የኢትዮጵያ ዋና ከተማ በሆነችውና የተለያዩ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች በሚገኙባት አዲስ አበባ ውስጥ በተለይም ቤተመንግሥትን ጨምሮ ትላልቅ ተቋማት በሚገኙባቸው ዋና ዋና በተባሉት አካባቢዎች ማብሰያና መፀዳጃቤት ያልተሟላላቸው፣ እጅግ የተጠጋጉ ለመኖሪያ ምቹ ያልሆኑ የመኖሪያቤቶች እንደነበሩ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ደረጃቸውን የጠበቁ የተለያዩ አገልግሎት መስጫ ተቋማትም እንዲሁ አልነበሩም። ምንም እንኳን አሁንም የተጐሳቆሉና ለኑሮ ምቹ ያልሆኑ መኖሪያዎች መኖራቸውና ሙሉ ለሙሉ ችግሩ አለመቀረፉ ቢታወቅም ካለፉት ሃያ ዓመታት ወዲህ ግን በከተማዋ ለውጦች በመታየት ላይ ናቸው። ለመሬት ቁጠባ፣ ፍትሐዊ አጠቃቀምን ለማስፈንና ተደራሽ ለማድረግ፣ ለዘመናዊ አኗኗርና የከተማዋንም ደረጃ ታሳቢ ባደረገ ለመኖሪያም ሆነ ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ የግንባታ ሥራዎች በትላልቅ ሕንፃዎች እየተተኩ ይገኛሉ።
ከሌሎች ጋር ሳይጋሩ መፀዳጃና ማብሰያ ቤት በተሟላለት መኖሪያቤት ውስጥ መኖር በብዙዎች በበጎ ይወሰዳል። ዘመናዊ ኑሮ ከሚያሰኙት አንዱ እንደሆነም ይጠቀሳል። በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ጥቂት የማይባሉ ዜጎችም ዘመናዊ የሚባለውን ኑሮ ተያይዘውታል። መኖሪያቸው ብቻ ሳይሆን የሚፈልጓቸው አገልግሎቶችም እየዘመኑ በመሆኑ በአካባቢ ደራሽ እየሆኑ ነው። የዚህ ርዕሰ ጉዳይ ማጠንጠኛው ከተሞች ሲዘምኑ የነዋሪውም ኑሮ ሲሻሻል አጠቃቀሙስ ምን ይመስላል የሚለውን ለመዳሰስ ነው።
ለመኖሪያም ሆነ ለተለያየ አገልግሎቶች የሚገነቡ ሕንፃዎች የመሸከም አቅም እና አጠቃቀማቸው ምን ይመስላል? የሚታዩ ክፍተቶችስ ምንድናቸው? ምን ዓይነት ጥንቃቄዎች ያስፈልጋሉ? ከማንስ ምን ይጠበቃል? በሚሉት ላይ ትኩረት አድርገናል። በሕንፃ አጠቃቀም ላይ ከሚስተዋሉት ክፍተቶች አንዱ ሕንፃው መሸከም ከሚችለው በላይ ጫና ማብዛት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ በግንዛቤ እጥረትና በግዴለሽነት የሚነሳ ጉዳይ ነው።
በዚህ ዙሪያ ለአብነት የጋራ መኖሪያ ቤትን ማንሳት ይቻላል። በነዚህ ቤቶች ውስጥ እየኖረ ያለው ማህበረሰብ አብዛኛው ቀደም ሲል በፎቅቤት ውስጥ የመኖር ባህል ወይንም ተሞክሮ ያለው አይደለም። የቤቱ ስያሜ እንደሚያመለክተው ኑሮው የጋራ በመሆኑ ለሕንፃው ደህንነት እያንዳንዱ ነዋሪ ኃላፊነት አለበት። ሆኖም ግን ኃላፊነት የመወጣት ሚናው በተግባር እየታየ ነው ለማለት የማያስደፍሩ ብዙ ክፍተቶችን ማንሳት ይቻላል። ነዋሪው በቤት