የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም ወደ ባንክ በማደግ “ሲንቄ” ባንክ በሚል ስያሜ ባንኩ ተመስርቷል። ባንኩ እስከዛሬ የነበረውን ጉዞ አጠናክሮ በመቀጠሉና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሰጠውን እድል ተጠቅሞ እንዲሁም ማሟላት የሚገባውን መስፈርቶች አሟልቶ ማክሮ ፋይናንስ ሆኖ የጀመረው ስራ የሚገባውን መስፈርቶች አሟልቶ ወደ ባንክ መሸጋገር ችሏል።
የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም የባለሀብቱ ጠቅላላ ጉባኤና የባንኩ አመራሮች በተገኙበት የባንክ ምስረታው ተከናውኗል። ሲንቄ ባንክ የተከፈለ ሰባት ቢሊዮን ብር ካፒታል እና ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ጠቅላላ ሀብት ኖሮት የተመሰረተ ሲሆን፤ ባንኩ ተወዳዳሪ ባንክ ሆኖ መቀጠል የሚያስችለውን ዝግጅት አጠናቅቆ በአሁን ወቅት ወደ ሥራ ለመግባት የስኬት ጉዞውን ጀምሯል።
የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም ወደ ባንክ ሲያድግ ይዞ የሚመጣውን አዲስ ነገር እንዲሁም ተቋሙ እስከዛሬ በነበረው እንቅስቃሴ ለማህበረሰቡ እያበረከተ ያለውንና ወደፊትም ሊያበረክት የሚችለውን አስተዋጽኦ፤ ባንኩ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ሊያሳድር የሚችለውን አበርክቶና አጠቃላይ ያለውንና የሚኖረውን እንቅስቃሴ እንዲሁም ተደራሽነቱን አስመልክተው የባንኩ ተቀዳሚ ዳይሬክተር አቶ ዘውዴ ተፈራ የሚከተለውን ሀሳብ አካፍለውናል።
ተቋሙ ከዛሬ 24 ዓመታት በፊት በአምስት ሚሊዮን ብር ካፒታል ሥራ የጀመረ ሲሆን፤ ዛሬ ላይ ግዙፍ የፋይናንስ ተቋም መሆን ችሏል። በመሆኑም አራት መቶ ቅርንጫፎችን በማፍራት ለስድስት ሺህ ሶስት መቶ አርባ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ተበዳሪ ደንበኞችን አፍርቷል። ከሁለት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎችንም ደንበኛ በማድረግ ገንዘባቸውን ማስቀመጥ የቻለ ተቋም ነው።
ተቋሙ አገልግሎቱን እየሰጠ ያለው ሰፊ የማህበረሰብ ክፍል ለሆነው አርሶ አደሩና ታች ላለው ህዝብ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ እስከዛሬ በሰጠው አገልግሎትም አስር ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ለሚጠጉ ዜጎች 55 ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር ብድር ሲሆን፤ እነዚህ ዜጎችም የብድር አገልግሎቱን ተጠቅመው ኑሯቸውን ማሻሻል እንዲችሉ አድርጓል። በተመሳሳይ በየዓመቱ በአማካኝ ከስምንት ቢሊዮን እስከ 12 ቢሊዮን ብር ብድር ይሰጣል።
የማይክሮ ፋይናንሱ ወይም ደግሞ ባንክ ሆኖ የሚቀጥለው ተቋም ዋናው ዓላማ የማህበረሰቡን የፋይናንስ ተደራሽነት በማረጋገጥ የተለያዩ ብድሮችን በመስጠት የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል ነው። ይህም ሲባል ባንኮች ገንዘብ ለማበደር ማስያዣ ይፈልጋሉ። ስለዚህ ንብረት አስይዘው መበደር የማይችሉት የማህበረሰብ ክፍሎች በተለይም ከዩኒቨርሲቲ ተምረው የሚወጡ ወጣቶች ተደራጅተው ሥራ ፈጥረው መስራት የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው። አርሶ አደሩም እንዲሁ በተለያየ ጊዜ የሚያስፈልገውን ወጪ መሸፈን እንዲችልና ተጨማሪ ገቢ ለማመንጨት የተለያዩ ሥራዎችን መስራት ለሚፈልጉ ዜጎች በማበደርና ውጤታማ እንዲሆኑ ከጎናቸው ሆኖ ይደግፋል።
ለማህበረሰቡ ድጋፍ መስጠትን ዓላማው አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ያለው ሲንቄ ባንክ ድጋፍ ከማድረጉ ባሻገርም የራሱንም የውስጥ አቅም እያሳደገ መጥቷል። በመሆኑም በአሁን ወቅት ሰባት ቢሊዮን የተከፈለ ካፒታል ይዞ ወደ ባንክ ለመሸጋገር በሂደት ላይ ይገኛል።
ተቋሙ ባንክ ሆኖ ሲቋቋም ከሌሎች ባንኮች በተለየ ሁኔታ ለማህበረሰቡ ምን አዲስ ነገር ይዞ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል ለሚለው ጥያቄ ዳይሬክተሩ ሲናገሩ ባንኮች የማይክሮ ፋይናንስ ሥራዎችን አይሰሩም። ነገር ግን የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም ወደ ባንክ ሲያድግ ሁለት ስራዎችን የሚሰራ መሆኑን አንስተዋል። ይህም ማለት የማይክሮ ፋይናንስ ሥራዎችንም ሆነ የባንክ ሥራን የሚሰራ ይሆናል። እስካሁን ባለው ሂደትም ተቋሙ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ደንበኞች በማሳደግ ወደ ከፍተኛ ደረጃ በማድረስ ወደ ባንክ ሲያቀብል ኖሯል። ይሁንና በአሁን ወቅት እነዚህ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱት ደንበኞችንም ወደ ባንክ ሳይልክ በራሱ ባንክ ያስተናግዳል።
የፋይናንስ ተቋማት መበራከትና መጠናከር ለአንድ ሀገር የኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ መሆኑ ይታመናል። የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባም በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ አስተዋጽኦ ሲያበረክት ነበር አሁንም እያበረከተ ይገኛል።
የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም እስካሁን በነበረው የጉዞ ሂደት በክልሉ በሚገኙ አካባቢዎች ላይ ብቻ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ቢሆንም ሲንቄ ባንክ ሆኖ ከተመሰረተበትና ዕውቅና ካገኘበት ጊዜ ጀምሮ በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ላይ ተደራሽ በመሆን አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። ባንኩ የራሱ በሆነ መሬት ባለ ሰባት ፎቅ ህንጻ ገንብቶ የባንክ ሥራውን ለመጀመር ወደ ሥራ ገብቷል።
በመጨረሻም ማህበረሰቡ የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም ሲንቄ ባንክ ሆኖ በይፋ የተመሰረተ በመሆኑና ባንኩም ወደ ሥራ እየገባ መሆኑን አውቆ ደንበኛ እንዲሆን ወደ ባንኩ ይምጣ በማለት ተቀዳሚ ዳይሬክተር አቶ ዘውዴ ተፈራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ፍሬህይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 20/2013 ዓ.ም