‹‹ልጄ በ2011 ዓ.ም በወጣው ሁለተኛ ዙር የ40/60 የቤት ዕጣ ላይ ዕድለኛ ሆና ባለሁለት መኝታ ቤት እንደደረሳት ማወቅ ችለናል።›› የሚሉት ወይዘሮ ሙሉ ገዛኽኝ፤ ልጃቸው ዱባይ ሄዳ እየሰራች የጋራ መኖሪያ ቤት ቁጠባን ትከፍል እንደነበር እና ፈጣሪዋም ድካሟን አይቶ የቤት ዕድለኛ መሆኗ እንዳስደሰታቸው ይናገራሉ።
ልጃቸው ሰው አገር ተንከራታ ያገኘችውን ገንዘብ በአገሯ ላይ የቤት ባለቤት ለመሆን ባላት ፍላጎት የተነሳ እስካሁን ድረስ የ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም ተመዝግባ ስትቆጥብ መቆየቷን አውስተው፤ የቤት ዕድለኛ መሆኗ በይፋ ዕጣ ከወጣለት ሁለት ዓመታት ቢያልፉና ከባንክና ከቤቶች ልማት ጋር ከተዋዋሉም ቢቆዩም እስካሁን ቤቱ ቁልፍ እጃቸው እንዳልገባ ይናገራሉ። የቤት ግዢ ውሉ ላይ በተፈራረሙት መሠረት ልጃቸው በየወሩ በውጪ ምንዛሬ ለባንክ እየከፈለች እንደምትገኘ የሚናገሩት ወይዘሮ ሙሉ፤ የቤቱን የግንባታ ደረጃ እየሄዱ ቢከታተሉም አሁን ላይ የቁልፍ ርክክቡ መዘግየት ጉዳይ ግራ ያጋባቸው መሆኑን ይገልፃሉ።
የወይዘሮ ሙሉ ልጅ፤ ቤቱ የደረሳት በቦሌ ክፍለ ከተማ ሐያት ሁለት በሚባለው ሣይት ነው። በአቅራቢያው ሐያት አንድ ሣይት አንድ፣ ሐያት አንድ ሣይት ሁለት፣ ሐያት አንድ ሣይት ሦስት እንዲሁም ሐያት ሁለት ሣይት አንድ፣ ሐያት ሁለት ሣይት ሁለት፣ ሐያት ሁለት ሣይት ሦስት እና አራት የሚባሉ ሣይቶች የሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታቸው በአብዛኛው ተጠናቆ የቁልፍ ርክክብ ተካሂዷል። ነገር ግን ሐያት ሁለት ግንባታው የተጓተት ሲሆን፤ የተወሰኑ ህንፃዎች የተጠናቀቁ ቢሆንም የቁልፍ ርክክቡ ላይ በመዘግየቱ ምክንያት ግራ ተጋብተዋል።
ቤቱ በሚገኝበት ማለትም ቦሌ ክፍለ ከተማ ሐያት 2 በሚባለው ሣይት ተገኝተው የቤቱ ግንባታ መጠናቀቁን ቢያረጋግጡም፤ በአካባቢው ኮሚቴ የተባሉ ሰዎችም ሆኑ እዚያ አካባቢ የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች የሐያት ሁለት 40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም ዕድለኛ ለሆኑ ሰዎች የቁልፍ ርክክብ መካሄዱን ይነግሯቸዋል። ሆኖም የቤት መረከቢያ ቅፅ ከክፍለ ከተማ የሚመጣ መሆኑንና በዚህ ቅጸ መሠረት ከክፍለ ከተማ በሚሰጣቸው ወረቀት የቤቱን ቁልፍ ብቻ ሳይሆን መብራትና ውሃም በዚህ መሠረት እንደሚያስገቡ ገልፀውላቸው፤ ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ እንዲሄዱ ይመሯቸዋል።