ውስጥ የሚጠቀማቸው ቁሳቁሶች መጠን፣ የሚወቀጥና የሚከተከት ነገርን በቤት ውስጥ ማከናወን፣ በበረዳ ላይ ትላልቅ ሚስማሮችን መትቶ ክብደት ያላቸውን አልባሳት ማስጣት፣ ሦስት መቶ ሊትርና ከዚያ በላይ ውሃ የሚይዙ ማጠራቀሚያዎችን ቤት ውስጥና በበረዳ ላይ ማስቀመጥ፣ የውሃ ማጠራቀሚያዎቹን ሥር ከእርጥበት ነፃ አለማድረግ፣ የውስጥ ለውስጥ ፍሳሾችን በወቅቱ አለማስወገድ፣ የሳተላይት መቀበያ ዲሾች በሕንፃው ላይ መትከል እንዲሁም ተከራይ ሲፈራረቅ በተደጋጋሚ ዲሽ መስቀልና የሚቆረቆሩ ነገሮች መብዛት የሕንፃውን የቆይታ ጊዜ ከሚያሳጥሩ መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።
መኖሪያቤቶቹ ሲገነቡ እነዚህን ምን ያህል ታሳቢ አድርገዋል? ማህበረሰቡም በአጠቃቀሙ ላይ ቀድሞ ግንዛቤ አግኝቷል? የሚሉ ጥያቄዎችን የሚያስነሱ ሀሳቦች ይሰነዘራሉ። ሕንፃዎች ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ሀብት ፈሶባቸው የሚገነቡ በመሆናቸው ተገቢው ጥንቃቄ ካልተደረገላቸው የኢኮኖሚ አቅም በሌላት ኢትዮጵያ ቶሎ መተካት የሚቻልበት ዕድል የለም። በአንድ በኩል ለዜጎች የመኖሪያቤት ለማሟላት ፈተና ሆኖ ሳለ፣ የተገነባውን በአግባቡ አለመያዝ ደግሞ ችግሩን ውስብስብ ያደርገዋል። ለተለያየ የአገልግሎት መስጫ የተገነቡት ተቋማትም በተመሳሳይ ትኩረት ሊያገኙ ይገባል። በአጠቃላይ በሕንፃዎች የመሸከም አቅምና አጠቃቀም ዙሪያ የተለያዩ ባለሙያዎችን አስተያየት አካተን አቅርበናል።
በቅድሚያ ሙያዊ ሀሳባቸውን ያካፈሉን ባለሙያ ሲቪል ኢንጂነር ሲሆኑ፣ ሀብቱ ገብረማርያም ይባላሉ። እንደ እርሳቸው ማብራሪያ አንድ ሕንፃ ከግንባታው በፊት የራሱ የሕንፃው ክብደትና ከሰው ጀምሮ የሚንቀሳቀሱ ነገሮችን ታሳቢ የሚያደርግ ሲሆን፣ እነዚህን ሁሉቱን ማዕከል ያደረገ የሕንፃ መዋቅር ከተሰራ በኋላ ነው ወደ ግንባታ የሚገባው። እንዲህ ባለው ሁኔታ ቢገነባም በአጠቃቀም ጥንቃቄ ጉድለት ሕንፃዎች ለተጽዕኖ ይጋለጣሉ። አላስፈላጊ ክብደቶችና የሕንፃ መዋቅሮች ከሚታይባቸው ውስጥ የጋራ መኖሪያቤት ይጠቀሳሉ። አንዱ የሚስተዋለው ችግር መዋቅራዊ ለውጥ ማድረግ ነው።
የተቀናጣ ወይንም ተጨማሪ የሆነ ነገር በመፈለግ ሌላው ደግሞ ቤቱ ጠቦት የቤቱን የውስጥ ይዘት በመቀየር ለማስፋት የሚደረጉ ጥረቶች ሲሆኑ፣ እነዚህ በሕንፃው ላይ ጉዳት ያደርሳሉ። አላስፈላጊ የሆኑ ክብደቶችን የሚጨምሩ ነገሮችን አለማስወገድም ይስተዋላል። እንዲህ ያሉ ድርጊቶች ደግሞ ሕንፃው ከአገልግሎት ዘመኑ በፊት ለጉዳት የመጋለጥ ዕድሉን ያሰፋል። ምንም እንኳን ማህበረሰቡ ቤቶቹን ሲረከብ በሽያጭ ውሉ ላይ በሕንፃው ላይ የመዋቅር ለውጥ ማድረግ እንደሌለበትና ለጋራ ኑሮ ተገዥ እንዲሆን ግዴታ ፈርሞና ተስማምቶ የተቀበለው ቢሆንም በተግባር እያደረገው ያለው ግን የገባውን ግዴታ የሚያከብር ባለመሆኑ ተጨማሪ የግንዛቤ ሥራ ያስፈልገዋል። ይህም በአስፈጻሚው አካል ቢከናወን የተሻለ ይሆናል። ሕንፃው በተወሰነ ጊዜ እድሳት ከተደረገለትና የሚስተዋሉት ክፍተቶች ከተቀረፉ ስጋቶችን ማስወገድ ይቻላል።
