ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲካሄድ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ቀን ቆርጦለታል፡፡ በዚህ ዓመት መጨረሻዎቹ ወራት ውስጥ ሊካሄዱ የታሰቡና ኢትዮጵያ ቀነ ቀጠሮ ከያዘችላቸው ጉዳዮች መካከል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌትም ሌላኛው አንኳር ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የሲዳማ ክልል ምርጫው ስኬታማ እንዲሆንና የግድቡ የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ውጤታማ እንዲሆን ብሎም አጠቃላይ የአገሪቱና የክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሁልጊዜ ተባባሪ ከሆኑት ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡ መልካም ንባብ ይሁንልዎ፡፡
አዲስ ዘመን፡– ሲዳማ ከክልልነት በኋላ ያላት አጠቃላይ እውነታ እንዴት ይገለጻል?
አቶ ደስታ፡– ሲዳማ ከክልልነት በኋላ በጣም የተረጋጋ ቀጣና ነው የሆነው። በአጠቃላይ ትኩረቱ ልማት ላይ ነው። ልማቱን ደግሞ አቅም በፈቀደው መጠን ከህዝቡ ጋር ተባብረን እየሰራን እንገኛለን። በዚሁ ምክንያት ህዝቡና መንግስት የተግባባ ነው የሚመስለው። በትብብር የሚሰራ ስለሆነ ውጤቱም የዚያኑ ያህል የተሻለ ነው፤ በተለያየ መልኩ ጫናዎችን ለመፍጠር የሚሞክሩ አካላት ቢኖሩም ህዝቡ ከመንግስት ጋር የተግባባ በመሆኑ ስራዎች እየተሰሩ ያሉት ፍጹም ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ነው። ከዚህ አንጻር ያለው ነገር ሁሉ መልካም ነው የሚል እይታ ነው ያለን።
አዲስ ዘመን፡– ሲዳማ ክልል ከሆነ በኋላ በዋናነት እያጋጠሙት ያሉ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው ይላሉ?
አቶ ደስታ፡– ተግዳሮቱ ከበጀት እጥረት ጋር የተያያዙ ናቸው። እንደሚታወቀው አገሪቷም በተወሰነ ደረጃ በቂ በጀት የላትም። ከዚሁ የሚመነጭና ከየአካባቢው የሚሰጥ በጀት በድጎማ የውስጥ በጀት የመሰብሰቡን ጉዳይ በድምሩ ስናየው ከልማት ፍላጎት ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም። በመሆኑም ክልል ከሆንን በኋላ በርካታ ተቋማት የተፈጠሩ በመሆናቸው እነዚያ ተቋማት በራሳቸው የየራሳቸውን ፍላጎት ይዘው መጥተዋል። ያገኘነው በጀት ደግሞ እነዚህን ወጪዎች ችሎ ህዝብ የሚጠብቀውን ልማት ከማረጋገጥ አንጻር እጥረት አጋጥሞናል። ያንን ለማለፍ የተለያዩ ዘዴዎችን ለመፍጠር ሞክረናል። የሚያግዙን አጋር አካላትም፣ ክልሎችም፣ ባለሀብቶችም አዲስ ክልል ከመሆናችን አኳያ ልትደግፉን ይገባል በሚል የአብሮነትና የመረዳዳት የኢትዮጵያንን ባህል መሰረት ያደረገ ድጋፍ በመጠየቅና በማስተባበርም ጭምር ህዝቡንም እንዲሁ የልማት አቅም አድርገን በማንቀሳቀስ ችግሩን ለማለፍ ሞክረናል። በተወሰነ ደረጃ እንደተግዳሮት የምንወስደው የልማት ጥያቄን በአግባቡ መመለስ የሚያስችል በጀት አለመገኘቱ ነው።
አዲስ ዘመን፡– በክልሉ አሁን ያለው ሠላምና ፀጥታው እንዴት ይገለጻል?
አቶ ደስታ፡– በክልሉ አሁን ያለው የሠላምና የፀጥታ ሁኔታ በጣም አስተማማኝ ነው። አስተማማኝ የሆነበትም ዋናው ምንጩ ከህዝቡ ጋር ያለው ሁኔታ ተግባቦት ያለበት በመሆኑ ህዝቡ የመጀመሪያ ጥያቄ ክልል እንሁን ነው። እሱ ጥያቄው በአግባቡ ከተመለሰ በኋላ በባህሪውም የሲዳማ ህዝብ ተግባብቶና ተባብሮ የሚኖር ህዝብ ነውና አካባቢያችንን ሰላማዊ አድርገን ከዚህ በኋላ ባገኘነው እድል አሟጠን በመጠቀም ፈጣን ልማት ማረጋገጥ ይኖርብናል የሚለውን ነው ይዘን እየተጓዝን ያለነው። በዚህ ሂደት ደግሞ አብሮን ተባብሮ ብሄር ብሄረሰብ ተቃቅፎና ተጋግዞ እንደአቅም ያለውን አብሮ በመካፈል የሚያስፈልገውንም አብሮ በማዋጣት ቀጣናውን አንድ ሆኖ ሰርቶ በመለወጥ እየተግባባን እንገኛለን። ይህ በመሆኑም ነው ሠላምን ማረጋጋጥ እምብዛም አስቸጋሪ ያልሆነው።
ከዚያ በተጨማሪ በመንግስት ደረጃም ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን በርቀት በመመልከት ችግር ከመፈጠራቸው በፊት የህግ የበላይነትን ማረጋገጥና መለሳለስ በሌለበት ቁርጠኛ አመራርና አቋም በውሰድ በምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ህገ ወጦች ችግር ሊፈጥሩ የሚዳዳቸው አካላትም ጭምር መፈናፈኛ አጥተዋል ማለት ይቻላል።
በአጠቃላይ ቀጣናችን ፍጹም ሠላማዊ ነው። ከህዝቡ ጋር ያለው ተግባቦትም ቢሆን እርስ በርስ በጣም የተቀናጀና የተናበበ በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ካሉ ከሁሉም ኮርነር ከምናየው የተሻለ አካባቢ ነው ብለን ነው እኛ የምንረዳው።
አዲስ ዘመን፡– በክልሉ ያለው የኢኮኖሚና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ምን ደረጃ ላይ ደርሷል?
