
አዲስ አበባ፦ የዘመኑ አርበኝነት ምርታማነትን በማሳደግ የኢትዮጵያ መዳረሻ የሆነውን ብልፅግናን እውን ማድረግ እንደሆነ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የሸገር ኢንቨስትመንት ኤክስፖ ከትናንት በስቲያ ሲጠናቀቅ እንዳሉት፤ የእኛ ዘመን አርበኝነት ማምረት ነው፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ዓላማው ምርትን በማስፋት እና ገቢ ምርትን በመተካት የውጭ ምንዛሪን ማስቀረት መቻል ነው። የኢትዮጵያ መዳረሻ የሆነውን ብልፅግናን እውን ለማድረግ ምርታማነትን ማሳደግ የእኛ ዘመን አርበኝነት ነው ብለዋል።
ብልፅግናን እውን ለማድረግ በምርት ራስን መቻል ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ አርሶ አደሮች ኢንቨስትመንት ወደ አካባቢያቸው ሲመጣ መጣባችሁ እየተባሉ የሚሸሹት ሳይሆን የሚሳተፉበት መሆን እንደሚገባው ገልጸዋል።
ሁሉንም የሚያካትትና የሚያሳትፍ ኢንቨስትመንት ለሀገር እድገት ወሳኝ እንደሆነም ተናግረዋል። ባለሀብቱም ሆኑ አርሶ አደሮች ብቻቸውን ሊያሳኳቸው ያልቻሏቸውን በጋራና በጥምረት ውጤታማ ሥራ መሥራት እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል።
በምግብ ራስን መቻል ብቻ ሳይሆን በኢንዱስትሪ ምርቶችም ራስን መቻል እና ኤክስፖርት ማድረግ አስፈላጊ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ተኪ ምርቶች ላይ በስፋት እየተሠራ ያለውም በዚህ እሳቤ መሆኑን ጠቅሰዋል፤ ለዚህም በሸገር ከተማ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ዋነኛ የመቻላችን ማሳያ ናቸው ብለዋል።
ሰፊ ሀገር እና ብዙ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ መሠረተ ልማቶችን በማስፋት አምራቾችን የመደገፍ ሥራ መሥራት እድገትን የሚያፋጥን እንደሆነ ገልጸው፤ ፖሊሲዎችን በማውጣት አምራቾችን ለማበረታታት ብዙ ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
የመንገድ እና ሎጂስቲክስ ሥራዎችንም በማዘመን የዘርፉን ከባቢ ለማሳለጥ እየተሞከረ እንደሚገኝ ገልጸው፤ መጪው ዘመን የተሻለ ስለሚሆን አምራቾች እና ባለሀብቶች ዘርፉን እንዲቀላቀሉም ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በዕለቱ ለአርሶ አደሮች የተሰጠው ዕውቅናም፤ አርሶአደሮች ግብር ከፋይ፣ የሥራ ዕድል ፈጣሪ፣ አምራች፣ ላኪ እና ገቢ ምርትን የሚተኩ መሆናቸውን ያረጋገጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተሰጠው ዕውቅና አርሶ አደሮች የኢንቨስትመንት ተጠቃሚ መሆናቸውን አጉልቶ ያሳያል ብለዋል።
የሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሸገር ከተማ አዲስ እሳቤን ይዞ የመጣ እና እሳቤውም የምርት እና የኢንዱስትሪ ከተማ በመፍጠር የኢኮኖሚ ስበት ማዕከል መሆን ነው ብለዋል።
የኢኮኖሚ ማዕከል የመሆን ዓላማ ያለው ከተማ ማምረት፣ አምራችን መደገፍ እና ወደ ዘርፉ እንዲቀላቀል እገዛ ማድረግ ይገባዋል ያሉት ተሾመ (ዶ/ር)፤ የሸገር ከተማ ይሄንን ለማድረግ ቀን ከሌሊት እንደሚሠራ ጠቁመዋል፤ ኤክስፖውም የዚህ ማሳያ እንደሆነ አመልክተዋል።
ለሦስት ቀናት ሲካሄድ በቆየው ኤክስፖ የሚፈለገው ውጤት እንደተገኘ የተናገሩት ከንቲባው፤ በርካታ ኢትዮጵያውያን ዜጎች እንደጎበኙት፣ ከ150 በላይ አምራቾች እንደተሳተፉበት እና ከ30 በላይ የውጭ ዜጋ ባለሀብቶች እንዲሁም 10 ዓለምአቀፍ ዲፕሎማቶች እንደተገኙበት አብራርተዋል።
በመርሐ ግብሩ ለሞዴል አርሶ አደሮች፣ አገልግሎት ሰጭዎች እና አምራቾች እውቅና እና ሽልማት ተበርክቷል።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሐምሌ 2 ቀን 2017 ዓ.ም