በኢትዮጵያ የሲሚንቶ አቅርቦት እና ፍላጎት መመጣጠን አልቻለም። ይህን ተከትሎም የሲሚንቶ ዋጋ መረጋጋት ተስኖታል። ፋብሪካዎች በአቅማቸው መጠን አለማምረታቸው የሲሚንቶ ዋጋ እንዳይረጋጋ ብሎም የዋጋ ንረት እንዲከሰት ማድረጉም በምክንያትነት ሲቀርብ ቆይታል። ከአቅርቦት እና ፍላጎቱ አለመጣጣን ባሻገር የግብይት ሰንሰለት ችግር ምርቱ ደላላው እጅ ላይ መውደቁም ገበያውን እንደረበሸው በተደጋጋሚ ተገልጿል።
ችግሩን ለመቅረፍ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ላይ ታች ሲል ከርሟል። የሲሚንቶ አቅርቦት እጥረትና የገበያውን መመሰቃቀል በመረዳት በግብይት ሰንሰለቱ የተሰገሰገውን ደላላ በማስወጣት ብሎም ገበያውን ለማረጋገት ያስችላል ያለውን አዲስ አሰራር ዘርግቷል።
የሲሚንቶ ንግድና ግብይቱ በተለየ መንገድ እንዲከናወን የሚያስችል ውሳኔንም አስተላልፏል። የትኛውም የሲሚንቶ ተጠቃሚ የንግድ ፈቃዱን እያሳየ መንግስት በተመነለት ዋጋ እና ይበቃሃል ያለውን መጠን ከተፈቀደላቸው ቸርቻሪዎች ይግዛ ብሏል።
ይህን አሰራር ተከትሎ ታዲያ የተለያዩ ውጤቶችን መመልከት ስለመቻሉም አሳውቋል። ይሁንና አዲሱ አሰራር ለአንዳንድ የምርቱ ተጠቃሚዎች ምቾትን አልሰጠም። በተለይም የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ይበልጥ ለፈተና አጋልጦታል። ከሁሉ በላይ በትላልቅ ግንባታ እየሰሩ ለሚገኙ የስራ ተቋራጮችን ጭንቀት መሆኑም ሲገልፅ ተሰምቷል።
በተለያየ ቦታ ግንባታ በማከናወን ላይ የሚገኙ የስራ ተቋራጭም መንግስት ሲሚንቶ ምርት ግብይት ላይ እጁን ካስገባ ወዲህ የሚያገኙት የሲሚንቶ መጠን በቂ ባለመሆኑ ስራቸውን ለመስራት እንደተቸገሩ እና በሲሚንቶ እጥረት ምክንያትም ስራ ለማቆም እንደተገደዱ የሚገልፅ ቅሬታን ሲያቀርቡም ተሰምቷል።
በቀደመው አሰራር በቀጥታ ከሲሚንቶ ፋብሪካዎች የፈለጉትን ያህል ሲሚንቶ ይገዙ እንደነበር የሚያስታውሱት ተቋራጮቹ፣ ዋጋ ሲጨምር እንኳን ዞር ዞር ብለው ምርቱን ለማግኘት እንደማይቸገሩ ሲገልፁም ይሰማል። በተለይ በአሁኑ ወቅት መንግስት ዋጋ ተምኖ በክፍለ ከተሞች በኩል ተመጥኖ እንዲከፋፈል ከተደረገ በኋላ ግን በቂ ሲሚንቶ ማግኘት አልቻልንም ሲሉም ተደምጠዋል። ችግሩን ያስተዋለው የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርም አሰራሩን ተከትሎ የተፈጠረውን ቅሬታ ምላሽ ለመስጠት ማሻሻያዎችን ማድረጉን አሳውቋል።
ከአዲሱ አሰራር ጋር ለተከሰተው ችግር ራስ ምታት የሆነው ለግንባታ ተቋራጮች ብቻም አይደለም። የሲሚንቶ ምርትን በመጠቀም የተለያዩ የኮንስትራክሽን ግንባታ ምርቶችን ለሚያቀርቡ ድርጅቶችም ከባድ ፈተና ሆኗል። የተለያዩ ድርጅቶችም ምርቱን ማግኘት እንዳልቻሉ የሚጠቁም ቅሬታ በማቅረብ ላይ ናቸው።
ከእነዚህ ድርጅቶች አንዱም የአሌክ ቴራዞ ፋብሪካ ሃላፊነቱ ተወሰነ የግል ድርጅት ነው። የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ ኪዳኔ እንደሚልፁትም፣ ከተማው ላይ ሲሚንቶ ማግኘት ትልቅ ከባድ ችግር ሆኖባቸዋል። ውጤቱም ስራቸውን እጅግ እየፈተነው ይገኛል። ‹‹ቴራዞ ለማምረት ሲሚንቶ ወሳኝ ግብዓት ነው›› የሚሉት ስራ አስኪያጁ፣ ምርቱን ማግኘት እንዳልቻሉና ረጅም ወረፋዎችን ለመጠበቅ መገደዳቸውን ይናገራሉ። ለመጠባበቂያ ያስቀመጡትን አሟጠው በመጠቀማቸው እያደር ችግሩ ተባብሶባቸዋል። በመሆኑም መንግስት ፈጣን መፍትሄ እንዲሰጣቸውም ነው የጠየቁት።
የንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበልም የአገሪቱ የሲሚንቶ ፍላጎት ከዓመት ዓመት ከፍተኛ በሆነ መልኩ እየጨመረ ቢመጣም የሚመረተው ምርት በአንፃሩ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ እድገት አለመኖሩን ይናገራሉ።
እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ፣ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የሲሚንቶ ፍላጎቷን መመለስ የሚያስችሉ ኢንዱስትሪዎች የላትም። የማምረት አቅሟ በጣም ውስን ነው። ገበያው ላይ ያለው ፍላጎት እየጨመረ በሚሄድበት ጊዜ በመሃል ደግሞ ደላላ ይገባል። ይህ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ አባብሶታል።
የችግሩን ክብደት መሰረት በማድረግም መንግስት የተለያዩ ተግባራት ያከናወነ ሲሆን፤ በተለይ ከባለፈው ሚያዝያ ወር ጀምሮ በርካታ ስርዓቶች እና የአሰራር ማሻሻያዎችን ሲተገብር ቆይቷል። የመጨረሻ መፍትሄ የሆነው ሲሚንቶን ለሚፈልጉ ዜጎች በቀጥታ ተደራሽ ማድረግ ነው። አሁን ባለው ሁኔታም ገበያው በቁጥጥር እየተመራ ነው።
ይህ አሰራርም ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰውን የሲሚንቶ ውዝግብ ፈር ለማስያዝ ዓይተተኛ ሚና ስለመጫወቱ የሚጠቁሙት ሚኒስትሩ፣ ይሁንና በዚህ አሰራር ተዘለልን የሚሉ ሪል እስቴቶች፣ ትላላቅ ግንባታዎች የሚያከናውኑ ድርጅቶች፣ የቴራዞ ምርትን ጨምሮ ሲሚንቶን በግብዓትንነት የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም ያመላክታሉ። ይሁንና በቅርቡ በተደረገ ማሻሻያ የሲሚንቶ ግብዓትን ይበልጥ የሚጠቀሙ ድርጅቶች የቅድሚያ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ምርቶችን እንዲያገኙ እየተደረገ ስለመሆኑም ነው ያስታወቁት።
‹‹ከሁሉ በላይ ችግሩን በዘላቂነት ሊፈታ የሚችለው ሲሚንቶን በሬሽን በማዳረስ አይደለም›› የሚሉት አቶ መላኩ፣ የሲሚንቶ ተግዳሮት ለመፍታት የመጀመሪያው ነገር የምርት አቅምን ማሳደግ እንዲሁም ተጨማሪ የሲሚንቶ ምርት ወደ አገር ወይንም ወደ ገበያው እንዲገባ ማድረግ የግድ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
መንግስት ከዓመት ዓመት እየጨመረ የሚመጣውን የሲሚንቶ ፍላጎት እና የአቅርቦት ችግር ፈር ለማሳያዝ የተለያዩ የፖሊሲ ማስተካከያዎችን አድርጓል። ከማስተካካያዎቹ መካከል ሁነኛ ሆኖ የሚጠቀሰውም በአገር ውስጥ ባለሃብቶች ጥምረት ወይንም በሽርክና ሲሚንቶ ፋብሪካ የመገንባት ፈቃድ መስጠት ነው።
ከዚህ ቀደም በነበረው መንግስታዊ አስተዳደር ይህ ፈፅሞ የሚታሰብ አልነበረም። 14 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ስላሉን እዚህ አገር ላይ በውጭ እና በአገር ውስጥ ባለሃብቶች ጥምረት ሲሚንቶ ፋብሪካ ሊቋቋም አይገባም የሚል ክልከላ ነበር። የክልከላው ዋነኛ ምክንያት አንድን ፋብሪካ ይበልጥ ተጠቃሚ ማድረግ ስለነበር ነው።
በዚህ ዓመት ይህ የፖሊሲ ማስተካከያ በመደረጉ የሲሚንቶ አቅርቦቱን በመጨመር ረገድ ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው የሚያስገነዝቡት ሚኒስትሩ፤ ማሻሻያውን ተከትሎም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁለት እና ሶስት ፋብሪካዎች ወደ ግንባታ እንደሚገቡ፤ በቅርብ ጊዜ ውስጥም እነዚህ እና ሌሎችም ፋብሪካዎች ወደ ምርት ማማረት እንደሚሸጋገሩ ነው ያስረዱት።፡
በፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተት ለማጥበብ የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ የውጪ ባለሀብቶች በጥምረት እንዲቀላቀሉ ተደርጓል፤
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2013 ዓ.ም