አቶ ደስታ፡– የመሰረተ ልማት ሁኔታ ቀጥሎ የሚመጣውን የክልልን ልማት ለመሸከም ከሞላ ጎደል ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው። ከአዲስ አበባ እስከ ሲዳማ ክልል ዋና ከተማ እንዲሁም ወደወረዳዎች የሚያደርሰው መንገድ ዋና ዋናው የአስፓልት መንገድ ነው። እንዲሁም ከሞጆ ሻሸመኔ በቅርቡ የተመረቀው የክፍያ መንገድም ጭምር ወደእዚያ እየመጣ ይገኛል።
ከዚህ በተለየ ሁኔታ ኢንቨስተሮች ያለምንም ስጋት ወደክልላችን መምጣት ይችላሉ። ምክንያቱም ወደክልሉ መምጣት ቢፈልጉ የትራንስፖርት ሁኔታ ተግዳሮት አይሆንባቸውም። ምክንያቱም አማራጮች ብዙ እንደመሆናቸው ሲያሻቸው በአውሮፕላን መጠቀም ይችላሉ። ብዙ ወጪ ሳያወጡ እውቀትና ማሽናቸውን ይዘው መምጣት ለሚፈልጉ ደግሞ አስቀድሞ የተገነባ መሰረተ ልማት ያለ ሲሆን፤ በኢንዱስትሪ ፓርኮችና መሰል የመሰረተ ልማቶች ቀድመው የተዘጋጁ ናቸው። ይህን ተከትሎ አሁን ላይ ጥያቄው በብዛት ወደክልላችን በመምጣት ላይ ነው። ያንን ለመሸከም የሚችል አሰራርና ቅድመ ዝግጅት ነው እኛ እያደረግን ያለው።
ፈጣን አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የሰው ኃይል አደረጃጀትና የአስተሳሰብ ቅኝት በሌላ በኩል የቱ አካባቢ ያለው ሀብት ለየቱ ኢንቨስትመንት ይውላል የሚለውን ልየታና አቅምን የማወቅ ብሎም ትስስርን የመፍጠር ስራዎችን እየሰራን ነው የምንገኘው። ከዚህ አንጻር በተወሰነ ደረጃ ጥያቄዎችን እየመለስን ነው የምንገኘው።
በአሁኑ ወቅት የኢንቨስትመንት ፍላጎት በጣም ጨምሯል። ይህ ደረቅ ኢንቨስትመንት ብቻ ሳይሆን የቱሪዝምና የአገልግሎት አሰጣጡንም የሚያካትት ሲሆን፤ በዚህ ዘርፍ ስንመለከት ሰዎች በብዛት ወደሃዋሳ እየመጡ ያለበት ሁኔታ አለ። ከአርብ ጀምሮ ቅዳሜና እሁድ ከተማው በእንግዶች ይጨናነቃል። እንዲሁም ሳምንቱን ሙሉ የተለያዩ ስብሰባዎች ይደረጋሉ። ከአገር አቀፍ ጀምሮ የሚደረጉ ስብሰባዎች አሉ። የእነዚህ ሁሉ ድምር እንቅስቃሴ አካባቢውን በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው መልካም እያደረጉት ነው ያለው። ኮሮና እንኳን ባለበት በአካባቢው ያለው የንግድ እንቅስቃሴና የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ መልካም የሚባል ነው ብለን ነው የምንወስደው።
አዲስ ዘመን፡ በክልሉ በኑሮ ውድነት በተለይ ዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍሎች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ምን እየሰራችሁ ነው?
አቶ ደስታ፡– ከዚህ አንጻር በተለየ መልኩ የሰራነው ነገር የለም። በጥቅሉ ግን እንደ አገርም የኑሮ ውድነቱን ያባባሱ ምክንያቶች የአቅርቦት እጥረት ነው። እንዲሁም የአቅርቦት መሰናክሎች ናቸው። መሰናክሎች ብለን የምንወስዳቸው ያሉ ምርቶችን በመደበቅና በማከማቸት ጊዜያዊ እጥረት በመፍጠር ቀስ በቀስ በማውጣት ከፍተኛ የዋጋ ንረት እንዲፈጠሩ የሚደረጉ አሻጥሮች አሉ። በሌላ በኩል የምርት አቅርቦቱ በራሱ በባህሪው የዋጋ ውድነትን ያስከትላልና ልክ በተመሳሳይ እንዲህ አይነት እጥረት በአገር ደረጃ አለ።
ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ የበጋ መስኖ ጭምር በአገር ደረጃ እየተሞከረ እንዳለ ይታወቃል። በእኛም አካባቢ በተለይ በጓሮ አትክልት ጭምር ሰፊ የመስኖ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ አቅርቦቱን ከፍ ለማድረግ ሰርተናል። እነዚህ በሶስት ወር ውስጥ የሚደርሱ በመሆናቸው የኑሮ ውድነቱን ሊያረግቡ በሚችሉ የአትክልት አይነቶች ላይ በማተኮር በመስራታችንም መረጋጋትን ፈጥሯል።
የዋጋ ንረትን በአሻጥር የሚፈጥረውን አካል ደግሞ ያሉ ምርቶች ያለአግባብ እንዳይከማቹ ተከማችተውም ሲገኙ በግብረ ኃይል ርምጃ በመውሰድና በማስተማርም የግብይት ፍሰቱ ጤናማ ሆኖ እንዲቀጥል እንዲደረግ በመስራት ላይ ነን። በመሆኑም በሁለቱ በመታዝ ከዚህ በላይ የኑሮ ችግር እንዳይሰፋ አድርገናል፤ ይሁንና ችግሩ አሁንም ቢሆን ቀጥሏል። በቀጣይም ምን አይነት ርምጃዎች ቢወሰዱ ነው ከችግር መውጣት የሚቻለው የሚለው ላይ እንደአገርም የሚቀመጡ አቅጣጫዎችን ተከትለን ተግባራዊ የምናደርግበት ሁኔታ ነው ያለው። በተለያየ ደረጃ ግን ይህን አድርገናል ብለን የምንናገረው ነገር የለም።
አዲስ ዘመን፡– በክልሉ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በአሁኑ ወቅት ከእርሻ ዝግጅትና ከግብርና ግብዓት አቅርቦት አንጻር ምን እየተሰራ ነው? ግብርናውን ለማዘመንስ ምን ታስቧል?
