
አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የእጩዎች ምዝገባን አስመልክቶ ለቀረቡ አቤቱታዎች ምላሽ ሰጠ።
ቦርዱ ትናንት በማህበራዊ የትስስር ገጹ እንዳስታወቀው ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች በተመዘገቡ እጩዎች ላይ ያላቸውን ቅሬታ እና አቤቱታ ሲቀበል መቆየቱን አስታውሷል። ዋና ዋናዎቹ ውሳኔ የተሰጠባቸው አቤቱታዎችንም አስታውቋል።
በዚሁ መሰረት የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ በወላይታ ዞን ዓቃቤ ሕግ በእጩነት ተመዝግበዋል ብሎ አቤቱታ ያቀረበውን ጥያቄ ቦርዱ ተቀብሎ ለብልጽግና ፓርቲ የዓቃቤ ሕግነት ሥራቸውን መልቀቃቸውን ወይም ዓቃቤ ሕግ መሆን አለመሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ እንዲያቀርብ ቦርዱ ጠይቋል።
የጋምቤላ ህዝብ ነፃነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ብልጽግና ፓርቲ ካቀረባቸው እጩዎች መካከል የክልሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ቢሮ ሃላፊ እንደሆኑና ይህም ከሕጉ ጋር እንደሚቃረን በመግለጽ አቤቱታ አቅርበዋል። በዚህም መሰረት ቦርዱ ለብልጽግና ፓርቲ እጩው ሥራውን መልቀቅ እንዳለባቸው ወይም እጩነታቸውን መተው እንደሚገባቸው ወስኖ ለፓርቲው አሳውቋል።
የጋምቤላ ህዝብ ነፃነት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ብልጽግና ፓርቲ በአኮቦ ወረዳ ምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረባቸው እጩ ተወዳዳሪ የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ፣ በአቦቦ ወረዳ ምርጫ ክልል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩት የፀጥታ ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሃላፊ፣ እንዲሁም በአቦቦ ወረዳ ምርጫ ክልል ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩት የክልሉ ሚሊሺያ ጽ/ቤት ሃላፊ መሆናቸውን እና ይህም ከሕጉ ውጭ መሆኑን በመግለጽ አቤቱታ አቅርቧል። ቦርዱ አቤቱታውን መርምሮ እና ሕጉን ተመልክቶ ተቀባይነት እንደሌለው በመወሰን ለፓርቲው አሳውቋል።
ከኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሴያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) በቀረበ አቤቱታ ብልጽግና ፓርቲ ካቀረባቸው እጩ ተወዳዳሪዎች መካከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪ በአዋጅ ቁጥር 1162/11 አንቀጽ 31 በተደነገገው መሠረት ለእጩነት የሚያበቁ መመዘኛዎችን ተወዳዳሪው እንደማያሟሉ እና በምርጫ ክልሉ ለረጅም ዓመታት በሥራም ሆነ በትምህርት ምክንያት እንዳልነብሩ በመግለጽ አቤቱታ አቅርበዋል።
ቦርዱ አቤቱታውን መርምሮ፤ ተወዳዳሪው በምርጫ ክልሉ መስፈርቱን ስለማሟላታቸው ተረጋግጦ በእጩነት ተመዝግበው ሠርተፊኬት የተሰጣቸው በመሆኑ እና ፓርቲው አቤቱታውን በወቅቱ ባለማቅረቡ አቤቱታው በቦርዱ በኩል ተቀባይነት ያላገኘ መሆኑን ለፓርቲው በደብዳቤ አሳውቋል።
ኢሶዴፓ በሌላ አቤቱታ ለቦርዱ ባስገባው ደብዳቤ የብልጽግና ፓርቲ ካቀረባቸው እጩ ተወዳዳሪዎች መካከል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እጩ ተወዳዳሪ የሆኑት በ2005 የአካባቢ ምርጫ የማረቆ ወረዳ ምክር ቤት በቆሼ አካባቢ ቀ/ገ/ማ የወረዳ ምክር ቤት ተመርጠው የነበሩ እና አሁን ደግሞ የወረዳ ምክር ቤት አባል እና የማረቆ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ሆነው በመሥራት ላይ እንደሚገኙ በመግለጽ ከሕጉ ጋር ስለሚቃረን እንዲሰረዙ በማለት አቤቱታ አቅርቧል።
ቦርዱ አቤቱታውን በመመርመር እጩ ተወዳዳሪው የማረቆ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ሆነው መሥራታቸው እጩ ተወዳዳሪ ሆነው ከመቅረብ የሚያስቀራቸው ባለመሆኑ ፓርቲው ያቀረበው አቤቱታ በቦርዱ በኩል ተቀባይነት ያላገኘ መሆኑን ለፓርቲው አሳውቋል።
የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) ለቦርዱ ባስገባቸው ሁለት አቤቱታዎች በሰዳል ምርጫ ክልል የቀረቡ እጩ አድራሻቸው እንዲሁም የትውልድ ቦታቸው ከዚህ ምርጫ ክልል ውጭ መሆኑን በመግለጽ ከእጩነት እንዲሰርዙ፤ እንዲሁም ሌሎች እጩዎች ከማሽ ዞን ያሶ/ዛይ ወረዳ ለክልል ምክር ቤት ተወዳዳሪ የዞኑ ብልጽግና ሃላፊ በመሆናቸው ፣ እንዲሁም የቡለን ምርጫ ክልል ተወዳዳሪ የክልሉ የፀረ-ሙስና ባለሙያ በመሆናቸው እንዲሰረዙ በማለት አቤቱታ አቅርቧል።
ቦርዱ አቤቱታውን መርምሮ የመጀመሪያው እጩ በምርጫ ክልሉ መስፈርቱን ስለማሟላታቸው ተረጋግጦ በእጩነት ተመዝግበው ሠርተፊኬት የተሰጣቸው በመሆኑ እና ፓርቲው አቤቱታውን በወቅቱ ባለማቅረቡ፣ እንዲሁም ሌሎቹ ሁለት እጩዎች የተሰማሩባቸው የሥራ ዘርፎች በሕጉ መሠረት ከእጩነት የሚያስቀሩ ባለመሆናቸው አቤቱታዎቹ በቦርዱ ተቀባይነት ያላገኙ መሆኑን ለፓርቲው በደብዳቤ አሳውቋል።
ብልጽግና ፓርቲ ለቦርዱ ባቀረበው አቤቱታ የአፍዴር ዞን ምርጫ አስተባባሪ የሆኑት የቦርዱ ሠራተኛ አባታቸው እጩ መሆናቸውን በመጥቀስ ተቃውሞ አቅርቧል። ቦርዱም ይህን አቤቱታ መርምሮ የምርጫ አስፈፃሚውን ጉዳይ፣ አስፈፃሚዎች ግምገማ በሚያደርግበት ወቅት በመገምገም እርምጃ እንደሚወስድ እጩው ግን በእጩነት እንዲቀጥሉ መወሰኑን ለፓርቲው ማሳወቁን ገልጿል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 18 ቀን 2012 ዓ.ም