የጋራ መኖሪያ ቤቶች የውሃ ማጠራቀሚያ (ታንከር) ታሳቢ ተደርጎ አለመገንባታቸው ያመጣው ችግርና የውሃ እጥረቱ ከፍተኛ መጠን ያላቸው የውሃ ማጠራቀሚያዎችን በቤት ውስጥ እንዲጠቀም መገደዱን ያስታወሱት ኢንጂነር ሀብቱ ካለፈው ተሞክሮ በመውሰድ ወደፊት በሚገነቡት ላይ ማስተካከያ በማድረግ መገንባት እንዳለበት ይገልፃሉ። ቀደም ሲል ያልተሟላላቸውም ቢሆኑ ምንም እንኳን ቤቶቹ የገዥው ነው ተብሎ ቢታሰብም የቤቱ ክፍያ ያልተጠናቀቀ ደግሞ የመንግሥት ንብረት ስለሆነ መፍትሔው ከአንድ አካል ብቻ አይጠበቅም። የጋራ መሆን ይኖርበታል።
የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ በተለያዩ የመንግሥት ፕሮጀክቶች የግንባታ ሥራ ላይ ከሚሳተፉ ተቋራጮች መካከል አንዱ የሆነውን የእቴቴ ሪል እስቴት ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋ ታደሰም በተመሳሳይ ሀሳባቸውን አካፍለዋል። በቅድመ ግንባታ ታሳቢ ያልተደረጉ ነገሮች በሕንፃው የአገልግሎት ዘመን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ይገምታሉ። በረጅም ጊዜ ሊያጋጥም የሚችለውን ነገር ታሳቢ አድርጎ ወደ ሥራው መግባት ጥቅሙ የጎላ እንደሆነም ይገልፃሉ። እርሳቸው እንዳሉት እስካሁን ባለው ተሞክሮ ኮንትራክተሩ ውል ፈጽሞ ወደ ሥራ ከገባ በኋላ ከተሰጠው ዲዛይን (ንድፍ) ውጪ የዲዛይን ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ሀሳብ ቢያቀርብ በበጎ ስለማይወሰድ ግንባታውን በወቅቱ አጠናቅቆ ማስረከቡ ላይ ነው ትኩረት የሚያደርገው። የተዘነጉ ነገሮች መኖሩን ኮንትራክተሩ ቢገነዘብ እንኳን ተቋራጩ ተጨማሪ ክፍያ ፈልጎ እንደሆነ ስለሚታሰብ ተጨማሪ ሀሳብ ከመስጠት በመቆጠብ የማያምንበትን ነገር ሰርቶ ያስረክባል። ክፍተቶቹ የሚታዩት ኮትራክተሩ ጨረታውን አሸንፎ ለሥራ ዝግጁ ከሆነ በኋላ መሆኑም ወደኋላ ተመልሶ ችግሩን ለማስቀረት ያስቸግራል።
የመንግሥት ፕሮጀክቶች የሚቀረጹት በአብዛኛው ቆጣቢ ግንባታን መሠረት ባደረገ ንድፍ ስለሚሰራ የግንባታ ሥራው ሲጀመር ለማስተካከል ይከብዳል። ሌላው ኮንትራክተሩ በተሰጠው ዲዛይን መሠረት ግንባታውን ማከናወን እንጂ ቀድሞ ሕንፃው ለምን አገልግሎት እንደሚውል የማወቅ ዕድል የለውም። የሚያከናውነው ግንባታም ለመኖሪያቤት አገልግሎት የሚውል መሆኑን ቢያውቅም በዚያ ቤት ውስጥ ስለሚኖረው የሰው ቁጥርም ሆነ ሌላ መረጃ ስለማይኖረው ሀሳብ ለመስጠት ይቸገራል።