አቶ ደስታ፡– ግብርና በተለይ አሁን ባለንበት በዝቅተኛ የእድገት ደረጃ ብዙ ሰው የሚያስተናግድልን የሥራ ዘርፍ ነው። ከምግብ ፍጆታ አኳያ ሲታይ ደግሞ የአገሪቱ የምግብ ፍጆታ የሚገኘው ከግብርና ምርት ነው። በተወሰነ ደረጃ እንዲያውም ለኢንዱስትሪዎች እንደግብዓት ሆኖ ያገለግላልና አስፈላጊቱ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም።
በዚህ መሰረት ግብርናን የማዘመኑ ነገር ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አንጻር አተኩረን እየሰራን ነው። ለዚህም አቅጣጫ አስቀምጠናል። ቀደም ብዬ እንዳልኩት በመስኖም አሁን ደግሞ በበልግም በተለያዩ ጊዜያት ነው ስራዎች የሚሰሩት። ከዚህ አንጻር የሲዳማ ክልል ሁሉንም አይነት የአየር ንብረት የያዘ ክልል እንደመሆኑ እንደየአየሩ ጸባይ የሚስማሙ የምርት አይነቶችን በመለየት ዓመቱን ሙሉ በአካባቢው ምርት ይመረታል።
በዚህም ያልታረሱ መሬቶች እንዲታረሱ በማድረግና ከትንሽ መሬት በርካታ ምርት ማግኘት የሚያስችለውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለምሳሌ በመስመር የመዝራት፣ ግብዓት የማቅረብና የአፈሩን አይነት በመለየት አስፈላጊውን ህክምና የማድረጉ ስራ ሁሉ ከግምት ውስጥ ገብቶ እየተሰራ ነው። መኸሩንም እንዲሁ ነው ሰርተን ያለፍነውና ምርትና ምርታማነት በተወሰነ ደረጃ አድጓል።
በአጠቃላይ ግብርና ሲባል ግን በእኛ አካባቢ ብዙ መልክ አለው። አካባቢው እንደሚታወቀው ዓመቱን ሙሉ አረንጓዴ ነው። የቡና ማሳ ያለበት አካባቢ ቢወሰድ ሁልጊዜ የሚኖር ቋሚ ሰብል ነው። በጫትም የሚሸፈኑ ሰፊ ማሳዎች አሉ። በእንሰት የተያዘም ወደ 150 ሺህ ሄክታር መሬት ያለ ሲሆን፤ እነዚህ ቋሚ ሰብሎች የሚባሉ ናቸው። የእነዚህን ሰብሎች ምርት የማሳደጉ ስራ ላይ እየተሰራ ነው፤ ለምሳሌ ከቡና አንጻር ዝርያውንና እንክብካቤውን በማሻሻል ምርታማነቱ እንዲያድግ ተደርጓል። ከዚህም አኳያ በዚህ ዓመት ካቀድነው በላይ የቡና ምርት ሰብስበናል። በእንሰት ምርት ላይ እንዲሁ አስፈላጊው እንክብካቤ በመደረጉ ከአንድ ሄክታር መሬት ላይ የሚሰበሰበው የምርት መጠን እንዲያድግ በትኩረት እየሰራን ነው። ለዚህም ነው ስለግብርና ስናስብ በክልላችን ስለ ገብስ፣ ስንዴና በቆሎ ብቻ አይደለም ማለታችን።
ከዚህ ውጭ የእንስሳት ምርትም ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ነው። እንደሚታወቀው የሲዳማ የቆዳ ስፋት ውስን ነው። በዚህ ምክንያት ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ ዘመናዊ ግብርናን ነው መከተል የሚያስፈልገን። ይህ በመሆኑ የሰብል ምርት ላይ ብቻ ሳይሆን የእንስሳት ምርት ላይም በማተኮር የምንሰራው፤ በዚህ ዙሪያ ያቀድነው የተለያዩ ዝርያዎችን በማሻሻል ምርታማነትን ለመጨመር ነው። አገር በቀል የሆኑ የዳልጋ ምርቶችን ስንመለከት ምርታማነታቸው ውስንነት ያላቸው ስለሆነ የውጭ አገር ዝርያ ያላቸውን በማዳቀል የተሻለ የወተት ምርትንም የሚሰጡትን ላሞች የማዳቀል ስራ ትኩረት የሚሰጠው ይሆናል። በዶሮ፣ በዓሳና በንብ ማነቡም ላይ እንዲሁ በትኩረት የምንሰራው ነገር ይሆናል። በዚህ ቅኝት ማህበረሰባችንን ከግብርናው ተጠቃሚ ለማድረግ ነው እየሰራን ያለነው።
አዲስ ዘመን፡– ምርጫውን በሁሉም መስኩ የተሳካ እንዲሆን እንደክልል መንግስት ምን እየሰራችሁ ነው ?
አቶ ደስታ፡– የዘንድሮን ምርጫ በጣም ታሪካዊ ምርጫ ነው ብዬ ነው የምወስደው። ምክንያቱም ከዚህ በፊት የተካሄዱ ምርጫዎች ህዝብ በተለያየ መንገድ ትችት የሚያቀርቡባቸው ናቸው። በተለይ ምርጫ ዴሞክራሲያዊም አሳታፊም አይደለም በሚል ሲነገርባቸው መቆየቱ የሚታወስ ነው። ያንን ሁሉ ሊቀርፍ የሚችል ዴሞክራሲያዊ የሆነና የዚሁ የዴሞክራሲ ባህሉም እንዲዳብር ነው እየተኬደ ያለው። በእኛ አካባቢ ፍጹም ሠላማዊ፣ ሂደቱም ምንም አይነት ማደናቀፍ የሌለበትና ዴሞክራያዊ እንዲሁም ነጻ እንዲሆን ነው እየሰራን ያለነው።
ህዝብ ድምጹን በነጻነት መስጠት ከቻለ ምርጫውና ውጤቱ ተዓማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ ያስችላል በሚል አስበን ነው እየሰራን ያለነው። እንደመንግስት መደገፍና ማመቻቸት ያሉብንን ጉዳዮች ደግፈን የምርጫ ሂደቱ ሠላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል አድርገናል። የምርጫ ጣቢያዎችና ክልሎች አመቺ በሆኑ ሁኔታዎች እንዲደራጁ እና የውስጥ ቁሳቁሱም እንዲሟላ አድርገናል። ጸጥታውን በተመለከተ የምርጫ ጣቢያው አካባቢና እንቅስቃሴውን የጸጥታ አካላት ጥበቃ እንዲያደርጉላቸው አድርገናል። ይህ በመሆኑ ሂደቱ እስካሁን ሠላማዊ ሆኖ ነው የቀጠለው።
እንደእኛ ክልል 12 ተፎካካሪ ፓርቲዎች አሉ። እነዚህ ፓርቲዎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው አባሎቻቸውንም አንቀሳቅሰው እንዲሁም እጩዎቻቸውን በሠላማዊ መንገድ አስመዝግበው እንቅስቃሴያቸውን ቀጥለዋል። አባሎቻቸውን በማንቃት ደጋፊውን የማሰባሰብ ስራ በነጻነት እየሰሩ ነው።
እኛም እንደመንግስት አባሎቻችንን የማወያየት፣ የማሰልጠንና የምርጫ ሂደቱ መንግስት ከመሰረቱ ሂደቱ ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲፈፀም ካለፉትም በተለየ ሁኔታ ቁርጠኛ ሆነን ለማለፍ ነው። ከአባሎቻችንም የሚጠበቀው ተፎካካሪዎችን የማደናቀፍ ሳይሆን የሚፈልጉትን የመደገፍና በሠላማዊና በህጋዊ መንገድ ብቻ ውሳኔዎችን ማሳለፍ መሆኑን በማስገንዘብ ያለምንም እንቅፋት ተፎካካሪዎች በነጻነት መንቀሳቀስ የሚችሉበትን ሁኔታ ፈጥረናል። ምናልባት ችግር ተፈጥሮ የሚገኝ ከሆነ በጋራ ምክር ቤት ተወያይቶ እና በጋራ አጣርቶ እና ወስነው መፍታት እንዲችሉ ነው የሚደረገው። እስካሁን ባለው ሁኔታ ምንም ኮሽታ አልተፈጠረም ማለት ይቻላል። ውጤቱን ደግሞ ሁላችንም መጨረሻ ላይ የምናየው ነው የሚሆነው፤ እሱን አሁን ላይ መተንበይ አልችልም።
አዲስ ዘመን፡– ምርጫውን በተመለከተ ያጋጠሟችሁ ችግሮች ምንድን ናቸው? በስጋት ያስቀመጣችኋቸው ችግሮች አሉ? ካሉስ እንዴት ፈታችኋቸው?
