
አዲስ አበባ፡- በየካ ክፍለ ከተማ የተገነቡ ከ200 በላይ የህብረተሰብ አገልግሎት ሰጪ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው በሚቀጥለው ሳምንት አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ተክሌ ገለጹ።
ፕሮጀክቶቹ ትናንት በብዙሃን መገናኛ ባለሙያዎች በተጎበኙበት ወቅት ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ አስፋው እንደገለጹት፤ በዚህ ዓመት ከተጀመሩት 113 ከፕሮጀክቶች መካከል 111 ተጠናቀዋል።
ፕሮጀክቶች በክፍለ ከተማው 96 ቦታዎች ላይ የተገነቡ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ አስፋው፤ 503 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገባቸውና የህብረተሰቡን የቆየ ቅሬታ የሚፈቱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቶቹ የትምህርት፣ የጤና፣ የወጣቶች የስብዕና ግንባታ ማዕከላትና የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው። በመንግሥት ብቻ ሳይሆን በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተሰሩ፣ አዲስ አበባ ከተማን የሚመጥኑና የሚያስውቡ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
‹‹ኮብልስቶን የነበረ አንድ ኪሎ ሜትር መንገድ በ24 ሰዓት ውስጥ አስፋልት ተደርጓል›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ይህ፣ የኮብልስቶን መንገዶችን ወደ አስፋልት በፍጥነት መቀየር እንደሚቻል ማሳያ ይሆናል ብለዋል።
የየካ ክፍለ ከተማ ኮንስትራክሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወልደሰንበት ገብሬ በበኩላቸው፤ እየተሰሩ ያሉ ፕሮጀክቶች የሥራ ዕድል ፈጠራን ያካተቱ ሼዶች እንዳሏቸው አስታውቀዋል።
ከዚህ በፊት አንድ ዓመት መውሰድ የሌለበት ፕሮጀክት ሁለትና ሦስት ዓመታትን ይወስድ እንደነበር ጠቁመው፤ ክፍለ ከተማው በጀመረው ለውጥ የአንድ ዓመት ፕሮጀክት በስድስት ወር መጨረስ እየተቻለ ነው ብለዋል።
‹‹በክፍለ ከተማው በሁለት ሳምንት ውስጥ 272 ትምህርት ቤቶች ተጠናቀዋል›› ያሉት ኃላፊው፤ ትምህርት ቤት ባልነበረባቸው ወረዳዎች ትምህርት ቤት መገንባቱን አስታውቀዋል። ለአብነትም በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ኪዳነ ምህረት አካባቢ ባለ አራት ወለል ትምህርት ቤት ተገንብቶ አገልግሎት መጀመሩን ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ወልደሰንበት ገለፃ፤ በየካ ክፍለ ከተማ 02 አካባቢ ወንድራድ ትምህርት ቤት የአካል ጉዳተኞች ትምህርት ቤት በ30 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ ነው።
ትምህርት ቤቱ ባለ ሦስት ወለል ሲሆን፤ ሁሉንም አይነት የአካል ጉዳተኝነት ታሳቢ ተደርጎ የተገነባ መሆኑን ጠቁመው፣ የህንፃው መውጫ በደረጃዎች ሳይሆን ለዓይነ ሥውራን በሚያመች መንገድ የተሠራ ነው። በውስጡ የተለያዩ አገልግሎቶችን ይዘዋል ብለዋል።
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 18 ቀን 2012 ዓ.ም