ክፍለ ከተማ ሲደርሱ ግን ያገኙት ምላሽ የተለየ ነው። የእናንተ ህንፃ ባለመጠናቀቁ የቁልፍ መረከቢያ ወረቀት አንሰጣችሁም የሚል ነው። በመሃል ግራ መጋባታቸውን የሚገልፁት ወይዘሮ ሙሉ፤ በዚህ ሣቢያ ጊዜው አልፏል በሚል ሰበብ ልጃቸው ቤቱን እንዳታጣ እጅግ መሥጋታቸውን በመግለፅ ጉዳዩን አጣሩልን ሲሉ ጥያቄውን ለዝግጅት ክፍላችን አቅርበዋል።
በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የቤት ማስተላለፍና ማስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አውራሪስ ከበደ፤ በገዛ ቤታቸው ጊዜው አልፏል የሚባል ነገር በፍፁም ሊኖር እንደማይችል ይገልፃሉ። ይህ ሥጋት ተገቢነት ያለው አይደለም ካሉ በኋላ፤ የቤቱ ግንባታ ከተጠናቀቀ ቁልፉን ማግኘታቸው የማይቀር መሆኑን በእርግጠኝነት ይናገራሉ።
እንደአቶ አውራሪስ ገለፃ፤ ቢሯቸው በማንኛውም ጊዜ መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ መሆኑን ማንኛውም ሰው ከቁልፍ ርክክብ ፕሮግራም ጋር ተያይዞ ጥያቄ ካለው መጠየቅ መብቱ እንደሆነ እና እነርሱም ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።
በእርግጥ የቁልፍ መረካከቢያ ቅጹን ከክፍለ ከተማ መውሰድ ግዴታ መሆኑን በመጠቆም፤ ክፍለ ከተማው ከሲስተም ላይ በማውጣት መረካከቢያ ሠነድ በእጃቸው የሚሰጣቸው መሆኑን ተናግረው፤ ቢሮው ለቁልፍ ርክክቡ ፕሮግራም ያወጣ በመሆኑ ሰዎቹ ፕሮግራሙን ማወቅ ከፈለጉ ቤታቸው ባለበት ሣይት ላይ ተገኝተው ቢጠይቁ የሚነገራቸው መሆኑን እና በእነርሱ በኩል የቤቶቹ ግንባታ ተጠናቋል የሚል መረጃ የሚደርሷቸውን ቤቶች ቁልፍ በማስረከብ ላይ መሆናቸውን ይገልፃሉ።
‹‹ሐያት ሁለት በእርግጥም ግንባታቸው ያላለቁ ቤቶችና ለቁልፍ ርክክብ ያልደረሱ ቤቶች አሉ። ነገር ግን መረከብ የጀመሩ ቤቶች ካሉ በማጣራት ምላሽ የሚሰጥ ሲሆን፤ የቤት ዕድለኞቹ የቤታቸው ግንባታ ከተጠናቀቀ በማንኛውም በፈለጉበት ጊዜ መጥተው የቤቱን ቁልፍ ማግኘት ይችላሉ›› ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።
ሁለተኛ ዙር የ40/60 የመኖሪያ ቤት ዕድለኞች በተደጋጋሚ የቤቱን ቁልፍ የማግኛ ጊዜው መዘግየቱን እየገለፁ ነው። አሁን ግንባታቸው የተጠናቀቁ ቤቶች የቁልፍ ርክክብ መካሄዱ መልካም ቢሆንም፤ ተያይዞ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ላይም በሥፋት መሰራት አለበት። በተለይም በቤቱ ለመኖር ወሣኝ የሆኑ ውሃ እና ኤሌክትሪክና መንገድ መሠረተ ልማቶች በፍጥነት ከመኖሪያ ቤቶች ህንጻዎች ጋር የማገናኘት ሥራዎች ካልተሰሩ የቤቱን ቁልፍ ብቻ ማስረከብም በቂ አይደለም። ስለዚህ ኮርፖሬሽኑ ቤቱን ለመኖሪያ ምቹ በማድረግ በኩል አሁንም ብዙ መስራት ይጠበቅበታል።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 20 ቀን 2013 ዓ.ም