አቶ ደስታ፡– የእኛ ስጋት በሲዳማ ክልል ላይ አይደለም። ምናልባት ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች ምን ሊፈጠር ይችላል ብለን እንደአንድ አገር ዜጋና ከፍተኛ አመራር ያሰጋን ይሆናል እንጂ በእኛ ክልል ምንም ይፈጠራል ብለን አንሰጋም። እስካሁን ባለውም ሁኔታ በመግባባት ላይ ነው እየተሰራ ያለውና እኛ አካባቢ ሳንካ ይመጣል ብለን አናስብም። በጥቅሉ ከምርጫ በኋላ ወይም ደግሞ ምርጫ ሲቃረብ ተጀምሮም ቢሆን እስካሁንም ችግር የለም፤ በቀጣይም ችግር እንደማይፈጠር ነው የምንሰራው።
ችግር የሚኖር እንኳን ቢሆን በሁለት ነገሮች ላይ ታሳቢ በማድረግ ነው የተዘጋጀነው። የመጀመሪያ ነገር ህዝቡ እስካሁን ሂደቱን እያመነ እንዲሄድ ሁኔታውን በተመለከተ ግልጽና አሳታፊ እንዲሆን ነው እያደረግን ያለነው። ሐቅ ላይ ቆመው ትክክለኛነቱን እንዲመሰክሩ የሚያስችል ስራ እየተሰራም ነው። ከዚህም የተነሳ ህዝቡ የማይጠበቅ እንቅስቃሴ ያደርጋል የሚል እምነት የለንም። በግለሰቦች ደረጃ ምናልባት ከተለያየ ቦታ ተልዕኮ ወስደው ለመበጥበጥ የሚሞክሩ አካላት የሚኖሩ ከሆነ ህገ ወጥ ናቸውና በህግ አግባብ ለመመከት በቂ ዝግጅት አድርገናል። እንዲያም ሆኖ ምንም ነገር አይፈጠርም ብለን እናምናለን። ቢፈጠርም እንኳ ከህዝቡ ጋር በመወያየት ምንም እንዳይፈጠር እናደርጋለን ብለን እናስባለን። ከዚህ ውጭ የተለያየ እንቅስቃሴ የሚኖር ከሆነ ግን ህዝብም ጭምር አጋልጦ ስለሚሰጥ እኛም በህግ አግባብ እየተቆጣጠርን ምርጫውን ሠላማዊ አድርገን እንቀጥላለን። በዚህም እምነት አለን።
አዲስ ዘመን፡– ሲዳማ ክልል የኮቪድ 19 ከተስፋፋባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው፤ ይህንን ወረርሽኝ ለመከላከል ምን እየሰራችሁ ነው? የመተንፈሻ ማሽኖችም እጥረት እንዳይኖር ምን እየተሰራ ነው?
አቶ ደስታ፡– ከኮሮና ስርጭት አንጻር ካለፉት አራትና አምስት ወራት ወዲህ በአገሪቱም ደረጃ ስርጭቱ ከፍ ማለቱ ይታወቃል። እኛም ይህ ስርጭት እንዲባባስ አድርገን ነበር የሚል ግምገማ አለ። እነዚህ ሁሉ ተደምረው በሁለትና ሶስት ወራት ውስጥ የነበረው ሁኔታ በሲዳማና በሐዋሳ አካባቢ ከፍተኛ የኮሮና ስርጭት አለ የሚል ነገር ሲወጣ ነበር የሰነበተው። ያንን ለማስተካከል ህዝብን በማስገንዘቡ ደረጃ ሌት ተቀን ሰርተናል።
ከዚያ ባለፈ ደግሞ ህመሙ ያጋጠማቸው ወገኖቻችን ሂደቱ እንዳይባባስ የሚሰሩ የህክምና ስራዎች አሉ። ለዚህም የተለያዩ የህክምና ማዕከላትን በመክፈት ስራችንን ስንሰራ ቆይተናል። በዩኒቨርስቲው ስር የሚተዳደር ሪፈራል ሆስፒታል አለ። በዚህም ሆስፒታል ህሙማኑ በመጠቀም ላይ ናቸው። የኮቪድ ማዕከል በሚል አንድ የእናቶችና የህጻነት ህክምና የሚሰጥበት በቅርቡ የተመረቀ ሆስፒታል አለና እሱን ነጻ በማድረግ ለኮቪድ ህመምተኞች አገልግሎት እንዲሰጥ አድርገናል። ከሃዋሳ ውጭ ያሉትንም የህክምና ማዕከላት ለዚሁ እንዲሆን አድርገናል። በዚህ የተነሳ ከፍተኛ ጉዳት እንዳያደርስ የበኩላችንን ለመወጣት እያደረግን ነው። በተሰራው ስራ መከላከል ቢቻልም የደረሰው የህይወት ህልፈትና ጉዳትም ቀላል ነው የሚባል አይደለም።
ይህ በመሆኑ በቅርቡ የፍቼ ጨምባላላ በዓል ጨምሮ ሰዎች በአደባባይ ላይ የሚያፈጥሩ የኢድ በዓልንም ጭምር ጥንቃቄ በማድረግ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ እንዳይሰባሰብ ለማድረግ ተሞክሯል። በቤተሰብ ደረጃ በዓሉ በጥቂት ሰዎች በመሆን እንዲያልፍ ነው ጥረት እየተደረገ ያለው። ይህን ስናደርግ ግን በኃይማኖት የሚወሰኑ ጉዳዮችን ከኃይማኖት አባቶች ጋር በመምከር፣ በባህላዊ መንገድ የሚፈጸሙትንም እንዲሁ ከባህል አባቶች ጋር በመሆን ነው የወሰነው። ይህም የተደረገው የየራሳቸውን ውሳኔ ከወሰኑ በኋላ ነው ተግባራዊ ለማድረግ የሰራነው።
