የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎቹ እየሞቱ ወይም ተናጋሪዎቹ ቋንቋቸውን መጠቀም ትተው ሌሎች ቋንቋዎችን ወደ መናገር እየተሸጋገሩ ሲሄዱ ቋንቋዎች የመጥፋት አደጋ ይጋረጥባቸዋል። በዚህ መልኩ በዓለም ላይ በርካታ ቋንቋዎች ሞተዋል። ዛሬም በሞት አፋፍ ላይ ያሉ አሉ ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) መረጃ እንዳመላከተው፤ እ.ኤ.አ. ከ1950 እና 2010 መካከል 230 ቋንቋዎች ጠፍተዋል።
በቀጣይ ጊዜያትም በርካታ ቋንቋዎች የመጥፋት አደጋ እንደሚያጋጥማቸው የተለያዩ አካላት እየተነበዩ ነው። ዩኔስኮ ከሁለት ዓመት በፊት ያወጣው ሪፖርት እንዳመላከተው በዓለም ላይ ከሚነገሩ ቋንቋዎች ውስጥ አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት ከአንድ ሺህ በታች ተናጋሪዎች ብቻ ቀርተዋል። አንዳንድ ወግ አጥባቂ ግምቶች እንደሚተነብዩት በዓለም ላይ ከሚገኙት ቋንቋዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት እ.ኤ.አ እስከ 2100 ድረስ ይጠፋሉ። ይህም ማለት በቀጣይ 77 ዓመታት በየሁለት ሳምንቱ አንድ ቋንቋ እንደሚሞት ይገመታል። ይህም የችግሩን አሳሳቢነት እና ጥልቀት አመላካች ነው።
በቋንቋ አደጋ ላይ እንዲወድቅ የሚያደርጉ ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች እንዳሉ የዩኔስኮ ጥናት ያስረዳል። ከውጫዊ ምክንያቶች መካከል ወታደራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ሃይማኖታዊ፣ ባህል ወይም ከትምህርት ጋር ተገዥነት ያላቸው ውጫዊ ምክንያቶች ለቋንቋ መዳከም አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል።
ከውጫዊ ምክንያቶች ባሻገር የተለያዩ ውስጣዊ ምክንያቶችም ለቋንቋ መጥፋት አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። እንደ ማህበረሰብ ለቋንቋቸው አሉታዊ አመለካከት እያደገ መሄድ ለቋንቋው መጥፋት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል። በተለያዩ በተዛቡ አመለካከቶች ምክንያት ሰዎች ቋንቋውን መናገር እና ለልጆቻቸው ለማስተማር ሊወስኑ ይችላሉ። ውስጣዊ ምክንያቶች ከውጫዊ ምክንያቶች ጋር ቁርኝት አላቸው። ሁለቱ ምክንያች ተዳምረው ቋንቋው ከትውልድ ወደ ትውልድ መተላለፍን ያቆማል።
የስነ ቋንቋ ዘርፍ ባለሙያዎች እንደሚሉት ቋንቋ የሰዎችን ባህል ፤ ወግ ፤ አኗኗርና ውስጣዊ ስሜታቸውን ለመግለጽ የሚያገለግል መሳሪያ ነው ። ይህ ለሰው ልጆች ብቻ የተሰጠ የተግባቦት መሣሪያ ታዲያ ፤ አንዳንዴ ሊጎዳ ባስ ካለም ከአነአካቴው ጨርሶ ሊጠፋ ይችላል። የቋንቋ መዳከም ወይም መጥፋት በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊ ፤ ባህላዊና ትውፊታዊ ሀብቶችም አብረው እንዲጠፉ ያደርጋል። በተለይም ማህበረሰቦች በቋንቋቸው መጥፋት ወይም መሞት ምክንያት መሰረታዊ የባህል ማንነታቸውን በማጣት ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ ይታመናል።
የቋንቋ መጥፋት የሰዎችን የማንነት እና የባለቤትነት ስሜት ያዳክማል፣ ይህም በመጨረሻ መላውን ማህበረሰብ መጥፋት መንገድ ይጠርጋል። በእርግጥ ማህበረሰቦች የራሳቸውን ቋንቋ ትተው በአካባቢያቸው የሚነገር አውራ ቋንቋ ሊጠቀሙ ይችላሉ። ግን በዚህ ሂደት ላይ ርስታቸውን (ቋንቋቸውን) ያጣሉ።
