
አዲስ አበባ፦ አሜሪካ በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ላይ የጣለችው የጉዞ እገዳ እና ሌሎች ማዕቀቦች ኢትዮጵያ በቀጣናው በምታካሂደው ሽብርተኞችን የመከላከል ሥራ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስታወቁ።
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሳምንታዊ መግለጫቸው ትናንት እንዳስታወቁት፤ በአሜሪካ የተጣለው የጉዞ እገዳ እና ሌሎች ማዕቀቦች ኢትዮጵያ በቀጣናው በምታካሂደው አልሸባብን የመከላከል እና ሌሎች የፀጥታ ጥበቃ ሥራዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አለው። እገዳው ኢትዮጵያ ላይ የሚያስከትለው ጫና ቢኖርም መልሶ አሜሪካኖችንም ሆነ የአፍሪካ ቀጣናን ተጎጂ የሚያደርግ ነው።
ውሳኔው የአሜሪካ እና ኢትዮጵያን ለዘመናት የቆየ ግንኙነት የሚያሻክር ከመሆኑ ባለፈ የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ፀጥታ ጥበቃ ሥራ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል ያሉት አምባሳደር ዲና፤ በተለይም ሁለቱ አገራት በቀጠናው ሽብርተኝነትን ለመከላከል ለበርካታ ዓመታት በጋራ ሲሰሩ የነበሩትን ሥራ ይጎዳል። ጉዳዩ ተመልሶ አሜሪካኖቹን እንደሚጎዳ ማወቅ ያስፈልጋል ብለዋል።
የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ የሥራ ኃላፊዎች ላይ የጣለው የቪዛ ክልከላ እና ውሳኔው ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በዜሮ የሚያባዛ ነው። ውሳኔው የሁለቱን አገራት የ120 ዓመታት ግንኙነት ቁመና የማይመጥን ነው። እገዳውን ለመጣልም በቂ ምክንያት የሌለ በመሆኑ ተቀባይነት እንደማይኖረው አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ አልሸባብን ለመዋጋት ከምታከናውነው ዘመቻ አስቀድሞም በኮሪያ ዘመቻ በብቸኝነት ከአፍሪካ የአሜሪካ አጋር ሆና ሠርታለች። በቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋትም ኢትዮጵያ ወሳኝ ድርሻ አላት። በመሆኑም ግንኙነቱ ሲበላሽ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን አሜሪካም ተጎጅ እንደምትሆን አመልክተዋል።
በአሁኑ ወቅት ከእኔ ጋር ብቻ ሁኑ የሚል አነጋገር እና ቁጥጥር የማድረግ ጉዳይ ይኖራል፤ ነፃነትና እኩልነት ግን በጫና እንደማይመጣ ኢትዮጵያ ታምናለች። ኢትዮጵያ ነፃነቷን ከጉልበትና ሀብት ጋር በተያያዘ አሳልፋ አትሰጥም። እንደሀገር ግን የማናጎበድድበት ገደብ አለን። አሜሪካ የወሰደችውን የጉዞ እግዳ እና ሌሎች እርምጃዎች በማጤን የሁለቱን አገራት የቆየ ግንኙነት ላለማበላሸት መሥራት ይኖርባታል። አሜሪካ የወሰነችው ውሳኔ አግባብ ባይሆንም ጉዳዩን በማያጋግል እና የሁለቱን አገራት ግንኙነት በማይጎዳ መንገድ ለመፍታት ይሞከራል ብለዋል።
በተጨማሪ አሜሪካ በትግራይ ክልል ስላለው የሰብዓዊ ድጋፍና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የምታቀርበው መረጃ የተሳሳተና ነባራዊ ሁኔታውን የማይገልፅ ነው ያሉት አምባሳደር ዲና፤ አሜሪካኖች እና ምዕራባውያን በትግራይ ጉዳይ የሰብአዊ ዕርዳታ ማቅረቢያ መንገድ ተዘግቷል እያሉ የሚናገሩት በአካባቢያው ያለው ለሁሉም ክፍት የሆነ አሠራር ጠፍቷቸው እንዳልሆነ ገልፀዋል።
አሜሪካኖችንና ያደጉት አገራት የረቀቁ ቴክኖሎጂዎችን እየተጠቀሙ እንኳንና በትግራይ አካባቢ ያለውን ሁኔታ ይቅርና አሁን የምንሰበሰብበትን አዳራሽ የሚነገረውን ለማዳመጥ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ይኖራቸዋል። ይሁንና ሆን ብለው በትግራይ ጉዳይ ላይ መሬት ላይ የሌለውን ጉዳይ ይገልፃሉ። በኢትዮጵያ በኩል ግን ልቦና ይግዙና የሚያስተላልፉትን መረጃ ያጢኑት ነው የምንለው ብለዋል።
የሱዳን እና የግብጽ ጦር በድንበር አካባቢ የናይል ንስሮች በሚል ስያሜ የጋራ የጦር ልምምድ እያደረጉ ነው። እንደከዚህ ቀደሙ እንደምንለውም ልምምዱን የማድረግ መብት አላቸው። ነገር ግን ልምምዳቸው ኢትዮጵያ ላይ ኪሳራ የሚያመጣ ከሆነ ተቀባይነት እንደማይኖረው አመልክተዋል።
በአገሩ ሉአላዊነት ጉዳይ የሚተኛ ዜጋም ሆነ መከላከያ ሠራዊት እንደሌለን ይታወቃል ያሉት አምባሳደር ዲና፤ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ የሚሰራው ኃይልም ማንኛውንም ችግር ለመመከት ዝግጁ ነው። በኢትዮጵያ በኩልም 24 ሰዓት የሚሰራ መከላከያ እንዳለን ሊታወቅ ይገባል። በዚህ ጉዳይ ላይ በህዝብ እና በሠራዊቱ ላይ እምነት አሳድረን እየተንቀሳቀስን ነው ብለዋል።
ከአሜሪካ የጉዞ እና ሌሎች እገዳዎች ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ አልሸባብን ለመከላከል ሶማሌ ያስገባችውን ጦሯን ስለማስወጣት እና አለማስወጣቷ ግን እስካሁን ምንም አይነት ውሳኔ አለመተላለፉን አምባሳደር ዲና ገልፀዋል።
ጌትነት ተስፋማርያም
አዲስ ዘመን ግንቦት 18 ቀን 2012 ዓ.ም