መንግስት ደግሞ የወጣውን የኮቪድ ፕሮቶኮል መተግበር ግዴታው ስለሆነ ተግባራዊ በማድረግ የተለያዩ ስራዎች ተሰርተዋል። ከዚህም የተነሳ ከፍተኛ መሻሻሎች ታይተዋል። ለሰው ህይወት መጥፋት ግን የመተንፈሻ መሳሪያ አለመኖር ብቸኛ ምክንያት አይደለም። ችግር የነበረው የመመርመሪያ ማሽን እንጂ ሌሎች ማሽኖች ነበሩ። ምክንያቱም በዚያው ማሽን እየተረዱ ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች በመኖራቸው ነው። በእርግጥ የማሽን ቁጥሩ ቢጨምር ኖሮ የጉዳቱ መጠን ሊቀንስ ይችል ይሆናል። ምክንያቱም ማሽኖቹ መኖራቸው ጉዳቱን በተወሰነ መልኩም ቢሆን ሊቀንስ መቻሉ ይታመናል። ነገር ግን የማሽን መኖርና አለመኖር ነው ብሎ መደምደም አይቻልም። ከምንም በላይ ግን ወሳኙ እንዳንያዝ የሚደረጉ ጥንቃቄዎች ናቸው። ከዚህም አንጻር ዋና ትኩረታችን አድርገን ነው እየሰራን ያለነው። ህዝቡ ግን የቸልተኝነት ባህሪውን መለወጥ አለበት የሚል መልዕክት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡– በቅርቡ የተመረቀው የሞጆ ሻሸመኔ የክፍያ መንገድ ለክልሉ እድገት የሚያበረክተው አዎንታዊ ሚና ምንድን ነው?
አቶ ደስታ፡– ማንኛውም መንገድ አዎንታዊ ሚና አለው፤ የዚህ አይነቱ ሰፊ መንገድ ሲመረቅ ደግሞ አዎንታዊነቱ ላቅ ያለ ነው። ስለዚህ ከሞጆ-ዝዋይ-ሻሸመኔ-ሐዋሳ የሚዘልቅ መንገድ ነው። ይህ መንገድ ከተጠናቀቀ በኋላ ከአዲስ አበባ ሐዋሳ፤ ከሐዋሳ አዲስ አበባ የሚደረገውን ምልልስ በጣም ያፋጥነዋል። ብዙ ወጪና ጊዜንም ይቆጥባል።
እሱ ብቻ ሳይሆን መንገዱ ወደፊት የሚመረቱ ምርቶችን በቀላሉ ወደማዕከላዊ ገበያ እንዲደርሱ ለማድረግም የሚያስችል በመሆኑ የኢንቨስትመንት ፍላጎትንና ፍሰትን በቀላሉ ያሳድጋል። ለአገራችንም ታላቅ የጀርባ አጥንት ነው የሚሆነው። ልማታችንንና ብልጽግናችንን በፍጥነት እንድናረጋገጥ የሚያደርግ ነው። የሲዳማን የማደግ ፍጥነትን የሚያሳልጥ በመሆኑ ቀጣዩም ስራ እስከ ሲዳማ ዘልቆ ስለሚሰራ ከወዲህ ለመንገዱ ዘላቂ ጥቅም ሰዎች ጥንቃቄ ያደርጉ ዘንድ ነው የምናገረው።
አዲስ ዘመን፡– ሰሞኑን በአዲስ አበባ የባህል ማዕከል ለመገንባት የሚያስችል ቦታ እንደተሰጣችሁ ተገልጿል፤ የት አካባቢ ነው፤ በዚያ ላይስ ምን ለመስራት አስባችኋል፤ ይህ ሃገራዊ አንድነትን ከማጠናከር አንጻር ምን አንድምታ አለው?
አቶ ደስታ፡– የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሲዳማ ባህል መገንቢያ ማዕከል ትክክለኛ ስራ ሰርቷል ብለን ነው የምናስበው። አዲስ አበባ ከተማ የአገራችን ዜጎች ሁሉ ዋና መዲና ነች። ይህ በመሆኑ ደግሞ ሁላችንም የምናስባት እንደአገራችን ነው። ሁላችንንም የምታስተናግድ ከተማ ነች። ከዚህም አንጻር የከተማዋ አስተዳደር ክልላችን የጠየቀውን ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል። ለዚህም በዕለቱ ያመሰገንን ሲሆን፣ በድጋሚም ላመሰግን እወዳለሁ።
በዚህ ስፍራ ላይ ከተማውን ሊመጥን የሚችልና የከተማ አስተዳደር የሚከተለውን ህገ ደንብ ጠብቀን ከፍተኛ የባህል ማዕከል ህንጻ ነው ለመገንባት ያሰብነው። ለህንጻው ዝርዝር ዲዛይን በቀጣይ የሚወጣ ሲሆን፤ በርካታ ነገሮችንም የሚይዝ ተደርጎ ይነደፋል ብለን እናምናለን። የሲዳማን ህዝብ ባህልና እሴት ሊያንጸባርቁ የሚችሉ ግብዓቶች የሚቀመጡባቸው እንዲሁም ለእይታ እድል የሚያስገኝላቸው ሙዚየም በውስጡ ይኖራል ብለን እናስባለን። ከዚህ ባለፈ የሲዳማ በአገር ውስጥ ያለና ከውጪ አገር የሚመጣ የሲዳማ ማህበረሰብ በቀላሉ የሚሰባሰብባቸው ቦታ ሆኖ ያገለግላል ብለን እናስባለን። ከዚህ ጋር ተያይዞ ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች ያላቸውን ጉዳዮች አያይዘን ለመገንባት ነው የምናስበው። የሲዳማን አካባቢ ወካይ የሆነ የባህል ማዕከል ነው ይገነባል ብለን መጥቀስ የምችለው። ከዚህ የባህል ማዕከል ጋር የሚመጥን የተለያየ ዲዛይን ያላቸው መዝናኛ ነው ለመገንባት ያሰብነው።
አዲስ ዘመን፡– ታላቁ የህዳሴ ግድብ እውን እንዲሆን የሲዳማ ክልል የራሱን ድርሻ ከማበርከት አንጻር ምን እያከናወነ ነው?