የተለያዩ አገራት የቋንቋዎች መጥፋትን ለመከላከል የተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። ነገር ግን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ችግሩን በዘላቂነት የሚቀርፍ መፍትሄ ሳይገኝ ቆይቷል። በተለይም የሉዓላዊነት መስፋፋትን ተከትሎ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚጠፉ እና አደጋ የሚጋረጥባቸው ቋንቋዎች ቁጥር እያሻቀበ ሄዷል። በቅርቡ ግን ጎግል የዘመናት ችግር የሚቀርፍ አዲስ መፍትሄ ይዞ ብቅ ብሏል።
ጉግል ‹‹ዉላሮ›› ሲል የጠራውን በሰው ሰራሽ አስተውሎት (በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) የሚታገዝ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸውን ቋንቋዎች የሚተረጉም መተግበሪያ አስተዋውቋል። መተግበሪያው ማሽን ለርኒንግ እና ምስል መለያዎችን በመጠቀም በስልኮቻችን የምናነሳቸውን ፎቶዎች በመተግበሪያው ወደ ተካተቱት ሀገር በቀል ቋንቋዎች በቅፅበት ይተረጉማል።
ቴክ ኤክስፕሎር የተሰኘ ድረገጽ እንዳስነበበው፤ መተግበሪያው ትርጉም ከማቅረብ ባሻገር ማህበረሰቡ አዳዲስ ቃላትን እንዲሁም ትክክለኛ አጠራራቸውን ለመገንዘብ የድምፅ ቅጅዎችን ወደ መተግበሪያው እንዲያካትቱ አማራጮች አሉት። ይህም የመተግበሪያውን ፋይዳ ላቅ ያለ እንዲሆን ያደርገዋል።
መተግበሪያው አሁን ባለበት ደረጃ በዓለም ዙሪያ ለመጥፋት የተቃረቡ ያላቸውን የተለያዩ ቋንቋዎች አካቶ ወደ ስራ ገብቷል። በአውስትራሊያ ኩዊንስላንድ ግዛት፣ በጣልያን፣ በአሜሪካ ሉዚያና ግዛት፣ በኒውዚላንድ፣ በኤል ሳልቫዶር፣ በሞሮኮ እና አልጄሪያ፣ በቺሊ፣ በቻይና እንዲሁም በእስራኤል የሚነገሩ አስር ቋንቋዎችን አካቶ በስራ ላይ ውሏል።
የመተግበሪያው ዋና ዓላማ ለመጥፋት የተቃረቡ ቋንቋዎችን ለማቆየት እና ለማስተማር እንደሆነ በዘገባው ተጠቅሷል። ጉግል ዉላሮ የተሰኘውን መተግበሪያ የማበልጸግ ሀሳብ የመነጨው በደቡብ ምስራቅ አውስትራሊያ አካባቢ የሚነገረው ዩማግቤህ የተሰኘ ቋንቋ ያለበት ሁኔታ ነው።
ዩማግቤህ እንደሌሎች ብዙ ጥንታዊ እና አካባቢያዊ ቋንቋዎች ሁሉ ለአንዳንድ ዘመናዊ ዕቃዎች እና ፅንሰ ሀሳቦች አቻ ቃላት የላቸውም። በመሆኑም በዚህ ማህበረሰብ ውስጥ የሚወለዱ ህጻናት ባለንበት ዘመናዊ ዓለም ውስጥ ዩጋምቤን ለመማር ይቸገራሉ። ለምሳሌ ዩጋምቤህ “ማቀዝቀዣ” ወይም “ስልክ” የሚል ቃል የለውም ፣ ማለትም የቋንቋ ተናጋሪዎች እነዚያን ነገሮች እንደ “ቀዝቃዛ ቦታ” እና “የድምፅ መልዕክት ማስተላለፊያ” የሚሉ አይነት አቻ ቃላትን መተካት አለባቸው ።
እንደ ቴክ ኤክስፕሎር ዘገባ ዩጋምቤህ በጎግል መተግበሪያ ላይ ለሙከራ ከተካተቱት በመጥፋት ላይ ከሚገኙ ቋቋዎች አንዱ ለመሆን በቅቷል። ጎግል ዩማግቤህ ቋንቋን በመተግበሪያው ውስጥ ለማካተት የዩማግቤህ ቤተ ቅርስ (ሙዚየም) በመጠቀም እና የተለያዩ ጥናቶችን አካሂዷል።
የዩጋምቤህ ተወላጅ የሆነው የአካባቢውን ሰራተኛ አለን ሊና እና የዩጋምቤህ ሙዚየም ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ሮሪ ኦኮነር ዉላሮ ለዩምግቤህ ቋንቋ ህልውና ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።
መተግበሪያው እንደ ዩጋምቤህ ያሉ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ተናጋሪዎች ቋንቋውን ለመጠበቅ እንዲሁም ለብዙ ህጻናትና ወጣቶች ቋንቋን ለማስተዋወቅ ብሎም ባህልና ትውፊቶችን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ እንደሚረዳ ትልቅ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል። ይህንን ቋንቋ አቀላጥፈው የሚናገሩ ጥቂት ሰዎች በመሆናቸው ዉላሮ ይህንን ወሳኝ እውቀት ለአዲሱ ትውልድ ሊያካፍል ይችላል ይላል።
