሮበርት ሊቲዘር ቻይና በምትከተለው አደገኛ የንግድና የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተነሳ አሜሪካ በውጭ የሚገኙ ፋብሪካዎቿንና ኩባንያዎቿን ወደ ሀገር ቤት መመለስ ያስፈልጋታል ሲል የትራምፕን የተነጣይነት ፖሊሲ ያቀነቅናል። ትራምፕ በዚህ አያበቃም። ሳይሳካለት ቀረ እንጂ የቻይናን የኢኮኖሚ ዕድገት ግስጋሴን ለመገዳደር የሚችል የተለያዩ አገራትን ግንባር ለመፍጠር ጥረት አድርጓል። ዴሞክራቶች ይህን የትራምፕ ገዳዳ አቋም በገደምዳሜ ከመደገፍ አልፈው በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት የነበረውን አይነት ትንቅንቅ እስከመቆስቆስ ደርሰዋል። የዛን ጊዜው እጩ የዛሬው ዴሞክራት ፕሬዚዳንት ባይደን በተደጋጋሚ የቻይናውን ፕሬዚዳንት ዢ ዥንፒግ ከማድነቅ አልፈህ ፊት ትሰጥ ነበር በማለት በምርጫው ክርክር ወቀት ይከስ ነበር።
ሪፕብሊካኖች ከዚህ አልፈውም በእነሱ ሊበራል ዓለምአቀፋዊነት መርህ መሠረት የተቋቋሙ እንደ የዓለም ንግድ ድርጅት ያሉ ተቋማትን የቻይና መጠቀሚያ እየሆኑ ነው በማለት ማብጠልጠል መጀመራቸው፤ ሳያንስ ቻይና የአሜሪካውያንን የሥራ ዕድል እየተሻማች ነው በሚል መክሰሳቸውን ሒርሽ ያትታል። ይሁንና ይህ የቀራጮች ተነጣይነትም ሆነ የዴሞክራቶች ዓለምአቀፍ ተቋማትንና ቻይናን የማጠልሸት አባዜ ነባራዊውን ዓለምአቀፍ ሁኔታ ለየፓርቲዎቻቸው ማህበራዊ መሠረት መስዋዕት የማድረግ የሕዝበኝነት populism አጉል አመል። የደጋፊዎቻቸውን ብሶት በመጋለብና ቁስል በማከክ ጊዜያዊ ፖለቲካዊ ነጥብ የማስመዝገብ ዘመን አመጣሽ ፖለቲካዊ ስብራት ነው።
የኢንፎርሜሽን ኮምንኬሽን ቴክኖሎጂ እና ዘመናዊና ፈጣን መጓጓዣ ምስጋና ይግባውና ዓለምአችን ወደ አንድ ትንሽ መንደርነት እየተለወጠች ነው። በቻይናዋ ውሃን ግዛት ቀድሞ የተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በፍጥነት ዓለምን ያዳረሰው ለዚህ ነው። የእሥራኤልና የፍልስጤም ሰሞነኛ ያልተመጣጠነ እርምጃ የነዳጅ ገብያውን የተጫነው በአጋጣሚ ሳይሆን የቦታ ርቀትና ጊዜ በቴክኖሎጂ ተሽረው ቤተሰብ ስላደረጉን ነው። የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የቁልቁለት ጉዞ ዳጎስ ዳጎስ ያሉ በርከት ያሉ መጽሐፍት የወጣው ጉዳይ ስለሆነ በዚች ምጥን አምዴ ስለማልዘልቀው በክፍል ሁለት መጣጥፌ በስሱ እመለስበታለሁ።
አገራችን ኢትዮጵያ በሀቀኛና ጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!!
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/2013