አቶ ደስታ፡– ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ በጉጉት የምንጠበቀውና ሁላችንም በጋራ እየገደብነው ያለነው ፕሮጀክት ነው። ስለዚህ የጋራ ሀብታችን ነው ማለት ነው። ከዚህ አንጻር የሲዳማ ህዝብ ያደረገው አስተዋጽኦ ግድቡ እንዲጠናቀቅ ካለው ፍላጎት የተነሳ የሚያስፈልገውን ገንዘብ እንዲሁም የሞራል ድጋፍ አበርክቷል። በተለይ ቀደም ብሎ በተደረገው የሀዝብ ንቅናቄ በአንድ ዙር ብቻ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ማዋጣት ችሏል። አጠቃላይ ለዚህ ግድብ ክልሉና የክልሉ ነዋሪዎች ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ወደፊትም ግድቡ ተገንብቶ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፉም ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ግድቡ እንዳይጠናቀቅ አንዳንድ አካላት በግድቡ ዙሪያ ሲያንዣብቡ ይታያል። ግድቡ እንዳይሳካ የሚፈልጉ የውስጥና የውጭ ተላላዎች ተቀናጅተው የሚፈጥሩት ጫና አለ፤ ይህ የሁሉም የኢትዮጵያን ፍላጎት የሚቃረን በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በዚህ አይነት ጉዳይ ላይ ቸልተኞች አይደሉም። ከዚህ በፊትም በተነኩና በተደፈሩ ጊዜ ሁሉ ማንኛውንም ጥቃት በጋራ የመከቱበትን ሁኔታ ማስተዋል ይቻላል። አሁንም ቢሆን ከግድቡ ጋር ተያይዞ የሚቃጡ ጥቃቶች ካሉ በአካልም ጭምር ሄዶ እስከመከላከል ድረስ የሲዳማ ወጣቶች ዝግጁ ናቸው። ባለፈው በአንዳንድ ተሳትፎዎች ላይ ግልጽ ተሳትፎዎችን አድርገናል። በወጣቶች በኩል አንዳንድ ዳርድንበር ከመጠበቅ አንጻር፣ የአገር ሉዓላዊነትና ህልውናን ከማስቀጠል አንጻር፣ መንግስት የሚያቀርባቸውን ጥሪዎች ተቀብሎ ፈጣን ምላሽ ከመስጠት አንጻር አካባቢውና ህዝቡ እያደረገ ያለው ትብብር ቀላል ስላልሆነ ይኸው አሁንም ተጠናክሮ ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን፡– የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰሞኑን የምርጫ ቀን እንደሚራዘም ጥቆማ ሰጥቷዋል፤ በዚህም ምርጫው ተራዝሟል። በዚህ ጉዳይ ላይ እንደክልል ያላችሁ ሀሳብ ምንድን ነው?
አቶ ደስታ፡– ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ሂደቱን በበላይነት የሚመራ ተቋም ነው። መንግስት በቁርጠኝነት ዴሞክራሲን ለማስረጽ ሲል ከሚሰራቸው ስራዎች ውስጥ አንዱ የምርጫ ሂደትን በገለልተኛነት እንዲፈጸም ማድረግ ነው። ለዚህ የሚሆን ግብዓትን የማሟላትና በቦርዱ ጣልቃ ያለመግባት እንዲሁም በነጻነት ውሳኔ እንዲያሳልፉ የማድረግ አቋሞች በመንግስት በኩል በቁርጠኝነት የተያዙ ጉዳዮች ናቸው። እኛም የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች እንደመሆናችን የእነዚህ ጉዳዮች በስራ አስፈጻሚ ሲወሰኑ አብረን የወሰንን እንዲሁም በየክልላችን የምናስፈጽም አካላት ነን። ከዚህ አንጻር በዚህ ጉዳይ ወሳኙ ምርጫ ቦርድ ነው ማለት ነው።
እንደመንግስትና እንደክልላችን መንግስት አሁን ባለው ሁኔታ ምዝገባ ተጠናቋል። በአገር አቀፍ ደረጃም ሰሞኑን በተደረገው ውይይት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ ሲገልጹ እንደሰማነው ከ36 ሚሊዮን የሚበልጥ ሰው መመዝገቡ ነው። ይህ ካለፈው ጊዜ ከነበረው ተሳትፎ የሚልቅ መሆኑን ሲገልጹ አስተውለናል። በአጠቃላይ ድምጽ ለመስጠት የሚያስችል በቂ ቅድመ ዝግጅት ከህዝብም ከመንግስትም አንጻር ተደርጓል ብዬ ነው የማስበው።
ሆኖም ግን ቦርዱ ድምጽ ከመሰጠቱ በፊት ማሟላት የሚገባቸው ጉዳዮች በመጀመሪያው አካባቢ የምዝገባውም ሂደት የተንገራገጨ መሆኑ ይህም በምርጫ ቦርድ ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥርና በምርጫ ቦርድ ላይ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚጠቀም በቦርዱ መገለጹ ይታወቃል። ይህንን ደግሞ መወሰን ያለበት እንዲሁም በህግም የተሰጠው ቦርዱ መሆኑ በግልጽ የተቀመጠ ጉዳይ ነው። እኛ እንደመንግስት በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የምርጫ ቀን ሆኖ የተቀመጠውን እቅድ ደግሞ መስራት ብንችል መልካም ቢሆንም የሚወስነው ምርጫ ቦርድ በመሆኑ እሱ ያለውን እናስፈጽማለን። ያንን የመጋፋት አዝማሚያ ሆነ ዝንባሌ የሌለን ሲሆን፤ መንግስት ተቀብሎ የሚያስፈጽም እንደሆነ እናስባለን። እኛም ቦርዱ የሚወስነውን ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ ነን ያለነው። ያንን ተግባራዊ እንደርጋለን።
ከዚህ አንጻር ጥቂት ሳምንት እንዲራዘም መደረጉ በምርጫው ላይ ተጽዕኖ አለው የሚል ግምት የለኝም። ምርጫ ቀን መራዘሙ በሌሎች ስራዎች ላይ የራሱ ተጽዕኖ ግን ይኖረዋል። ለምሳሌ የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ስራ መሰራት ያለበት በሙሉ ትኩረት ነው። የቅድመ ዝገጅትም ስራ ነው። በተጨማሪ ደግሞ ከፊታችን የበልግ ጊዜ ደርሷል። ስለዚህ አመራሩ በአሁኑ ጊዜ ምርጫን ለማስፈጸም ነው ታች ላይ ሲል የሚታየው። ይህን ጉዳይ ቶሎ አጠናቀን አረንጓዴ አሻራችንን ወደምናሳርፍበት መሄድ ነው የሚጠበቅብን። ከጸጥታውም አንጻር ብዙ ስራ አለ። ከዚህ አንጻር የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችን ትኩረት ይፈልጋል። የመኸር እርሻ ስራም ከአሁኑ ንቅናቄ የሚጠይቅ ነው። ተፈናቃዮችን ጭምር መልሶ የማቋቋም ጉዳይ ይጠይቃል። ይህን ሁሉ ገምግሞ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ ካሳለፈ ውሳኔውን መተግበር እንጂ ሌላ ድርድር አይኖርም።
አዲስ ዘመን፡– ምዕራቡ አለም የሀገሪቱን ሉአላዊነት የሚገዳደሩ ጫናዎችን ለማሳረፍ እየሄደበት ያለውን መንገድ እንዴት ያዩታል?
