“የጥናትና ምርምር ሥራዎች ተተግብረው ለውጥ ማምጣታቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል” – ወይዘሮ ሎሚ በዶ

-ወይዘሮ ሎሚ በዶ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ

አዳማ፦ የሚሠሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ሥራ ላይ ውለው የኅብረተሰቡን ሕይወት በመቀየር ውጤት ማምጣታቸውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ ገለጹ።

ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራሮችና አባላት ጋር ትናንት በአዳማ ከተማ ምክክር ሲካሄድ እንዳሉት፤ በተለዋዋጭ ዓለም ውስጥ በተለመደው የአሠራር ሥርዓት የምናልመውን ብልፅግና ማሳካት አይቻልም። ያለንን የሰው ሀብትና እምቅ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ሀብቶች በሳይንሳዊ ዘዴ ጥቅም ላይ ማዋል ያስፈልጋል። በመሆኑም የሚሠሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ሥራ ላይ ውለው በኅብረተሰቡ ሕይወትና አኗኗር ላይ ውጤት ማምጣታቸውን ማረጋገጥ ይኖርብናል ብለዋል።

ከጥናትና ምርምር ተቋማት የሚወጡ ሳይንሳዊ የአሠራር ዘዴዎችን እና ምክረ ሀሳቦችን መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመው፤ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ላለፉት ዓመታት ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱንና ከኢንስቲትዩቱ የሚወጡ ጥናቶችና ምክረ ሀሳቦች ለሕዝብ ግልጋሎት መዋላቸውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል።

ለምክር ቤቱ የተሰጡ ተልዕኮዎችን ለመፈጸምም የኢንስቲትዩቱ የጥናት ውጤቶች ትልቅ ግብዓት መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በረከት ፍስሐጽዮን በበኩላቸው፤ ፖሊሲዎቻችን እና ስትራቴጂዎቻችን ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር የተጣጣሙ ከሆኑ የእድገት ጉዞችን ፈጣን መሆኑ አይቀሬ ነው ብለዋል።

ለዚህም ጥልቅ ሃሳብ አመንጭ ተቋማት የሕዝብን አስተያየት በማዳመጥ እና የመንግሥትን ፍላጎት በመረዳት፣ በማስረጃ ላይ የተመሠረቱ ምክረ-ሃሳቦችን በማፍለቅ እና ተደራሽ በማድረግ ጥያቄዎች እንዲመለሱ፣ ችግሮችም መፍትሔ እንዲያገኙ መሥራት እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋማት የሚቀርቡ የመፍትሔ ሃሳቦችን የሚያውቁበትና ሀገራዊ የዕቅድ ሂደቶችም ሁሉን ባለድርሻ አካላት ባሳተፉ ማስረጃዎች የተመሠረቱ እንዲሆኑ ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢንስቲትዩቱ የሚከናወኑ ጥናቶች የፖሊሲ ክፍተቶችን ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ዕድሎችንና የተግባር አቅጣጫዎችን እያሳዩ መሆኑን አንስተው፤ ከዘላቂ ልማት ግቦች አተገባበር አፈፃፀምና ከመዋቅራዊ የኢኮኖሚ ለውጥ እና የድህነት ቅነሳ እስከ የሥነ ሕዝብ አወቃቀር ለውጦች፣ የአየር ንብረት መቋቋም እና የአካታች አስተዳደር የመሳሰሉ በርካታ ምርምሮችን ማካሄዱን ጠቅሰዋል።

ምርምሮች የጋን መብራት ሆነው በሸልፍ ላይ የማይቆዩ፣ በምትኩ ወደ ተጨባጭ ፖሊሲዎች፣ የሕግ ማሕቀፎች፣ የአፈፃፀም መመሪያዎች እና ሊመዘኑ ወደሚችሉ ውጤቶች እንዲተረጎሙ ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።

በፖሊሲ አወጣጥ ሂደት ላይ እያጋጠሙ ካሉ ፈተናዎች አንዱ በማስረጃ ማመንጨት ዙሪያ፣ በፖሊሲ ቀረጻ እና በተጨባጭ አፈፃፀም መካከል ያለው ልዩነት ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በአብዛኛው ተስፋ ሰጪ ምርምሮች ከበጀት አመዳደብ፣ ከዕቅድ ማሕቀፎች፣ ከትግባራ ተቋማዊ አደረጃጀቶች ግልፅ አለመሆን፣ ከትግበራ አቅም እጥረት ወይም ከክትትልና ግምገማ ሥርዓቶች መዛነፍ ምክንያት ሲመክኑ ይስተዋላሉ ነው ያሉት።

መድረኩ ሕግ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ እቅድ አውጪዎች እና አስፈፃሚዎች ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እንደሚያስችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ፀጋ፤ ኢንስቲትዩቱ በመረጃ ላይ ተመሥርቶ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ሃሳቦችን በማመንጨት የፖሊሲና ስትራቴጂ ሠነዶችን በማዘጋጀት፤ ለለውጡ አጋዥ የሆኑ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የቱሪዝምና የአረንጓዴ ልማት ምክረ ሃሳቦችን እያቀረበ መንግሥትን እያማከረም ይገኛል፡፡ ለአንድ ሀገር ዘላቂና ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ትክክለኛና ችግር ፈቺ ፖሊሲዎችን መንደፍ ይጠይቃል ብለዋል።

ኢንስቲትዩቱ ሀገራዊ ለውጡን በብቃት ለመደገፍ እንዲቻል በሥራ ላይ ያሉትን ፖሊሲዎች ጥንካሬዎች፣ ያስመዘገቧቸውን ስኬቶች፣ ያሉባቸውን ድክመቶች እና ተግዳሮቶች በማጥናት፣ ፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀሩ የበለጠ እንዲጠናከር የሚያደርጉ እና ተግዳሮቶቹን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ተጨባጭ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትንና ሀገራዊ ብልፅግናን የሚያረጋግጡ ችግር ፈቺ የሆኑ አዳዲስ ምክረ ሃሳቦችን እያቀረበ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

በሥራ ላይ የሚገኙትንም ፖሊሲዎች በመፈተሽ፣ ጥልቀትና ወቅታዊ እንዲኖራቸው በመረጃ ላይ ተመርኩዞ ምክረ ሃሳብ በማዘጋጀት በሀገር ልማት ላይ ጉልህ አስተዋፅዖ በማበርከት ላይ መሆኑንም አብራርተዋል።

በአማካኝ በየዓመቱ 50 የጥናትና ምርምር ሥራዎች እያጠናቀቀ ለፖሊሲ ግብዓት እንዲሆኑ ለሚመለከታቸው አካላት አሰራጭቷል ያሉት አቶ ፍቃዱ፤ በ2017 የበጀት ዓመት ብቻ በኢኮኖሚ ዘርፍ 8፣ በማኅበራዊ ዘርፍ 7፣ በኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ዘርፍ 12፣ በመልካም አስተዳደርና በሕግ የበላይነት 4፣ በግብርና እና ገጠር ልማት ማዘመን 2፣ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ 2፣ በአጠቃላይ 35 ምርምሮችን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡

የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ለማካሄድ ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑ ከመንግሥት በጀት በተጨማሪ የፋይናንስ ምንጭን ለማሳደግ ባቀደው መሠረት በያዝነው በጀት ዓመት ብቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚወጡ የጥናትና ምርምር ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ሥራውን እየደገፈ መሆኑን አስረድተዋል። በቀጣይነትም የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ የሆኑ ዘርፎች ላይ በትኩረት እንደሚሠራ አመልክተዋል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You