ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ የኖረች አገር ብትሆንም ብዙ የእርስ በእርስና ከውጭ ወራሪዎች ጋር ጦርቶችን አካሂዳለች። ይህም ሆኖ ሉዓላዊነቷን አስከብራ እስካሁን ዘልቃለች። ቀደምት አባቶችና እናቶች በቻሉት አቅም የአገሪቱን ሀብትና ክብር አስጠብቀው ለትውልድ ሲያስተላልፉ ኖረዋል። ይህ ሁኔታም እስካሁን በመዝለቁ የአሁኑ ትውልድ የአገሪቱን ህልውና ለማስቀጠል ትግል እንዲያደርግ መሰረት ጥሎለታል። ለዚህ ደግሞ ለትውልድ የሚሻገሩ ስራዎችን ከመስራት ባለፈ ያሉትን ለማስጠበቅ ደፋ ቀና ማለቱም መዘንጋት የለበትም።
ለመንደርደሪያ ያክል አገሪቱ ሉዓላዊነቷን ጠብቃ እንድትቀጥልና በአንድነት መንፈስ እንድትኖር ካደረጓት መሪዎች ወይም አስተዳዳሪዎች መልካም ሥራና ለውጭ ጣልቃ ገብነት የከፈቱትን በር በመጠኑ እንመልከት። ተፈሪ መኮንን (አፄ ኃይለስላሴ) ከንግስተ ነገስታት ዘውዲቱ ስልጣን ከተረከቡ በኋላ አገሪቱን አንድ አድርጎ ለመግዛት ይበጃል የሚሉትን ስራ ሲያከናውኑ ቆይተዋል። ለዚህም ደግሞ ዘመናዊ ትምህርት ማስጀመር ተጠቃሽ ነው። በአገሪቱ የሚገኙ ወጣቶች አዕምሯቸው በትምህርት የጎለበተ እንዲሆን ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ አድርገዋል።
የፋሽስት ጣሊያን በአድዋ ላይ የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል ዳግም ኢትዮጵያም ወረራ በፈጸመበት ወቅት አፄ ኃይለስላሴ ወደ እንግሊዝ አገር በስደት ለመሄድ ተገደዋል።አርበኞች በአገር ውስጥ ሲያደርጉት የነበረው ተጋድሎ እንደተጠበቀ ሆኖ ንጉሱ በእንግሊዝ በነበራቸውም ቆይታ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን በማከናወናቸው በእንግሊዝ አጋዥነት የጣሊያን ፋሽስት ከኢትዮጵያ እንዲወጣ ተደርጓል። ነገር ግን ጣሊያን ፋሽስት ከኢትዮጵያ ቢወጣም እንግሊዝ በእጅ አዙር ኢትዮጵያን ለማስተዳደርና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ሙከራ ማድረጓን በወቅቱ ተከትበው የተቀመጡ ታሪኮች ያሳያሉ። የእንግሊዝ ጣልቃ ገብነት በብዙ ነገር የሚገለፅ ቢሆንም በኤርትራ ጉዳይ ላይ ያሳየችው ሁኔታን ማስታወስ በቂ ነው።
የንጉሡን ሥርዓት በመጣል ወደ ሥልጣን የመጣው የደርግ መንግስት በሩስያ ሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም አገሪቱን መምራት በመጀመሩ በወቅቱ ካፒታሊዝምን የሚከተሉ አገራት ጣልቃ ገብተው ምን ያክል የእርስ በርስ ግጭቶች እንደነበሩ የሚታወስ ነው። ደርግ ከሚመራበት ርዕዮት አለም ጀምሮ የሚዋጋበትን መሳሪያ ከሩስያ በእርዳታ የሚያገኝ በመሆኑ ሩሲያ በአገር ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ብትገባም ምንም መቃወም አይቻልም ነበር። በተመሳሳይ እንደ አሜሪካ ያሉ የሶሻሊዝም ጠል የደርግን መንግስት ለመጣል በአገር ውስጥ ለሚገኙ የታጠቁ ተቃዋሚዎች ድጋፍ ያደርጉ ነበር።
በአሜሪካ እገዛ ድጋፍ ተደርጎላቸው ከመጡ ታጣቂዎች አንዱ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ነው። ህወሓት በውጭ ድጋፍ የደርግን መንግስት ከስልጣን ካስወረደ በኋላ አገሪቱን ማስተዳደር ጀመረ። በዚህም በሩስያ ተይዞ የነበረው የእጅ አዙር አስተዳዳሪነት ወደ አሜሪካ ተቀየረ። አሜሪካም በእርዳታ ስምና በሌሎች ስራዎች ኢትዮጵያን ጨምሮ ምስራቅ አፍሪካን መቆጣጠር ጀመረች። ህወሓት ከሌሎች አጋር ብሔር ተኮር ፓርቲዎች ጋር በመቀናጀት ኢህአዴግን በመመስረት ለ27 ዓመታት አገሪቱን ስትመራ ቆየች።
እዚህ ጋር መነሳት ያለበት ጉዳይ በ27 ዓመታት ውስጥ የውስጥ አንድነትን የሚፈታተኑ ጉዳዮች በብዛት እየተፈበረኩ የወጡ መሆናቸውን ነው። በዚህም መቀመጫቸውን ውጭ አገራት ያደረጉ ተቃዋሚዎች እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል። እነዚህ ተቃዋሚዎች ታድያ በብዛት አሜሪካ በመመላለስ አገሪቱ ላይ ጫና እንዲፈጠር ሲጥሩ እንደነበር የሚታወስ ነው። ኢህአዴግ ውስጣዊ አንድነቱን እያጣ በመምጣቱ በለውጥ አራማጅ አመራሮች ጥረት ህወሓትን በመነጠል የተቀሩት ፓርቲዎች አንድ በመሆን አገሪቱን ማስተዳደር ጀመሩ።