ከአጠቃቀም አንፃርም በሰጡት አስተያየት መኖሪያ ቤቶች ሲገነቡ በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖረው የሰው ቁጥር አማካይ፣ በቤት ውስጥ ሊኖሩ ስለሚገባቸው ቁሶች ግምት ውስጥ ቢገባም፤ የማህበረሰቡ አኗኗር ከዚህ ጋር የማይጣጣምበት አጋጣሚ ይበዛል። በቤቱ ውስጥ የሚኖረው ሰው ቁጥር ሳይቀር ታሳቢ ከተደረገው በላይ ሊሆን ይችላል። ቅርጽን በመለወጥ በኩልም ለማብሰያ አገልግሎት እንዲውል የተሰራውን ክፍል ለመኝታ ይጠቀምበታል። እንዲህ ያለው ሁኔታ ለሕንፃው መጎዳት አንዱ ምክንያት ይሆናል። በሕንፃ አጠቃቀም ላይ ማህበረሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ የበለጠ የተሻለ እንደሆነ አቶ ተስፋ ሀሳብ ሰጥተዋል።
‹‹ባደጉት አገራት የሕንፃው የቆይታ ጊዜ ሲጠናቀቅ አፍርሶ መልሶ መገንባት የተለመደ ነው። በኢኮኖሚ ዝቅተኛ በሆኑ አገራት ይሄን ማድረግ አቅም ስለሚጠይቅና ነዋሪውም እንዲህ ዓይነቱን ስላለመደ በሥጋት ይነሳል›› በማለት የገለጹት ሌላው ሀሳብ ሰጪ ተጠሪነቱ በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በሆነው በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት በመንግሥታዊ ተቋማት በሚከናወኑ የግንባታና ጨረታ አገልግሎቶች የምክር አገልግሎት ክፍል ባለሙያ አቶ ሞገስ ይትባረክ ናቸው።
እንደ አቶ ሞገስ ማብራሪያ በአጠቃላይ በግንባታ ዘርፉ ሕንፃው ይፈርሳል ወይንም ይጎዳል የሚለውን ስጋት ለመቀነስ ሲባል በንድፍ ወቅት ግብአቱ ከፍ ብሎ ጥቅም ላይ እንዲውል ተደርጎ ነው የሚካተተው። ለአብነትም ለግንባታ ግብአት የሚያስፈልገው ብረት መጠን ወይንም ብዛት 10 ቢሆን በዲዛኑ 20 ተደርጎ ሊካተት ይችላል። በዚህ ረገድ በዲዛይኑ የግብአት አጠቃቀሙ ከፍተኛ ነው የሚል ትችት ይነሳል። ዲዛይኑ በዚህ መልክ ቢሰራም በትግበራው ላይ ክፍተቶች ያጋጥማሉ። በተቀመጠው ዲዛይን መሠረት ብረቱን፣ ጠጠሩን፣ አሸዋውንና ሲሚንቶውን በመጠቀም በጥራት በመሥራት ረገድ አላስፈላጊ ጥቅም ለማግኘት ሲባል በተቀመጠው ዲዛይን ግብአቶችን አለመጠቀም ይስተዋላል። ይሄ በጥራትና በሕንፃው ደህንነት ላይ እንደስጋት ሊነሳ ይችላል። እንዲህ ያሉ ክፍተቶች ግዙፍ በሆኑ ፕሮጀክቶች ላይ በብዛት አይስተዋልም። ሥራዎቹም ዓለም አቀፍ ልምድ ባላቸው ድርጅቶች የሚከናወኑ በመሆናቸው ጭምር ጥንቃቄ ይደረጋል።
