
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ አጀንሲ አገልግሎቱን በይበልጥ ለማሳለጥ ለአየር ጠባይ ለውጥ ተጋላጭ ከሆኑ አራት ተቋማት ጋር በቅንጅት ለመሥራት መወሰኑን ገለፀ።
ኤጀንሲው አገልግሎቱን ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ ለአየር ጠባይ ለውጥ ተጋላጭ ከሆኑት፤ ከግብርና ሚንስቴር፣ ከደን አካባቢና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን፣ ከጤና ሚንስቴር፣ ከውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚንስቴርና ከብሔራዊ አደጋ ሥጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር የጋራ ማዕቀፍ ስምምነት ተፈራርሟል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ እንደገለጹት፤ እያደገ የመጣውን የሚቲዎሮሎጂ ፍላጎት ለማሟላት በተለይ በአየር ሁኔታና ጠባይ መለዋወጥ ምክንያት ጉዳት የሚደርስባቸው ተቋማትን በጥናት በመለየት በጋራ ለመሥራት ወስኗል።
ሚቲዎሮሎጂ ኤጄንሲ የአገሪቱን መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥና ሥነ ምዳርን የሚወክሉ የመረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎችን በማቋቋም የአገርን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት በሚደግፍ መልኩ የአየር ሁኔታ መረጃዎችን በመተንተንና በማሰራጨት ረገድ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑንም ገልፀዋል።
ኤጀንሲው በአሁኑ ጊዜ አንድ የዋናው መስሪያ ቤትና 11 የክልል ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከላትና የተለያዩ ደረጃ ያላቸው የገጸ-ምድርና በሰው አማካኝነት መረጃ የሚሰበሰብባቸው ማዕከላቱን ከፍ ማድረጉንም ጠቁመዋል።
አየር መከታተያ ራዳር በመጠቀምና ዘመናዊ የአየር ብክለት መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂን በመጠቀም አገልግሎት ከመስጠት አኳያ ኤጀንሲው ከአፍሪካ ተመራጭ ከሆኑት የሚቲዎሮሎጂ ተቋማት አንዱ ለመሆን መብቃቱንም አስታውቀዋል።
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚንስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው፤ መንግሥት የኤጀንሲውን ሥራ ለማጎልበት ከሌሎች ተጓዳኝ ዘርፎች ጋር በቅንጅት እንዲሠራ ተገቢውን ድጋፍ ሲያደረግ መቆየቱን አስታውቀዋል።
ኤጀንሲው የላቀ አገልገሎት በመስጠት አገሪቱ የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ እውን በማድረግ ረገድ ድርሻውን በተገቢው እንዲወጣ ከአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር በይበልጥ ተቀራርቦ መሥራት እንደሚጠበቅበት ገልፀዋል።
የዓለም ሚትዎሮሎጂ ድርጅት እ.ኤ.አ በ1953 እንደ ተቋቋመ ኢትዮጵያ አባል አገር መሆኗን ያስታወቁት ኢንጅነር ስለሺ፣ የኢትዮጵያ ሚትዎሮሎጂ ኤጀንሲም በዓለም አቀፍ ትብብር ረጅም ታሪክ ያለው መሆኑን ጠቁመዋል።
ከዓለም አቀፉ ትብብር በተጨማሪ ለአገራዊ ትብብር ትኩረት መስጠቱ በበጎነት የሚጠቀስ መሆኑን አመልተው፤ ተቋማቱ በቅንነት በመውሰድ በሃላፊት መንፈስ እንደየተቋሙ ተጨባጭ ሁኔታ በመተርጎም ጥቅም ላይ እንዲያውሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በተያያዘ ዜና በኢትዮጵያ በክረምት ወቅት ሊከሰት እንደሚችል የሚጠበቀውን መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ወደ መልካም አጋጠሚ በመቀየር እንደሚገባም የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ገልጿል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ እንደገለጹት፤ በመጪው የክረምት ወቅት ሊኖር የሚችለውን መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ ኤጀንሲው የሚሰጣቸውን የቅድመና ሌሎች የማስጠንቀቂያዎችን ባግባቡ በመተግበር ወደመልካም አጋጣሚ በመቀየር የአደጋ ሥጋቶችን መቀነስ ይገባል።
በዘንድሮው የክረምት ወቅት ሊኖር የሚችለውን የአየር ጠባይ አዝማሚያ አስቀድሞ በመተንበይ ከክስተቱ ተጠቃሚ ለመሆን፣ ተጽዕውንና የአደጋ ተጋላጭነቱንም ለመቀነስ ኤጀንሲው የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል።
እንደ ሀገር የተያዙ የልማት ሥራዎችን ለማሳካት የዘንድሮውን የክርምት ወቅት መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ ክስተት መኖር ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን በመቀነስ በኩል ሴክተር መሥሪያ ቤቶችም በቅርበትና በክትትል ሊሠሩ እንደሚገባም አስታውቀዋል።
ዋቅሹም ፍቃዱና ሙሳ ሙሀመድ
አዲስ ዘመን ግንቦት 18 ቀን 2012 ዓ.ም