አሁን ደግሞ ለውጭ አገራት ጣልቃ ገብነት የዳረጉ ጉዳዮችን እንመልከት። ኢትዮጵያ በአገሪቱ ያለውን የኤሌክትሪክ ችግር ለማቃለልና የአባይን ወንዝ ጥቅም ላይ ለማዋል የሕዳሴ ግድብ ግንባታ 2003 ዓ.ም ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ጣለች። የግድቡ ግንባታ ያሳሰባት ግብፅ ያላትን ኃይል ተጠቅማ ኢትዮጵያ ብድር እንዳታገኝ ብታደርግም በሕዝብ አቅም ግድቡ አሁን ወደ መጠናቀቅ ደርሷል። የህዳሴ ግድብ ግንባታ አሜሪካንን ጨምሮ ብዙ አገራት ኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጥሩ መንገድ ቢፈጥርም በነበረው የውስጥ አንድነት መቋቋም ተችሎ ነበር። የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በግልፅ ኢትዮጵያ አሜሪካ የምትላትን ማድረግ እንዳለባት ሲናገሩ እንደነበር ይታውሳል።
ሌላው ለውጭ ጣልቃ ገብነት የዳረገን ጉዳይ የትግራይ የተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ነው። የሕግ ማስከበር ዘመቻው የህወሓት አሸባሪ ቡድንን ለመደምሰስ የተደረገ ቢሆንም በሕግ ማስከበሩ ዘመቻ ወቅት በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት ዓለም አቀፍ አገራት በመንግሥት ላይ ተቃውሟቸውን እንዲያሰሙ አድርጓል። ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመግባት መንገድ ስትፈልግ ለነበረችው አሜሪካ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላታል። አሜሪካን ይህን አጋጣሚ ተጠቅማ የኢትዮጵያ መንግሥት ‹‹እኔ በማወጣለትና በምነግረው መንገድ መመራት አለበት›› እስከማለት አድርሷታል። በዚህም ሳይበቃ መንግሥት ከህወሓት ሽብርተኛ ቡድን ጋር ድርድር ማድረግ አለበት ብላ ትዕዛዝ ሰጥታለች።
አሜሪካ እንዴት በግልፅ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እንድትገባ ያደረጋት የዲፕሎማሲ ውድቀት መሆኑን የሚናገሩ አሉ። በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻው በተጀመረበት ወቅት ሽብርተኛውን ህወሓት የሚደግፉ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸው ምሁራን አሜሪካ በመመላለስ ኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጠር ሲወተውቱ ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ ግን የኢትዮጵያን መንግሥት ወክለው በየአገሩ የሚገኙ አምባሳደሮች የተሻለ ውጤታማ ስራ አለመስራታቸው ሽብርተኛው ህወሓት የሚነዛቸው ፕሮፖጋንዳዎች ታማኝነት እንዲያገኙ አድርጓል።
በውጭ አገራት የሚገኙ ዳያስፖራው ማህበረሰብ አንድነት የሌለው ከመሆን ባለፈ በአገሩ ጉዳይ ላይ የጠራ አቋም ማንጸባረቅ ተስኖት ሲዠዋዠው የኖረ ነው። በተለይ የለውጥ አመራሩ ከመጣና በትግራይ የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከተጀመረ በኋላ ዲያስፖራው በሚኖርባቸው አገራት እርስበርስ እስከመደባደብ የሚደርስ ልዩነት ውስጥ ገብቷል። በሌላ በኩል በየኤምባሲው የሚገኙ ዲፕሎማቶች ባለሁለት ስለት ቢላዋ በመሆን ለመንግሥትም ለተቃዋሚ ኃይሎችም የመስራት አዝማሚያዎች መበራከት ለውጭ አገራት ጣልቃ ገብነት ዳርጎናል።
ሰሞኑን ታድያ የውጭ አገራትን ጣልቃ ገብነት በመቃወም ዘመቻዎች ተካሂደዋል። ዘመቻው እኛ ኢትዮጵያውያን ሉዓላዊነታችን ለውጭ ጣልቃ ገቦች አሳልፈን እንደማንሰጥ በተጨባጭ ያሳየ ነው። ኢትዮጵያውያን በውስጣችን የሚስተዋሉ ጥቃቅን ልዩነቶች ወደ ጎን በመተው በሀገር ሉዓላዊነትና አንድነት ላይ ለሚያዣንብብ ማንኛውም ጥቃት የማይበገር መንፈሰ ጠንካራና ኩሩ ሕዝቦች መሆናችንን በእውነተኛ መረጃ በማስደገፍ ልናሳያቸው ይገባል።
አዝማቹ ክፍሌ
አዲስ ዘመን ግንቦት 17/2013