የሕንፃ ግንባታ ሲከናወን የሚንቀሳቀሱና የማይን ቀሳቀሱ ነገሮች ታሳቢ ይደረጋሉ። ለመኖሪያ ቤትና ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎች በተመሳሳይ ግንባታ ሳይሆን በየራሳቸው በወጣላቸው ደረጃ (ኮድ) ነው የሚከናወኑት። ከዚህ አንጻር የጋራ መኖሪያ ቤት ላይ የሚነሱት ስጋቶች ተገቢ ቢሆኑም ያን ያህል ደግሞ አያስፈራም። ከግንባታው ጋር ተካትቶ የውሃ ማጠራቀሚያ (ሴፍቲ ታንከር) ቢሰቀልም አሁን ነዋሪው በቤት ውስጥ ለማጠራቀሚያ ከሚጠቀመው ዕቃ በታች ባለመሆኑ ከጋራ መኖሪያቤት ጋር ተያይዞ የሚነሱት የውሃ ማጠራቀሚያዎች ሕንፃውን ለጉዳት ይዳርገዋል በሚባል ደረጃ ላይ አይደለም።
ጫና ሊሆን የሚችለው ለንግድ አገልግሎት የሚውሉ እንደ ማጠቢያ ያሉ ከፍተኛ መጠን ያላቸው ማሽኖች ከሆኑ ብቻ ነው። የጋራ መኖሪያቤቶች ሲገነቡ 50 ዓመት ታሳቢ ተደርጎ በመሆኑ አሁን በሚነሳው ልክ በአጭር ጊዜ የሚያጋጥም ችግር ባይኖርም ጥገና ማድረግ ግን ያስፈልጋል። በማህበረሰቡ በኩል የዲዛይን ለውጥ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ለማስቀረት ደግሞ ቀድሞ ፍላጎትን ማዕከል ያደረገ ግንባታ ለማድረግ መሞከር፣ በግንባታ ወቅትም ዲዛይኑ እንዲተገበር በመከታተልና በመቆጣጠር ችግሩን ማስቀረት እንደሚቻል አቶ ሞገስ ሀሳብ ሰጥተዋል።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አማካሪ አቶ አቡዬ አንለይ አገሪቱ የሕንፃ ፈቃድ አዋጅ እንዳላትና ግንባታውም በአዋጁ መሠረት እንደሚመራ አስታውሰዋል። ግንባታ ሲታሰብ የመሸከም አቅም ብቻ ሳይሆን ከአካባቢ ተጽዕኖ ጋር የሚነሱ፣ ከእሳት አደጋ፣ የግብአት አጠቃቀም፤ ከመሬት መንቀጥቀጥ፣ ከብዙ ነገሮች አንጻር ታሳቢ መደረግ አለበት ይላሉ። ወደ ግንባታ ሥራ ከመገባቱ በፊት ግንባታው የሚያርፍበትና የሚሰራው ፎቅ ከፍታ፣ ለደህንነት ሥጋት የሆኑት ሁሉ የሚቀረፉት የግንባታ ፈቃድ ከመሰጠቱ በፊት እንደሆነ፣ ይህን ለማስፈጸምም የሕንፃ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን መቋቋሙን፤ ለከተሞች ደግሞ የግንባታ ፈቃድ የሚሰጥ ጽሕፈት ቤት መደራጀቱን፣ የግንባታ ሹሞችም መኖራቸውን ጠቅሰው፤ የሕንፃ ሹሙ ከተማ ላይ ያሉትን ሕንፃዎችን የበላይ ሆኖ እንደሚከታተል ገልጸዋል። የአሠራር ሥርዓቱ በዚህ መልኩ ቢዘረጋም ሕጉን መሠረት አድርጎ መተግበሩ ላይ ክፍተተት መኖሩን አቶ አቡዬ አልሸሸጉም። ችግሩ የሕግ ሳይሆን ሕጉን ተከትሎ አለመፈጸም በመሆኑ በግንባታ ዘርፉ ላይ ያለውም ሆነ በሕንፃው ተጠቃሚ የሆነው ለሕግ ተገዥ ሆኖ ከተንቀሳቀሰ የሚነሱ ስጋቶች እንደሚቀንሱ አቶ አቡዬ ያምናሉ።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2013