አቶ ደስታ፡- እውነት ነው ምዕራባውያን ይህን የሚያደርጉበት ምክንያት አላቸው። ሁሉም ሰው የሚሰራው ለጽድቅ ሳይሆን ለጥቅም ነው። ምዕራባውያንም ከዚህ የሚመደቡ ናቸው። የምዕራባውያን አውራ ማን እንደሆነ ይታወቃል። አውራዋ ከአፍሪካ ቀንድ የምትፈልገው ነገር አለ። በተለይ ከግብጽ ጋር ያላት ግንኙነት የአረቡንም ዓለም ለመያዝ እንዲሁም አፍሪካ ላይ ስጋት አላት። ቻይና ከእሷ በላይ አፍሪካን እየተቀራመተች ነው የሚል ሌላ ግምገማና ስጋት ነገር አለ፤ ስለዚህ አፍሪካን በእጅ አዙር መጠምዘዝና መያዝ ትፈልጋለች። አገራችን ደግሞ ከቻይና ጋር ያላት ግንኙነት ጠበቅ ያለ ነው። ከዚህ አንጻር ከቻይና ማላቀቅም ትሻለች። ለዚህ ሁሉ የኢትዮጵያ አቋምና ቁመና የተመቸ አይመስለኝም። እንደፈለግች የምታዘው አገርና መንግስት መፍጠር ነው የምትፈልገው። እነዚህ በርካታ ምክንያቶች ተሰብስበው የምዕራባውያን አቋም አሁን እንደምናየው አይነት አድርጎታል ብዬ ነው የማስበው። ሌሎቹ ደግሞ ከእርሷ የሚገኘውን ጥቅም መሰረት በማድረግ የተቃኘ አዝማሚያ ነው የሚያሳዩት። እነዚህን ሁሉ ፈተናዎች ግን እኛ መጋፈጥና ማለፍ የምንችለው የውስጥ አንድነታችንን በማጠናከር ነው። ከዚያ ውጭ አሁን የምንላቸው አገራት ግፋ ቢል ማዕቀብ ለመጣል ቢችሉ እንጂ ከኢትዮጵያ ጋር በአካል መጥተው መዋጋት አይችሉም። ማዕቀብ ለመጣልም የከረረ ግጭት ውስጥ መግባትን ይጠይቃል። የእኛ ዲፕሎማሲ ደግሞ በዚያ መልኩ ተጋላጭ ሆኖ አይሄድም። ድርድር፣ ውይይት የሚያስቀድም ነው። ይኸው ከሱዳን ጋር እንኳን ድንበር ተሻግረው ስንቱን ትንኮሳ እየፈጸመ አሁን የምንከተለው አቅጣጫ ግጭትን በሚያከር ሳይሆን በሚያለዝብ መልኩ ጊዜን በመግዛት ሂደት ውስጥ ነው ስራዎች እየተሰሩ ያሉት። እነዚህ ድምር አካሄዶች ለማዕቀብ አይመቹም። ማዕቀብ ቀርቶ የአባይን ጉዳይ የጸጥታው ምክር እንዲበይን ጭምር የተፈለገበት ሁኔታ ነበር። ወደማዕቀብም የሚመጣው በዚያ በኩል ነበር።
በዲፕሎማሲያዊና በተኬደበት ስልታዊ በሆነ አካሄድ ከጸጥታው ምክር ቤት በማውጣት ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ ድርድሩ ወደአፍሪካ መድረክ እንዲመጣ የተደረገበት ሁሉ ፈጥኖ ወደማዕቀብ የሚያደርሰን አይሆንም። የሚሆነው በእጅ አዙር ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለማሰማራት ነው። ይህንንም የሚያደርጉት ፍርፋሪ በመስጠት፣ ጥቅምና ስልጠናም በማከል ኢትዮጵያን ራሳቸው ኢትዮጵያውያን እንዲያፈርሱት የማድረግ ተልዕኮና ስትራቴጂ ነው የሚከተሉት።
አንድነታችንን በማጠንከር ነው የምንሻገረው ስንል ይህንን አዝማሚያ ኢትዮጵያውያን አውቀው አገር የሌለው ጥቅም፣ አገር ተዋርዳ ዜጋው የቱንም ያህል ሀብታም ቢሆን አያምርበትም። ስለዚህ ቅድሚያ የአገር ክብር ይበልጣል። አገር የአሁን ነዋሪው ብቻ ሳይሆን የመጪውም ትውልድ ህልውና ነው። ስለዚህ መልሰን መላልሰን በማሰብ ለአሁን ብቻ ሳይሆን ለመጪው ትውልድ ጭምር ማሰብ ይኖርብናል። እልህ በመጋባት አገርን የሚያክል ጥቅም አሳልፎ መስጠት በጣም ከባድ ውሳኔ ይመስለኛል። ይህ በመሆኑ ከዜጎቻችንና ከህዝቦቻችን ተላላኪ ለመሆን የሚዳዳቸው ሁሉ መላልሰው ቢያስቡበት መልካም ነው።
መላ ኢትዮጵያ ህዝብ ግን ሁኔታውን ተረድተው በተለያየ መልኩ የሚደረገውን ውዥንብር፣ ፕሮፓጋንዳዎችና ትንኮሳዎችን አንድነቱን በማጠናከር ማክሸፍ ይኖርበታል። ሁላችንም አላስፈላጊ ጫና እንዳይደረግብን ድምጻችንን ከፍ አድርገን አንድነታችንን በማጠናከር አልፎ አልፎ እነዚህ አካላት ተሳክቶላቸው ትንኮሳ ቢያደርጉም መንስኤያቸውን በማጤን የሚደረጉ ምላሾች የሰከኑ መሆንና አንድነታችንንም የሚያጠናክሩ መሆን ይገባቸዋል። የሚመጣውን ጫና በጋራ በመጋፈጥና ቀዳዳውን በመድፈን ነው ልንወጣው የምንችለው።
አዲስ ዘመን፡– የአሜሪካ መንግስት ሰሞኑን በትግራይ ጉዳይ ላይ ያወጣውን መግለጫ እንደ ክልል ፕሬዚዳንትና እንደ ዜጋ እንዴት አገኙት ?