ዉላሮ የማህበረሰቡ አባላት በመተግበሪያው ላይ የራሳቸውን ለውጦች እንዲያደርጉ እና የራሳቸውን የቃላት ዝርዝር በመተግበሪያው ላይ እንዲጨምሩ ክፍት መሆኑ ፋይዳውን ከፍ እንደሚያደርገው የተገለጸ ሲሆን የቃላት ዝርዝሮችን በመደርደር እንዲሁም የድምፅ አወጣጥን ለማገዝ ይረዳል ተብሏል ። በአሁኑ ጊዜ መተግበሪያው 10 ዓለም አቀፍ ቋንቋዎችን ከሞት ለመታደግ ስራ ላይ እየዋለ
ሲሆን ቋንቋዎቹም ካላብሪያን፣ ሉዊዚያና፣ ሉዊዚያና፣ ማኦሪ ፣ ናዋት ፣ ታማዝት ፣ ራፓ ኑይ ፣ ሲሲሊያን ፣ ያንግ ዙንግ ፣ ይዲሽ እና ዩጋምቤህ ናቸው።ዉላሮ በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን ዋነኛ ጠቀሜታው ተጠቃሚዎቹ በመተግበሪያው ላይ አዳዲስ ይዘቶችን ለማከል እና አርትኦት ለማድረግ ክፍት መሆኑ ጥቅሙን የትየሌሌ ያደርገዋል።ያ ማለት አንድ ተጠቃሚ ወይም ማንኛውም የቤተሰብ አባል በእነዚህ ቋንቋዎች በአንዱም ቢሆን ጥቂት ቃላትን የሚናገር ከሆነ ለዉላሮ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለማበርከት ያስችላል ማለት ነው ።
የዚህ መተግበሪያ ተጨማሪ ጥቅም ማንኛውም ሰው የቋንቋ ተናጋሪ ቤተሰብ አባልም ሆነ ሌሎች ሰዎች ቋንቋውን መማር ሲፈልጉ አጋዥ ሳያስፈልጋቸው ቋንቋውን መማር እንዲጀምሩ እድል የሚሰጥ መሆኑ ነው። በዚህ መንገድ ብዙ የተለያዩ የኋላ ታሪክ ያላቸው እና በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ሰዎች በሚኖሩበት አካባቢ ውስጥ ስለሚነገሩ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ቋንቋዎች የበለጠ እንዲያውቁ በር ይከፍታል።
የብዙ ቋንቋዎች፣ ባህሎችና ብሔሮችና ብሔረሰቦች መናኸሪያ በሆነችው ኢትዮጵያ ውስጥም ቋንቋዎች በተገቢው መንገድ ባለመልማታቸው ምክንያት ፤ ከዚህ ቀደም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉት ቋንቋዎች መክሰማቸውን የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል በተለያዩ ጊዜያት ያካሄዳቸው ጥናቶች ያመለከታሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ በከፍተኛ ጉዳት ውስጥ እንደሚገኙ በቅርቡ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ።
በሞት አፋፍ ላይ የሚገኙ ቋንቋዎችን ለመታደግ መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ጥረት እያደረጉ ነው።የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች ለማስተማሪያነት እንዲያገለግሉ መደረጉ ከበጎ ስራዎች አንዱ ማሳያ ነው። ባለፉት 10 ዓመታት በተሰሩ ስራዎች ከ50 በላይ የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች ለማስተማሪያነት እንዲያገለግሉ መደረጉ እንደ አንድ በጎ ጥረት ይታያለ።
ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ቋንቋዎቹ በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ የሚካተቱበትን ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሌላኛው መልካም ጅምር ነው። ሆኖም በሀገሪቱ ለቋንቋዎች እድገት ሥርዓት ባለመበጀቱ በሚፈለገው ልክ ውጤት አልተመዘገበም። በመሆኑም ዉላሮ አይነት ቴክኖሎጂዎች በስራ ላይ የሚውሉበትን ሁኔታዎችን በማመቻቸት ቋንቋዎቹን ከመጥፋት ለመታደግ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2013