አቶ ደስታ፡– እኛ መግለጫው ተገቢነት ያለው ነው ብለን አናምንም። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ አሜሪካ መዳኘትም አትችልም። ምክንያቱም ይህ የውስጥ ጉዳይ ነው፤ የሉዓላዊነት ጉዳይ ነው። ህግ የማስከበር ጉዳይ ነው። አንድ ሉዓላዊ አገርና መንግስት እነዚህን ርምጃዎች የመውሰድ ህጋዊ መብት አለው። አሜሪካ ድንበር ተሻግራ ኢራቅ ላይ፣ ሱማሊያ ላይ፣ አፍጋኒስታንና ሌሎች ላይ የምትሰራውን ስራ እኛ በይነን አናውቅም። ስለዚህ እኛ ደግሞ የምንወስዳቸውን ርምጃዎች ወንጀል ከሆኑ በወንጀል መክሰስ የሚችለው አካል መብት አለው። ወንጀል ካልሆነና ህጋዊነት ካለው የዓለም አገራት የማክበር ግዴታ አለባቸው። ያንን በጣሰ መልኩ ዳኛ የመሆንና የመበየን እንዲሁም የመጠምዘዝ አካል አድርገን ስለምንመለከት የተሰጡ መግለጫዎች ተገቢነት ያላቸው ናቸው ብለን አንወስድም፤ አናምንምም። የአሜሪካ መንግስትም እንዲያቆም ነው የምንጠይቀው። በአሜሪካ የተደረገብን ጉዳይ እንደእኔ ኮሮና ባይከለክለን ኖሮ ኢትዮጵያውያንን ሰልፍ ልንወጣ የሚያስገድደን ጉዳይ ነበር። የኮሮና ሁኔታ የማይፈቅድ በመሆኑ ሁላችንም በተለይ ደግሞ ሚዲያዎች ከሰራችሁበት ድምጻችን ከፍ በማድረግ በአንድ ላይ ልናሰማበት የሚያስችለን ሁኔታ ነው መመቻቸት ያለበት።
አዲስ ዘመን፡– የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት?
አቶ ደስታ፡– በሁለት ጉዳይ ላይ መልዕክት ማስተላለፍ መልካም ይመስለኛል። የመጀመሪያው በአገራችን በዚህ ዓመት ለማካሄድ የታሰበው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ከፍተኛ ትርጉም የሚሰጠው ነው። ለዚህ አገር መድኃኒቱ ዴሞክራሲ ነው። ዴሞክራሲ የሚሰርጽባቸው መንገዶች በጣም በርካታ ቢሆኑም የመንግስት ስልጣን በከፍተኛ የህዝብ ወሳኝነት ሲረጋገጥ ነው። ይህ ለህዝብ የመወሰን ጉልበት የሚሰጠው እና የስልጣን ባለቤትነቱን የሚያረጋግጥለት ክዋኔ ደግሞ ምርጫ ነው፤ ስለዚህም ምርጫ ከዴሞክራሲ አንጻር ያለው ጉልበት ከፍተኛ ነው።
ከዚህ በፊት የምንፈልገውን ለማሳካት እንጓዝ የነበረው በጉልበት ነው፤ አገራችንንም ስንት ዙር ከእድገቷ ወደኋላ እየጠለፍን፣ እየሰራን፣ እያፈረስን፣ እያቃጠልን መጥተናልና እንደዚህ አይነት አዝማሚያዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቁ ለልጆቻችን ጭምር ዴሞክራሲን እንድናወርስ፣ የሚፈልጉትን በነጻነት በወረቀት ላይ ብቻ እንዲወስኑ ይህን በር የሚከፍትልን ምርጫ ከአሁኑ የሚጀመርና ስድስተኛው ምርጫ እድልም በመሆኑ ህዝባችን በነጻነት በነቂስ ወጥቶ የሚሻውን ፓርቲ እንዲመርጥና በመምረጥ ሂደት በነጻ እንዲወስን ነው። ለመወሰን ግን ካርድ ይዞ በዕለቱ መገኘት ነው። በዚህም ዴሞክራሲውን ሁላችንም ተባብረን ወደፊት እንድንወስድ የሚል መልዕክት ነው ያለኝ።
ሁለተኛው መልዕክቴ አሁን ያለንበት ወቅት ኢትዮጵያን በእጅጉ መተባበርን የሚጠይቀን ነው። ለሁላችንም የሚያምርብን በዚህች በታላቅ፣ ብዙ እድሎችን በውስጧ አጭቃ በያዘችው፣ ነገር ግን በአግባቡ በማናውቃትና በድህነት በምትገለጽ አገራችን ነው ብዬ አስባለሁ። አገራችንን ሁላችንም ልንጠብቃትና ልንከባከባት ይገባል።
አገራችን በአሁኑ ጊዜ ተወጥራ ነው ያለችው፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ከዚህ ካንዣበበብን የውስጥና የውጭ ጫና አገራችንን በማላቀቅ ክብሯን ጠብቃ ለዜጎቿ አለኝታና መከታ ሆና ሁላችንም የምንመካባት እንድትሆን ማድረግ ይገባናል። ይህ ኃላፊነት የሁላችንም ነው። ሁላችንም ከልዩነታችን ይልቅ አንድነታችንን አጠናክረን በረባው ባልረባው ከመገፋፋት ይልቅ መከባብርንና መተባበርን፣ ሰጥቶ የመቀበልንና የወንድማማችነት እሴቶችን በማጠናከር ዳር ድንበሯን በማስጠበቅ ለትውልድ የተሻለች አገር ማውረስ ይኖርብናል። ለዚህ ስኬት ደግሞ ሁላችንም እንትጋ። አንድነታችንን በማጠናከር ሁላችንም ለአገራችን ዘብ እንቁም።
አዲስ ዘመን፡– ለሰጡኝ ሰፊ ማብራሪያና ለሁልጊዜ ተባባሪነትዎ ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ደስታ፡– የፕሬስ ድርጅት ሐሳባችንን በመስማትና ለኢትዮጵያውያን በማድረስ ፈር ቀዳጅ በመሆኑና ቀኝ እጃችን በመሆኑ በተለየ መልኩ ላመሰግን እወዳለሁ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2013